(ክፍል ሁለት)
በዋካንዳ ኢትዮጵያ
በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉና ነገ ሥልጣን ላይ ለመውጣት እየተዘጋጁ ያሉ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ዘርና ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት ባለበት አገር፣ “ወገኔ” የሚሉት ማኅበረሰብ በሰላም ጊዜ ለሥልጣን የሚያበቃቸው በችግራቸው ጊዜ ደግሞ ሌላውን ማኅበረሰብ ማስፈራሪያቸው አድርገው ሊጠቀሙበትና ለዚህም ተግባር ሊያንቀሳቅሱት መሞከር አይገባቸውም:: ይልቁንም የተደመሩትን ከሌላው የአገሪቱ ማኅበረሰቦች ጋር አብረው በሰላም እንዲኖሩ መምከርና በወገናዊነታቸው የተለየ እንክብካቤና ጥቅም እንደማይሰጧቸው ቁርጥ አድርገው መንገር ይጠበቅባቸዋል:: ለወገኖቻቸው የአንድ የስልክ ጥሪ ርቀት፣ ለሌላው ማኅበረሰብ የሰማይ ያህል ርቀት ካላቸው ያው የበፊቱን ስህተት ስለሚደግሙት፣ ውሎ አድሮ ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ቅራኔ ውስጥ ይገቡና ለውጡ ባይቀለበስም ይጨናገፋል:: ይህ እንዳይሆን የሁሉም ማኅበረሰብ አባሎች በእኩልነት ትኩረት የሚያገኙበትን ተቋም ማቋቋም ያስፈልጋል::
እውነትን እንነጋገር ከተባለ በወገናዊ ፍቅር ብቻ (ብቻ ማለቴን ልብ በሉልኝ) የተመሠረተ መደመር እንኳን ለተጀመረው ለውጥ ድጋፍ ሊሆን ለራሱም የትም አይደርስም:: በአገራችን አንጋፋ የተባሉና በወገናዊ ፍቅር ብቻ የተሰበሰቡ ድርጅቶች ከፍጅትና ከፖለቲካ ኪሳራ በስተቀር ያመጡት ውጤት የለም:: አሁንም ይህንን በስፋት እያቀነቀኑ ያሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች አገራችን ኢትዮጵያ እንድትሆንልን ለምንፈልገው የሰላም፣ የእውነተኛ ዴሞክራሲና የላቀ ዕድገት የሚኖራቸው አስተዋጽኦ አነስተኛ ነው፡፡ ይልቁኑም ከፖለቲካ ድርጅትነት ወደ አክቲቪስትነት ተቀይረው ቢንቀሳቀሱ የተሻለ ሥራ ይሠሩ ይሆናል:: በዚህ ፍቅር ላይ የተመሠረተን ትግል አላዋጪነት የተረዱ ድርጅቶች ወገናቸውን ሊያስተባብርላቸው የሚችል፣ ሌላውን ማኅበረሰብ ሥጋት ውስጥ የማይከት፣ የሕዝብን አመኔታን የሚያስገኝና ዘላቂ የሆነ ውጤት ያመጣልናል ያሉትን የፖለቲካ ፕሮግራም በመቅረፅ የተሻለ አመራር በመስጠት ላይ ይገኛሉ::
ወገናዊ ፍቅርን ከሰው ሕይወት ውስጥ ማስወገድ አይቻልም፣ የተፈጥሮ ፀጋና ለሰው ልጆች ፍቅር ለመስጠት እንድንችል መሠረት ነው:: በቅርብ ያሉትን ወንድሞችና እህቶቻቸንን መውደድ ካልቻልን በሩቅ ያሉትን መውደድ እንዴት ይቻላል? ወገናዊ ፍቅርን የተለያዩ መጥፎ ቅጥያዎች በመስጠት ለማጥፋት መሞከር ትርፉ ድካም ነው፣ አይጠፋም:: ነገር ግን የፍቅር አድማሱን ማስፋትና ሚዛናዊ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡ ለዚህም እንዲረዳው ሌላ ዓይናማ ፍቅር ያስፈልገዋል:: ይህ ፍቅር የጓዶች ፍቅር ነው::
የጓዶች ፍቅር
የጓዶች ፍቅር “ዓይናማ” ሲሆን ከወገናዊ ፍቅር ግን የተሻለና የሰፋ ዕይታ አለው:: ምክንያቱም የጓዶች ፍቅር መሠረቶች የጋራ ዓላማ፣ ርዕዮት፣ እምነት፣ ሃይማኖትና አስተሳሰብ ስለሆኑ ነው:: ይህ ፍቅር የዘር፣ የቆዳ ቀለም፣ የባህልና የቋንቋ ልዩነቶች ሳይገድቡት ከእርሱ እሳቤ ጋር የሚመሳሰሉትን ሁሉ ይወዳል:: በተለይ በጋራ እምነታቸው ላይ ተቀራርበው የሚሠሩ ሰዎች በመካከላቸው የሚኖራቸው የጓደኝነት ፍቅርና መግባባት ጥልቅ ስለሚሆን፣ መልካም ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ትልቅ አቅም ይኖራቸዋል:: ይህ ፍቅር ከለውጡ ጋር ለመደመር ዋናው መሥፈርቱ የለውጡን ግንባር ቀደም መሪዎችን የፖለቲካ አቋማቸውን፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ፖሊሲ፣ ርዕዮታቸውን፣ ባህርያቸውን፣ ምግባራቸውን፣ ሚዛናዊነታቸውን፣ ለተቃዋሚዎቻቸው ያላቸውን ዕይታና የመሳሰሉትን እንጂ ዘራቸውንና የሚናገሩትን ቋንቋ አይደለም::
የጓዶች ፍቅር እንደ ስሜታዊ ፍቅር ወረተኛና ግልብ፣ እንደ ወገናዊ ፍቅር በአንድ ማኅበረሰብ ጉያ ሥር የተሸጎጠ አይደለም:: ነገር ግን ሁኔታዎችን ለመተንተንና አቋም ለመውሰድ ችሎታ ያለው፣ በአመክንዮና በሐሳብ ፍጭት የሚያምን፣ ከተለያዩ ማኅበረሰቦች የመጡ ሰዎችን ለትልቅና አገር አቀፋዊ ዓላማ ማሠለፍ የሚችል ነው:: የዚህ ፍቅር ትልቁ ኃይሉ የሐሳብ ልዕልናና የአዕምሮ ነፃነት ነው:: ስለዚህ ለውጡ ሥር ሰድዶ ወደታለመለት ግብ እንዲደርስ ታላቅ ሚና ይጫወታል:: ሁላችንም እንደምናውቀው በሰላማዊና መንገድና በነፍጥ ከመንግሥት ጋር ይፋለሙ የነበሩ ተቃዋሚ ድርጅቶችና ግለሰቦች የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት ገብተዋል:: አብዛኛዎቹ ይህንን ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያት የተጀመረው የሰላም፣ የዴሞክራሲና የአገር ግንባታ እሳቤ የእነርሱም አጀንዳ በመሆኑ የድርሻቸውን ለማበርከት ነው እንጂ በስሜት ወይም በወገናዊ ፍቅር ተነሳስተው አይደለም::
በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፕሮግራም በመቅረፅ ከተለያዩ ማኅበረሰቦች የተውጣጡ ሰዎችን ያቀፉ ድርጅቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ:: አንዳንድ ዘር ተኮር የሆኑ ድርጅቶችም ከሌላው ማኅበረሰብ ዘር ተኮር ከሆኑ ድርጅቶች ጋር የጋራና አገር አቀፋዊ ግብ እስካላቸው ድረስ፣ አብረው ለመሥራት በመስማማት ወገናዊ ፍቅር የጎደለውን ዕይታ አስፍተውለታል:: ይህ አቅጣጫ ለተጀመረው ለውጥ ብርቱ ድጋፍ ነው:: ነገር ግን የፓርቲዎቹ ቁጥር መብዛትና አቅም ማነስ ግዙፍ ለሆነው ገዥ ፓርቲ ያለ ተቀናቃኝ ሥልጣን በቀላሉ ይዞ እንዲቀመጥና ሕዝቡ ጥሩ አማራጭ እንዳይኖረው በማድረግ ለውጡ የታለመለትን ግብ እንዳይመታ ያደርገዋል::
የመጪው ምርጫ ክርክሮች ከወሰን፣ ከማንነትና ከአዲስ አበባ አጀንዳዎች ባሻገር ሊሆኑ የሚችሉት በጓዶች ፍቅር በተሰባሰቡ ድርጅቶችና ፓርቲዎች አማካይነት ስለሆነ የተበታተኑት ሰብሰብ ብለው ሞቅና በሳል ክርክር ለማድረግ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል:: ይህንን ካላደረጉ ግን ጭቆና ያንገፈገፈውንና እውነተኛ ዴሞክራሲ የተራበውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ “በአዲስ አበባና በፊንፊኔ”፣ “በወልቃይትና በራያ አማራነትና ትግሬነት” ለመሳሰሉ ውዝግቦችና አማራጮች አሳልፈው በመስጠት ትልቅ የታሪክ ስህተት ይሠራሉ:: የምርጫ ካርዳችንን የምንሰጠው ተወዳዳሪዎች ስለዴሞክራሲ፣ ኢኮኖሚ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ የውጭ ጉዳይ፣ የአገር ደኅንነትና መከላከል፣ ሴቶችና የመሳሰሉት ላይ በሚኖራቸው ፖሊሲ መሆኑ ቀርቶ ለወሰን አስማሪዎች ከሆነ፣ መጪው ምርጫ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን የሕፃን ጨዋታ ይሆናል:: ምክንያቱም ወሰን አስተማሪዎችን ለመምረጥ ምርጫ ማድረግ አላስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ለእውነተኛ ዴሞክራሲ መጎልበትና የአገር ዕድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ እጅግ ውስን በመሆኑ ነው:: በዴሞክራሲ የጎለበቱ አገሮችና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “ኋላ ቀር ለሆነ ጥቁር ሕዝብ በቂው ነው” የሚለውን አሽሙር ሰንዝረው፣ ቀጣዩን ዕርምጃችንን ይጠባበቃሉ:: ተስፋችን ግን ብልህና ብዙ ኃላፊነት የሚሰማቸው መሪዎች፣ ድርጅቶች፣ ፓርቲዎችና ግለሰቦች በአገራችን ስላሉ ከዚህ ጉድ ይታደጉናል የሚል ነው::
የወሰንና የማንነት ጉዳዮች ተገቢ ጥያቄዎች መሆናቸው አልጠፋኝም፡፡ የብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ስሜት የሚነኩ ናቸው:: ነገር ግን እውነተኛ መፍትሔ የሚያገኙት በምርጫ ሳይሆን በይቅርታና በፍቅር ብቻ ነው:: ይቅርታና ፍቅር በሰዎች መካከል መቀራረብን፣ መቀባበልንና መተሳሰብን ስለሚያመጡ የራስ ዳሸን ተራራ የመሰለው ችግራችን የምስጥ ኩይሳ ይሆናል:: በሕዝብ መካከል ፍቅርና ይቅር መባባል ካለና አብረን ለመኖር ከተስማማን ምድርስ ወሰንስ ምንድነው? ምድር ለሰው ተፈጥሯል እንጂ ሰው ለምድር አልተፈጠረም:: ምድርስ ያለ ሰው ምን ዋጋ አለው?
የጓዶች ፍቅር የሚከስመው በውስጡ የሚነሱ አዳዲስ ሐሳቦችን ማስተናገድ ሲሳነው፣ እኔና እኔ ብቻ ትክክል ነኝ ማለት ሲጀምርና ጓደኛሞች ለወገናዊ ፍቅር እጅ ሲሰጡ ነው:: ይህ በሚሆንበት ጊዜ ትልቅ ራዕይ ያለው የጓዶች ፍቅር ወደ ጭፍን የድርጅትና ወገናዊ ፍቅር ዝቅ ይላል:: በዚህም ሳይወሰን ሌላ እሳቤ ያላቸውን ሁሉ በጠላትነት በመፈረጅ ያለውን አቅም ሁሉ አሰባስቦ “የጡንቻ” ፖለቲካ ውስጥ ይገባና ለለውጡም ሆነ ለአገር ደንቃራ ይሆናል:: በአሁኑ ወቅት “በዚህና በዚህ ጉዳይ ድርድር የለም” የሚሉ አባባሎች የእውቀት ማነስና የሐሳብ ድህነትን ማሳያ ከመሆናቸውም በላይ፣ የዚህ ፍቅር መልካምነትን ወደ ጨለማነት የሚቀይሩ ናቸውና ከአገራችን ፖለቲካ ውስጥ መወገድ ይኖርባቸዋል:: የሌላው ሐሳብ ከእኛ ሐሳብ ከላቀ የራሳችንን ብንተው ምን ጉዳት አለው? ደግሞስ በዴሞክራሲ ካመንን የሕዝብ ድምፅ ይዳኘን የለ? ስለዚህ ከእኛ በተለየ ሐሳብ አንሸበር፣ መንገድ አንዝጋ፣ ሰው አናፈናቅል፣ ይልቁኑም ሐሳብን በማመንጨት የሰውን ልብና አዕምሮ እንማርክ::
በአንድ ወቅት የአማራና የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደሮች አቶ ገዱ አንዳርጋቸው (አሁን ተለውጠው) እና ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል በሃይማኖት መሪዎችና በአገር ሽማግሌዎች ፊት በሁለቱ ክልሎች መካከል የተከሰቱትን ችግሮች በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በጋራ ቃል በገቡበት ወቅት፣ ዶ/ር ደብረ ጽዮን “ከገዱ ጋር ወንድማማቾች ብቻ አይደለንም፣ በፖለቲካም ጓዶች ነን ከወንድምነት በላይ ነው ግንኙነታችን፤” ብለው ነበር:: ይህንን ያሉት ከልባቸው ይሁን ወይም አይሁን በጊዜ ውስጥ የሚታይ ቢሆንም፣ ይህ ከወንድምነት በላይ ያለ ግንኙነት የጓዶች ፍቅር ነው:: ዶ/ር ደብረ ጽዮን በተደጋጋሚ “አዝኛለሁ” ሲሉ የነበረው ይህ ፍቅር ከወገናዊ ፍቅር የተሻለ ሆኖ እያለ፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል ያሉትን ችግሮች ያለ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት መፍታት ባለመቻላቸው ይመስለኛል::
ችግሮቻቸውን መፍታት ያልቻሉበት መሠረታዊ ምክንያት ወይ መስተዳድሮቹ በተሻለ መንገድ ተባብረው ከክልሎቻቸው ባሻገር፣ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሆን ቁም ነገር መሥራት የሚያስችላቸውንና ያፋቀራቸውን የጋራ አመለካከት ወደ ጎን ብለው በወገናዊ ፍቅር ስለተሸበቡ ነው፡፡ አለበለዚያም ለጓዳዊ ፍቅራቸው መሠረት የሆነው የጋራ አስተሳሰብ ዛሬ በመካከላቸው ባለመኖሩ ሊሆን ይችላል:: ስለዚህ የሁለቱም ክልሎች መስተዳድሮች በጎንዮሽ ያሉትን አናሳ ጉዳዮች እንደ ዋና አጀንዳና መነጋገሪያ ከማድረግ ይልቅ፣ መሠረታዊ በሆኑት ችግሮቻቸው ላይ በትሁት ልብ ተነጋግረው ካስፈለገም ሐሳብን በማቻቻል ለክልሎቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዘላቂ ሰላምንና ዕፎይታን እንደሚያመጡ ተስፋ አደርጋለሁ:: ዛሬ ብቸኛ አማራጮች ናቸው የተባሉት ነገ የሚያረጁና ላይሆኑ እንደሚችሉ ለመረዳት የሰው ልጅ ከምንም ተነስቶ ዛሬ የደረሰበትን መመልከት በቂ ነው::
እስካሁን ካየናቸው ፍቅሮች የጓዶች ፍቅር ለጋራ ዓላማ ብዙ ማኅበረሰቦችን በማካተትና በሐሳብ ልዕልና በማመኑ የተሻለ ቢሆንም፣ ለራሱ ጓዶች አድልኦ ከማድረግ ግን ነፃ አይሆንም:: በተለይ በአገራችን ያሉ ድርጅቶችና ፓርቲዎች ከሌላው ለመማር ያላቸው ፍላጎት አናሳ ነው:: ልክ እንደ ወገናዊ ፍቅር ለራሳቸው የድርጅትና የፓርቲ አባላት በማድላት ሌሎቹ ተፎካካሪዎቻቸው የእነርሱን ጉድለት የሚያሳዩ መስተዋቶች እንደሆኑ ለመቁጠር ይቸገራሉ:: ለሚመጣው ምርጫ ዝግጅት የሚደረጉት ክርክሮች በተለያዩ ርዕዮቶች፣ የኢኮኖሚ፣ የአገር ግንባታ፣ የሕዝብ አስተዳደር አማራጮችና የመሳሰሉት ላይ እንዲሆኑና የዴሞክራሲ ባህላችን እንዲያድግ በማድረግ፣ በጓዶች ፍቅር ላይ የተመሠረቱ ድርጅቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው:: ይህንን ሳይዘነጉ የአገራችንና የለውጡ ትልቁ የቤት ሥራ የሆነውን ሁላችንንም የሚያፋቅረን የጋራ እሳቤ ማካተት ይገባቸዋል:: የጓዶች ፍቅር ለወገናዊ ፍቅር ዕይታውን እንደሚያሰፋለት ሁሉ፣ የጓዶች ፍቅር አድማሱን የሚያሰፋለት ፍቅር ያስፈልገዋል:: ይህን ፍቅር “እያየ የማያይ ፍቅር” ብዬዋለሁ::
እያየ የማያይ ፍቅር
ይህ ፍቅር ሰዎች በፆታ፣ በቀለም፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በርዕዮት፣ በሀብት፣ ዕውቀት፣ በሥልጣንና በመሳሰሉት የተለያዩ እንደሆኑ በሚገባ ያውቃል:: ስለዚህ “ዓይናማ” ነው:: ነገር ግን ሰዎች ሁሉ ውድና ክቡር የሆነ የጋራ ነገር እንዳላቸው ስለሚረዳ ልዩነቻውን ወደ ጎን ትቶ ሁሉንም ይወዳል:: ስለዚህ “አውቆ ይታወራል”:: እያየ የማያይ ፍቅር ከወገናዊና ከጓዶች ፍቅር የሚበልጠው ሰዎችን የለያያቸው ከእነርሱ ቁጥጥር ውጪ ያሉ ነገሮች መሆናቸውን አውቆ፣ ለሰዎች ሁሉ ፍቅር በመለገሱና በብይኑ ሚዛናዊ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የሚጠላው “ጥላቻን” ስለሆነ ነው:: የሰዎች ውድና ክቡር የሆነው የጋራቸው ሚስጥር “ሰዎች” መሆናቸው ነውና እያየ የማያይ ፍቅር ሰዎችን አይጠላም:: ይህን ፍቅር ለማግኘት ሰው መሆን በቂ ነው::
ለምሳሌ ደሃንና ባለፀጋን እንውሰድ፣ በሀብት እንጂ በሰውነት እኩል ናቸው:: ሁለቱም ራቁታቸውን ከእናታቸው ማህፀን ይወጣሉ፣ ልዩነቱ የሚጠቀለሉበት ጨርቅ ነው:: ሁለቱም ይበላሉ፣ ልዩነቱ የምግቡ ዓይነት ነው:: ሁለቱም ይፀዳዳሉ፣ ልዩነቱ የመፀዳጃ ቦታው ነው:: ሁለቱም ይማራሉ፣ ልዩነቱ ትምህርት ቤቱ ነው:: ሁለቱም ይለምናሉ፣ ልዩነቱ የሚለምኑት ነገር ነው:: ሁለቱም ይለግሳሉ፣ ልዩነቱ የልግስናው መጠን ነው:: ሁለቱም ይሰርቃሉ፣ ልዩነቱ የሚሰርቁት ዓይነቱና ብዛቱ ነው:: ሁለቱም ይታመማሉ፣ ልዩነቱ የበሽታው ዓይነትና የሚታከሙበት ቦታ ነው:: ሁለቱም ይሞታሉ፣ ልዩነቱ መቃብሩና የቀባሪው ብዛት ነው:: ሰዎችን የሚለያቸው ከእውነተኛ ማንነታቸው ውጭ ያሉ ነገሮች ናቸው:: እውነተኛ ማንነታቸው አንድ ዓይነትና እኩል ነው:: ስለዚህ ሰውን ሁሉ ማክበርና መውደድ ራስን ማክበርና መውደድ ነው:: በሌላ አባባል ሌላውን የሚንቅና የሚጠላ ራሱን የናቀና የሚጠላ ነው:: እስቲ ወላጆቹን፣ ዘሩን፣ ፆታውን፣ ቀለሙን፣ ቋንቋውን፣ ባህሉን፣ ሃይማኖቱን፣ የሚኖርበትን አገር ከካታሎግ ላይ መርጦ ወደዚች ዓለም የመጣ ማነው? ካልሆነስ ለምን ባልመረጠው ጉዳይ ይገፋል?
እኛ ኢትዮጵያውያን ዓይናችንና ማስተዋላችን ተደፍኖብን ካልሆነ በስተቀር ይህ ሊጠፋን አይችልም:: ምክንያቱም የምንከተላቸው ሃይማኖቶች ሁሉ የሚያስተምሩት ይህንን ነውና:: ይህንን ለማወቅ የሃይማኖት መሪ መሆን አያስፈልግም፣ የሚያዳምጥ ጆሮ፣ የሚያነብ ዓይንና የሚታዘዝ ልብ እንጂ:: ከምንከተላቸው ሃይማኖቶች በስተጀርባ የሁላችንም ፈጣሪ አለና የፈጠረውን ሰው በመጥላታችን፣ በማፈናቀላችንና በመግደላችን ይጠይቀናል:: ይዘገይ ይሆናል እንጂ የዘራነውን ማጨዳችን አይቀርም:: ፍቅርን ዘርተን ከሆነ በረከትን፣ ጥላቻን ዘርተን ከሆነ እርግማንን እናጭዳለን:: ፈጣሪ አይዘበትበትም::
እያየ የማያይ ፍቅር ለለውጡ ብቻ ሳይሆን ለአገርም ምሰሶና ፈውስ ነው:: በኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች ጉዳይ እንደተራገበው ጎን ለጎን የሰዎች እኩልነትና ክቡርነት ተራግቦ ቢሆን ኖሮ ዛሬ መፈናቀል አይኖርም ነበር:: እውነተኛ የብሔር ብሔረሰቦች መብት የሚከበረው በሰው ልጆች እኩልነት ከልብ በማመን ነው:: የፍቅርም የጥላቻም ምንጩ የሰው አዕምሮ ነውና መቀየር ያለበት የሰው አስተሳሰብ ነው:: የሰው ልጆችን መከባበርና መፋቀር በውጫዊ መንገድ ለማምጣት መሞከር ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም:: የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ማክበር መፍትሔ ቢያመጣ ኖሮ፣ ዛሬ ዓለም የሚያውቀን በፍቅራችን እንጂ በተፈናቃዮች ብዛት አይሆንም ነበር:: “ከመቅረት ዘግይቶ ወደ ቀጠሮ ቦታ መድረስ ይሻላልና” ዘግይተንም ቢሆን አሁን ብንጀምረው የምንመኛትን አገር መገንባት እንችላለን:: ኔልሰን ማንዴላ፣ “ሰዎች ጥላቻን መማር ከቻሉ ፍቅርንም መማር ይችላሉ” እንዳሉት፣ በአገራችን ያሉ የሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮቻቸው፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የወረዳና የክልል መስተዳደሮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ልሂቃንና አክቲቪስቶች በፍቅር ዙርያ በሚጠበቅባቸው ልክ ቢንቀሳቀሱ በሰው አስተሳሰብ ውስጥ ብዙ ለውጥ ያመጣሉ::
ሰዎችን ማክበርና መውደድ ስንጀምር የምንሠራው ሁሉ ጥራት ይኖረዋል:: ሌሎች የሚጠቀሙበት ቢሆንም እንኳ ለራሳችን እንደሆነ ስለምናስብ መልካም ነገርን ሠርተን እናቀርባለን:: በትንሿ ዱባይ የአውቶብስ መጠበቂያ ሥፍራዎች ያማሩና የአየር ማቀዝቀዣ ያላቸው ናቸው:: የዚህ ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው? ብንል መኪና ወይም የሞተር ቢስክሌት ገዝተው መንዳት የማይችሉ፣ በታክሲ ተሳፍረው ለመሄድ በቂ ገንዘብ የሌላቸው፣ ቤተሰቦቻቸውንና አገራቸውን ትተው ያልፍልናል ብለው የመጡ ድሆች ናቸው:: የዱባይ የመንገዶችና ትራንስፖርት ባለሥልጣናት ይህን ያደረጉት ከተማዋን ለማስዋብ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ ድሆች እንደ ባለፀጋዎቹ ሰዎች መሆናቸውን ስለተረዱ ነው፡፡
ሰዎችን ስንወድ እውነተኛ የአገር መውደድ ይኖረናል:: በኢትዮጵያዊነት ላይ ውዝግብ ሊኖር ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ግን ሊኖር አይገባም፣ አይችልምም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ መላው የዓለም ማኅበረሰብ የሚያውቃት፣ በዓለም ካርታ ላይ ድንበሮቿ ተከልሎ የምትታየው ይህቺ ምድር ናት:: ይህንን ለመረዳት የተማረና የተመራመረ መሆን አይጠይቅም:: በዚች አገር የምንኖር ወይም ዜግነት ያለን ሁሉ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ እኛም ሆንን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያምነው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በዚህች ግዛታቸው ውስጥ ያለምንም ገደብ መኖር እንደሚችሉ ነው:: አለመታደል ሆኖ ዛሬ በየትኛውም ቦታ እንደፈለግን ለመሄድ፣ ሳንሸማቀቅ ለመኖር፣ ሠርተን ሀብት ለማፍራት አንችልም:: አውቀንም ይሁን ባለማወቅ ይህ ድርጊታችን መሠረታዊ የሆነውን የሰው ልጅን መብት መጋፋት ነው፡፡ በሕግ ሲያስጠይቅ ባልሰማም በፈጣሪ ዘንድ ግን ያስጠይቃል:: ሰውን ስናከብርና ስንወድ ኢትዮጵያውያንን እንወዳለን፣ ኢትዮጵያውያንን ስንወድ ኢትዮጵያን እንወዳለን:: ያኔ በአንድ ልብ ለኢትዮጵያ እንሠራለን:: በበጎ ሐሳብ የተጀመረው ለውጥም ስኬታማ ይሆናል::
ማጠቃለያ
ፍቅር መልካም ነው:: ፍቅር ጥላቻን ከወለደ ግን አውዳሚ ነው:: ስለዚህ የፍቅርን አሉታዊ ተፅዕኖ ከልባችንና ከመካከላችን ማውጣት ያስፈልጋል:: በፍቅር የተሸፈነን ጥላቻ ከውስጥ ፈልቅቆ ለማውጣት ራሳችንን መመርመር ይጠይቃል:: ሌላውን በመጥላት የተጀመረ ፍቅር ዘላቂ አይሆንም:: ያ የጋራ “ጠላት” በሽንፈትም ሆነ በፈቃደኛነት ሲወገድ ጥሉና ጥላቻው በፍቅረኞች መካከል ይሆናል:: የለውጡ መሪዎች ከተለያየ ማኅበረሰብና ድርጅት የተውጣጡ ናቸው:: ያፋቀራቸው ጥላቻ ከሆነ ይዋል ይደር እንጂ ለውጡ ይጨናገፋል:: ስለዚህ በተደጋጋሚ በመገናኘት ልባቸውንና አቅጣጫቸውን ማስተካከል ይገባቸዋል::
በፍቅር ተደምረናል የምንል ሁሉ ፍቅራችን በጥላቻ ተለውሶ ከሆነ ለምንመኘው እኩልነት፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና መሰናክል ስለሚሆን ራሳችንን እናስተካክል፡፡ ለውጡ የሚሳካው በቂምና በጥላቻ ሳይሆን በይቅርታና በፍቅር ብቻ ነው:: ለታማኝ በየነ ያለን ፍቅር ለጃዋር መሐመድ ጥላቻን ከወለደ፣ ለጃዋር ያለን ፍቅር ለእስክንድር ነጋ ጥላቻን ካለበሰን ፍቅራችን “በማር የተለወሰ ኮሶ” ነው:: እነዚህ ለአብነት ያነሳኋቸው ግለሰቦች የተለያየ እሳቤ ቢኖራቸውም ሰዎች ናቸው:: እንደነሱ በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ አክቲቪስቶች፣ ልሂቃን፣ የፌደራል መንግሥት፣ የወረዳና የክልል መስተዳድሮች ባለሥልጣናት ጥላቻ ቢያስተምሩ ምግባራቸውንና ትምህርታቸውን ሳንከተል እነርሱን ግን መውደዳችንን እንቀጥል፣ ሰዎች ናቸውና! ለእኩይ ትምህርታቸውና ምግባራቸው ግን ከፈጣሪም ከሕግም ብይን ያገኛሉ፡፡
ማንኛውም ሕዝብ በሌላው ሕዝብ ላይ ዝም ብሎ አይነሳም፣ አይጠላምም:: የሚያነሳሱትና ጥላቻን የሚዘሩት የራሳቸው ዓላማ ያላቸው ጥቂት ሰዎች ናቸው:: የጀርመን ሕዝብ በዓለም ሕዝብ ላይ አልተነሳም፣ ያነሳሱት ናዚዎች ናቸው:: ከናዚዎችም እውነተኛውን ምክንያት የሚያውቁት ከላይ ሆነው የናዚ ፓርቲን የሚመሩት ነበሩ:: ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ የተጠቀሙት በአገር ፍቅር የተለወሰ ጥላቻ ነበረ:: ጥላቻ ተከታይ የሚያገኘው በጎና አጓጊ ተስፋዎችን በመስጠት ነው:: ነገር ግን የገባውን የተስፋ ቃል መፈጸም አይችልም፣ አቅምም የለውም:: ምክንያቱም በጎና አጓጊ ነገሮችን መገንባትና ማምጣት የሚቻለው በፍቅር ስለሆነ ነው:: የጥላቻ ተስፋዎች ከእርሱ ባህርይ ጋር ስለሚጋጩ ወደ ህልውና አይመጡም:: በአገራችንም ጥላቻን በወገናዊ ፍቅር ጠቅልለው የሚያጎርሱ ሰዎች ለሐሳባቸውና ለምኞታቸው ማስፈጸሚያ እንዲሆን ለሚጠቀሙበት ሕዝብ የሚሰጡት ተስፋ “ምድራዊ ገነት”ን ነው:: የዚህች “ምድራዊ ገነት” ተቋዳሾች ጥቂት ግለሰቦች ሊሆኑ ቢችሉም፣ በእርግጠኛነት ግን ሕዝቡ አይደለም፡፡ እስቲ ወንድሞቹንና እህቶቹን አፈናቅሎና ገድሎ ኑሮው የተቀየረ ማኅበረሰብና ሕዝብ፣ ኢኮኖሚው ያደገ ክልልና አገር የትኛው ነው?
የመጀመሪያው ወርቃማው ቃል ግን እንዲህ ይላል፡፡ “ለእናንተ እንዲደረግላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ ለሌሎችም አድርጉ”፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ “በእናንተ ላይ እንዲደረግባችሁ የማትፈልጉትን ሁሉ በሌሎችም ላይ አታድርጉ”::
ጥላቻን የሚጠላ ፍቅር ያሸንፋል፣ ሁልጊዜም ተፈላጊ ነው:: የሰላም ሚኒስቴር ሰላም ከመጣ በኋላ በሌላ ይተካል፣ የእርቅ ኮሚሽንም እርቅ ከወረደ በኋላ ይፈርሳል፣ የማንነትና የወሰን ኮሚሽንም ተልዕኮውን ከፈጸመ በኋላ ይበተናል፣ ሰዎችን ሁሉ የሚወድና ጥላቻን የሚጠላ ፍቅር ግን ሁልጊዜም ይኖራል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡