[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ታዋቂ ግለሰብ ጋር ሆቴል ተገኝተው እያወሩ ነው]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ?
- አገሪቱ ወዴት እያመራች ነው ክቡር ሚኒስትር?
- አገሪቱማ በለውጥ ጎዳና ላይ ናት፡፡
- በነውጥ ጎዳና ማለትዎ ነው?
- ምን ይላል ይኼ?
- ክቡር ሚኒስትር ለምን የሚነገራችሁን አትሰሙም?
- ምንድነው የተነገረን?
- ሮድማፕ አዘጋጁ፡፡
- የምን ሮድማፕ ነው?
- ለውጡ ሮድማፕ ያስፈልገዋል፡፡
- ሮድማፕ ምንድነው?
- ለውጡ የሚጓዝበት አቅጣጫ ጠቋሚ ሮድማፕ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
- ለምን ያስፈልጋል?
- የምንሄድበትን እንድናውቀው ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምንሄደውማ ወደ ልማት፣ ዲሞክራሲና ዕድገት ነው፡፡
- እንዳይሸወዱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት?
- የተዘጋጀ ሮድማፕ ከሌለ በመሀል ጉዟችን ወደ ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡
- ወደ ሌላ ወዴት?
- ወደ ዕልቂትና ፍጅት፡፡
- አንተ ደግሞ ሁሌ ሕዝብ ማሸበር ትወዳለህ፡፡
- እውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኔ ያልኩት ለምን አልሆነም ማለት ትወዳለህ፡፡
- እስከ ዛሬም እኔን ብትሰሙኝ እንዲህ ባልሆናችሁ ነበር፡፡
- እንዴት? እንዴት?
- ለውጡ እንዴት መሄድ እንዳለበት ነግሬያችሁ ነበር፡፡
- አንተን ማን ነው መካሪ ያደረገህ?
- ከእርስዎ ጋር እንዲህ መነጋገር አይገባንም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኮ ለምን?
- በአሁኑ ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለአገሪቱ ዕጣ ፈንታ የመወሰን አቅም አለው፡፡
- እሱስ ልክ ነው፡፡
- እኔ ደግሞ ምን ያህል ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደሆንኩ ያውቃሉ፡፡
- ምን ይደረግ እያልክ ነው?
- አሁንም የምንነግራችሁን ካልሰማችሁ አገሪቱ ወደባሰ ነገር መሄዷ አይቀርም፡፡
- እንዴት?
- ክቡር ሚኒስትር በየቦታው መፈናቀሉ እኮ በጣም እየጨመረ ነው፡፡
- ምን ይደረግ?
- ሁሉንም አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ አስቀምጣችሁ አወያዩ፡፡
- አሁን ከእኔ ጋርም መወያየት አለባችሁ ለማለት ነው?
- መልሱን መቼም እርስዎም ያውቁታል፡፡
- ወይ ጣጣ፡፡
- የአገሪቱ ኢኮኖሚም ከድጡ ወደ ማጡ እያዘገመ ስለሆነ በአፋጣኝ ይታሰብበት፡፡
- እ…
- ለማንኛውም እኔ በግሌ ያሰብኩት ፕሮጀክት አለ፡፡
- የምን ፕሮጀክት?
- ለአገሪቱ በጣም ጠቃሚ ፕሮጀክት ነው፡፡
- እሺ፡፡
- ስለዚህ በአፋጣኝ እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፡፡
- ምን?
- የውጭ ምንዛሪ፡፡
- ስማ አገሪቱ ያላት የውጭ ምንዛሪ ለመድኃኒትና ለነዳጅ ነው ሲባል አልሰማህም?
- ቢሆንም እኔ ለፕሮጀክቴ የውጭ ምንዛሪ እፈልጋለሁ፡፡
- ምን ልትገዛ?
- ላሰብኩት ፕሮጀክት ስልሳ አዝዣለሁ፡፡
- ስልሳ ምን?
- ቪ8!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ሆንክ?
- ስንት ተስፋ አድርገንባችሁ፡፡
- እኮ ምን ሆንክ?
- ክቡር ሚኒስትር የእውነቴን ልንገርዎት፡፡
- ንገረኝ፡፡
- በለውጡ ትልቅ ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡
- አሁንም ተስፋ አትቁረጥ፡፡
- አይ ክቡር ሚኒስትር በዚህ ከቀጠልንማ ትኬት መቁረጤ አይቀርም፡፡
- የምን ትኬት?
- አገር ለመክዳት ነዋ፡፡
- ምን ሆንክ ደግሞ አንተ?
- ዓይናችን እያየ እኮ አገሪቱ እንደ አውሮፕላናችን ልትከሰከስ ነው፡፡
- የለውጡ አደናቃፊ ነህ ልበል?
- ኧረ የለውጡ ደጋፊ ነበርኩ፡፡
- ታዲያ አርፈህ ድጋፍህን ቀጥላ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እያስፈራችሁኝ ነው፡፡
- ለውጥ እኮ ዝም ብሎ አይመጣም፡፡
- ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው አሉ፡፡
- ምን እያልክ ነው?
- ዝም ብላችሁ በቃላት እየሸነገላችሁን አገሪቱ ወዳልሆነ አቅጣጫ እያመራች ነው፡፡
- ስማ ታፍኖ የነበረ ሕዝብ ነፃ ሲወጣ ከዚህም የባሰ ሊታይ ይችላል፡፡
- ማን ነው ነፃ የወጣው?
- ሁሉም ሕዝብ ነዋ፡፡
- እ…
- እናንተ ራሳችሁ እንደ ልባችሁ መናገር የጀመራችሁት አሁን አይደል እንዴ?
- የመናገር መብታችን እኮ በአጭሩ ሊቀጭ ነው፡፡
- ማን ነው የሚቀጨው?
- እናንተው ናችኋ፡፡
- እንዴት አድርገን?
- ይኸው የጥላቻ ንግግር ሕግ እያወጣችሁ አይደል እንዴ?
- የጥላቻ ንግግር ይፈቀድ እያልክ ነው?
- እሱማ እንዲቆም እኔም እታገላለሁ፡፡
- ታዲያ ምን እያልክ ነው?
- ፈርዶብኝ በማር ውስጥ የተደበቀን መርዝ የመለየት ችሎታ አለኝ፡፡
- አልገባኝም?
- በዚህ ሕግ በኃላፊነት የሚሠሩ ሚዲያዎችም እንደሚታፈኑ አውቃለሁ፡፡
- እ…
- በፀረ ሽብር ሕጉ እኮ የተደረገው እንደዚያው ነው፡፡
- እሱ እኮ ሊሻሻል ነው፡፡
- ይሻሻላል ስትሉን እኮ በጥሩ መስሎን ነበር፡፡
- በጥሩ ነው የሚሻሻለው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ያሻሻላችሁት ይኼኛው እኮ ይብሳል፡፡
- እ…
- ለማንኛውም የተባላችሁትን ልንገራችሁ፡፡
- ምን ተባልን?
- ትሻልን ፈተን…
- እ…
- ትብስን አገባን!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ተመራማሪ ስልክ ይደውልላቸዋል]
- በጣም አዝኛለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን አዘንክ?
- አገሪቱን እያሰብኩ ነዋ፡፡
- ሁሉም ነገር መልክ መልኩን ይይዛል፡፡
- ተው እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምነው?
- ከዚህ በላይ አገሪቱ ምን እስክትሆን ነው የምትጠብቁት?
- የተላለፈችልን አገር ምን ዓይነት እንደነበረች አትርሳ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ላለፉት 27 ዓመታት ሕዝብ ከሕዝብ ጋር እንዲተላለቅ ሲሠራ ነበር እኮ፡፡
- እሱንማ አውቃለሁ፡፡
- ታዲያ የ27 ዓመት ወጣት እንዴት ከአንድ ዓመት ጨቅላ ጋር ይወዳደራል?
- ሁሉም ነገር ይገባኛል፡፡
- ስለዚህ የአገሪቱ ችግር እንዲህ በቀላሉ አይፈታም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አሁን ችግሩ ከዕለት ወደ ዕለት እየባሰበት እኮ ነው፡፡
- የሴራ ፖለቲካውን እያወቅከው?
- ቢሆንም በኋላ የታሪክ ተጠያቂዎች እንዳትሆኑ መጠንቀቅ አለባችሁ፡፡
- ምን ማድረግ እንችላለን?
- የአገሪቱ ኢኮኖሚ እኮ በአፍጢሙ እየተደፋ ነው፡፡
- አገሪቱ እንዲህ እየታመሰች ኢኮኖሚው እንዴት ይረጋጋ?
- በነገራችን ላይ ክቡር ሚኒስትር፣ ኢኮኖሚው መፍትሔ ቢያገኝ አገሪቱ ትረጋጋ ነበር፡፡
- እንዴት?
- ባለፈውም ነግሬዎት ነበር፡፡
- ምንድነው የነገርከኝ?
- ለወጣቱ የሥራ ዕድል ቢፈጠርለት በየቦታው ብጥብጥ ሊኖር አይችልም፡፡
- እ…
- ወጣቱ ወደ ጎዳና የሚወጣው የሚሠራው ስለሌለው ነው፡፡
- እሱማ እናውቃለን፡፡
- ስለዚህ ለወጣቱ ሥራ ፍጠሩለት፡፡
- ሥራ ከተፈጠረለት ማን ይሠለፋል?
- እ…
- ማለቴ ለውጥ መኖሩ የሚታወቀው ሰው እንደ ልቡ መሠለፍ ሲችል ነው፡፡
- አሁን ገባኝ፡፡
- ምኑ?
- እናንተ መፍጠር የምትፈልጉት ሥራ አይደለም፡፡
- ታዲያ ምንድነው?
- ሥራ አጥ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከደላላው ጋር እያወሩ ነው]
- ሥራ እንዴት ነው?
- ሁሉም ነገር ተቀዘቅዟል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንተ ሁሌ መለኛ አይደለህ እዴ?
- አዎን ግን አሁን ትንሽ ከበድ ብሏል፡፡
- እና ሥራ የለም እያልክ ነው?
- እሱማ አንድ ሐሳብ መጥቶልኝ ነበር፡፡
- ምን ዓይነት ሐሳብ?
- ያው ከለውጡ በኋላ የሥራ አጡ ቁጥር ጨምሯል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሱማ ይታወቃል፡፡
- በለውጡ ደግሞ ሕዝቡ እንደፈለገ ወደ ጎዳና ወጥቶ መሠለፍ ችሏል፡፡
- ሥራ ከሌለ ቢሠለፍ ምን ያደርጋል?
- አሁን ባሰብኩት ሐሳብ ለወጣቱም ሥራ ልንፈጥርለት እንችላለን፡፡
- እንዴት?
- በለውጡ ሁሉም ሰው መሠለፍ ይፈልጋል፡፡
- እ…
- ስለዚህ አጀንዳ ኖሯቸው ሠልፍ ለሚጠሩ ሠልፈኞችን ማቅረብ እንችላለን፡፡
- እንዴት? እንዴት?
- አዩ ክቡር ሚኒስትር እኛ ጎዳና የሚወጡ ሠልፈኞችን በማዘጋጀት አጀንዳ ኖሯቸው ሠልፍ ለሚጠሩ እናቀርባለን ማለት ነው፡፡
- አንተ እኮ አባ መላ ነህ፡፡
- ሠልፈኞችን ሲፈለግ በፆታ፣ ሲያስፈልግ በዕድሜ፣ ከዚያም በብሔርና በሃይማኖት እየከፋፈልን እናቀርባለን፡፡
- ይኼማ ወሳኝ ሥራ ነው፡፡
- ስለዚህ በአስቸኳይ ቢልቦርድ ላሠራ፡፡
- ምን የሚል?
- ሠልፈኞችን ከአሠላፊዎች ጋር እናገናኛለን!