Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች በአዲስ አበባ የዳኝነት ሥልጣን አላቸውን?

የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች በአዲስ አበባ የዳኝነት ሥልጣን አላቸውን?

ቀን:

በውብሸት ሙላት

የአዲስ አበባ አስተዳደርን በሚመለከት ጎዶሎዎቹ ብዙ ናቸው፡፡ ጎዶሎዎቹን ለመሙላት የተጀመሩ ጥረቶች ቢኖሩም ያልተጀመሩም መኖራቸው ሐቅ ነው፡፡ ከተጓደሉት መካከል፣ የዳኝነት ሥልጣንን ቅጥ ያለው መልክና ፈርጅ ማስያዝ አለመቻል አንዱ ነው፡፡ ትንሽ አፍታተን እንመልከተው፡፡

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የራሷ ፍርድ ቤቶች አሏት፡፡ በጥቅሉ ከተማ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን አከራክሮ ዳኝነት የመስጠት ሥልጣን አላቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዲስ አበባ ላይ የሚፈጸሙ የፍትሐ ብሔርም ይሁን የወንጀል ጉዳዮች ላይ የዳኝነት ሥልጣን አላቸው፡፡

ግልጽ ያልሆነው ነገር፣ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ስለሆነች የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች አዲስ አበባ ላይ በሚፈጸሙ ጉዳዮች ላይ የዳኝነት ሥልጣን አላቸው ወይስ የላቸውም የሚለው ነው፡፡ ቢያንስ ከክልሉ አስተዳደር ጋር የሚገናኙ የፍትሐ ብሔርም ይሁን የወንጀል ጉዳዮችን በሚመለከት፣ አዲስ አበባ የሚፈጸሙ፣ የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን የመኖር አለመኖር ነገር ደግሞ ሌላው ነው፡፡

በአጭር አገላለጽ፣ በአዲስ አበባ ከተማና በፌዴራል ፍርድ ቤቶች መካከል ያለው የዳኝነት ሥልጣን መጓተት፣ የኦሮሚያና በአዲስ አበባ ፍርድ ቤቶች፣ በፌዴራልና በኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች መካከል የሚኖረው ግልጽነት የጎደለው የዳኝነት ሥልጣን ክፍፍል መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ ሦስትዮሻዊ የዳኝነት ሥልጣን ጉተታ አንዱ ጎደሎ ነው፡፡

አዲስ አበባ ራሷን ችላ የምትተዳደር፣ ከክልልነት ዝቅ ባለ ደረጃ የምትገኝ ራስ ገዝ ከተማ ናት፡፡ ይኼንን ራስን የማስተዳደር አቋም ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 ላይ አፅድቆላታል፡፡ ስለሆነም ራሷን የቻለች አስተዳደር ናት፡፡ ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ተርጓሚ አላት፡፡ ሕግ አውጪው የከተማውና የወረዳ ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ ሕግ አስፈጻሚው በከንቲባው የሚመራው ካቢኔን ይዞ እስከመጨረሻው ዕርክን ድረስ የሚወርደው ነው፡፡ ሕግ ተርጓሚው የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመርያ ደረጃና  ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም ማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ናቸው፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓብይ ማጠንጠኛ የዳኝነት ጉዳይ ስለሆነ ወደ ፍርድ ቤቶቹ እንመለስ፡፡ አዲስ አበባ የራሷ የአስተዳደር ወሰን ቢኖራትም እንደ ሕግ አውጭውና ሕግ አስፈጻሚው ሁሉ አዲስ አበባ ላይ የሚፈጸሙ ጉዳዮች አከራክሮ ዳኝነት የመስጠት ሥልጣኑ ለፌዴራል መንግሥት ስለተሰጠ፣ በዳኝነት ረገድ ‹‹ከተማ ነክ›› ጉዳዮችን ብቻ ላይ ነው የዳኝነት ሥልጣን የተተወላት፡፡ በፍትሐ ብሔር ጉዳይ ከተማ ነክ የሆኑትን፣ በወንጀል ደግሞ ደንብ መተላለፍና የከተማው ፋይናንስ ጋር የሚገናኙት ላይ ብቻ እንዲወሰን ተደርጓል፡፡

ለአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች በአዋጅ ከተሰጠው የዳኝነት ሥልጣን የተረፈው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ነው፡፡ አዲስ አበባ የፌዴራሉ መንግሥት ዋና ከተማ ናት፡፡ በመሆኑም፣ መሬቱም የፌዴራሉ መንግሥት ይዞታ እንደሆነ ታስቦ የዳኝነት ሥልጣኑን ወስዷል፡፡ ከፌዴራል ከመንግሥቱ ዋና ከተማነት ባለፈም በተደራቢነት የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም ዋና ከተማ ናት፡፡ ጥያቄው የሚመጣው፣ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ከሆነች የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች አዲስ አበባ ላይ ለሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮች የዳኝነት ሥልጣን አላቸው ወይ የሚለው ነው? ጉዳዩን በአግባቡ ለመረዳት ያግዝ ዘንድ ስለ ዳኝነት ሥልጣን የተወሰኑ ነጥቦችን አስቀድመን እናንሳ፡፡

በፌዴራልም ሆነ በክልል የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው በሚል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79(ለ) ተደንግጓል፡፡ ይኸው ድንጋጌ ከአንቀጽ 37 ጋር ተገናዝቦ ሲታይ ፍርድ ቤቶች በማናቸውም ጉዳይ ገደብ የለሽ ሥልጣን አላቸው ለማለት ሳይሆን ይልቁንም አንድን ጉዳይ ተቀብለው ለማየትና ለመወሰን ሥልጣን የሚኖራቸው ጉዳዩ በፍርድ ሊወሰን የሚገባው ሆኖ ከተገኘ ብቻ ነው፡፡

ይኼው አንቀጽ 37 ንዑስ ቁጥር 1 ‹‹ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው፤›› በሚል ከተገለጸውን እንዲሁም አንቀጽ 79 (5) በተደነገገው መሠረት ለሃይማኖትና ለባህል ፍርድ ቤቶች በሕግ የመዳኘት ሥልጣን መስጠቱ፣ ብሎም በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 4 በሌላ አኳኋን እንዲፈጸም በሕግ ካልተገለጸ፣ ክሱን ተቀብሎ ለማከራከር ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት ብቻ ነው በሚል መደንገጉ በፍርድ ሊወሰን በሚችለው ጉዳይ ፍርድ ቤቶች ብቸኛ ሥልጣን አላቸው ማለት አያስችልም፡፡

ስለሆነም ፍርድ ቤቶች አንድን ጉዳይ ተቀብለው ከማየታቸው በፊት በቅድሚያ ጉዳዩ በፍርድ ሊወሰን የሚችል መሆኑንና አለመሆኑ፣ ጉዳዩ በፍርድ ሊወሰን የሚችል መሆኑ ቢረጋገጥ ይህንን ጉዳይ ዓይቶ የመወሰኑ ሥልጣን ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል ያልተሰጠ መሆኑን በቅድሚያ በራሳቸው አነሳሽነት መመርመር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር አዲስ አበባ ላይ የሚፈጸሙና ዳኝነት የሚጠየቅባቸው ጉዳዮችን የማየት ሥልጣኑ የፌዴራል፣ የአዲስ አበባ ወይስ የኦሮሚያ የሚለውን መለየት ያስፈልጋል፡፡

እንደሚታወቀው፣ የፍርድ ቤቶች ሥልጣን በሦስት ዓይነት ክፍሎች ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ እነሱም ብሔራዊ የዳኝነት ሥልጣን፣ በሥረ ነገር ክርክር ላይ የተመሠረተ የዳኝነት ሥልጣን በአጭር አጠራር የሥረ ነገር ሥልጣንና በግዛት ክልል የተወሰነ የዳኝነት ሥልጣን ናቸው፡፡ አንድ ፍርድ ቤት ክስን ተቀብሎ ለማየትና ለመወሰን ሥልጣን አለው የሚባለው እነዚህ ሦስት ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው፡፡

ብሔራዊ የዳኝነት ሥልጣን (Judicial Jurisdiction) የአንድ አገር ፍርድ ቤቶች በአንድ ሰው ወይም ንብረት ላይ ተፈጻሚ ሊሆን የሚችል ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችላቸው የሥልጣን ዓይነት ነው፡፡ ክስ የቀረበበት አገር ብሔራዊ የዳኝነት ሥልጣን አለው የሚባለው ከተከሳሹ ወይም የክርክሩ ምክንያት የሆነው ተግባር ከተፈፀመበት ወይም አከራካሪ የሆነው ንብረት ከሚገኝበት ቦታ ጋር በቂ የሆነ ግንኙነት ያለው ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡

አንድ ጉዳይ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ሊታይ የሚችል መሆኑንና አለመሆኑን የሚወሰንበት የፍርድ ቤት ሥልጣን ዓይነት ነው፡፡ ክርክር የተነሳበት ጉዳይ ከውጭ ዜጎች ወይም ንብረት ጋር ግንኙነት ካለው አዲስ አበባ ላይ የተፈጸመ ድርጊት ቢሆን እንኳን ሥልጣኑ የፌዴራል ፍርድ ቤት ስለሆነ በዚህ ረገድ በሦስቱ ፍርድ ቤቶች መካከል የሚነሳ የፍርድ ቤት ሥልጣን ውዝግብ አይኖርም፡፡

የግዛት ክልል ሥልጣን (Local Jurisdiction) አንድን  ጉዳይ ተቀብሎ ለመስማትና ለመወሰን አቅም ካላቸው ፍርድ ቤቶች መካከል በየትኛው ፍርድ ቤት ቀርቦ መታየት እንዳለበት የሚያመለክት ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ የየትኛው ወረዳ፣ ዞን ወይም የየትኛው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው ጉዳዩን የማየት ሥልጣን ያለው የሚለውን የሚመልስ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አዲስ አበባ ላይ ሊነሳ የሚችለው የከተማዋና የኦሮሚያ ክልል ወሰን ተለይቶ ባልታወቀባቸው አካባቢዎች ላይ ወደ ኦሮሚያ ክልል (ፊንፊኔ ዙሪያ) ወይስ አዲስ አበባ ነው የሚለውን መለየት ካስቸገረ የዳኝነት ሥልጣን ውዝግብ ሊፈጠር ይችላል፡፡

 የሥረ ነገር ሥልጣን (Material Jurisdiction)  ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ጉዳዩን በትክክል ተመልክቶ አግባብነት ያለው፣ ፍትሕን ያገናዘበ ፍርድ ለመስጠት እንዲረዳ ታስቦ አቅምን ባገናዘበ ሁኔታ የተደረገ የሥልጣን ድልድል ሲሆን፣ ይህንንም በማድረግ እግረ መንገዱንም በተለያዩ ደረጃ በቅደም ተከተል ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥራን ያከፋፈለ ነው፡፡

አንዳንድ ጉዳዮች ሊያስነሱ በሚችሉት የክርክር ባሕርይ ምክንያት ለተወሰኑ ፍርድ ቤቶች እንዲቀርቡ በሕግ ተለይተው ከተመለከቱት በቀር የሥረ ነገር ሥልጣን የተደለደለው በክሱ በተመለከተው የገንዘብ ወይም የንብረት ግምት መነሻ እንደሆነ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 14 እና 15 እንዲሁም የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 8፣ 11፣ 14 እና 15 በግልጽ ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡

የሥረ ነገር ሥልጣን የሚወሰነው በገንዘቡ መጠንና በጉዳዩ ዓይነት ቢሆንም፣ የፌዴራል መንግሥቱን አደረጃጀት ተከትሎ የጉዳዩ ባለቤት የክልል ወይስ የፌዴራል ፍርድ ቤት ነው? የሚለውንም ይጨምራል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥታዊ አስተዳደር በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች የተዋቀረ ነው የሚለውን መነሻ በማድረግ የዳኝነቱም ሥልጣን በፌዴራል መንግሥቱና በክልል መንግሥታት መካከል እንደተከፋፈለ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 5ዐ እና 51 ሥር ተደንግጓል፡፡ በዚህም መሠረት በአንቀጽ 8ዐ ‹‹የፍርድ ቤቶች ጣምራነትና ሥልጣን›› በሚል ርዕስ በፌዴራል ጉዳዩች ላይ የበላይና የመጨረሻ  የዳኝነት ሥልጣኑ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በክልል ጉዳዮች ላይ በክልሉ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሆኑን መረዳት ቀላል ነው፡፡

በመሆኑም የክልል ፍርድ ቤቶች በሕገ መንግሥቱ በተሰጣቸው የውክልና ሥልጣን መሠረት ካልሆነ በቀር የፌዴራልን ጉዳይ ለማየት፣ እንዲሁም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የክልልን ጉዳይ ለማስተናገድ የሚያስችል ሥልጣን የላቸውም፡፡

አንድ ጉዳይ የፌዴራል ነው ወይስ የክልል የሚለውን ለመለየትም መነሻ የሆነው አዋጅ ቁጥር 25/88 ሲሆን፤ በዚሁ ሕግ አንቀጽ 5 ሥር በተመለከቱት ጉዳዮች ላይ ብቸኛ ሥልጣን ያላቸው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የክልል ፍርድ ቤቶች ከላይ እንደተመለከተው በሕገ መንግሥቱ በተሰጣቸው የውክልና ሥልጣን ካልሆነ በቀር የማየት  ሥልጣን አይኖራቸውም፡፡

በዚህ አኳኋን በጉዳዩ ባለቤትነት የተደረገው የሥልጣን ክፍፍል እንደተጠበቀ ሆኖ ከጉዳዩ አካሄድ ቅደም ተከተል አንፃር በሕግ የተሰጠውን መብት ለማስከበር ክስ ለማቅረብ የፈለገ ወገን በማን ላይ ክስ እንደሚያቀርብ ከወሰነ በኋላ ክሱን በየትኛው ደረጃ ለሚገኝ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንዳለበት መለየት ይኖርበታል፡፡ ክሱም መቅረብ ያለበት ጉዳዩን አይቶ ለመወሰን የሥረ ነገር ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ነው፡፡

አዲስ አበባ ላይ የሚፈጠሩና ዳኝነት የሚጠየቅባቸው ጉዳዮችን የማየት ሥልጣኑ የየትኞቹ መንግሥታት ፍርድ ቤት ነው የሚለውን መለየት ግድ ነው ማለት ነው፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ ላይ በሚፈጸሙና ዳኝነት የሚጠየቅባቸውን ጉዳዮች በሚመለከት የሦስቱንም መንግሥታት (የፌዴራል፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ) ፍርድ ቤቶች ሥልጣንን መጓተታቸው መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ በመቀጠል፣ የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን ክፍፍልን እንቃኘው፡፡

ከሕገ መንግሥቱ መረዳት እንደምንችለው፣ የክልሎችም ይሁኑ የፌዴራልም መንግሥታት በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ዝርዝር ሕጎች እንደተገለጸው የፍትሐ ብሔርም ይሁን የወንጀል ጉዳይን አከራክሮ የመወሰን ወይም የመዳኘት ሥልጣን አላቸው፡፡ መርሁም የፌዴራልን ጉዳይ በፌዴራል ፍርድ ቤት፣ የክልልን ጉዳይ በክልል ፍርድ ቤቶች ዳኝነት መስጠት ነው፡፡

የፌዴራሉ መንግሥት  የራሱ የሆነ የተከለለ ብቻውን የሚያስተዳድረው ግዛት ስለሌለውና የሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ድምር ውጤት ስለሆነ በሁሉም ቦታ ይኖራል፡፡ ነገር ግን የፌዴራል መንግሥት በግዛት ሳይወሰን የጉዳዮቹ ዓይነት ላይ የተመሠረተ ሥልጣን አለው፡፡ ለክልሎችም በግዛታቸው ውስጥ የሚያከናውኗቸው፣ የሚያዙባቸው፣ የሚናዙባቸው ጉዳዮች አሏቸው፡፡ 

ለፌዴራሉ ፍርድ ቤቶች ብቻ የሚቀርቡ፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ብቻ የሚወሰኑ የወንጀልም የፍትሐ ብሔርም ጉዳዮች አሉ፡፡ ጉዳዮቹ የተከሰቱት፣የተፈጸሙት፣ አልያም ባለመፈጸማቸው የክርክር መነሻ የሆኑት በክልሎችም ይሁን በሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች ከግምት ውስጥ ሳይገባ የጉዳዮችን ዓይነት መሠረት በማድረግ ብቻ የፌዴራል የሆኑ አሉ፡፡

የጉዳዮቹን ዓይነት ለመለየት በመሥፈርትነት የሚያገለግሉት በፍርድ ቤት ታይቶ ዕልባት የሚሰጠውን ጉዳይ ለመዳኘት በሥራ ላይ የሚውለውን ሕግ ያወጣው የፌዴራል ወይም የክልል መንግሥት መሆኑ፣ ጉዳዩ የተፈጸመበት ቦታና የተከራካሪ ወገኖቹ ማንነት (ዜግነት፣ መኖሪያ ቦታ፣ የሚሠሩበት መሥሪያ ቤት ወዘተ) ናቸው፡፡

ከቦታ አንፃር ካየነው አዲስ አበባ ራሷን የቻለች አስተዳደር ናት፡፡ ወሰን አላት፡፡ በተደራቢነት የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ናት፡፡ አዲስ አበባ የራሷ ግዛት ካላት፣ ተደራቢ ሌላ መንግሥት አዲስ አበባ ላይ ግዛት አይኖረውም ማለት ነው፡፡ የአንዱ ግዛት መሆን የሌላው እንዳይሆን ያደርጋል፡፡ ስለሆነም፣ አዲስ አበባ ላይ የሚፈጸሙ ተግባራት ከቦታ አንፃር የኦሮሚያም ናቸው ሊባል የሚችልበት የሕግ መሠረት ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከሕግ አንፃር እንመልከተው፡፡ ሕጉን ያወጣው የትኛው መንግሥት ነው? የፌዴራል ወይስ የክልል? የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ባወጣው ሕግ መሠረት በወንጀል የሚያስቀጣ ድርጊት አዲስ አበባ ላይ ቢፈጸም፣ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ በመሆኗ ወንጀሉ ፈጻሚዎቹን ተጠያቂ ማድረግ ይቻላልን? ይህም ቢሆን ‹‹አዎ! ይቻላል›› በማለት ለመከራከር የሚያስችል ሕጋዊ አመክንዩ ማገኘት አዳጋች ነው፡፡

ከተከራካሪዎቹ ማንነት አንፃርም እንመልከተው፡፡ ክልል ላይ የተቋቋሙ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ ሰዎች ወንጀል ቢፈጽሙ ጉዳዩን የሚመለከተው የፌዴራል ፍርድ ቤት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የክልል ሠራተኞች ከሆኑ ደግሞ በክልል ፍርድ ቤት ይታያል፡፡ አዲስ አበባ ላይ ባሉ የኦሮሚያ መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ የኦሮሚያ ክልል ሠራተኞች ወንጀል ሲፈጽሙ ሊጠየቁ የሚችሉት ቦታው አዲስ አበባ ስለሆነ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ወይስ ደግሞ የክልሉ ሠራተኞች ስለሆኑ በኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች?

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደራዊ ጽሕፈት ቤቶች በአዲስ አበባ ስላሉት፣ በእነዚህ መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ ሰዎች የሚፈጽሟቸውን ወንጀሎች በሚመለከት የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች አዲስ አበባ ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ የዳኝነት ሥልጣን ሊኖራቸው እንደሚችል ሁለት ምክንያቶችን በማቅረብ መከራከር ይቻላል፡፡

 አንዱ የዳኝነት ሥልጣንን የፌዴራልና የክልል ብሎ ለመለየት መሠረት የሆነው የተከራካሪዎቹ ማንነት ስለሆነ የኦሮሚያ ክልል ሠራተኞች፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጥቅም ላይ ላደረሱት ጉዳት የክልሉ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ስለተሰጣቸው ነው፡፡ በዚህም መሠረት ወንጀል የፈጸሙት (ለምሳሌ ሙስና ቢሆን) ፈጻሚዎቹ የክልሉ መንግሥት ሠራተኞች፣ የጉዳቱ ሰለባ የክልሉ መንግሥት ስለሚሆን በፌዴራሉ የፍርድ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅም ቢሆን ይህንኑ ይደግፋል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት፣ ተፈጻሚ የሚሆነው ክልሉ ያወጣው ሕግ ስለሚሆን  ነው፡፡ ክልሉ ባያወጣው እንኳን፣ የክልል ፍርድ ቤቶች ሥልጣን እንዲሆኑ የተተው ጉዳዮች ላይ የሚያርፍ እስከሆነ ድረስ ኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች አዲስ አበባ ከተማ ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን በሚመለከት የክልሉ ሠራተኞች የክልሉን መንግሥት ጥቅም ከጎዱ ሥልጣን ሊኖረው ይችላል፡፡

ከዚህ ባለፈ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕግ የበላይነትና የፀጥታ ሁኔታን የማስከበር ኃላፊነት ባለበት ጉዳዮችን በሚመለከት (ለምሳሌ ስርቆት፣ ግድያ ወዘተ.) ማንም ይፈጽመው ማንም የዳኝነት ሥልጣኑ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች እንጂ የኦሮሚያ ሊሆን የሚችል አይመስልም፡፡

አዲስ አበባ፣ የፌዴራሉና የኦሮሚያ ክልል መንግሥታት ዋና ከተማ በመሆኗ ከፍርድ ቤት የዳኝነት ሥልጣን ጋር በተያያዘ ያልጠሩ ወይም የተጓደሉ አካሄዶች መኖራቸውን ከላይ እንደቀረበው ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...