Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች ለደረሰባቸው ግድያና ዝርፊያ የክልሉንና የፌዴራል መንግሥትን ተጠያቂ አደረጉ

የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች ለደረሰባቸው ግድያና ዝርፊያ የክልሉንና የፌዴራል መንግሥትን ተጠያቂ አደረጉ

ቀን:

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በአጣዬ ከተማና ዙሪያው ከመጋቢት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ጀምሮ በታጣቂዎች ለደረሰባቸው ግድያ፣ ዘረፋና መፈናቀል ተጠያቂዎቹ የአማራ ክልል መንግሥትና የፌዴራል መንግሥት መሆናቸውን ተናገሩ፡፡

ሁለቱን አካላት በዋናነት ተጠያቂ ያደረጉበትን ምክንያት ነዋሪዎቹ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከወራት በፊት በክልሉና ከአካባቢው ወጣ ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች በርከት ያሉ የማይታወቁ ሰዎች ወታደራዊ ሥልጠና የሚመስል እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን በመስማታቸው ለክልሉ መንግሥት አስታውቀዋል፡፡ በመቀጠልም ባለፈው ሳምንት ውስጥ ከሚሴ ችግር ሲፈጠር በቀጣይ ወደ አጣዬና አካባቢው ሊመጣ እንደሚችል በመሥጋት፣ ለክልሉና ለአካባቢው የፀጥታ አካላት ጥንቃቄ እንዲደረግ በተለያዩ መንገዶች ቢያሳውቁም ምንም ባለመደረጉ የፈሩት ነገር እንደደረሰባቸው አስረድተዋል፡፡

ችግሩ ከተከሰተ ከቅዳሜ መጋቢት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊት በከተማው በጊዜ ቢደርስም፣ ከበላይ ኃላፊዎች ትዕዛዝ እንዳልተሰጠው በመግለጽ ድርጊቱን በዝምታ ማለፉ ጉዳታቸውን የከፋና በመጠንም የበዛ እንዲሆን ማድረጉን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ሁለቱም አካላት (የክልሉና የፌዴራል) ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አክለዋል፡፡

በተለይ በአጣዬ ከተማና ዙሪያው በታጣቂዎቹ የደረሰው አስከፊ ግድያ፣ ዝርፊያና አፈና ላለፉት 27 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ሁለቱም አካላት የሐዘን መግለጫና ማፅናኛ ቃላትን ከመናገር ባለፈ፣ የድርጊቱ ፈጻሚዎችን በአስቸኳይ በሕግ ተጠያቂ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የኦሮሞና የአማራ ማኅበረሰቦች ለዘመናት አንድ ሆነው በፍቅርና በመተሳሰብ በኖሩበት ከተማና አካባቢ የሞተ ሰው እንኳን ለመቅበር በማያስችል ሁኔታ በሠለጠነና ዘመናዊ መሣሪያ በታጠቀ ኃይል ሲገደሉ፣ ሲዘረፉና ታፍነው ሲወሰዱ ማየትና መስማት እንደ አገር አሳፋሪና የሚያም መሆኑንም አክለዋል፡፡ የአገር ድንበር፣ የሚያስተዳድረውን ሕዝብና ከውጭ ያለውን ግንኙነት በሰመረ ሁኔታ የሚይዝ መንግሥት ባለበት አገር፣ በሕገወጥ ታጣቂዎች ተወሮ የግፍ ግፍ እስከሚፈጸም ድረስ ቀድሞ መቆጣጠር አለመቻሉ እንዳስገረማቸውም ገልጸዋል፡፡

በአጣዬ ከተማ ጥቃቱ እንዴት እንደተጀመረ የከተማው ነዋሪ የሆኑት አቶ ሙሉዓለም ፈይሳ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ቅዳሜ ከቀትር በኋላ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ከወትሮው ለየት ባለ ሁኔታ ሦስት ሦስት ሆነው መሣሪያ የያዙ ሰዎች ግራና ቀኝ አስፋልት ዳር ተቀምጠው ታይተዋል፡፡ ትንሽ ቆይተው ባልታሰበ ሁኔታ ወደ ላይ መተኮስ ጀመሩ ይላሉ፡፡ በሁኔታው የተደናገጡ ነዋሪዎች ግማሹ ወደ ቤታቸው ሲገቡ፣ ግማሹ በመሯሯጥ ላይ እያሉ ታጣቂዎቹ እየተኮሱ ወደ 02 ቀበሌ መሄዳቸውን ያስረዳሉ፡፡

ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ የዳሸን ባንክ አጣዬ ቅርንጫፍ ረዳት ሥራ አስኪያጅ መቁሰላቸውን፣ ሌላ አንድ የባንኩ ሠራተኛ መገደላቸውንም እማኞች ተናግረዋል፡፡

በቀበሌው ውስጥ (02 ቀበሌ) ያሉ ነዋሪዎች ትጥቅ እንዳላቸው ስለሚወራ፣ ታጣቂዎቹ ቤት ለቤት አሰሳ መግባታቸውንና ነዋሪዎችን እያስገደዱ አፍነው መውሰዳቸውን አክለዋል፡፡ ተጣቂዎቹ ድርጊቱን ሲፈጽሙ በዜሮ አንድ ቀበሌ ጫፍ ላይ ከተሠራ ባለሦስት ፎቅ ሕንፃ ላይ ያለማቋረጥ በሚተኮስ ጥይት ሽፋን እየተሰጠ ድርጊቱ እንደተፈጸመም አቶ ሙሉዓለም ተናግረዋል፡፡ ታጣቂዎቹ በደንብ የተዘጋጁ፣ ቀድመው ቦታ የያዙና ዘመናዊ መሣሪያም ያላቸው በመሆናቸው በአካባቢው ያለውን ሕዝብ እየገደሉ፣ እየዘረፉና እያፈኑ ለመውሰድ ለእነሱ ቀላል እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ ቅዳሜ ለሊቱን አፍነው የወሰዱት ፆታ ሳይለዩ ቢሆንም፣ ሴቶቹን ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደመለሷቸውና ወንዶቹን እንዳልለቀቋቸው አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ሙሉዓለም የዓይን ምስክርነት የሞቱት ሰዎች ብዛት ከ15 እንደሚበልጥ፣ በርካቶች በጥይት ተመትተው የአካል ጉዳት የደረሰባቸው የሕክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ነው፡፡ ዝርፊያ መፈጸሙን፣ ጥቂት ቤቶች መቃጠላቸውንና ከአጣዬ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ አንድ የእምነት ተቋም መቃጠሉ ቢነገርም አለማረጋገጣቸውን አስረድተዋል፡፡ ምንም ይሁን ምንም የድርጊቱ ፈጻሚዎችን መንግሥት ሳይውል ሳያድር በቁጥጥር ሥር በማዋል፣ በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባሩ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችና በርካታ ነዋሪዎች በአጣዬ ከተማና ዙሪያው የተፈጸመውን ድርጊት አስመልክተው፣ ሰላማዊ ሠልፍ በማድረግ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡ አጣዬ፣ ካራ ቆሬ፣ ከሚሴ፣ ማጀቴ፣ ጨረርቶ፣ ኤፍራታና ሌሎች አካባቢዎች ባሉ ነዋሪዎች ላይ የደረሰው ግድያ፣ ዝርፊያና አፈናን መንግሥት በአስቸኳይ እንዲያስቆምና ‹‹ሕገወጥ ታጣቂዎች ናቸው›› እየተባለ በጥቅል መፈረጁን ትቶ፣ ከውስጥም ከውጭም ያሉ ተሳታፊዎችን በማጣራት አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወስድና ለሕግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል፡፡

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለተለያዩ ሥራዎች ወደ ውጭ አገሮች በወጡባቸው የተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚነሱ ግጭቶችና ሁከቶች ዜጎች እየሞቱ፣ እየተዘረፉና እየተፈናቀሉ በመሆናቸው ትኩረት ሰጥተው ምክንያቱን ጭምር እንዲያጣሩም ጠይቀዋል፡፡ ተወላጆቹ ባወጡት የአቋም መግለጫ በአጣዬና ዙሪያው ግድያ፣ ዘረፋና አፈና እንዲቆም፣ ችግሩን የፈጠሩና ያስፈጠሩ ተለይተው ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በቂ ኃይል እንዲመድብና ለተዘረፉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ቁሳዊ ዕርዳታ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡     

በአጣዬና አካባቢው የደረሰውን ግድያ፣ ዘረፋና አፈና የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎችም የተቃወሙ ሲሆን፣ ከመጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ጀምሮ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በከተማው ሰላማዊ ሠልፍ በማድረግ ተቃውአቸውን ገልጸዋል፡፡ የመንግሥትና የግል ተቋማትም አገልግሎት ሳይሰጡ ተዘግተው መዋላቸውን፣ ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን ሸዋ ከእሑድ መጋቢት 29 ቀን እስከ ሚያዝያ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ጉዞ ተቋርጦ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ከሚያዝያ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሁሉም አካባቢዎች እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን፣ በተለይ ዋናው ችግር በተፈጠረበት አጣዬ ከተማና መዳረሻ አካባቢዎች እንቅስቃሴዎቹ ሁሉ  በሥጋት ውስጥ እንደሆኑ በአካባቢው የተጓዙ ገልጸዋል፡፡

በአጣዬ ከተማ የደረሰው ግድያ፣ ዘረፋና አፈናን በሚመለከት የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር የፀጥታ ጉዳዮች መምርያ ኃላፊ አቶ ካሳሁን እምቢአለ ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፣ ቀደም ባሉት ቀናት ኬሚሴ ውስጥ ችግር ተፈጥሮ የፀጥታ መዋቅሩ ዕርምጃ ወስዶ ነበር፡፡ በዚያ ዕርምጃ ምክንያት ብቀላ በሚመስል ሁኔታ ድርጊቱ ወደ አጣዬ ሊዛመት መቻሉን፣ ጥቃቱን የሚፈጽመው በተለየ መንገድ የተደራጀ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ልዩ መሣሪያ የታጠቁ የሠለጠኑና ቦታ ይዘው ጥቃት የሚፈጸሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ተቀናጅቶ የማያዳግም ዕርምጃም እንደሚወስድም ገልጸዋል፡፡  

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ምክር ቤት ያወጣውን መግለጫ አብራርተዋል፡፡ ምክር ቤቱ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና በሰሜን ሸዋ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ሰላም መደፍረሱን አስታውቆ ሕይወታቸውን ላጡ፣ አካላቸው ለጎደለና ንብረታቸው ለወደመባቸው ጥልቅ ሐዘኑን ገልጿል፡፡ በመሆኑም የፌዴራልና የክልል የፀጥታ አስከባሪ ተቋማት አስፈላጊውንና ተመጣጣኝ ዕርምጃ እንዲወስዱም ትዕዛዝ መስጠቱንም አቶ ንጉሡ አክለዋል፡፡

ብጥብጡን ባቀነባበሩት፣ ባነሳሱትና በፈጸሙት አካላት ላይ በትኩረት በመሥራት ለሕግ እንዲቀርቡ እንደሚያደርግ ምክር ቤቱ የሰጠውን መግለጫ አብራርተዋል፡፡

ግርግሩን ተጠቅመው ለዘመናት አብረው የኖሩትን ማኅበረሰቦች ለመከፋፈልና ለመለያየት፣ በድረ ገጾች፣ በፌስቡክና በተለያዩ የጥላቻ ንግግሮች የሚነዙ ስላሉ ሕዝቡ እንዲጠነቀቅ አቶ ንጉሡ አሳስበዋል፡፡

ችግሩ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች መከላከያ ሠራዊቱ ገብቶ የማረጋጋት ሥራ እያከናወነ መሆኑን የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ ኮሎኔል ተስፋዬ አያሌው ለመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል፡፡ ኮሎኔሉ እንደተናገሩት፣ የመከላከያ ሠራዊት ችግር ተፈጥሯል በተባለበት ቦታ ሁሉ ዘው ብሎ አይገባም፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የክልሉ መንግሥት ችግሩ ከአቅሙ በላይ መሆኑን አሳውቆ፣ ዕርዳታ ሲጠይቅ ብቻ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ክልሉ በጠየቀው መሠረት መከላከያ ገብቶ ማረጋጋቱንና የመቆጣጠር ሥራ እያከናወነ መሆኑን ኮሎኔል ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በመሆን የችግሩን መንስዔ በማጣራትም ዕርምጃ እንደሚወስድም አክለዋል፡፡ ተዘግተው የነበሩ የደብረ ብርሃን፣ የደብረ ሲና፣ የኮምቦልቻና የደሴ መንገዶችም ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ከግጭቶቹ ጀርባ ማን እንዳለ ተጣርቶ ዕርምጃ እስከሚወሰድ ድረስ፣ ኅብረተሰቡ ተረጋግቶ መደበኛ ሥራውን እንዲያከናውንም አሳስበዋል፡፡  

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ማክሰኞ ሚያዝያ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች የዴሞክራሲ ምኅዳሩ ሰፍኖ ማንኛውም አካል በነፃነት የመደራጀት፣ የፈለገውን የፖለቲካ አጀንዳ በሰላማዊ መንገድ እንዲያራምድ፣ የአገሪቱ ሕዝቦች ለዘመናት የታገሉለትንና የከፈሉለትን ውድ መስዋዕትነት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን እንዲሆን በርካታ ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ሆኖም አንዳንዶች የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በሠለጠነና በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ከማራመድ ይልቅ፣ የብሔር ጽንፈኛ አስተሳሰብን አንግበው በመነሳት ሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴን ከሕገወጥና ከግጭት ጋር በማጣቀስ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ እንደተደረሰበት ገልጿል፡፡

ሰሞኑንም በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና የሰሜን ሸዋ ዞን አንድንድ ወረዳዎች ውስጥ በእነዚህ ኃይሎች ምክንያት ግጭቶች በመከሰታቸው ሰው መሞቱን፣ አካል መጉደሉንና የንብረት ጉዳት መድረሱን ጠቁሟል፡፡ ለደረሰው አጠቃላይ ጉዳት ኦዴፓ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጾ፣ በሕዝብ ደም በሚነግዱ የፖለቲካ ቁማርተኞች የተፈጸመውን ጥፋት ማውገዙን አስረድቷል፡፡

የግጭቱን ጠንሳሾችና ተሳታፊዎች ለሕግ ለማቅረብ በሕግ አስከባሪ አካላት የሚደረገውን የሕግ የበላይነት የማስከበር እንቅስቃሴ እንዲሳካ፣ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...