የዓለም ዋንጫ በእግር ኳሱ በርካታ ትዕይንትን በማስተናገድ ይታወቃል፡፡ በአዳዲስ ድርጊቶች የተሞላና በአራት ዓመት አንዴ ብቅ የሚል ተወዳጅነት ያተረፈ ተናፋቂ ውድድር ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2018 በሩሲያ የተከናወነው የዓለም ዋንጫ እስከዛሬ ከተከናወኑት በተለይ አድናቆትን ያተረፈ ነበር፡፡ በተለይ የውድድሩ አሸናፊ ፈረንሣይ አነጋጋሪ ክስተት ነበረች፡፡ የውድድሩ አሸናፊ መሆንዋን ተከትሎ ትችቶችንም አስተናግዳለች፡፡
የትችቱ ዋና ምክንያት በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ በርካታ መሠረታቸው ከአፍሪካ የሆኑ ዜግነት ለውጣ መያዟ ነው። ምንም እንኳ ፈረንሣይ የትችቱ ሰለባ ብትሆንም የ2018 ዓለም ዋንጫ አሸናፊ መሆን አስችሏታል፡፡ የፈረንሣይ ብሔራዊ ቡድን ከአንጋፋዎቹ ዚነዲን ዚዳን ጀምሮ እስከ የዛሬው ትውልድ የሆነው ፖል ፖግባ ጭምር የዘር ግንዳቸው ከአፍሪካ ይመዘዛል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ ሁሉም ብሔራዊ ቡድኖች ይኼንን መንገድ መከተልን ተያይዘውታል፡፡ ዘንድሮ ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች ዜጎቻቸውን በመመልመልና በማስመጣት ዕድሉን ሲጠቀሙበት ተስተውሏል፡፡
ከእነዚህ ልምዶችን መቅሰም ያልቻለችው ብቸኛው አገር ኢትዮጵያ መሆኗ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የሚኖሩት ከኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች የተገኙትን ተጫዋቾች በአግባቡ ስትጠቀም አለመስተዋሏ ጥያቄዎችን ሲያስነሳ ሰንብቷል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ባለፈችበት ወቅት ትውልዳቸው በተለያዩ አውሮፓ አገሮች ላይ የተመሠረቱ ኢትዮጵያዊያን በጥቂቱም ቢሆን ማስተዋል ተችሎ ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል በሰውነት ቢሻው ቡድን ውስጥ ተካቶ የነበረው ትውልደ ጀርመናዊ ዴቪድ በሻ የሚጠቀስ ነው፡፡ ተጫዋቹ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ እምብዛም ዕድል ማግኘት ባይችልም ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር መሆኑ የራሱ የሆነ ድምቀትን መፍጠር ችሏል፡፡ ተጫዋቹ እ.ኤ.አ. 2012 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ በጉልበቱ ላይ ጉዳት እስኪደርስበት ድረስ መጫወት ችሏል፡፡ ከእግር ኳስ መጫወት ካቆመ በኋላ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾችን ለተለያዩ የውጭ እግር ኳስ ክለቦች በማዘዋወርና የኤጀንትነት ሥራ ላይ ተሰማርቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተከታታይ የጨዋታ መዋዠቅ ተከትሎ በተለያዩ የአውሮፓና አሜሪካ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያዊ የዘር ሐረግ ያላቸውን ተጫዋቾች ከተለያዩ ክለቦች ጋር በግሉ ለብሔራዊ ቡድን ለማቅረብ ክለቦችንና ተጫዋቾችን ማነጋገር መጀመሩን ተጫዋቹ ይናገራል፡፡
ከ38 በላይ ኢትዮጵያዊ የዘር ሐረግ ያላቸውን ተጫዋቾች መርጦ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ይሁንታ እየጠበቀ እንደሆነና ጥያቄውን ካቀረበ ከአሥር ወራት በላይ ቢሆንም ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳላገኘ ይገልጻል፡፡
‹‹በርካታ ተጫዋቾችን ማነጋገር ችያለሁ፡፡ ለዚህም ለአገራቸው ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት ፈቃደኝነታቸውን ያሳዩኝ ብዙ ናቸው፤›› በማለት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋችና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች ዴቪድ በሻ ለሪፖርተር ያስረዳል፡፡
እንደ ተጫዋቾች አስተያየት ከሆነ እሱ ለሚተገብረው ተግባር ምንም ዓይነት ክፍያ እንደማይፈልግ በአንፃሩ ግን የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ሎጎ መጠቀም እንደሚፈልግ የሚያትት ፕሮፖዛል ማቅረቡን ያስረዳል፡፡
በተጨማሪ ታኅሣሥ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ከፕሮፖዛሉ ጋር አባሪ ሆኖ ተጫዋቾቹ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች ተሠልፈው ለመጫወት የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚደረግ የውል ስምምነት አቅርቧል፡፡
በስምምነቱም አንቀጽ 2 ሥር የውል ዓላማ በሚል በመላው ዓለም በሚገኙ የእግር ኳስ ክለቦች ታቅፈው እየተጫወቱ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በወቅቱ በሚኖራቸው የእግር ኳስ የመጫወት ብቃትና ቴክኒክ መሠረት በኢትዮጵያ የወንዶችና የሴቶች የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ ተካተው እንዲጫወቱ ውል ሰጪ ፍላጎት ያለው በመሆኑ በሌላ በኩልም ውል ተቀባይ ለብሔራዊ ቡድኑ የሚመረጡትን በውጭ አገር የሚገኙት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን በመፈለግ ረገድ ከውል ሰጪ ጋር በጋራ ለመሥራት በመስማማቱ የተደረገ ውል ነው የሚል ተካቶበታል፡፡
በአጠቃላይ የውል ስምምነቱ 13 አንቀጾች ሲኖሩት የተለያዩ ጉዳዮችን በሥሩ ያካተተም ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ጉዳዩ ተቀባይነት ያለውና ብሔራዊ ቡድኑን ለማጠንከር ሚናው የጎላ ቢሆንም፣ በራሴ መንገድ ለመመልመል አቅጃለሁ በማለት አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ አስተያየት የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቴክኒካል ክፍል ጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ከውሳኔ የደረሰ መሆኑን ጠቅሰው በበጎ ፈቃደኝነት ማገልገል የሚፈልግ ማንኛውም አካል በፌዴሬሽኑ ተቀባይነት አለው ብለዋል።
‹‹ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በውጭ አገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ሐረግ ያላቸውን ተጫዋቾች እየመረጠ ይገኛል፡፡ ሌሎች በጎ ፈቃደኞችም ተጫዋቾችን ቢያቀርቡልን ለመቀበል ዝግጁ ነን፡፡ ተጫዋቾችን ለመቀበል ግን ከግለሰብ ጋር የምንዋዋልበት ምንም አግባብ የለም፤›› በማለት አቶ ኢሳያስ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ዴቪድ በሻ ተጫዋቾቹን ወደ ኢትዮጵያ ከማምጣቱ ባሻገር አሁን እየተማረበት ባለው የእግር ኳስ አማካሪ ሥራን ከብሔራዊ ፌዴሬሽንና ክለቦች ጋር መሥራት ፍላጎት እንዳለው አስረድቷል፡፡ በዚህ ሙያውም በእግር ኳሱ የበኩሉን ማበርከት እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤቱ እያሽቆለቆለ የመጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወቅቱን የተከተለ ዘመንኛ መንገድ አለመከተሉ እንደ ችግር ይከሰታል፡፡ አዲስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በስሙ በርካታ ጉዳዮች ማለትም የምግብ ባለሙያ፣ የቪዲዮ፣ የሚዲያና ሌሎችም ጉዳዮች ተካተው ዝግጅቱን ያደርጋል ቢባልም፣ እስካሁን ግን ምንም ዓይነት አዲስ ነገር ሲካተት አለመስተዋሉ እያስተቸው ይገኛል፡፡
በአገር ውስጥ ከሚገኙት ተጫዋቾች በተጨማሪ የውጭ ተጫዋቾችን መጠቀም ከውጤትም በላይ የልምድ ልውውጥ ያለው ጥቅም ከፍተኛ በመሆኑ ዓለም አቀፍ የእግር ኳሱን መንገድ መከተል ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡