ጨኖ ግራጫ ቢጤ የሆነ፣ ፈርጠም ያለ፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪካ፣ በተጨማሪም በኮንጎ ደኖች የሚገኝ ጦጣ ነው። በኢትዮጵያ የሚገኘው ዓይነት ጨኖ የፀጉሩ ቀለም ግራጫና ጥቁር የሆነ፣ ፊቱ የጠቆረ ሰማያዊ የሆነ፣ አገጭና አንገቱ ነጭ ነው። የወንዶቹ ክብደት እስከ 12 ኪሎ ግራም ሲሆን፤ አማካዩ 4.5 ኪሎ ግራም ይመዝናሉ። ጨኖ የደን ጦጣ ነው። የደን ጦጣዎች ብዙ ጊዜ ከዝናባማ ሥፍራ ደኖች ውጪ አይገኙም። ጨኖ ግን ከእነዚህ ደኖች ውጪም በሚገኙ ደኖች ውስጥ ይኖራል። በኢትዮጵያ በጎደሬ ደን ውስጥ፣ ቴፒ አጠገብ ሜጢ አካባቢ ይገኛሉ።
ጨኖ ከማንኛቸውም የጦጣ ዓይነቶች የበለጠ ቅጠል በል ቢሆንም ብዙ ዓይነት ምግቦች ይመገባል። ቅጠላ ቅጠል፣ ፍራፍሬ፣ ትላትልና ሦስት አፅቄዎች፣ አበቦች፣ ጥራጥሬዎች ወዘተ ይበላሉ። ዛፍ ላይ ታቁሮ የሚያገኙትን ውኃ ይጠጣሉ። የሚያስፈልጋቸውን ብዙ ውኃ የሚያገኙት ግን ውኃማ ከሆኑ ፍሬዎችና ቅጠሎች ነው። የተገኘውን ብዛት ያለው ምግብ በመመገብ፣ ጨኖዎች አነስተኛ በሆነ የመኖሪያ አካባቢዎች ሊኖሩ ይችላሉ።
ሰሎሞን ይርጋ (ዶር.) «አጥቢዎች» (2000)