በሁለተኛ ማጣሪያ ከካሜሮን ይገናኛሉ
በአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በጥንካሬያቸው ከሚጠቀሱ ብሔራዊ ቡድኖች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) አንዱ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤት እየራቀው በመምጣቱ በጥንካሬው ሲጠቀስ የቆየውን የሴቶች እግር ኳስ፣ አሁን ላይ ምድቡ ወደ የማጣሪያ ማጣሪያ እንዲካተት ግድ ብሎታል፡፡
በቶኪዮ የ2020 ኦሊምፒክ ተሳትፎ የመጀመሪያ የማጣሪያ ማጣሪያውን ከኡጋንዳ አቻው ጋር በደርሶ መልስ አድርጎ በሜዳው 3 ለ 2፣ ከሜዳው ውጪ ደግሞ 1 ለ 0 በድምሩ 5 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፎ ለሁለተኛው ማጣሪያ የበቃው የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሊምፒክ ቡድን፣ በነሐሴ ወር የካሜሮን አቻውን በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚገጥም የአኅጉራዊው ኮንፌዴሬሽን መርሐ ግብር ያስረዳል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ ዋና አሠልጣኝ ሰላም ዘርዓይ የሚሠለጥኑት ሉሲዎቹ፣ ቀጣይ ተጋጣሚያቸው ካሜሮን በሴቶች እግር ኳስ ከአኅጉራዊ ተሳትፏቸውም በላይ፣ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በሚያዘጋጃቸው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን በመወከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይጠቀሳል፡፡ ቡድኑ ከሉሲዎቹ ጋር ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ያከናወነ ከመሆኑ አኳያ ከወዲሁ ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅበት ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማክሰኞ ሚያዝያ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ሉሲዎቹን ጨምሮ፣ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ በመጀመሪያው ማጣሪያ በማሊ አቻው በድምር ውጤት 5 ለ 1 ተሸንፎ የተሰናበተውን የኦሊምፒክ ቡድን ተሳትፎ ግምገማ አድርጓል፡፡
ፌዴሬሽኑ የወንዶቹ ቡድን ያስመዘገበውን ውጤት ተከትሎ በተለይም ከአሠልጣኝ የመምረጫ መሥፈርትና ተያያዥ ክንውኖች ጋር ግልጽነት የጎደለው አሠራር ይከተላል በሚል በስፖርቱ ቤተሰብ ዘንድ ቅሬታዎችና ትችቶች ሲቀርቡበት መሰንበቱ አይዘነጋም፡፡