Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዚህ ዓመት ከ4.6 ሚሊዮን ቶን በላይ የስንዴ ምርት እንደሚኖር ተገምቷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጫት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሲያስገኝ የብርዕ ሰብሎች ግማሽ ሚሊዮን ገደማ አስመዝግበዋል

በየወቅቱ እየታተመ የሚወጣውና ስለዓለም አገሮች የግብርና ሸቀጦችና የንግድ እንቅስቃሴ መረጃዎችን የሚያሠራጨው የአሜሪካ የግብርና አገልግሎት ተቋም ሪፖርት፣ በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ የ4.6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ምርት እንደሚኖር ትንበያውን አስቀምጧል፡፡

በአሜሪካ የግብርናው መሥሪያ ቤት ሥር፣ የውጭ ግብርና አገልግሎት በተሰኘው ተቋም በኩል ‹‹ግሎባል አግሪካልቸራል ኢንፎርሜሽን ኔትወርክ-ጌይን›› በሚል መጠሪያ እየተሠራጨ የሚገኘው ይህ ሪፖርት፣ በየጊዜው የአገሮችን ወቅታዊ የግብርና መረጃዎችና ትንበያዎች ያሠራጫል፡፡ ሪፖርቱ ምንም እንኳ በይፋ የአሜሪካ መንግሥትን ፖሊሲ በተለይም የግብርናውን መሥሪያ ቤት አይወክልም ይባል እንጂ በአብዛኛው ከዚህ ተቋም ጋር ተመጋጋቢ መረጃዎችና ተቀራራቢ ትንበያዎችን ይፋ ሲያደርግ የቆየ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ኢትዮጵያን በሚመለከተው የሪፖርቱ ክፍል ከቀረቡት ውስጥ በስንዴ ምርትና ፍጆታ፣ ግብይትና አቅርቦት መስክ ብቻም ሳይሆን በበቆሎ፣ ገብስና ማሽላ ምርቶች ረገድ መረጃዎችን ይፋ አድርጓል፡፡

ባለፈው ዓመት በኢትየጵያ 4.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ተመርቷል ያለው ሪፖርቱ፣ ይህም የሆነው በዚህ ዓመት የተሻለ የአየር ጠባይ ሁኔታ እንደሚኖር ትንበያዎች በመኖራቸው፣ የተሻለ የግብዓት አቅርቦት እንደሚኖር በመታመኑ፣ የተባይና የበሽታ ክስተት ዝቅተኛ እንደሚሆን በመታሰቡ እንደሆነ ለምርት ጭማሪው ትንበያ በምክንያትነት የቀረቡ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የስንዴ ምርት ሰንሰለቶች በአሁኑ ወቅት የሜካናይዜሽን እርሻ በመጀመራቸው ጭምር ምርት ሊጨምር እንደሚችል ትንበያው ያስቀምጣል፡፡

ከዚህም ባሻገር መንግሥት በግብርናው መስክ የመስኖ እርሻን አስፋፋለሁ ማለቱ፣ የሜካናይዜሽንና የግብርና ኤክስቴንሽን ሥራዎችን በቆላማ አካባቢዎች ጭምር እንደሚያስፋፋ ማስታወቁ ጭምር የስንዴና የሌሎችም የሰብል ምርቶች ምርታማነት መጨመር ታሳቢ መደረጋቸውን ሪፖርቱ ያጣቅሳል፡፡ በዚህም ሳቢያ እስካሁን ከ30 እስከ 35 በመቶ የሚሆነው የስንዴ ምርት ከውጭ በማስገባት የአገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት ሲሞከር እንደነበርና ወደ ውጭ የሚላክ የሰብል ምርት ላይ በተለይም በስንዴ፣ ጤፍ፣ በቆሎና የመሳሰሉት ምርቶች ላይ ዕገዳ መጣሉ የአገር ውስጥ አቅርቦት እንዲሻሻል ሊያደርገው እንደሚችል ታስቧል፡፡ ይህም ይባል እንጂ እስከ 500 ሺሕ ብር ግምት ያለው የሰብል ምርት በተለይም እንደ በቆሎ ያለው ምርት ለውጭ ገበያ እየቀረበ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ለስንዴ ተስማሚ ሁኔታዎች በመኖራቸው በ1.66 ሚሊዮን ሔክታር መሬት የሚለማ 4.6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ እንደሚጠበቅ ተተንብዩዋል፡፡ በዚሁ አግባብ በ2.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ 7.3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በቆሎ፣ በ1.84 ሚሊዮን ሔክታር መሬት 4.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማሽላ፣ በ1.2 ሚሊዮን ሔክታር እርሻ 2.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ገብስ እንዲሁም ከ420 ሺሕ ሔክታር ማሳ 810 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ዳጉሳ እንደሚመረት ትንበያው አስፍሯል፡፡

ከአገሪቱ የብዕር ምርት ውስጥ ስንዴ 20 በመቶውን እንደሚሸፍን መረጃው ይጠቅሳል፡፡ በሔክታር 2.7 ቶን የሚገኝበት ስንዴ ከ90 በመቶ በላይ ምርቱ ግን በአነስተኛ ገበሬዎች በአነስተኛ የእርሻ ይዞታ የሚመረት ከመሆኑም ባሻገር መስኖ የማያውቀው እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ ከኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ውስጥ ጠንካራ ቀይ የሚባለው ዝርያ እስከ 80 በመቶ ድርሻ ሲኖረው፣ ቀሪውን 20 በመቶ የሚይዘው ዱረም የሚባለው የስንዴ ዓይነት ነው፡፡ ቀይ ስንዴ በአብዛኛው ለድፎ ዳቦ፣ ለንፍሮና ቆሎ፣ ለጠላ መጥመቂያነት ጭምር ጥቅም የሚሰጥ ሲሆን፣ የዱረም ስንዴ ግን ለዱቄት ፋብሪካዎች፣ ለዳቦ ቤቶችና ለፓስታና ማካሮኒ ማምረቻነት ይውላል፡፡

በስንዴ አምራችነት ከ4.7 ሚሊዮን በላይ አነስተኛ አርሶ አደሮች ኑሯቸውን እንደሚገፉም ይታመናል፡፡ በእነዚህ ገበሬዎች አማካይነት የአገሪቱ 95 በመቶ ስንዴ እንደሚለማ ሲታመን፣ አምስት በመቶ ብቻ በሰፋፊ እርሻዎች አማካይነት እንደሚለማ የአሜሪካው ጌይን ሪፖርት ያትታል፡፡

ከምርቱ ባሻገር የስንዴ ፍጆታንም የቃኘው ይህ ሪፖርት፣ በመጪው ዓመት ከ6.3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ያላነሰ የስንዴ ፍላጎት እንደሚኖር ግምቱን አስፍሯል፡፡ በተለይም ከስምንት ሚሊዮን በላይ አስቸኳይ የዕለት ደራሽ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ ዕርዳታ ፈላጊዎች በኢትዮጵያ ስለሚገኙ ይህ የፍጆታ መጠን ሊኖር እንደሚችል በማመሳከር ግምቱን ያጠናክራል፡፡ የአገሪቱ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር የገቢ አቅም መሻሻልም ለስንዴ ፍጆታ መጨመር አስተዋጽኦ አድርጓል ይላል፡፡ ይህም በመሆኑ በአቅርቦትና በፍላት መካከል ክፍተት ፈጥሯል፡፡

በዚህ ዓመት ብቻ ከ1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ያላነሰ ስንዴ ከውጭ በግዥ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡ በቅርቡ እንኳ ከ400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ የስንዴ ግዥ ለመፈጸም ጨረታ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ ይህም በመሆኑ በምርት እጥረት ሳቢያ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ መንግሥት ስንዴ በድጎማ ለዱቄት ፋብሪካዎች እያረቀበ፣ ዱቄት ፋብሪካዎችም ለዳቦ ቤቶች በማቅረብ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ሲሞከር ቆይቷል፡፡

ይህም ሆኖ መንግሥት በሁለት መንገድ ትችት ላይ መውደቁ አልቀረም፡፡ የስንዴ ድጎማው በተለይ ከውጭ ለሚገባው ስንዴ የሚውል በመሆኑ፣ በአንድ በኩል የአገር ውስጥ አምራቾችን በዋጋ እንዲጎዱ የሚያደርግ ሥጋት ላይ ጥሏቸዋል የሚል ስሞታ ይቀርብበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በድጎማ የሚገባው ስንዴም መዳረሻው እንደታለመው ሳይሆን፣ ወደ ውጭ እየወጣ ነው የሚል ወቀሳ በኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጭምር ሲቀርብ ይደመጣል፡፡ ስንዴው ተምልሶ ወደ ውጭ መውጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ በድጎማ ሊቀርብለት የሚገባው ደሃው የኅብረተሰብ ክፍል እንደሚገባው ተጠቃሚ አለመሆኑም መንግሥትን ለትችት ከሚጋብዙ ክፍተቶች ውስጥ ይካተታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ወደ ውጭ ተልከው ከ612 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካስገኙ የሰብል ምርቶች ውስጥ ጫት፣ የቅባት እህሎችን በመከተል ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘቱን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ካሠራጨው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመሆኑም የቅባት እህሎች የ37.42 በመቶ ድርሻ ሲይዙ፣ ጫት የ33.81 በመቶ ድርሻ በመያዝ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ አስገኝቷል፡፡ የጥራጥሬ ሰብሎች 28.05 በመቶ፣ የተፈጥሮ ሙጫ 0.46 በመቶ፣ ባህር ዛፍ 0.19 በመቶ እንዲሁም የብርዕና አገዳ ሰብሎች 0.07 በመቶ ወይም ከ430 ሺሕ ዶላር በላይ ያስገኙበት ድርሻ ነበራቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች