የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በውጫዊ ገበያዎችና እንቅስቃሴዎች የሚፈተንበት ወቅት ለመቃረቡ ማሳያ እንደሆነ የሚነገርለት የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ወደ ተግባር መሻገር የሚችልበት ደወል ከወደ ጋምቢያ ተስተጋብቷል፡፡
የአፍሪካ የንግድ እንቅስቃሴ ያለ ገዳቢ ሁኔታዎች እንዲካሄድ፣ ምርትና አገልግሎቶችም በታሪፍም ሆነ ታሪፍ ነክ ባልሆኑ ክልከላዎች ከአንዱ ድንበር ወደ ሌላው መሻገር የሚችሉበትን ነፃ የንግድ ገበያ ለመፍጠር ለዓመታት ሲመከርበት የቆየው ውጥን፣ ከወረቀት ወደ ተግባር እንዲለወጥ የሚያደርግ ስምምነት ከጥቂት ወራት በፊት በሩዋንዳ መፈረሙ ይታወሳል፡፡
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር በ52 አገሮች የተፈረሙት ይህ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት፣ በ22 አገሮች ከፀደቀ ወደ ተግባር ለመግባት የሚችልበት ዕድል አለው፡፡ በመሆኑም ጋምቢያ 22ኛዋ ስምምነቱን ያፀደቀች አገር በመሆን የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና መመሥረት የሚቻልበትን ውሳኔ አሳልፋለች፡፡
ኢትዮጵያ ከሁለት ሳምንት በፊት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት መቀበሏንና የገበያውን መፈጠር የአገሪቱ የሕግ አካል አድርጋ ማፅደቋን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡ በዚህም ሳቢያ ስምምነቱ ሕጋዊ አስገዳጅነት እንዲኖረውና በመላው አፍሪካ ዘንድ ተቀባይነት ኖሮት ወደ ሥራ ለማስገባት የአንድ አገር ስምምነት ብቻ ሲጠበቅ ቆይቶ በጋምቢያ አማካይነት ሕጋዊ መሠረት ተጎናፅፏል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት በፍኖተ ካርታ መሠረት ይህንን ነፃ የንግድ ቀጣና ለመመሥረት ስምምነት ላይ ሲደርስ ገበያውን ለመፍጠር ከተስማሙት 44 አገሮች 22ቱ በአገራቸው ከፍተኛ ሕግ አውጪ አካል በኩል ካፀደቁት ገበያውን ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚቻል ቢታወቅም፣ እንደ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገሮች ከስምምነቱ ማፈግፈጋቸው ስምምነቱን በወሬ ሊያስቀረው ይችላል የሚችል ሥጋት ፈጥሮ ነበር፡፡ ይሁንና ስምምነቱን የተቀበሉት አገሮች ቁጥር በመጉላቱ አኅጉራዊው የጋራ ገበያ ስምምነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕውን እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ እያንዳንዱ አገር ምርቱንና አገልግሎቱን ከቀረጥና ከኮታ ውጪ እንዲገበያይ የሚያስችለው ይህ ስምምነት፣ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ጣጣውን ጨርሶ ወደ ገበያ ይገባል ተብሏል፡፡
በዚህም በአፍሪካ አገሮች መካከል የሚደረገውን የእስር በርስ ግብይት አሁን ካለበት ከ12 በመቶ ገደማ ወደ 52 በመቶ ከፍ በማድረግ በዓለም ግዙፉን የጋራ ገበያ ለመፍጠር የሚያስችል ታሪካዊ ስምምነት እንደሚያደርገውም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡
እንደታሰበው ከተሳካ 1.2 ቢሊዮን የአፍሪካ ሕዝብ፣ በአፍሪካ የተመረቱ ሸቀጦችን ከቀረጥ ነፃ ግብይት መፈጸም የሚችልበትን ዕድል ያገኛል፡፡ ነፃ የንግድ ቀጣና እንዲፈጠር ከተስማሙና ካፀደቁ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ እንደመሆኗ እንዴት ትወጣው ይሆን? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ስምምነቱን ሲሸሹና ኢትዮጵያ ለዚህ ዝግጁ አለመሆኗን ሲገልጹ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡ በዚህ ስምምነት ዙሪያ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖዎች እንደሚኖሩ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም በአብዛኛው ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል ሰፊ እንደሚሆን የሚያመለክቱ ትንታኔዎች ከስምምነቱ ቀድሞም ሲደመጡ ቆይተዋል፡፡
እንዲህ ያለው ስምምነት ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ ምን ያስገኛል? ኢትዮጵያስ ምን ያህል ተዘጋጅታለች? የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው፡፡ በተለይም መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የነበረው አቋም በአንድ ጊዜ ተለውጦ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስምምነቱን ማፅደቁ ጥያቄዎች እንዲበራከቱ ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ደካማ በሆነበት ወቅት ወደ ስምምነቱ ትግበራ መግባቷ እንዴት ተወዳዳሪ ያደርጋታል? የሌሎች አገሮች ሸቀጥ ማራገፊያ አያደርጋትም ወይ? የሚለው ጉዳይ ማሳሰቡ አይቀርም፡፡ ስምምነቱ የፋይናንስ ተቋማትንም ጭምር ከተቀረው የአፍሪካ ክፍል ጋር ውድድር ውስጥ የሚከታቸው በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ምን ያህል ተዘጋጅታበታለች የሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ አመለካከቶችን እየተስተናገደ ነው፡፡
የገበያ መፈጠር ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነው ብለው ከሚያምኑት ወገን የሆኑት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ አንዱ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ስምምነት አማካይነት ከአፍሪካውያን ጋር መገበያየቷ እጅግ ይጠቅማታል ይላሉ፡፡ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም፣ ‹‹የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ኤክስፖርት መር በመሆኑና በኢንዱስትሪ ዘርፍም እያደረገች ያለችው እንቅስቃሴ በአፍሪካ ደረጃ ጥሩ ተወዳዳሪ የሚያደርጋት በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ የዚህ ገበያ መፈጠር ኢትዮጵያ 1.2 ቢሊዮን ሕዝብ ታሳቢ አድርጋ እንድትሠራ ዕድል ይሰጣታል ይላሉ፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች በአፍሪካ የተወዳዳሪነት ሚናችንን ከፍ ያደርጉታል የሚሉት አቶ እንዳልካቸው፣ ይህ ውድድር በአፍሪካውያን መካከል ብቻ መካሄዱ መልካም ዕድል ይሉታል፡፡ እንደ አቶ እንዳልካቸው ከሆነ፣ ‹‹በየትኛውም መመዘኛ ሲታይ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ጠቀሜታ ያመዝናል፡፡››
አቶ ዘመዴነህ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የተመረተ ልብስ በአሜሪካና በአውሮፓ ገበያዎች ውስጥ መሸጥ መጀመሩን በማስታወስ፣ ‹‹በእነዚያ ገበያዎች ውስጥ መሸጥ ከቻልን፣ አፍሪካ ውስጥ መሸጥ የማንችልበት ምክንያት የለም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ጥራት ያለው ምርት ማምረት ጀምራለች፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ከአምስትና አሥር ዓመታት በፊት እኛም የምናመርተው ኬንያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሚያመርቱት አንድ ዓይነት የግብርና ምርት ነው፡፡ ቡና፣ ሰሊጥና የመሳሰሉትን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እነሱ ከእኛ የሚፈልጉት አልነበረም፡፡ እኛም ከእነሱ የምንፈልገው አልነበረም፤›› ያሉት አቶ ዘመዴነህ፣ ‹‹አሁን ግን ኢንዱስትሪ መር ስትራቴጂ የያዘች፣ ይህንንም በሥራ ላይ እያዋለች በመሆኗ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ከሚሆኑት አገሮች አንዷ ነች፤›› ብለዋል፡፡ ያለ ታሪፍና ያለ ኮታ በኢትዮጵያ የተመረተ ምርት በየትኛውም የአፍሪካ አገር ውስጥ በቀጥታ መሸጥ የምትችልበትን ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ፣ ጠቀሜታው ላይ ምንም ጥርጥር እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ካለባት የውጭ ምንዛሪ ግኝትና ከወጪ ምርቶች ዝቅተኛነት ችግር አንፃር እንዴት ውጤታማ ይሆናል የሚለውን ሥጋት በተመለከተ አቶ ዘመዴነህ፣ ‹‹የዛሬን ብቻ መመልከት የለብንም፤›› በማለት በአጭሩ ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ሥራ ከጀመሩ ገና ጥቂት ጊዜ በመሆኑ ከዚህ በኋላ በሦስትና በአራት ዓመታት ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስትራቴጂ ሙሉ ለሙሉ ሥራ ላይ ሲውል፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ተጠቀሚ ትሆናለች በማለት ሥጋቱ ተገቢ እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡
ነገር ግን አሁን ያለው የኢትዮጵያ የኤክስፖርት አፈጻጸም ደካማ መሆኑን በመጥቀስ በብርቱ መስተካከል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው ጥሬ ዕቃ ወይም የግብርና ሸቀጥ መሆኑ አንዱ ችግር ነው የሚሉት አቶ ዘመዴነህ፣ ቡናና ሰሊጥ በጥሬው ከመላክ በቀር እሴት ተጨምሮባቸው አለመላካቸው ጉዳት እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ሲታሰብ እነዚህን ምርቶች እሴት ወይም ከፍታ ጨምሮ ለመላክ ጭምር የሚያስችል በመሆኑ፣ የወጪ ንግዱ ማስተካከያ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ማስተካከያዎች ከተደረጉ ለውጡ ለኢትዮጵያ አዎንታዊ ነው ይላሉ፡፡
የተለያዩ ጥናቶች በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አሸናፊ ከሚሆኑት አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ እንደምትሆን እንደሚያሳዩ የአቶ ዘመዴነህ ገልጸዋል፡፡ የንግድ ማኅበረሰቡ ምን ያህል ዝግጁ ነው? ለሚለውም አቶ ዘመዴነህ መልስ አላቸው፡፡ ‹‹ዛሬ በኢትዮጵያ ባሉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በብዛት እየገቡ ያሉት የውጭ ኩባያዎች ናቸው፡፡ የእነዚህ ኩባንያዎች መግባት ባለፉት ዓመታት ከግብፅ ቀጥላ ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ያስገባች አገር እንድትሆን አስችሏታል፡፡ ይህ ትልቅ ውጤት ነው፡፡ አሁንም እየተጠና ባለው ጥናት መሠረት በዓመት ስድስትና ሳባት ቢሊዮን ዶላር የሚገባበት ዕድል አለ፡፡ ስለዚህ ይህ ዕድል እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ኢትጵያውያንም መግባት አለባቸው፤›› ያሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ ግን በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ እየሠሩ ያሉት የውጭ ኩባንያዎች በመሆናቸው ኢትዮጵያውያን ከዕድሉ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባለሀብቶች እንዲገቡ ለማድረግ መንግሥት በፖሊሲ ደረጃ ምላሽ መስጠት እንዳለበትም ይጠቅሳሉ፡፡
ይህንንም መንግሥት እንደ ግዴታ ሳይሆን፣ የውጭ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ጋር በጥምረት እንዲሠሩ የሚያስችል ማበረታቻ በመስጠት ማስተናገድ አበለት ብለዋል፡፡
የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭዎቹ ጋር ተጣምረው እንዲሠሩ ለማድረግ ከሚያስችሉ ማበረታቻዎች መካከል አንዱ የታክስ ዕፎይታ ነው፡፡ የውጭ ኢንቨስተር ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ ሲገባ የሰባት ዓመታት የታክስ ዕፎይታ የሚያገኝ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያውያን ጋር ከሠራ ግን ማበረታቻውን ወደ አሥር ዓመት በማሳደግ የውጭዎቹ ባለሀብቶች ከኢትዮጵያውያን ጋር የመሥራት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
‹‹ከዚህም ሌላ የባንክ ብድር በሚፈለግበት ጊዜ በተቀላጠፈ ደረጃ ብድር አቀርብልሃለሁ፣ የወለድ መጠኑንም ቀነስ አደርግልሃለሁ ከተባለ የውጭ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያን ባለሀብቶች ጋር በመሥራት የሚቻልበት ዕድል በመፍጠር ተወዳዳሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች መፍጠር ይችላል፡፡››
ሌሎች የማበረታቻ አማራጮችንም መጠቀም እንደሚቻል ያወሱት አቶ ዘመዴነህ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥም ሆነ በሌሎች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሚሻል ሲያብራሩም፣ በግላቸው እያደረጉ ያሉትን ተግባር በማስታወስ ነው፡፡
እርሳቸው በሚሠሩበት ፌርፋክስ አፍሪካ ኩባንያ አማካይነት የውጭ ኩባንያዎች ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር ተጣምረው እንዲሠሩ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
አቶ እንዳልካቸው በበኩላቸው ተወዳዳሪ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለመፍጠርና ኤክስፖርት መር ወደሆኑ ኢንቨስትመንቶች እንዲገቡ ለማድረግ፣ ከወዲሁ ሊሠሩ የሚገባቸው ሥራዎች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ በሌላ በኩል ከአፍሪካውያን ብዙ የምናስገባው ሸቀጥ ባለመኖሩ እንደ ጥሩ ዕድል የሚታይ ቢሆንም፣ በዚህ ስምምነት መሠረት ለሚደረገው ውድድር ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ያላቸው ድርሻ እንዲጎላ ሥልጠናዎችና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድ ንግድ ምክር ቤታቸው እየሠራ ያለው ሥራ ስለመኖሩም ጠቁመዋል፡፡
በተለይ የወደፊቱ የአገሪቱ ጉዞ በግሉ ዘርፍ ወደሚመራ የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚያመራ በመሆኑ፣ ጥሬ ዕቃዎች ላይ እሴት በመጨመር ኢንዱስትሪውን ማጎልበት የግድ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዘመዴነህ፣ ይህ ከሆነ ዛሬ በአምስት በመቶ ደረጃ ላይ ያለው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ድርሻ ከሁለት አሥርታት በኋላ 20 እና 25 በመቶ ድርሻው እንዲያድርግ በማድረግ የኢኮኖሚውን ገጽታ መለወጥ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ይጠቅማል ሲባል እንዲህ ያሉ ነገሮች ታሳቢ ተደርገው በመሆኑ ጠቃሚ ነው፤›› የሚለውን ሐሳብ ያጎላሉ፡፡
‹‹በሌላ በኩል ግን በእርግጥ አሁን ላይ ኢትዮጵያዊ ነጋዴ ኢንዱስትሪ ላይ ግን በግል አይመርጠውም፡፡ እኔ ነግጄ ሁለት ሦስት መቶ እጥፍ ትርፍ ማግኘት ስችል ለምን ፋብሪካ እከፍታለሁ ይላል፡፡ መካድ የማይችለው በየትኛውም ዓለም በቶሎ የማትረፍ ፍላጎት አለ፡፡ ሆኖም ኢትጵያዊው ወደ ኢንዱስትሪ መግባት ይኖርበታል ሲባል የረዥም ጊዜ ጠቀሜታው የበለጠ በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ሲያደርግ እርሱንም የሚያበረታታ ፖሊሲ አብሮ መታየት አለበት፡፡››
ለምሳሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ኢትዮጵያውያን ሲገቡ 85 በመቶ የሚሆነው ፋይናንስ የሚያደርገው መንግሥት ነው፡፡ ይህ ጥሩ ማበረታቻ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት ኢትዮጵያውያን የተሻለ አቅም እንዲፈጥሩ ለማድረግ በተለይ ማበረታቻ ከውጭዎቹ ጋር እንዲሠሩ የሚያደርግ ፖሊሲው ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡
ወደ ነፃ የንግድ ቀጣናው መግባት ተወዳዳሪ በመሆኑ ኢትጵያውያን ባለሀብቶችን ከመፍጠር አንፃር ያለው ሥጋት ብቻ ሳይሆን የፋይናንስ ተቋማትንም ጉዳይ የሚመለከት ነው፡፡
እንደ አቶ እንዳልካቸው ማብራሪያ ደግሞ፣ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ከኢትዮጵያ ስምምነት ያደረገችባቸውና በቀጥታ ከምትተገብራቸው የቢዝነስ ዘርፎች ውስጥ አንዱ የፋይናንስ ተቋማት ናቸው፡፡ ይህ ማለት አፍሪካውያን የፋይናንስ ተቋማት በየትኛውም የአፍሪካ አገሮች ይንቀሳቀሳሉ፣ የኢትዮጵያም የፋይናንስ ተቋማት በዚሁ ስምምነት መሠረት ወደ ሌሎች አፍሪካ አገሮች ሄደው ተወዳዳሪ ሆነው ይሠራሉ፡፡
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ባላቸው አቅም እንዴት ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑ ባይቀርም፣ አቶ ዘመዴነህ ደግሞ ለየት ያለ ሐሳብ ይሰነዝራሉ፡፡ እንደ እሳቸው እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት 16 የግል ባንኮች በጣም ትንንሾች መሆናችን በመጥቀስ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ አንድ መቶ ቢሊዮን ዶላር ለመድረስ በተቃረበ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን መደገፍ አይችሉም የሚል እምነት አላቸው፡፡
ይህንንም ደፍረው የሚገልጹት ተቋማቱ ያሉበትን ደረጃ በደንብ የሚታወቅ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያላቸውን ልምድ ያስታወሱት አቶ ዘመዴነህ፣ እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱት እሳቸው በዳኝነት የሚሰየሙበት የአፍሪካ ባንኮች አዋርድ ላይ በየዓመቱ የአፍሪካ ባንኮች አቅምና ምዘና ይታያል፡፡ በዚህ ምዘና ውስጥ ከቶፕ 100 የአፍሪካ ባንኮች ውስጥ ስሙ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ነው፡፡
ይህ ማለት 16 የግል ባንኮች አቅም ያሉበት ደረጃ የቱ ጋር እንደሆነ ስለሚያሳይ፣ በዚህም ምክንያት ለውድድሩ አንድም የኢትዮጵያ ባንክ አቅም ኖሮት አያውቅም፡፡ ስለዚህ እየመጣ ያለውን ውድድር ለመቋቋም ሆነ በአገር ውስጥም አስተዋጽኦ ከፍ ለማድረግ፣ እነዚህ 16 ባንኮች የግድ ወደ ውህደት መግባት ያለባቸው ስለመሆኑ አጥብቀው ይሞግታሉ፡፡
እነዚህ 16 ባንኮች ተዋህደው ወደ አራትና አምስት ቢሆኑ የበለጠ ይጠቅማሉ ብለው፣ በባንክ ቢዝነስ ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን የሒሳብ ደብተራቸው ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሺቱ ማተር እንደሚያደርግ በመጥቀስም የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ፊት ለፊት ለሚጠብቃቸው ይህ ስምምነት የአገራችን የፋይናንስ ተቋማትንም የሚመለከት በመሆኑ፣ ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው በሚያስችላቸው ቁመና ላይ መሆን እንደሚገባቸው የሚጠቁም እንደሆነም ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡
‹‹‹በአገር ሁኔታ ግን የባንኮቹ ቁጥር የበዛው ነው፡፡ ስለዚህ ሰብሰብ ማለቱ ጠንካራ ባንክ ሆኖ ተወዳዳሪ መሆን ያስችላል፤›› በማለት፣ መጪውን ውድድር ለማሸነፍ ከተፈለገ የፋይናንስ ተቋማቱ ከወዲሁ ሊያስቡበት የሚገባው ጉዳይ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡ ይህ አቋማቸው ቀደም ብሎም ሲገልጹት የነበረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ባንኮች በአፈጻጸማቸው ምክንያት ማዋሀድ አይችልም የሚባል ቢሆንም፣ ይህ ዓይነቱ አመለካከት የትም የማያደርስ ነው ይሉታል፡፡ ምክንያቱም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል አማራጩ ተዋህዶ ጠንካራ መሆን ስለሆነ ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም ኢኮኖሚ እየተቀየረ በመሆኑ ከዚሁ ጋር ለመራመድ ከተፈለገ ባንኮቹ በራሳቸው መንገድ ወደ ውህደት እንዲገቡ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
ይህ ካልተቻለ ግን መንግሥት በራሱ መንገድ እንዲዋሀዱ ማድረግ ሊኖርበት ይችላል፡፡ ስለዚህ ባንኮች ውድድር እየመጣባቸው መሆኑን ተገንዝበው መሥራት አለባቸው ይላሉ፡፡ በጥቅል ሲታይ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት መተግበር ለኢትዮጵያ መልካም ዕድል እንደሆነ አስረግጦ መናገር እንደሚችል አቶ ዘመዴነህ ያምናሉ፡፡
አቶ እንዳልካቸውም የንግድ ስምምነቱ ተጨማሪ ሥራዎች የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንደምትሆንና ለዚህም ተባብሮ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ በዓመት ከ17 እስከ 18 ቢሊዮን ዶላር ኢምፖርት የምታደርግና ከዚህ ውስጥ ከአፍሪካ አገሮች ኢምፖርት የምታደርገው 4.1 በመቶ አካባቢ ብቻ በመሆኑ፣ ይህንን ለአፍሪካ የምትልከውን የወጪ ንግድ የማሳደግ ዕድል ይኖራታል፡፡ በአንፃሩ ከአፍሪካ ብዙ ኢምፖርት የምታደርግው ነገር የለም፡፡ ከወጪ ንግድ አንፃርም ሲታይ ደግሞ የኢትዮጵያ ዓመታዊ አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 20 በመቶ አካባቢ የሚሆነው ወደ አፍሪካ አገሮች ከምትልከው የሚገኝ ነው፡፡ ስለዚህ ኤክስፖርት የሚደረገው ከፍተኛ ሲሆን፣ ኢምፖርቱ ደግሞ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አባል በመሆናችን ተጠቃሚ ያደርገናል የሚል እምነት አላቸው፡፡