ይቅርታ መጠየቅዎ የልቤን ቀልብ ሳበው። ትልቅ ሰው እንዲህ ነው። በዚህ ደብዳቤዬ ባለፈው ዓመት በደከሙበት ፈንታ የሚቀጥለው አዲስ ዓመት የሚልቁበት ይሆን ዘንድ ልሞግትዎ ነው። ይህ ሕዝብ አሁንም ዕድል እየሰጠዎ እንደሆነ በማወቅ በቃልዎ እንደሚተጉ አምናለሁ። ባለፈው ዓመት ብዙ ግሩምና ድንቅ ሥራ አደረጉ። በተጨማሪም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ግሩምና ድንቅ የተስፋ ቃል ሰጡን። በፊታችን ያለው አዲሱ ዓመትም ከዚህ በፊት የተናገሩትን መልካም የፈውስና የአንድነት የተስፋ ቃል ወደ መሬት አውርደው በተግባር በመግለጽ ታሪክ የሚሠሩበት ይሆን ዘንድ ነው።
እንግዲህ መደመርን የምናቀነቅነው ዜሮን እያዋጣን መሆን የለበትም። ሁሉንም በእኔነት አጥር እያጠርን፣ ለጋራ ኢትዮጵያዊነት የዜሮ ድምር መዋጮ መቅረት አለበት፡፡ ከራሳችን የብሔር አጥር እንውጣ ሲባል በቃል ብቻ ሳይሆን፣ በምግባርም ይሁን። አዲስ አበባ ከእኛ አልፎ የአፍሪካ መዲና ነች ማለት ያልቻልን፣ በዚያ ፈንታ አዲስ አበባን በየኔነት ደካማ አጥረን ገድበን ስለ ኢትዮጵያ አንድነት መዘከር ከንቱነት ነው። አንድነት ከእኔነት ወደ እኛነት የማያሻግረን ከሆነ ትርጉሙ ምንድነው? በመደመር ዘመነ መንግሥት እስክንድር ነጋ በምደረበዳ የሚጮህ የመደመር ድምፅ ሆኖ ሲገኝ እርስዎ ግራ መጋባትዎን ግራ ያጋባልና አንድ ይበሉ።
ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆ ብሎ በፍፁም ፍቅር እርስዎን ማወደሱና መደገፉ፣ የእርስዎን ታላቅነት ከማሳየቱ በላይ፣ የዚህን ሕዝብ የልብ ንፅህናና ቅንነት የሚያሳይ ነው። ይህን የፍቅር ሕዝብ ከዘረኛ ፌዴራሊዝም ቀንበር አርነት አውጥተው፣ ወደ ቤተሰባዊ ፌዴራላዊ አስተዳደር ያሻግሩት ዘንድ ምድርና ሰማይ ይጮኸል። እባክዎን ጆሮ ይስጡ።
እርስዎን የኢትዮጵያ ሙሴ ብሎ ሕዝብ ተስፋ አድርጎ ነበር። እናስተውልና ትምህርት ከጥንቱ ታሪክ እንውሰድ። እስራኤል ከግብፅ ባርነት ነፃ ሲወጣ በደስታ ነበር። ጥቂት ሳይቆይ የግብፅ ሠራዊት የእስራኤል ሕዝብን ሊገድል ከበስተኋላቸው ሲያሳድዳቸው አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው ተጨነቁ፡፡ በመጨረሻም አምላክ ጣልቃ ገባና እስራኤል የኤርትራን ባህር ተሻገሩ፣ አሳዳጁም ሰጥሞ ቀረ።
(ዘለዓለም እሸቴ (ዶ/ር)፣ ከአሜሪካ)