በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችና መዳረሻዎችን የሚያለሙ ባለሀብቶችን ለመደጎም የሚያስችል አዲስ አሠራር ሊዘረጋ ነው፡፡
የቱሪዝም መዳረሻዎች በቂ የሆነ መሠረተ ልማት ባለማግኘታቸው ለጎብኚዎች ምቹ ያልሆኑ፣ ነገር ግን በበርካታ ቱሪስቶች ዘንድ ተመራጭ የሆኑ የቱሪዝም መስህቦችን ተጠቃሚ ያደረገ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ለባለሀብቶች እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
ማክሰኞ ሚያዝያ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ውይይት ላይ እንደተገለጸው፣ በቱሪስት መዳረሻዎች ላይ አስፈላጊው ጥናት ከተደረገ በኋላ የኢንቨስትመንት ድጎማዎችን በመስጠት የማኅበረሰቡ የገቢ መጠን እንዲያድግና የሥራ ዕድልም እንዲስፋፋ የሚያስችሉ ሥራዎች እንዲሠሩ ለማድረግ መታቀዱን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሌንሳ መኮንን አስታውቀዋል፡፡
ባሌ ብሔራዊ ፓርክ፣ ሰሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ አብያታ ሻላ፣ ጫሞ ዓባያ፣ ወንጪ፣ ኤርታሌና ሌሎችም መስህቦች የልማት ሥራዎች እንዲከናወኑባቸው ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመሆን መሠረተ ልማትን በማሟላትና ለባለሀብቶች ተመጣጣኝ ድጎማ በማድረግ ለማስፋፋት መታቀዱን ወ/ሮ ሌንሳ አስረድተዋል፡፡
ከውጭም ከአገር ውስጥም የተውጣጡ ባለሀብቶች በእነዚህ አካባቢዎች ለሚያከናውኗቸው መሠረተ ልማቶች አስፈላጊው ማበረታቻ እንደሚቀርብላቸው የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ በበርካታ የቱሪስት መስህቦች ላይ ለማሰማራት አቅም ያላቸው በርካታ ባለሀብቶች እንዳሉም አስታውሰዋል፡፡
ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ቱሪዝም ድርጅት በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይ፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቱሪዝም ገቢ ማግኘት የምትችልባቸው ሀብቶች እንዳሏት ጠቅሰው፣ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ለሚገኙ ኢንቨስተሮች ይሆን ዘንድ የቱሪዝም ልማት ፖሊሲ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ በዚህ መሠረት ወደፊት የሚስፋፋውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግና ያለውንም አጠንክሮ ለማቆየት አዳዲስ የቱሪስት መስህቦችን መፍጠር፣ መሠረተ ልማቶችን ማሟላትና በቱሪዝም መስክ ከሚሠሩ አካላት ጋር ግንኙነትን ማጠናከር ድርጅቱ ከሚንቀሳቀስባቸው መስኮች መካከል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡፡
ባለሀብቶች የቱሪስት ሆቴሎችንና ሌሎችንም አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሲገነቡ፣ ከከተማ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በማድረግ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የመፍጠር ብሎም በዓመት ከ7000 ያላነሰ ጎብኚ ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል የሚሉ ይዘቶች ከወዲሁ እየተካተቱ ነው፡፡
በቱሪዝም ዘርፍ እንቅፋት የሆኑ በርካታ ችግሮች የተጠቀሱ ሲሆን፣ በተለይ የመሬት አቅርቦት፣ የፋይናንስ፣ የመረጃ፣ ከመንግሥት በኩል የሚሰጥ ማበረታቻ ማነስና ብክነት መብዛቱ ብሎም የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡