Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሶዴፓ አዳዲስ አመራሮች የሶማሌ ክልልን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ አስታወቁ

የሶዴፓ አዳዲስ አመራሮች የሶማሌ ክልልን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ አስታወቁ

ቀን:

ከሰኞ መጋቢት 23 እስከ ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው አሥረኛ ጉባዔ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶሕዴፓ) ወደ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ) የተለወጠው የማዕከላዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አዳዲስ አመራሮች፣ የሶማሌ ክልልን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ አስታወቁ፡፡

በሦስት ቀናት የድርጅታዊ ጉባዔ ማጠናቀቂያ ላይ 61 አባላት ያሉት የማዕከላዊ ኮሚቴ ምርጫ የተካሄደ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ዘጠኝ አባላት ያሉት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተመርጠዋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ የሶዴፓ ሊቀመንበርና ምክትል በመሆን ተመርጠዋል፡፡

የሶዴፓ ዘጠኝ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ደግሞ አቶ አህመድ ሺዴ፣ አቶ ሙስጠፌ መሐመድ፣ አቶ አደም ፋራህ፣ አቶ መሐመድ ሻሌ፣ አቶ አብዱራህማን አህመድ፣ አቶ አብዲ አዲል፣ አቶ ሞባሸር ዲግድ፣ አቶ አብዱራሂም ኢት እንዲሁም አቶ መሐመድ ፈታህ ናቸው፡፡

በጉባዔው ማጠናቀቂያ ወቅትም ተመራጮቹ የክልሉን ሰላም የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ በቆራጥነት እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡

በተጠናቀቀው አሥረኛው የሶዴፓ ጉባዔ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የክልሉ ፓርቲና ፖለቲካ ወደ አገር አቀፍ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲገባ አሳስበዋል።

ሶዴፓ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚቋቋመውን ፓርቲ ለመመሥረትና ለማገዝ ግንባር ቀደም ሆኖ እንደሚታገል እምነታቸው መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የጅግጅጋ ፖለቲካ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ መታገል አለባችሁ፤›› ብለዋል። ‹‹አንድ አገራዊ ፓርቲ ያስፈልጋል ሲባል ቋንቋን፣ ብሔርንና ማንነትን መጨፍለቅ አይደለም፤›› ብለው፣ አንድ አገራዊ ፓርቲ ያስፈልጋል ማለት በአንድነትና በጋራ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር መሥራት እንደሆነ አሳስበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሶማሌ ክልል ሕዝብ ኢትዮጵያ በገጠማት ችግር ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን ገልጸው፣ የዛሬ ዓመት ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመፍታት ወደ ክልሉ ማቅናታቸውን በማስታወስ፣ ‹‹የአምና መንፈስና የዛሬ መንፈስ ልዩነቱ በግልጽ ፊታችሁ ላይ ይታያል፤›› ሲሉ በክልሉ ከዚህም በላይ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል አስረድተዋል።

ከዚያን ጊዜ ወዲህ የተፈጠረው አዲስ የሰላም አየር መንፈስ ለሶማሌ ክልልና ለአገሪቱ ትልቅ የለውጥ ስኬት መሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦጋዴን ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) አባላትና አመራሮች፣ እንዲሁም በተለያዩ እስር ቤቶች የነበሩ ወገኖች በለውጡ ተጠቃሚ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ ለውጡ እንዲሳካና የክልሉ ሰላምና ፀጥታ እንዲጠናከር ከአገር ሽማግሌዎች ጋር የተደረጉ ውይይቶች አስተዋጽኦ የጎላ እንደነበርም ገልጸዋል።

የሶማሌ ክልል ለመጀመርያ ጊዜ በተሟላ ሁኔታ በምሁራን እንዲመራ መደረጉ መልካም ጅምር መሆኑንና ፓርቲውም የሶማሌ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ሶዴፓ) ተብሎ ስያሜውን መቀየሩ፣ የሶማሌ ሕዝብ ያለ ምንም ተቀፅላ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ያረጋገጠ እንደሆነ አስረድተዋል።

የክልሉ አመራርና ሕዝብም በቀጣይ የመስኖ ልማትን ማስፋፋት፣ የሥራ አጥነት ችግርን መፍታት፣ ኮንትሮባንድን፣ የፖለቲካና የገንዘብ ሌቦችን መታገል እንዳለበት አሳስበው፣ ይኼንን ለማሳካትም መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...