Friday, December 8, 2023

የሶዴፓ ድርጅታዊ ጉባዔ ያስተናገዳቸው ፖለቲካዊ መልዕክቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፈው አንድ ዓመት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሥራ ዘመን፣ አስደንጋጭና አሳዛኝ ግጭት ከተከሰተባቸው የአገሪቱ ከተሞች መካከል የጅግጅጋው  አደጋ አንዱ ነው፡፡ ሂጎ በተሰኘ የከተማዋ ቡድን አማካይነት በደረሰው ጥቃት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ሕዝብ ተፈናቅሏል፣ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ እንዲሁም በርካቶች ለዘለዓለማዊ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ አስደንጋጭና አሳዛኝ ክስተት የደረሰባት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና ጅግጅጋ ከወራት በኋላ አንፃራዊ ሰላም የሰፈነባት ሲሆን፣ በከተማዋ ያለው እንቅስቃሴም በተለመደው መስመር ፍሰቱን ቀጥሏል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መዲና የሆነቸው ጅግጅጋ ባለፈው ሳምንት ደግሞ የክልሉን ፓርቲ የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ) አሥረኛ ድርጅታዊ ጉባዔን በማስተናገድ ሥራ በዝቶበት የሰነበተች ሲሆን፣ በድርጅታዊ ጉባዔውም ሶዴፓ መሠረታዊ የሚባሉ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ አጠናቋል፡፡

ከሰኞ መጋቢት 23 እስከ ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በተጠናቀቀው የድርጅቱ ጉባዔ ወቅት፣ ፓርቲው በቀጣይ የሚጓዝባቸውን መስመሮችና አካሄዶች በውሳኔዎቹ አሳውቋል፡፡

በስብሰባው የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በመገኘት በአገር ደረጃ ለሚዋቀረው ፓርቲ የሶዴፓ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሚሆን እምነታቸውን በመግለጽ፣ የፓርቲው አመራሮች የፖለቲካ ጨዋታውን ወደ መሀል ገብተው እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአሥረኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ተገኝተው የመልካም ምኞት ንግግር አሰምተዋል፡፡ የተናጋሪዎቹ መልዕክት ከመልካም ምኞት ባሻገር በኢሕአዴግ ውስጥ ያለውን የኃይል አሠላለፍ፣ እንዲሁም ሶዴፓን ወደዚያ የመሳብ መልዕክቶች ላይ ያተኮሩ እንደነበር መታዘብ ተችሏል፡፡

የሶዴፓ ድርጅታዊ ጉባዔ

 

አጠቃላይ የጉባዔው መንፈስ

ጉባዔው ባለፈው ሳምንት ሰኞ ዕለት ሲጀምር ከተለያዩ የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች የመጡ የፓርቲው አባላት፣ ደጋፊዎችና አመራሮች ተገኝተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የወንድማማችነት መልዕክት ለማስተላለፍና የአጋርነት አብሮነትን ለማሳየት፣ የሶማሌላንድና የጂቡቲ ተወካዮች የድርጅታዊ ጉባዔው ታዳሚዎች ነበሩ፡፡

ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት የጉባዔው አዳራሽ ለመግባት አስቸጋሪ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ፣ የተከናወነው ድርጅታዊ ጉባዔው በርካታ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

በዚህ መሠረት 61 አባላት ያላት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫና ዘጠኝ አባላት ያሉትን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ አከናውኗል፡፡ የሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት ምርጫን ከማከናወን ባለፈ ግን፣ ፓርቲው ስያሜውን ከኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶሕዴፓ) ወደ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶዴፓ) አሸጋግሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ዋነኛው ውሳኔ ደግሞ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፓርቲውን ተቀላቅሎ መሥራት እንደሚችል መወሰኑ፣ ለክልሉ ፖለቲካ አዲስ መንገድ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ተገልጿል፡፡

እነዚህን ዓበይት ውሳኔዎች ያሳለፈው የድርጅቱ አሥረኛ ጉባዔ የገንዘብ ሚኒስትሩን አህመድ ሺዴን፣ እንዲሁም የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድን የፓርቲው ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ በመምረጥ ድርጅታዊ ጉባዔውን አጠናቋል፡፡

በድርጅታዊ ጉባዔው መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን እንደመጡ ወደ ጎበኟት ጅግጅጋ በድጋሚ መምጣታቸውን በማስታወስ ሲሆን ንግግራቸውን የጀመሩት፣ ‹‹የአምና መንፈስና የዛሬ መንፈስ ልዩነቱ በግልጽ ፊታችሁ ላይ ይታያል፤›› በማለት ነው፡፡ የዘንድሮ መንፈስ የተነቃቃና የታደሰ፣ እንዲሁም የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) የጉባዔው ታዳሚ መሆን የቻለበት መሆኑን በመጥቀስ በክልሉ የተከናወነውን ሥራ አወድሰዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት፣ ሶዴፓ አዲስ ለሚፈጠረው የኢሕአዴግ ውህድ ፓርቲ መመሥረት መጠናከር ከፍተኛ ሚና ሊጫወት እንደሚገባ በማሳሰብ ነው፡፡

በጉባዔው ላይ የተገኙና ከእርሳቸው በፊት የአጋርነትና የመልካም ምኞት ንግግር ያደረጉት አመራሮችም ከሕወሓት ተወካይ በስተቀር፣ በዚህ ጉዳይ ላይ አፅንኦት ሰጥተው መናገራቸው የክልሉን ፓርቲ ወደ ማዕከል ለማምጣት የሚደረግ ጥረት ውጤት አድርገው የተመለከቱት በርካቶች ናቸው፡፡

ሶዴፓ በአገር ደረጃ ለሚቋቋመው ፓርቲ ለመመሥረትና ለማገዝ ግንባር ቀደም ሆኖ እንደሚታገል ተስፋቸው ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹አንድ አገራዊ ፓርቲ ያስፈልጋል ስንል የሶማሌ ወይም የሌሎች ብሔሮች ማንነት ይጨፍለቅ እያልን አይደለም፡፡ ብሔሮች ቋንቋቸው፣ ባህላቸው፣ ማንነታቸው፣ የታገሉለትና ውጤት ያመጡበት ፍሬ እንዳይደበዝዝና በመደመር መንፈስ አንዲት ታላቅ ኢትዮጵያን በጋራ እንድትፈጠር የሚያስችል ድርጊት እንጂ ወደ ኋላ የማይመልሰን ነው፤›› በማለት አጋር አባል ሳይባል ሁሉም በጋራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሌ የሚለውን የክልሉን ፓርቲ መጠሪያነት ሶማሌ ብቻ ወደ የሚል መቀየሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ ‹‹የእንግሊዝ ሶማሌላንድ፣ የጣሊያን ሶማሌላንድ እንደሚባለው የኢትዮጵያ ሶማሌ የሚባል ነገር የለም፡፡ እናንተ ኢትዮጵያዊ ስለሆናችሁ፤›› የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በድርጅቱ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ንግግር ያሰሙት አመራሮች፣ የክልሉ ፓርቲና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ወደ መሀል መምጣትና መሳተፍ ላይ አፅንኦት ሰጥተው መናገራቸው፣ ፓርቲዎቹና አመራሮቹ የክልሉን ፓርቲ ከጎን ለማሠለፍ የሚደረግ ጥረት እንደሆነ የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡

ከዚህ አንፃር፣ ‹‹የሶዴፓ አመራሮች የጅግጅጋ ፖለቲካ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ መታገል አለባችሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ኢሳ፣ ኦጋዴን፣ ገሪ የሚባል ክፍፍል ሳይሆን የሚያስፈልጋችሁ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እኛ የተማርንና ኢትዮጵያን የምናሻግር ሲሆን፣ እኛ እያለን ሌሎቻችሁ መስመር ልቀቁ የሚል የአዲስ አበባ ፖለቲካ መለማመድ አለባችሁ፤›› በማለት፣ የክልሉ ፖለቲከኞና ፓርቲ ገፍተው የማዕከል ፖለቲካን እንዲቀላቀሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በበኩላቸው፣ አሥራ አንደኛው የኢሕአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ባስተላፈለው ውሳኔ መሠረት ኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶቹን በማካተት ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ የመቀየሩ ሒደት እየተፋጠነ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ ‹‹የመጪው ዘመን ግንኙነታችን የአጋርነት ሳይሆን የአንድ አገራዊ ፓርቲ አካልነት እንደሚሆን ይጠበቃል፤›› በማለት፣ ሶዴፓ ከኢሕአዴግ ፓርቲዎች እንደ አንዱ እንደሚሆንና ግንኙነታቸው የአቻ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በማከልም፣ ‹‹አገራዊ ፓርቲ በምንመሠርትበት ወቅት ከአሁን በፊት የነበሩ ክፍተቶችን በመዝጋት፣ ሁሉም የአገራችን ሕዝቦችና ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ እኩል የሚሳተፉበትን አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል፤›› ሲሉም፣ ቀጣይ የኢሕአዴግ ጉዞ ምን ሊመስል እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

አዴፓ፣ ኦዴፓ፣ እንዲሁም ሕወሓትን በመወከል በጉባዔው ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ተወካዮች ለጉባዔው ስኬት ከመመኘት ባለፈ፣ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለውን አለመግባባት የሚያንፀባርቅ መልዕክት የሚያስተላልፉ ይመስል ነበር፡፡

የአዴፓና የኦዴፓ ተወካዮች ባለፈው አንድ ዓመት የተካሄደው የፖለቲካ ለውጥ ለክልሉም ሆነ ለመላ አገሪቷ በረከትን ይዞ እንደመጣ የገለጹ ሲሆን፣ የሕወሓት ተወካይ በበኩላቸው ባለፈው አንድ ዓመት ምንም እንኳን የተሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም በአመዛኙ ግን የአገሪቱን አጠቃላይ ሰላምና መረጋጋት ጥያቄ ውስጥ የከተቱ ነበሩ በማለት በሶዴፓ ድርጅታዊ ጉባዔ መድረክ ላይ የጓዳውን ልዩነትና አለመግባባት አደባባይ አውጥተውታል፡፡

ከዚህ አንፃር የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ላቀ አያሌው፣ ‹‹ሁላችንም እንደምናውቀው ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት የተጀመረው ክልላዊና አገራዊ የለውጥ ጉዞ መጠነ ሰፊ የማሻሻያ ዕርምጃዎች የተወሰዱበትና ኢዴፓ ሶዴፓን ጨምሮ ለውጡ እንዲሳካ የተንቀሳቀሰበት፣ እንዲሁም በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡበት ነበር፤›› በማለት ባለፈው አንድ ዓመት የተካሄደውን ጉዞ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ለውጡን የሚፈታተኑና በቀጣይም የተለመደውን የጋራ ሥራ የሚጠይቁ ተግዳሮቶች ማጋጠማቸውን ጠቁመዋል፡፡ በማከልም፣ ‹‹የሶማሌ ክልል መንግሥትና ሕዝብ አሁን የምንገኝበትን የለውጥ መድረክ ለዚህ ፍሬና ውጤት እንዲበቃ ለውጡን ለመቀልበስ የተደረገውን ሙከራ በማክሸፍ፣ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያረጋገጠ ሕዝብና መንግሥት ነው፤›› በማለት ሶዴፓና የክልሉ ሕዝብ ለለውጡ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አወድሰዋል፡፡

በተመሳሳይ የኦዴፓ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የኦሮሞና የሶማሌ ግንኙነትና አብሮ መኖር ዛሬ የተጀመረ አለመሆኑን በመጥቀስ፣ ሁለቱ ሕዝቦች በአገር አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአኅጉር ደረጃ ለሚታቀዱ ውህደቶችና ትስስሮች መሳካት ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

‹‹ኦዴፓና ሶዴፓ የሚመሩት የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝብ አንድነቷ የተጠበቀ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ከመገንባት ባሻገር፣ እነዚህ ሕዝቦች ድንበር ተሻጋሪ ሕዝቦች ስለሆኑ ምሥራቅ አፍሪካን የማስተሳሰርና የማስተባበር ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎበታል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ሕወሓትን ወክለው የተገኙት ኪዳነ ማርያም በሪሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከላይ ከቀረቡት ንግግሮች በተለየ ባለፉት 27 ዓመታት በክልሉ የተመዘገቡ የሰላም፣ የልማት፣ የዴሞክራሲ፣ የነፃነት፣ እንዲሁም የእኩልነት ውጤቶች በፓርቲው አማካይነት መመዝገቡን ድርጅታቸው ሕወሓት እንደሚያምን ገልጸዋል፡፡

በተለይ ክልሉ የፀጥታ ችግር የነበረበት ስለነበር ሶዴፓና የክልሉ ሕዝብ ባካሄዱት እልህ አስጨራሽ ትግል በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን ከማድረግ አልፎ፣ የአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ እንዲጠበቅና ለፌዴራል ሥርዓተ ግንባታ ለተጫወቱት የማይተካ ሚና ክብርና ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ያለፈው አንድ ዓመትን የፖለቲካ ጉዞ አስመልክቶ የድርጅታቸውን ምልከታ አስቀምጠዋል፡፡ ‹‹ባለፈው አንድ ዓመት በኢሕአዴግ የተሃድሶ ጊዜ በአንድ በኩል ተስፋ የሚሰጡ ትልልቅ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ሥጋት የፈጠሩ የፖለቲካ አለመረጋጋቶችና የሰላም መጥፋት ማለትም የሕዝብ ለሕዝብ ግጭቶች፣ ንብረት ማውደም፣ ማፈናቀል፣ ሥርዓተ አልበኝነት መስፈን፣ የንፁኃን ሕይወት ማለፍና አካል መጉደል ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የተስተናገዱበት እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው እውነታ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ በሶዴፓ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ የታደሙት የየፓርቲው ተወካዮች፣ አጠቃላይ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታና አሠላለፍ ለመግለጽ የተጠቀሙበት መድረክ እንደነበር ካቀረቧቸው ንግግሮች ማየት እንደሚቻል የሚገልጹ አሉ፡፡

ለሶዴፓ ያላቸውን አጋርነት ከመግለጽ ባለፈ ተወካዮች አዲስ ስለሚመሠረተው ውህድ ፓርቲ፣ በዚሁ ውስጥ ሶዴፓ ስለሚኖረው ድርሻና አሠላለፍን ለማመላከት የተጠቀሙበት መድረክ እንደነበር መታዘባቸውን የገለጹም አሉ፡፡

በዚህ ሁኔታ ለሦስት ቀናት በጅግጅጋ ከተማ የተካሄደው አሥረኛው ድርጅታዊ ጉባዔ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -