የጀርመኑ ሲመንስ ኩባንያ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎቹን ለማስፋት በሚያደርገው እንቅስቃሴ በኢነርጂና ተያያዥ ኢንዱስትሪዎች ዙሪያ የአገሪቱን ዘላቂ የልማት ፕሮግራሞች ለማገዝ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር መጋቢት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ተፈራረመ፡፡
የመግባቢያ ሰነድ ስምምነቱ የኢትዮጵያ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2025 በዝቅተኛው ደረጃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የያዘውን ዓላማ ለማገዝ በማሰብ የተደረገ የትብብር ስምምነት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
የመግባቢያ ሰነዱ የአገሪቱን የኃይል አቅርቦትና የመሠረተ ልማት ችግሮች ለማቃለል የሚረዱ እንቅስቃሴዎችን የሚመለከት እንደሆነም ታውቋል፡፡ በስምምነቱ ከተካተቱት ዋና ዋና ነጥቦች መካከል የፋይናንስ ምንጮችን በማፈላለግ የኃይል ማሰራጫ አውታሮችን ማስፋፋትና ማሻሻል፣ በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ ሊገቡ የሚችሉ የኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማቶችን ለመተግበር የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ማቅረብ፣ ቴክኒክና ኢንጂነሪንግ ሥልጠናዎችን ማቅረብ፣ በጤናና ትራንስፖርት ሴክተሮች ላይ ዘላቂ የትብብር አጋርነትን እንዲሁም አነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎችን ማጠናከርና ማስቻል ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ሲመንስ ግዙፍ የአውሮፓ ኩባንያ ሲሆን፣ ከ170 ዓመታት በላይ በምኅንድስና ልቀት፣ ፈጠራ፣ ጥራትና አስተማማኝነት የሚታወቅ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ነው፡፡ ዓመታዊ ገቢውም ከ80 ቢሊዮን ዩሮ በላይ እንደሆነ የኩባንያው ያለፈው ዓመት የገንዘብ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የተጣራ ገቢውም ከስድስት ቢሊዮን ዮሮ በላይ እንደሆነ ተመዝግቧል፡፡
የሲመንስ ኩባንያ የደቡባዊና የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳቢን ዳሊኦሞ፣ ‹‹ይህ ወሳኝ ስምምነት ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ያለንን ጠንካራ ቁርጠኝነት የምናረጋግጥበት ሌላ ዕርምጃ ነው፡፡ አቅምን ያገናዘበና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር፣ ከአካባቢው አገሮች ጋር በመሆን የክህሎት ሽግግር እንዲኖር ለማገዝ፣ ከ1927 ጀምሮ እዚህ እንደነበርን ሁሉ ዛሬም አለን፤›› ሲሉ በጋዜጣዊ መግለጫው አስፍረዋል፡፡
እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን በምታደርገው ጥረት ሲመንስ ኩባንያን ከመሳሰሉት ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ልምድን ካካበቱ ተቋማት ጋር አብሮ በመሥራት የቴክኖሎጂ፣ የማኔጅመንትና ኦፕሬሽን እንዲሁም የፋይናንስ አውታር ልምዶችን ለመቅሰምና ለመተግበር ዕድል እንደሚሰጣት ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ኮሚሽኑ የስምምነቱን ዓላማዎችና ግቦች ለመተግበርና ለመከታተል የሚያስችል ኮሚቴ እንደሚዋቀር ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም በኮሚሽኑ በኩል ስምምነቱ የተካተቱትን ሐሶቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ትግበራ ለመቀየር ከሲመንስ ኩባንያ ጋር በመሆን በከፍተኛ መነሳሳት እንደሚሠሩ አክለዋል፡፡
ሲመንስ ኩባንያ ኃይል የሚቆጥብና ሀብት የማያባክኑ ቴክኖሎጂዎችን ከሚያመርቱ ግዙፍ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ውጤታማ የኃይል ማምረቻና ማስተላለፊያ ምርቶችን በማቅረብ፣ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ መሠረተ ልማቶችን፣ አውቶሜሽን፣ ድራይቭና ሶፍትዌር ምርቶችን በማቅረብ ቀዳሚ ነው፡፡