ካለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስ በማጦዝ ረገድ ቀዳሚ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደነበረውና አሁንም ይኸው ተፅዕኖው በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ጥቁር ደመናውን እንደጣለ የሚገኝ መሆኑ፣ ከልሂቃን እስከ ማኅበረሰቡ ድረስ የሚስማሙበት ግዙፍ ሥጋት ነው።
ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው ሂዩማን ራይትስ ዋች (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች) ተቋም የአፍሪካ ቢሮ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ፊሊክስ ሆርን ‹‹Tackling Hate Speech in Ethiopia›› በሚለው ጽሑፋቸው በመደበኛ የኅትመት ውጤቶችና በበይነ መረቦች አማካኝነት የሚለቀቁ የጥላቻ ንግግሮች፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ለተፈጠሩ አደገኛ የፖለቲካ አዝማሚያዎች ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸውና አሁንም በመንሰራፋት ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ሥጋት መሆናቸውን ይጠቁማሉ።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ፣ አክቲቪስቶችና ሌሎች ሲያደርጓቸው የነበሩ ንግግሮች ከእነ ዓውዳቸው ወይም ከዓውድ ውጪ ተወስደው በተለይ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በመሠራጨታቸው፣ የብሔር ግጭትን በመቀስቀስ እንዲሁም በማባባስ በኢትዮጵያ ሥጋት እንደደቀኑ ያስረዳሉ።
በጥላቻ የተቃኙ ንግግሮች በኢትዮጵያ ለሚስተዋለው የብሔር ግጭትና መካረር ብሎም ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች በማንነታቸው ምክንያት ብቻ ከመኖሪያ አካባቢያቸው እንዲፈናቀሉ፣ ሰዎች በማንነታቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት እስከመገደል የተደረሰበትን ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ትልቁን አሉታዊ ድርሻ እንዳበረከቱ ይጠቅሳሉ።
የጥላቻ ንግግር መልሶ የሚወልደው ጥላቻና መዘዙ ለኢትዮጵያውያንም የተሰወረ ባይሆንም፣ ከሊቅ እስከ ደቂቁ ተዋናይ ሆኖ ሃይ ባይ የጠፋ ይመስላል።
በአገሪቱ ለተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ ሐዋርያ ተደርገው የሚቆጠሩት የወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳም፣ የዚሁ የጥላቻ ንግግር ሰለባ የሆኑ ይመስላሉ። ሰሞኑን ከባለሀብቶች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተወያዩበት ወቅት ከዚሁ ጋር በተገናኘ በምሬት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
‹‹በግሌ ካጠፋሁ መገሰጽ አለብኝ። ልወቀስ፣ ልጠየቅ ይገባል፣ ተገቢም ነው። ነገር ግን በማንነቴ መሰደብ የለብኝም። ምክንያቱም የእኔ ማንነት ጀርባ ከብዙ ሰው ጋር ይተሳሰራል። ያቀያይመናል፣ ይጎዳናል፣ አንድ አያደርገንም፤›› ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል በተወሰኑ ጉዳዮች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሌሎችን ሊጎዳ እንደሚችል፣ ነገር ግን ተጠያቂነት የለም ማለት እንዳልሆነ በወቅቱ የገለጹት አቶ ለማ፣ በወሰኗቸው ጉዳዮች ትክክል ካልሆኑ ሊገሰፁና ሊወቀሱ ዝግጁ መሆናቸውን፣ ከዚህም ባለፈ ማብራርያ እንዲሰጡ ቢጠየቁ ተገቢነት እንደሚኖረውና በዚህም እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
ነገር ግን እንደ መሪ በወሰኗቸው ጉዳዮች ምክንያት በማንነታቸው ሳቢያ ክብረ ነክ ስድብ ሊሰነዘርባቸው እንደማይገባ አምርረው ተናግረዋል።
ለምርምር የወጡ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተወግረው የተገደሉበት፣ ሌሎች ተመሳሳይ አሰቃቂ ግፎች በማንነት ምክንያት ወይም ከማንንነት ጋር በተያያዘ የፖለቲካ አቋም፣ እንዲሁም አውቀው ባራመዱትም ሆነ ፈጽሞ የማይመለከታቸውን የፖለቲካ አቋም እንዳራመዱ በተሠራጨባቸው የሐሰት ወሬ በርካታ ኢትዮጵያውያን ላይ ጉዳት ደርሷል።
ይኼንን መሰሉን አስፈሪ የፖለቲካ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ዋናውን ድርሻ የሚይዘው፣ በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች የሚደረግ የጥላቻ ንግግር መሆኑ ግልጽ ነው።
ማርከሻው ምንድነው?
ማኅበረሰቦችን በማካረር፣ በመካከላቸው ግጭት በመቆስቆስና በማጋጨት፣ እንዲሁም በማባባስ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ቀውስ እያጦዘ የሚገኘውን ጥላቻና ንግግር አደብ ለማስያዝ፣ የፌዴራል መንግሥት በፍጥነት ሊተገበር ይገባል ብሎ የቀየሰው መፍትሔ የጥላቻ ንግግርን ወንጀል በማድረግ የሕግ ተጠያቂነትን መጣል ነው።
ይኼንንም ለማድረግ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታና የሌሎች አገሮች ተሞክሮን በማጥናት ረቂቅ ሕግ አዘጋጅቷል። በአጭር ጊዜ በተዘጋጀው በዚህ ረቂቅ ሕግና የጥላቻ ንግግር የደቀነውን አደጋ የተመለከተ ውይይት ዓርብ መጋቢት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፋካልቲና በአሜሪካ ኤምባሲ የጋራ አስተባባሪነት ውይይት ተካሄዶበታል።
በዚህ መድረክ ላይ የተገኙት የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌድዮን ጢሞጢዎስ (ዶ/ር)፣ በተቋማቸው የተዘጋጀውን ረቂቅ ሕግ ይዘት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
ሪፖርተር ያገኘው ይህ የመጀመርያ ደረጃ ረቂቅ የሕግ ሰነድ በመግቢያ ክፍሉ ሕጉን ማውጣት ያስፈለገበትን ምክንያት ያትታል።
የሕጉን አስፈላጊነት ምክንያት የሚገልጸው ይህ ክፍል እንደሚለው፣ ሰብዓዊ ክብርን የሚያጠቁ ንግግሮችን በሕግ መከልከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኝቱ፣ የጥላቻ ንግግር የሚያስከትለው ግጭትና መገለል ተከባብሮ የመኖር እሴትን የሚያጠፋና ለእኩልነትና ለሰላም ጠንቅ በመሆኑ ነው።
የረቂቅ ሕጉ አንቀጽ አራት የአዋጁ መውጣት ዓላማዎችን የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ ሰዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሰብዓዊ ክብርን፣ የሌሎችን ደኅንነትና ሰላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር ኢንዲቆጠቡ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ እኩልነት እንዲሰፍን፣ መከባበር እንዲኖርና መግባባት እንዲጎለብት ማድረግ በቀዳሚነት የተጠቀሱ ናቸው።
ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አደጋ የሆኑ የጥላቻ አመለካከትና ተያያዥ ወንጀሎችን መከላከልና ማስወገድ ሌላው በዓላማነት የተቀመጠ ድንጋጌ ነው። ከላይ የተጠቀሱትን መርሆች መነሻ በማድረግም ረቂቁ የክልከላ ድንጋጌዎችን ይዘረዝራል።
በዚህም መሠረት ማንም ሰው ሆነ ብሎ የሌላን ግለሰብን፣ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማኅበረሰብን፣ ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ ፆታን፣ አካል ጉዳተኝነትን፣ ዜግነትን፣ ስደተኝነትን፣ ቋንቋን፣ ውጪያዊ ገጽታን መሠረት በማድረግ የሚያጥላላ፣ የሚያንኳስስ፣ የሚያስፈራራ፣ መድልኦ እንዲፈጸም ወይም ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ጥላቻ አዘል ንግግር ወይም መልዕክት እንዳያስተላልፍ ክልከላ ይጥላል።
በዚህም መሠረት ጥላቻ አዘል መልዕክቶችን በመናገር፣ ጽሑፍ በመጻፍ፣ የኪነ ጥበብና ዕደ ጥበብ ውጤት በመሥራት፣ ጽሑፍ፣ ምሥል፣ ሥዕል፣ የኪነ ጥበብና ዕደ ጥበብ ውጤት፣ የድምፅ ቅጂ ወይም ቪዲዮ በማተም፣ በማሳተም ወይም በማሠራጨት ማስተላለፍ በሕግ ክልከላ የሚጣልበት መሆኑን ረቂቁ ያመለክታል። በተጨማሪም መልዕክቶችን ብሮድካስት ማድረግ ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ ማሠራጨት፣ ወይም በሌሎች ማናቸውም መገናኛ መንገዶች ለሕዝብ መልዕክቱ እንዲደርስ ማድረግ የሚከለከል መሆኑን ያመለክታል።
በሌላ በኩል ማንም ሰው ከላይ በተገለጸው አግባብ ጥላቻ የሚያስተላልፍ መልዕክት ለማኅበረሰቡ ወይም ለሦስተኛ ወገን እንዲደርስ በማሰብ፣ በኅትመት ወይም በጽሑፍ መልክ ይዞ መገኘት እንደማይችል ክልከላ ይጥላል።
ከላይ የተዘረዘሩት በወንጀል የሚያስጠይቁና የሚያስቀጡ መሆናቸውን የሚገልጸው ረቂቅ የሕግ ሰነድ፣ አንድ ንግግር እንደ ጥላቻ ንግግር ተወስዶ በወንጀል የማያስጠይቅበትን ልዩ ሁኔታንም ያመላክታል። ንግግሩ በወንጀል ላያስጠይቅ የሚችለው፣ ‹‹ድርጊቱ ለትምህርታዊ ወይም ሳይንሳዊ ምርምር የተደረገ እንደሆነ፣ ሚዛናዊና ትክክለኛ ዘገባ፣ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ተቀባይነት ያለው ትችትና የፖለቲካ ንግግር፣ የማስታወቂያ ወይም ማስጠንቀቂያ አካል እንደሆነ ወይም በቅን ልቦና የሚደረጉ ሃይማኖታዊ አስተምህሮና አተረጓጎም ከሆነ ነው፤›› ሲል ልዩ ድንጋጌ አስቀምጧል።
በልዩ ሁኔታ ከተመለከቱት ውጪ የሆኑት የተከለከሉ ተግባራት በቀላል እስራት ወይም እስከ 10,000 ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚያስቀጡና የተከለከሉት ተግባራት በመፈጸማቸው በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ ከሆነ፣ የተከለከሉትን ተግባራት የፈጸመውና ጥቃት ያደረሰው ግለሰብ አግባብ ባለው የወንጀል ሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን ያመለክታል፡፡
የማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎት የሚሰጥ አካል በአንቀጽ የተከለከሉት ንግግሮች እንዳይተላለፉ ወይም እንዳይሠራጩ የመቆጣጠር ግዴታ እንዳለበት፣ እንዲሁም በሚያቀርበው የግንኙነት ሥርዓትና አገልግሎት የታተሙ ከሆነ ንግግሮችን የማስወገድ ግዴታ እንደሚኖርበት ያመለክታል።
የመናገርና የሚዲያ ነፃነትን ይፃረራል?
የጥላቻ ንግግር ክልከላን በርካታ የሠለጠኑ ዴሞክራሲያዊ አገሮች አሜሪካን ጨምሮ በሕግ ደንግገዋል። ነገር ግን እነዚህ አገሮች የጎለበተ የዴሞክራሲ ሥርዓታቸው የሚያጎናጽፈው የመናገር ነፃነት የተለቀቀ በመሆኑ፣ የመናገር ነፃነት ወሰን የቱ ጋ እንደሚያበቃና የጥላቻ ንግግር ከየት እንደሚጀምር በመለየት ሚዛኑን ማስጠበቅ እንደተቸገሩ ይነገራል።
ይኼንኑ የሚዛን መዛባት በማንሳት በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርን የሚከለክል አዋጅ አያስፈልግም በማለት የሚከራከረው የሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ቢሮ ከፍተኛ ተመራማሪ ፊሊክስ ሆርን፣ ክርክሩን የሚመሠርተው የጥላቻ ንግግር በኢትዮጵያ ሥጋት ስላልሆነ ሕጉ አያስፈልግም በማለት አይደለም።
ይልቁንም የተለያዩ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ የሆኑ አገሮች ጭምር በሁለቱ መካከል ሚዛንን መጠበቅ አለመቻላቸውና የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ መገለጫ ባህሪው ከሚዲያና ከመናገር ነፃነት ጋር የተጣለ መሆኑን የኋላ ታሪኩ መረጃዎች ህያው ምስክር በመሆናቸው፣ የጥላቻ ንግግር ክልከላ ሕጉም ለዚህ ዓላማ ሊውል ይችላል በማለት ነው።
ሆርን ክርክሩን ለማስረፅም የኢትዮጵያ መንግሥት የፀረ ሽብር ሕግ አውጥቶ ሽብርን ከመከላከል ይልቅ የበለጠ ሲጠቀምበት የነበረው ተቀናቃኝ የፖለቲካ ሐሳብ አራማጆችን ለማፈን እንደነበረ፣ በዚህም ምክንያት በርካታ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች በአሸባሪነት ተከሰው በእስር ቤት ፍዳ ማየታቸውን፣ ገሚሶቹ ደግሞ ከአገር መሰደዳቸውን በማሳያነት በማቅረብ ይከራከራል።
የጥላቻ ንግግር ለኢትዮጵያ ሥጋት ቢሆንም በሕግ ከመከልከል ይልቅ፣ የጥላቻ ንግግር መከላከል የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂ መንደፍ የተሻለ መሆኑን በመፍትሔ አማራጭነት ያቀርባል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተካሄደው ውይይት ላይም ተመሳሳይ ሥጋቶች ተነስተው የነበረ ቢሆንም፣ የሕጉ አስፈላጊነት ላይ ግን በአመዛኙ ስምምነት ተንፀባርቋል።
የጥላቻ ንግግር በአገሪቱ ቀውስ ሲፈጥር ቆይቶ አሁን በድንገት መንግሥት ይኼንን ሕግ ለማውጣት መነሳቱ እሳት የማጥፋት ሩጫ እንደሆነ የተገነዘቡ ተወያዮች፣ ሰከን ተብሎ ከሕጉ ፋይዳ በዘለለ ከመናገርና ከሚዲያ ነፃነት ጋር አለመጣረሱን የሚከታተል ተቋማዊ ዝግጁነትን ማጤን እንደሚያስፈልግ፣ የመቆጣጠሪያ ሥልቱ በሌለበት ተፈጻሚ እንዲሆን የሚደረግ ሕግ ከፋይዳው ይልቅ ነፃነትን እንደሚጎዳ፣ ሥልጣን ላይ ለሚገኝ የፖለቲካ ቡድን የፖለቲካ መሣሪያ አለመሆኑን ማረጋገጥ እንደማይቻል በመጥቀስ ሥጋቶችን ጠቃቅሰዋል።