በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የምትመራው ኢትዮጵያ አንድ ዓመት አስቆጥራለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለመደው የአመራር ሥልት ወጣ ባለ መንገድ አገር መምራት እንደሚቻል አሳይተዋል፡፡ ይህ የአመራር ሥልት በርካታ ነገሮችን ቀይሯል ማለት ይቻላል፡፡ የተጠራቀሙ ችግሮችን ተሸክማ የቆየችን አገር ወደ ትክክለኛው መንገድ ለማስገባት ከባድ ከመሆኑ አንፃር፣ የለውጡ አመራር ሊመልሳቸው የሚገቡ በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች በሙሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊመለሱለት ይችላሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡
ነገር ግን የአብዛኛውን ሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ ጥቂት የማይባሉ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡ በተግባርም ለውጡ ያመጣቸው የተባሉ ዕርምጃዎች፣ ይሆናሉ ተብለው የማይታሰቡ ውጤቶችም ታይተዋል፡፡ ይህ ማለት ግን የሕዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ ተመልሰዋል ማለት አይደለም፡፡ ዛሬም በእንጥልጥል ላይ ያሉ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ዋናው ነገር ከቀደመው ስህተት ተምሮ የተሻለ አገር ለመፍጠር የተጀመረው እንቅስቃሴ ትልቅ ተስፋ መሆኑ ላይ ነው፡፡
ኢትጵያዊነትና አንድነት እንዲጠነክር የተሠራው ሥራ ነገን በተስፋ እንድንመለከት አድርጓል፡፡ ብሔርተኝነት ከፍ ከፍ እንዲል ለዓመታት ሲሰበክበት በነበረ አገር ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ እንዲወጣ እየተደረገ ያለው ጥረት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ አብሮ መኖር አማራጭ የሌለው ሀቅ ስለመሆኑ ማሳየት ተችሏል፡፡ መበታተን ኢትዮጵያውያንን የማይወክል ስለመሆኑ እንድናረጋግጥ የተሠራው ሥራ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ያህል፣ ከዚህ በተቃራኒ የሚታዩ እንቅስቃሴዎችም በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ በተለየ ሥጋት ስለመፍጠራቸው መሸሸግ አይቻልም፡፡
በጥቅል ሲታይ የለውጡ ኃይል የበዙት ተግባሮች እንደ አገር ልናወድሰው የሚገባ ጉዳይ የመሆኑን ያህል፣ ለውጡ ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም አውቀውም ሆነ ባለማወቅ እንደ እንቅፋት የሚታዩ ተግዳሮቶች ተስተናግደዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመግደል የተደረገው ሙከራ፣ ወደ ቤተ መንግሥት በመሄድ መንግሥት ለመገልበጥ የተደርገው ሙከራ በምሳሌነት ይቀርባሉ፡፡ ድርጊቶቹ አገሪቷን ወዳልሆነ መንገድ ይመሯት እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡
በለውጥ መንገድ ጉዞው ከአባጣና ጎርባጣ መብዛቱ የማይቀር ቢሆንም፣ አገሪቱ ያገኘችውን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ ከመጠቀም፣ የተሻለች ኢትዮጵያ ለመፍጠር መተባበርና መደማመጥ እንደ ባህል ሊወሰድ ይገባዋል፡፡ ነገር ግን ይልቅ በተቃራኒው መቆም የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል አለመሆኑን ያልተገነዘቡ አካላት ቆም ብለው የተሻለውን አማራጭ በመምረጥ በጋራ አገር በጋራ መሥራት ለሁሉም ጠቃሚ ስለመሆኑ ደጋግሞ መንገሩ መልካም ነው፡፡ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ከታዩት ችግሮች ውስጥ በተለይ የዜጎች መፈናቀልና ፅንፍ የረገጠ የብሔርተኝነት ተጠቃሽ ነው፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ትልቅ እንቅስቃሴዎች ያስከተሉትን ተፅዕኖ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከሁሉም በላይ ነፃነትን ያላግባብ በመጠቀም ትልቅ አደጋ ሆኗል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ልቅ እንቅስቃሴ ለዓመታት አገር ትመራበት የነበረው አካሄድ ውጤት መሆናቸውን ለመገንዘብ ባያዳግትም፣ ወደዚህ አንገት የሚያስደፋ ተግባር እንዲገባ ያደረጉት ደግሞ ጥቂቶች ናቸው፡፡ በአንድ ላይ እንኑር ከሚለው እጅግ ጠቃሚ አመለካከት አፈንግጦ ጽንፍ የረገጠ ቅስቀሳ ማድረግ ለማንም አይበጅም፡፡
ለመልካም የሚደረገውን ጉዞ ሲጎትተው ታይቷል፡፡ ሰላምን በስሜታዊነት ተነስቶ ግለኝነትን በማጉላት የሚነዙና ለዚህም የተገኘውን ነፃነት ያላግባብ የሚጠቀሙ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የማድረግን አስፈላጊነት ያየንበትም ወቅት ነው፡፡ በአጭሩ ነፃነትን በአግባቡ መጠቀም የግድ ነው፡፡ ነፃነትን በአግባቡ ባለመጠቀምና በእኔ አውቃለሁ አመለካከት እየተካሄደ ሕዝብ ላይ የሚፈጥረው ሥጋትና ተፅዕኖ አደገኛ ሊሆን ይችላልና ሕግ እንዳለ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ነፃነትም ገደብ አለው ብሎ ማስተማር ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ዛሬ በስም መለየት የማንችላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ አገር እንዲረጋጋና ሰላም እንዲሆን ምን ሠርተዋል? በእርግጥ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ እያረጉ ያሉትን ጥረት ባንክድም፣ እዚህም እዚያ ለሚፈጠር ግንጭትና አለመረጋጋት እንዲከስም ምን ያህል አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ለማወቅ ከባድ ነው፡፡ ጉዳዩ እነሱንም የሚመለከት በመሆኑ በዚህ አስተዋጽኦዋቸው ነገ እንጠብቃቸዋለን፡፡
ሕዝብ በመካከሉ ችግር የለበትም፡፡ ይሁንና ችግር አለብህ ብለው በግልም በቡድንም የሚንቀሳቀሱ አካላት ሕዝብን ወዳልተገባ መንገድ በመምራት ሲፈጸም የነበረው ያልተገባ ድርጊት የፈጠረው ተፅዕኖ፣ አገርን በሚያሳድጉ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ትኩረት እንዳይደረግ ማድረጉ መታወስ አለበት፡፡
አንድ ዓመት ውስጥ ከምናያቸው አንዳንድ እንቅስቃሴዎችና ይህም ይዞ የመጣው ችግር የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየሳረፈ ነው፡፡ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ኢኮኖሚውን ለማራመድ ያስችላሉ የተባሉ ክዋኔዎች የመኖራቸውን ያህል ኢኮኖሚው በፍርኃት ያሸበቡ ድርጊቶች ስለታዩ እንደ አገር እየተጎዳን ነው፡፡
እዚህ ጋር እንዲህ ሆነ፣ እዚያ ጋር እንዲህ ተፈጠረ የሚሉ ወሬዎች ኢኮኖሚውን ይጎዳሉ፡፡ ጉዳቱ ደግሞ የበለጠ የሚታየው ነገ ከነገ ወዲያ ነው፡፡ ስለዚህ አገር በፖለቲካ እሰጥ አገባ ታድግ ይመስል ሁሉም ዛሬ ምን ተባለ በሚለው ላይ ጊዜ ካጠፉ ኢኮኖሚውን በአግባቡ ለመያዝ ያስቸግራል፡፡
በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ስለፖለቲካና ከእዚህ ጋር በተያያዙ ችግሮች የባከነውን ጊዜና ጉልበት ኢኮኖሚውንም በዳሰሱ ጉዳዮች ላይ ብናውል ምንኛ በተጠቀምን ነበር፡፡ ስለኢትዮጵያ የሚያወራ ሁሉ ኢኮኖሚውን የተመለከቱ ጉዳዮችን የዘነጉ ይመስላል፡፡ ኢኮኖሚውን ያልዳሰሰ ፖለቲካ ውጤት ስለማይኖረው ስለኢኮኖሚውም እንዲታሰብ ሁሉም መጣር አለበት፡፡
ሌላው ቀርቶ ዛሬ ከ107 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሏት የምትባለዋ አገር እነርሱ በየስሜታቸው ሲወረጫጩ፣ የአገር ኢኮኖሚ እንዴት እየሄደ ነው? እኛስ ምን ማድረግ አለብን? ብለው ያለመጨነቃቸው ያሳዝናል፡፡ ነገ ሥልጣን የመያዝ ዕድል ሲያገኙ ኢኮኖሚው ምን ይሆናል ብለው ምን ያህል እያሰቡ እንደሆነ ባላውቅም፣ ፖለቲከኞች ለኢኮኖሚያዊ ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ አሁን ባለው ደረጃም ቢሆን ሐሳብ ቢያቀርቡ ይመረጣል፡፡ በዚህ አንድ ዓመት በተለይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለአንድ አገር ወሳኝ የሚባለውን ኢኮኖሚ ውጤት እንዲኖረው በማድረግ ባላቸው ዕውቀት መደገፍ ይኖርባቸዋል፡፡ የመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲህ ቢሆን ያዋጣል ብሎ የተጠና ሐሳብ ይዞ መቅረብ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡