Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከሦስት ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች የውኃና የንጽሕና ችግሮችን እየተጋፈጡ ነው

ከሦስት ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች የውኃና የንጽሕና ችግሮችን እየተጋፈጡ ነው

ቀን:

የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች በከፊል በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

በኢትዮጵያ ከ3.3 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ ተፈናቃዮች ከፍተኛ የሆነ የንጹሕ መጠጥ ውኃና የመፀዳጃ ቤት ዕጦት ገጥሟቸዋል፡፡ አጋጣሚው ለውኃ ወለድና ለተለያዩ የሆድ ትላትል በሽታዎች እየዳረጋቸው እንደሚገኝ፣ የክትባት እጥረትና የመጠለያ ዕጦት፣ እንዲሁም የሰው ኃይል እጥረትና የደኅንነት ሥጋቶች ችግሩን ውስብስብ እንዳደረጉት የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በየነ ሞገስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፣ የተከሰተውን የክትባት እጥረት ለመፍታት እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን፣ ተቀሩት ተግዳሮቶች ግን ከፍተኛ ርብርብ ይጠይቃሉ፡፡ በተለይ የመጠለያ ዕጦቱ ከክረምት ወራት ጋር ተያይዞ የከፋ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት ሊታሰብበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የደኅንነት ሥጋቶች የጤና ምላሽ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም የሚል ሥጋት እንዳለም ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በትግራይ፣ በአማራ፣ በሶማሌ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደር ከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሲሆኑ፣ ከ200,000 የሚበልጡት ደግሞ የሚያጠቡና ነፍሰ ጡር እናቶች መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፣ በጌዲኦ ዞን ብቻ በአሁኑ ወቅት ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው 675,000 ተፈናቃይ ወገኖች ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 103,585 ሕፃናት እንዳሉ ይገመታል፡፡ ከእነዚህም መካከል 82,700 በሚሆኑ ሕፃናት ላይ የምግብ እጥረት ልየታ ተደርጎባቸው 16,179 ያህሉ ለመካከለኛ፣ 2,282 የሚሆኑት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡

ከዚህም ሌላ 50,623 በሆኑ እናቶች ላይም የምግብ ልይታ ተካሂዶ 23,346 የሚሆኑ እናቶች መካከለኛ የሆነ የምግብ እጥረት እንዳለባቸው መረጋገጡን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በጤና በኩል ያለው ተጋላጭነት ሲፈተሽም የመጀመርያው የተቅማጥ፣ ሁለተኛው የሆድ ጥገኛ ትላትል፣ ቀጥሎ የመተንፈሻ አካላት ችግርና እከክ በተፈናቃዮች መካከል እየተከሰቱ ካሉ የጤና ችግሮች ተጠቃሾች መሆናቸውን ተደርሶበታል፡፡ በተለይም በሕፃናት ላይ የሚታዩ ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት፣ እንዲሁም የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥነ ልቦና ችግሮች ሳይጠቀሱ መታለፍ የሌለባቸው ተግዳሮቶች እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተጠቀሱት ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ ተፈናቃዮች የጤና ምላሽና ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱን፣ ከዛሬ ሳምንት ጀምሮ ደግሞ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ መስጫ ማዕከልን በማደራጀትና በቋሚነት የሚሠራ ግብረ ኃይል አቋቁሞ የጤና ምላሹን ሥራ አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

ከመንግሥትና ከግል የሕክምና ተቋማት የተውጣጡ ከ350 በላይ የሕክምና ባለሙያዎች (ሐኪሞች፣ ነርሶች) ተፈናቃዮች ባሉባቸው አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት መስጠታቸውን፣ እስካሁን ድረስ ለተፈናቃዮች የቀረቡት መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች በገንዘብ ሲተመን ከ468 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ከኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ካሉ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መካከል በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን ኩፍኝ ለመግታት ክትባት በተሰጠባቸው የሶማሌ ወረዳዎች የቀነሰ ቢሆንም፣ በሌሎች ወረዳዎች ግን እንደ አዲስ እየተከሰተ ይገኛል፡፡ እንደ ዶ/ር በየነ አገላለጽ፣ ለዚህም ምላሽ የሚሆን ክትባት በዓለም የጤና ድርጅት በኩል ተጠይቆ ውጤቱ በመጠበቅ ላይ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ የነበረው ወረርሽኝ ግን በተካሄደው የክትባት ዘመቻ የተጠቂዎች ቁጥር መቀነሱን ምክትል ዳይሬክተሩ ሳይናገሩ አላለፉም፡፡

በአፋር ክልል አዳር ወረዳ በኢልውሃ ከተማ 991 ሰዎች በተነሳው የችንኩንጉኒያ ትኩሳት መጠቃታቸውን፣ በዚህም የተነሳ ለሁሉም የሕክምና አገልግሎት መሰጠቱንና ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ዶ/ር በየነ መግለጫ በፌዴራል ማረሚያ ቤት የአሌልቱ ፖሊስ ማሠልጠኛ ማዕከል በተከሰተው የጉድፍ ወረርሽኝ ከተያዙት 35 ሰዎች መካከል 33ቱ በሕክምና ድነው መደበኛ ሥራቸውን በማከናወን ላይ እንዳሉና ሁለቱ ግን ክትትል እየተደረገላቸው ነው፡፡

በደቡብ ጎንደርና በቤንች ማጂ ዞኖች የተከሰተው የአባሰንጋ ወረርሽኝ በቁጥጥር ሥር ቢውልም በደቡብ ጎንደር ከተጠቁት 17 ሁሉም ሲፈወሱ፣ በቤንች ማጂ በበሽታው ከተያዙት 57 ሰዎች የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ለቀሩት ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን በሐመርና በና ፀማይ ወረዳዎች የተከሰተው የአዕዋፍና የዶሮዎች ሞት እስካሁን ድረስ በሰው ሕይወት አለመከሰቱን ያመለከቱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ሆኖም ግን ከአዕዋፋት ወይም ከዶሮዎች ወደ ሰው ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎች መኖራቸውን በመገንዘብ ክስተቱን የሚያጠናና የሚመረምር የባለሙያዎች ቡድን ወደ ሥፍራው መላኩን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከተቋቋመባቸው ተግባራትና ኃላፊነቶች መካከል የምርምር ተግባራትን ማከናወን፣ የላቦራቶሪ አገልግሎቶችን መስጠትን፣ በኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ማዕከል አማካይነት የበሽታዎች ቅኝት፣ የበሽታዎች ቅድመ ልየታ፣ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ዝግኙነትና አደጋዎች ማከናወን ይገኝበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...