Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የበለጠ ጌራ ጫካ ቡናን የማልማት ፋይዳ

የጫካ ቡና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ተፅዕኖ መሸከም የሚችልና በውጭውም ዓለም ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው ነው፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ቡና በብዛት የሚገኝባቸው ጫካዎች በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ተጋርጦባቸዋል፡፡ እርሻን ለማስፋፋት ሲባል የሚደረግ የደን መጨፍጨፍ፣ በአካባቢዎቹ ላይ የሕዝብ ቁጥር መጨመር በተለይም መሬት የሌላቸው ወጣቶች መብዛት፣ ለቡና ገበሬዎች በቂ ማበረታቻ አለመስጠት፣ የጫካ ቡናን ጠብቆ ለማቆየት ኃላፊነት የሚወስዱ መንግሥታዊ ቢሮዎችም ሆኑ ሌሎች ተቋማት በግልጽ አለመኖር፣ ጫካን፣ ብዝኃ ሕይወትን ወይም የቡና ምርትን አስመልክቶ የሚወጡ ስትራቴጂዎች እርስ በርስ መጣረስ እንዲሁም በቡና ዙሪያ የሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ አለመኖር የጫካ ቡናን ለማምረትም ሆነ በጫካ ቡና የሚተዳደሩ ገበሬዎችን ለመታደግ እንቅፋት ከሆኑ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ የጫካ ቡና በተለይም አረቢካ ቡና ከሚገኝባቸው አካባቢዎች የበለጠ ጌራ ጫካ ይጠቀሳል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ከጅማ ዞን 45 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው በለጠ ጌራ ጫካ ከአረቢካ ቡና በተጨማሪ ለቱሪስት መስህብ የሆኑ አዕዋፋት፣ አጥቢና ተሳቢ፣ በውኃ የሚኖሩና የተለያዩ እንስሳት የሚገኙበትም ነው፡፡ ከሁሉም ግን አሁን ላይ ትኩረት ያገኘው የጫካ ቡናው ሲሆን ለዚህም የኦሮሚያ አካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን፣ የኦሮሚያ ደንና የዱር እንስሳት ድርጅትና የጃፓን የልማት ተራድኦ ድርጅት (ጃይካ) በጋራ የሚሠሩበት የበለጠ ጌራ ጫካ ቡና ሰርተፍኬሽን ፕሮጀክት ዓይነተኛ ሚና  አለው፡፡ እ.ኤ.አ. ሐምሌ 2014 የተጀመረውና እስከ 2020 የሚቆየውን ፕሮጀክት አስመልክቶ የበለጠ ጌራ ጫካ ቡና አርሶ አደሮች፣ ገዥዎች፣ የጃይካና የክልሉ የሚመለከታቸው አካላት ተወካዮች በተገኙበት ፕሮጀክቱ ስላስገኘው ጠቀሜታና ያለበትን ሁኔታ አስመልክቶ ከሳምንት በፊት ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ከተሳተፉት መካከል የበለጠ ጌራ ጫካ ቡና ሰርተፍኬሽን ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ቂጡማ ጃለታ ይገኙበታል፡፡ ምሕረት ሞገስ በፕሮጀክቱ ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡-የቡና ሰርተፍኬሽን ፕሮጀክቱ በጅማ ዞን በምን ያህል ወረዳዎች ላይ ይተገበራል?

አቶ ቂጡማ፡- በሁለት ወረዳዎች ማለትም በሸቤ ሰምቦና በጌራ ወረዳዎች ላይ ነው፡፡ ሁለቱም ወረዳዎች የሚገኙት በበለጠ ጌራ ጫካ ውስጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቱ ሲጀመር በደን ጥበቃ ላይ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ቡና ማልማቱም ተካቷል፡፡ ስለዚህ ቢያብራሩልን?

አቶ ቂጡማ፡- ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ. በ2014 ሲጀመር ገበሬዎቹ ደኑ ውስጥ ያለውን ቡና እየለቀሙ ደኑን እንዲንከባከቡ ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ የጀመረውም ደን ጥበቃ ላይ ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን አርሶ አደሩ ደን በመንከባከብ ብቻ ምን እንጠቀማለን የሚል ጥያቄ ስላነሳ የቡና ሰርተፍኬሽን ሥራ ተጀመረ፡፡ አርሶ አደሩ የጫካውን ቡና ደረጃ እየጠበቀና በኮኦፖሬቲቭ እየተደራጀ ለኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት እየሸጠ ድርጅቱ ደግሞ በጃይካ ኩባንያ በኩል ወደ ጃፓን ይልካል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ አሠራር ገበሬውን ምን ያህል ጠቅሟል?

አቶ ቂጡማ፡- አሁን ከላክነው ቡና አርሶ አደሩ 1.9 ሚሊዮን ብር ትርፍ አግኝቷል፡፡ አርሶ አደሩ ከደኑ ጥበቃ ባለፈ ቡና ላይ እንዲሠራ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ ዘጠኝ ጊዜ ቡና ወደ ጃፓን ልከናል፡፡ እስካሁን ሌላ ገዥ ስላላገኘን የምንልከው ወደ ጃፓን ብቻ ነው፡፡ ሌላ ገዥም እየፈለግን ነው፡፡ የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ከቡና ገበሬው ገበያው ላይ ካለው ዋጋ በኪሎ የሁለትና ሦስት ብር ልዩነት ጨምሮ ነው የሚገዛው፡፡ ብድርም ያመቻቻል፡፡ አርሶ አደሩ ደን እየጠበቀ ቡና እንዲያለማ ለማበረታታትም ብድሩ ያለ ወለድ ይሰጣል፡፡ ቡናው የሚሸጠው ከነጀንፈሉ ነው፡፡ ለውጭ የሚላከውን ደግሞ ድርጅቱ አጥቦና ቀሽሮ ያቀርባል፡፡ የጃፓን ገዢዎች አርሶ አደሩ የአካባቢ ጥበቃንም እየሠራ ስለሆነ ለማበረታታት በገዙት የቡና መጠን ተጨማሪ ብር በኪሎ ይከፍላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለማን ነው የሚከፍሉት?

አቶ ቂጡማ፡- ከሚመጣው ክፍያ 30 በመቶ ኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ይወሰድና 70 በመቶው ለሁሉም ኮኦፖሬቲቮች ባመጡት የቡና መጠን ልክ ይከፋፈላል፡፡

ሪፖርተር፡- የበለጠ ጌራ ጫካን የተፈጥሮ ቡና የሚያለሙት ምን ያህል አርሶ አደሮች ናቸው?

አቶ ቂጡማ፡- በሁለቱ ወረዳዎች 124 የጫካ ጥበቃ ላይ የሚሠሩ ማኅበራት አሉ፡፡ እነዚህ ማኅበራት በሰባት ኮኦፖሬቲቭ ሥር ተደራጅተዋል፡፡ በጫካው ተጠቃሚ ብለን የመዘገብናቸው 10 ሺሕ ያህል አርሶ አደሮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ደኑ ተመናምኖ በነበረበት ሰዓት የቡና ምርቱም ቀንሶ እንደነበር ይነገራል፡፡ በጫካው ውስጥ ያለው ቡና የመስጠት አቅሙ እየተሻሻለ ነው?

አቶ ቂጡማ፡- አርሶ አደሩ ጫካ ውስጥ ገብቶ መኖር የጀመረው ቀድሞ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ከመምጣቱ በፊት ገበሬው ጫካውን እየመነጠረ መሬት ያስፋፋ ነበር፡፡ መንግሥት ከሥፍራው ያስለቅቀናል የሚል አመለካከትም ነበረው በመሆኑም ጫካውን እየመነጠሩ መኖሪያቸውን ሜዳ ያደርጉ ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ ተግባዊ ሲሆን በጫካ ውስጥ የመኖር መብት እንዳላቸው ተረጋገጠላቸው፡፡ መኖር እንደሚችሉ፣ በዛው ልክ ደኑን እንዲንከባከቡ ስለተደረገ፣ ‹‹የእኛ ደን ነው›› የሚል አመለካከት አዳብረዋል፡፡ ›ባዶ ቦታዎች ላይ ለሽያጭ የሚሆኑ ዛፎች እየተከሉ ይጠቀማሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ጫት ይተከላል ይባላል? ይህ ችግር አልሆነም?

አቶ ቂጡማ፡- ቤታቸው አካባቢ ጓሮ ላይ ይተክላሉ፡፡ ይህ ለእኛ ችግር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኮኦፖሬቲቭ አክሲዮን መግዛት ለገበሬው ጠቀሜታ ቢኖረውም ብዙዎች አልገቡም እዚህ ላይ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ቂጡማ፡- በፕሮጀክቱ ሥር ያሉ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ነገር ግን አንድ ገበሬ የኮኦፖሬቲቭ አክሲዮን ካልገዛ የትርፍ ተከፋይ (ዲቪደንድ) አያገኝም፡፡ በሸጣት ልክ ብቻ ነው የሚያገኘው፡፡ ስለሆነም አርሶ አደሩ ሼር እንዲገዛ እያበረታታን ነው፡፡ በሌላ በኩል የቡና ምርት እየጨመረ ነው፡፡ ነገር ግን ቡናውን ኦዲት የሚያደርጉ የገበሬ አባላት ይቀንሱታል፡፡ በጫካው ውስጥ እየሠሩ ያለመመዝገብ ችግር አለ፡፡ ይህን ለመቀየር እየሠራንበት ነው፡፡ ቢመዘገቡ የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በበለጠ ጌራ የጫካ ቡና አርሶ አደሮች ቡና  ወደ ውጭ ቢልኩም በአካባቢው ላይ ትምህርት ቤትና ሆስፒታል አለመኖሩ ቅር እንዳሰኛቸው ነግረውናል፡፡ ጥያቄውን  በተደጋጋሚ ቢያነሱም መልስ አላገኙም፡፡ ለምንድነው?

አቶ ቂጡማ፡- ፕሮጀክቱ ቀጥታ የሚሠራው የገበሬዎች ቴክኒካል ድጋፍ ላይ ነው፡፡ ትኩረቱም ቡና ላይ ነው፡፡ ለትምህርት ቤትና ለሆስፒታል ፈንድ የላቸውም፡፡ ገበሬው በተደጋጋሚ የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት ችግሩን እንዲፈታለት ጠይቋል፡፡ ነገር ግን አጥጋቢ መልስ አልነበረም፡፡ በዚህ ዓመት ለሽያጭ ከሚውለው ደን አምስት ከመቶ ለአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲገባ ተድርጓል፡፡ ከተሸጠው አምስት በመቶ ማኅበረሰቡ ካገኘ የሚፈልገውን ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- ከቡና በተጨማሪ የቱሪስት መስህብ የሆኑ እንስሳት በሥፍራው ይገኛሉ የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ቂጡማ፡- በጫካው ውስጥ ዓላማ ብርቅዬ የሆኑትን ጨምሮ በርካታ ወፎችና፣ ቢራቢሮዎች፣ ጎሽና ሌሎችም ይገኛሉ፡፡ ደኑ ነዋሪው ያለበትን ጨምሮ 166 ሺሕ ሔክታር ነው፡፡ በውስጡ ትልልቅ ወንዞች አሉ፡፡ ወደ ጎጀብ ወንዝ የሚገባው፣ ናስር ወንዝ፣ ጊቤ በዚሁ ጫካ የሚያልፉ ናቸው፡፡ አሁን ትኩረት የተሰጠው ግን ቡናው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አርሶ አደሩ ከጃይካ የሚያገኘው ሥልጠና ምን ዓይነት ነው?

አቶ ቂጡማ፡- ቡናው ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ሥልጠና ይሰጣል፡፡ የበለጠ ጌራ ጫካ ቡና ከሌሎች ምን ይለየዋል? በሚለው ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖር፣ በሌሎች አካባቢ ያሉ የቡና ዓይነቶችና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የቴክኒክ ሥልጠና ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- የአካባቢ ጥበቃ አርሶ አደሩ እንዲሠራ ተደርጓል፡፡ በክልሉ በኩል የሚሰጠው ድጋፍ ምንድነው?

አቶ ቂጡማ፡- የአካባቢ ጥበቃውን በጃይካ በኩል ሥራ ለአንድ አካል፣ ለአርሶ አደሩ ወይም ለጃይካ ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ወረዳውና ኅብረተሰቡ የራሱ ሥራ አድርጎ መያዝ ቢኖርነትም አላደረገውም፡፡ ሁሌም በዚህ እንደተፈተንን ነው፡፡ ጫካውን የመጠበቁ ሥራ የጃይካ ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ ነገር ግን ሥራውን ወደራሳችን አምጥተን መሥራት አለብን፡፡ የዘርፍ መሥርያ ቤቶችና ማኅበረሰቡ ደኑን ለማዳን የተቀረጸውን ስትራቴጂ ቢተገብሩ መልካም ነው እላለሁ፡፡ እንደ አጠቃላይ ሲታይ ደኑ እያገገመ፣ አርሶ አደሩም እየተጠቀመ ነው፡፡ ነገር ግን የአርሶ አደር ማኅበራት በሚያገኙት ገንዘብ ቋሚ ነገር እንዲሠሩ እገዛ ይፈልጋሉ፡፡ የበለጠ ጌራ ጫካን በጠበቅን ቁጥር ቡናው ይለማል አርሶ አደሩም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ የሰርተፍኬሽን ፕሮጀክቱ ፋይዳም፣ አካባቢን መጠበቅ ቡናን ማምረት፣ ወደ ውጭ መላክና አርሶ አደሩንና አገርን ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...