የዘቢዳር ቢራ አክሲዮን ማኅበር የ40 በመቶ ባለድርሻ የሆነው ዥማር ሁለገብ አክሲዮን ማኅበር አባላት አክሲዮናቸውን እንዲሸጡ ከካስትል ኩባንያ ጋር ሲደረግ የነበረው ድርድር የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ ቢያሳይም፣ ባለአክሲዮኖች ግን በጭማሪው ላይ ስምምነት ባለማሳየታቸው ድምፅ እንዲሰጡበት ተደረገ፡፡
የዥማር ባለአክሲዮኖች በቅርቡ ባደረጉት ጠቅላላ ጉባዔ፣ ካስትል ኩባንያ ያቀረበው አዲስ ዋጋ አንዱን አክሲዮን በ5.5 እጥፍ ዋጋ ወይም አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለውን አክሲዮን በ5,500 ብር ለመግዛት እንደተስማማ ጠቅሰው፣ በአክሲዮን ሽያጩ ላይ ሲደራደሩ የቆዩ የዥማር ቦርድ አባላት ካስትል በሰጠው አዲስ ዋጋ ላይ ባለአክሲዮኖች ድምፅ እንዲሰጡበት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ ይህም የሆነው የቀረበው የአክሲዮን ግዥ ዋጋ አሁንም ባለአክሲዮኖቹ ከሚጠይቁት ዋጋ አኳያ ዝቅ ያለ ነው የሚል ቅሬታ በመቅረቡ ነው ተብሏል፡፡
ከቦርድ አባላቱ የተገኘው መረጃ እንደሚገልጸው፣ ድምፅ ከሰጡት ባለአክሲዮኖች ሁለት ሦስተኛው አዲስ በቀረበው ዋጋ መሠረት የዥማር አክሲዮኖች እንዲሸጡ መስማማታቸው ተመልክቷል፡፡ በዚሁ መሠረት ቦርዱ ሽያጩን ለማስፈጸም እየሠራ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም ይባል እንጂ በዥማር ኩባንያ ውስጥ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው ባለአክሲዮኖች ቦርዱ የሄደበትን መንገድ አልተቀበሉትም፡፡
ከዥማር ኩባንያ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ድርድሩ የተካሄደበት መንገድ ግልጽ እንዳልሆነና ከዚህ ቀደም ባለአክሲዮኖች ባስተላለፉት ውሳኔ መሠረት ቦርዱ የሽያጭ ድርድሩን በሚያካሂድበት ወቅት ከፍተኛ ባለአክሲዮኖችም ተካትተው ድርድሩ እንዲከናወን ተወስኖ እንደነበር ባለአክሲዮኖቹ ይናገራሉ፡፡
ይህ ሆኖ ሳለ በቅርቡ ድርድር የተደረገበትና ድምፅ የተሰጠበት ዋጋ ላይ ቦርዱ የዥማር ሁለገብ ኩባንያን ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች ሳያሳትፍ ግልጽ ባልሆነ መንገድ ያካሄደው በመሆኑ ጉዳዩ እንዲጣራላቸው መጠየቃቸውም ተሰምቷል፡፡
ተሻሽሎ በቀረበው ዋጋ መሠረት የአክሲዮን ድርሻቸውን ለመሸጥ አለያም እንደያዙ ለመቆየት የሚያስችል የድምፅ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡ በዚህ አግባብ ድምፅ መሰጠቱም ቢሆን፣ ሽያጩን በቶሎ ለመፈጸም ሲባል በጥድፊያ የተደረገ ነው በማለት እነዚሁ ቅሬታ አቅራቢዎች ገልጸው፣ አክሲዮኑን አሁን ከቀረበለት በላይ በተሻለ ዋጋ እንዳይሸጥ ያደርጋል በማለትም ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
የ40 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው እነዚህ ባለሀብቶች፣ ከዚህ ቀደም በአራት እጥፍ ዋጋ አክሲዮኖቻቸውን እንዲሸጡ ተጠይቀው ሳይቀበሉ ቆይተዋል፡፡ ይህንን ያደረጉበት ምክንያት እንዳላቸው የሚናገሩት ባለአክሲዮኖቹ፣ በወቅቱ ቢጂአይ ኢትዮጵያ (የካስትል እህት ኩባንያ) ራያ ቢራን ሲገዛ ያቀረበውን ዋጋ በማነፃፀር ለዘቢዳር ቢራ እንዲያውም ከዚያ የተሻለ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል በማለት እየተከራከሩ ነው፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት ቢጂአይ ኢትዮጵያ ራያ ቢራን ሲገዛው፣ አንዱን አክሲዮን በሰባት እጥፍ ዋጋ ክፍያውን በመፈጸም ነበር፡፡ ይህም በመሆኑ ዘቢዳር ቢራ የተሻለ ዋጋ የሚያገኝበት ዕድል ስላለው፣ አንዱ አክሲዮን በአራት ዕጥፍ ዋጋ መሸጥ የለበትም በማለታቸው ሳቢያ በርካታ ድርድሮች እንዲካሄዱ ተወስኖ ጉዳዩ ሲታይ ቆይቷል፡፡ ቆይቶም በዥማር ባለአክሲዮኖች ድምፅ ብልጫ ይወሰን የሚል ሐሳብ ቀርቦ፣ ቦርዱ ከካስትል ጋር ባደረገው ድርድር ወቅት ይዞት የቀረበው የ5.5 ዕጥፍ ዋጋ ግን አሁንም አነስተኛ ሆኖ እንዳገኙት አስታውቀዋል፡፡ ችግሩ ግን ይህ ብቻ እንዳልሆነ የሚጠቁሙት ቅሬታ አቅራቢ ባለአክሲዮኖች፣ የድምፅ ቆጠራው ውጤትም ቢሆን በወቅቱ ባለመገለጹ ጥርጣሬ እንዳደረባቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
ከዚህም ባሻገር ከካስትል ጋር ስምምነት ተደርጎበታል ተብሎ የቀረበው ሒሳብ በ5.5 እጥፍ ሽያጩ ሲከናወን ክፍያው ግን በአንድ ጊዜ የሚፈጸም ሳይሆን በየጊዜው እንደሚሆን መነገሩም የተሰጠው ዋጋ አነስተኛ መሆኑ ሳያንስ ክፍያው በአራት ዙር ክፍያ እንዲፈጸም ስምምነት ላይ ተደርሷል መባሉንም ባለአክሲዮኖቹ አልተቀበሉትም፡፡
የካስትል እህት ኩባንያ የሆነው ቢጂአይ ራያ ቢራን ሲገዛ ክፍያውን በአንዴ የከፈለ ሲሆን፣ ለዘቢዳር ሲሆን ለምን በተቆራረጠ መንገድ ይከፈላል? የሚልም ጥያቄ አስነስተዋል፡፡
የዘቢዳር ቢራ ከፍተኛ ባለአክሲዮን የነበረውና የቤልጂየሙ ዩኒብራ ኩባንያ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ በተደረገ ድርድር አክሲዮኖቹን ለቢጂአይ መሸጡ ይታወሳል፡፡ በዘቢዳር ውስጥ የነበረውን የ58 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ለቢጂአይ የሸጠበት ዋጋ ግን በሁለቱም ወገን እስካሁን ድረስ ይፋ አልተደረገም፡፡ 40 በመቶ ድርሻ ያላቸውና በዥማር ሁለገብ አክሲዮን ኩባንያ ውስጥ ባለድርሻ የሆኑትም አክሲዮናቸውን ለካስትል እንዲሸጡ ጥያቄው የቀረበላቸው ከዩኒብራ ጋር የሽያጭ ስምምነቱ ከተፈጸመ በኋላ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዘቢዳር ቢራ ፋብሪካ ከአዲስ አበባ በ176 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በጉራጌ ዞን ጉብርዬ በተሰኘች ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ፋብሪካው በ150 ሺሕ ካሬ ሜትር ይዞታ ላይ ተገንብቶ ሥራ የጀመረው ከሦስት ዓመታት በፊት ነው፡፡
በዓመት 350 ሺሕ ሔክቶ ሊትር የማምረት አቅም ያለው ይህ ቢራ ፋብሪካ፣ በወቅቱ ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት ስለመገንባቱም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዘቢዳር ቢራ አክሲዮን ኩባንያ ውስጥ የ40 በመቶ ድርሻ የያዘው የዥማር አክሲዮን ማኅበር፣ በሥሩ ከሁለት ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖችን ያቀፈ ኩባንያ ነው፡፡ በዥማር ኩባንያው ውስጥም ከፍተኛ ባለአክሲዮን ተብለው ከሚጠቀሱት አንዱ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ነው፡፡