Monday, May 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

“የላሊበላ ውቅር ቤተ ክርስቲያናት”

በሕይወት ከተማ

ላሊበላን ሄደው ሲጎበኙ የተለያዩ ስሜቶች ይፈራረቃሉ። የመጀመሪያ ጊዜ ከሆነእንዴት እስከዛሬ ሳላየው ቀረሁ?” የሚል የቁጭት ስሜት፣ ከዚህ በፊት አይተውት ከሆነ ደግሞእንዴትስ ድጋሚ እያየሁት እንደ አዲስ ያስደንቀኛል?!” የሚል የመደመም ስሜት። እኔም በየተራ ሁለቱ ስሜቶች በተለያየ ጊዜ ተሰምተውኛል።

በአሁኑ ጊዜ ላሊበላ የሚጎበኘው እንደድሮው በከብት ጀርባ ተጭኖ፣ ሲመሽም ባስጠጋ ጎጆ ታድሮ፣ ወራትንም ፈጅቶ አይደለም። አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ አንስቶ ሰዓት ሳይሞላ ላስታ አንከብክቦ ያደርሳል። ባለታክሲውም በግማሽ ሰዓት ወደ ቱሪስት መናኸሪያዋ ላሊበላ ከተማ ገስግሶ ያወርዳል። ሆቴሎችም እንደአሸን ናቸው።ቤተ ክርስቲያኖቹ በየት ናቸውተብሎ ቢጠየቅም ከሕጻን እስከ አዋቂ መንገድ ያሳያል።

ከከተማው እምብርት በስተምዕራብ ዳገቱን ወጥተው ሲጨርሱ የዩኔስኮ ድንኳን በሩቁ ይታያል። ድንኳኑ ባይኖር ቤተ ክርስቲያኖቹን በሩቅ መለየት የሚከብድ ይመስለኛል። አንዴ ግን አጠገቡ ከደረሱ በኋላ የሚታየው የቤተ ክርስቲያናቱ ግዙፍነትና የራሳችን ትንሽነት ብቻ ነው።

ላሊበላ በዓለማችን ካሉት አስደናቂና አስደማሚ ክስተቶች መካከል ይሰለፋል ብል ማጋነን አይመስለኝም። በዓይን ካላዩት ግን የማስደነቁን ጥልቀት መረዳት የሚቻል አይመስለኝም።

ላሊበላን ስንጎበኝ በአእምሮዋችን የሚመላለሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። የላሊበላ ቤተ ክርስቲያናት እንዴት ተሠሩ? መቼ ተሠሩ? በማን ተሠሩ? ለምንስ ተሠሩ? በዚህም ጽሑፍ ስለነዚህ ጉዳዮች ያሉን የጽሑፍ መረጃዎች ምን እንደሚሉ መርምሬ በአጭሩ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ።

አንዳንድ ምስክሮች

ስለ ላሊበላ ብዙ ተብሏል፤ ተጽፏልም። በአገራችን ደራሲዎች ቢያንስ 15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የንጉሡ ላሊበላን ገድል፣ እንዲሁም ባለፉት ምዕት ዓመታት ስለ ንጉሡ አዳዲስ አፈ ታሪኮች እና ጥናቶች እንደገና ተከልሰው ቀርበዋል። በውጭ ጸሐፊዎችም በተለይ 16ኛው ክፍለ ዘመን  ጀምሮ እስካሁን የአጥኚዎችና የደራሲዎችን ቀልብ እንደሳበ ነው። በዛ ያሉ የውጭ አገር መጻሕፍትም በላሊበላ ዙርያ ለኅትመት በቅተዋል።

አፄ ላሊበላ የነገሠውና እነዚህን አስደናቂ ሕንፃዎችም የተሠሩት ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት 1200ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ እንደሆነ ይነገራል። የላሊበላ ገድል እንደሚገልጸው ንጉሡ ሁለተኛዋን ኢየሩሳሌም በላስታ ለማስገንባት እንዳለመና ቤተ ክርስቲያኖቹንም ማሠራት እንደጀመረ ነው።

ስለ ሕንፃዎቹ ታሪክ የሚያወጋው የመጀመሪያው ጽሑፍ መረጃ 15ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በተጻፈውገድለ ላሊበላነው። ይህም ገድል ከአፄ ላሊበላ ሞት ሁለት መቶ ዓመታት በኋላ እንደተጻፈ ሲገመት የገድሉም ጸሐፊ የላሊበላን ቤተ ክርስቲያናት ሲያደንቅ እንዲህ ይላል፣

ወዳጆቼ ሆይ! ተመልከቱ እንጂ። ይህ ሰው በእጆቹ የተገለጹለት እነዚህ ግንቦች በየትም በሌሎች አገሮች አልተሠሩም። ስለ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት አሠራር በምን ቃል ልንነግራችሁ እንችላለን? የቅጽራቸውንም ሥራ እንኳ መናገር አንችልም። የውስጡንስ ተዉት ታይቶ አይጠገብም፣ አድንቆና አወድሶም ለመጨረስ አይቻልም። በላሊበላ እጅ የተሠራ ይህ ድንቅ ሥራ በሥጋዊ ሰው የሚቻል አይደለም። የሰማይን ከዋክብት መቁጠርን የቻለ፣ በላሊበላ እጅ የተሠራውን መናገር ይችላል። እናም ለማየት የሚፈልግ ካለ ይመልከት። በላሊበላ እጅ የተሠሩትን የአብያተ ክርስቲያኖቹን ሕንፃዎች ይምጣና በዓይኖቹ ይመልከት!”

(ርእዩኬ ፍቁራንየ ዘከመዝ ብእሴ ዘበእዴሁ ተከሥታ እሎን ሕንጻ ማኀፈድ ዘኢተገብረ ዘከማሆን በኀበ ካልኣን በሓውርት። በአይ ልሳን ንክል ነጊረ ግብረቶን ለእሎን አብያተ ክርስቲያናት። ወግብረተ ቅጽሮንሂ ኢንክል ነጊረ ኅድጉሰ ዘእንተ ውስጦን ዘርእየሂ ኢይጽግብ በነጽሮ ወበአንክሮኒ ኢይክል ፈጽሞ። እስመ መንክር ተገብረ በላዕለ እደ ላሊበላ ዘኢይትከሀሎ ለሥጋዊ ከመ ይኈልቆሙ ለከዋክብተ ሰማይ ይኆልቆሙ ለመንክራትኒ ዘተገብራ በእደ ላሊበላ። ወለእመሰ ዘይፈቅድ ከመ ይርአይ ግብረ ሕንጻሆን ለአብያተ ክርስቲያናት ዘተገበረ በእደ ላሊበላ። ይምጻእ ወይርእይ በአዕይንቲሁ።)

ከአንድ መቶ ዓመታት ያህል በኋላም 1520ዎቹ ፍራሲስኮ አልቫሬዝ የተሰኘ ካህን ከፖርቱጋል መልእክት ለማድረስ መጥቶ ለስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጦ ነበር። በዚህም ወቅት የላሊበላን ውቅር ቤተ ክርስቲያናት ለመጎብኘት እድል አግኝቶ እያንዳንዱን ሕንፃ ከገለጸ በኋላ በመደነቅ እንዲህ ብሏል፣

ስለነዚህ ሕንፃዎች ከዚህ በላይ መጻፍ አልችልም። ምክንያቱም ከዚህ በላይ ብጽፍ የሚያምኑኝ አይመስለኝም። እስካሁን የጻፍኩትንም እውነት አይደለም ይሉኛል ብዬ እፈራለሁ። እኔ ግን በኀያሉ እግዚአብሔር እምላለሁ የጻፍኩት ሁሉ እውነት ነው! እውነታው እንዲያውም ከዚህም ከጻፍኩት እጅግ የበለጠ ነው። ውሸታም እንዳይሉኝ ግን ትቼዋለሁ።

ይህንንም አድናቆቱን 1532 .ም. በመጽሐፍ መልክ አሳትሞት የውጪው ዓለም ላሊበላን እንዲያውቅ አድርጓል። ስለ ላሊበላ ሕንፃዎች በጽሑፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመግለጽ የሞከረው የውጭ አገር ተጓዥ አልቫሬዝ ነበር። የአልቫሬዝ ገለጻ ምናልባትም ላሊበላ ከኢማም አሕመድ ኢብን ኢብራሂም (ግራኝ አሕመድ) ዘመን በፊት ምን ይመስል እንደነበር በመጠኑ ይገልጽልናል።

አልቫሬዝ ላሊበላን ከጎበኘ 10 ዓመታት በኋላ ኢማም አሕመድ በላሊበላ አካባቢ ሰፍሮ እንደነበረ ይነገራል። ኢማም አሕመድ ንዋየ ቅድሳቱንና ንብረቶቹን ከመውሰድ ውጭ እንደሌሎቹ ቤተ ክርስቲያናት ላሊበላን ለማቃጠል እና ለማውደም እንዳልሞከረ አንዳንድ ምንጮች ይጠቁማሉ። በቤተ ክርስቲያናቱ አሠራር ኢማም አሕመድም ተደምሞ የነበረ ይመስላል።

በድጋሚ 18ኛው ክፍለ ዘመን ከመጡ ጎብኚዎች ጀምሮም ብዙዎች ለላሊበላ አድናቆታቸውን በተለያየ ጊዜ ጽፈዋል። ነገር ግን በአፄ ላሊበላ ዘመን የነበሩ ምስክሮች የጻፉት ታሪክም ሆነ ስለ አሠራሩ የሚነግሩን መረጃዎች እጅግ ጥቂት ናቸው። በመሆኑም የተለያዩ አጥኚዎች ምሁራዊ መላምታቸውን በየጊዜው ሲሰጡን ከርመዋል።

 የላሊበላ ቤተ ክርስቲያናት እንዴት ?

በአገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም ክፍል ከተሠሩት ውቅር ሕንፃዎች አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት በተፈጥሮ ከተበጁ ዋሻዎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ከዋሻውም በመነሳት የተለመደውን የሕንፃ አሠራር አስመስሎ ድንጋዩን በመፈልፈል የሚሠሩ ናቸው። አንዳንዶቹ ግን አንድ ሙሉ ትልቅ ቋጥኝ ድንጋይን በመፈልፈል ከመሬት በታች ወይም ከተራራ በጎን በኩል ተፈልፍለው ይሠራሉ።

የላሊበላ ቤተ ክርስቲያናት ከመሬት በታች ወይም ጎን ተፈልፍለው ከሚሠሩት ዓይነቶች መካከል የሚመደቡ ናቸው። ይህም የሚሠራው እንደተለመደው የሕንፃ አሠራር ከመሠረቱ ተጀምሮ ወደላይ የሚቆለል ሳይሆን ከጣራው ተነስቶ ወደ ታች የሚፈለፈል ነው። ይህም ዓይነት አሠራር ከሕንፃ ሥራ ይልቅ ቅርጻ ቅርጽ ከመቅረጽ ጋር ይነጻጸራል። የቅርጻ ቅርጽ አሠራርን ዝነኛው የመሀከለኛው ዘመን ቀራጭ ሚኻኤል አንጀሎ ሲገልጸውእያንዳንዱ ድፍን ድንጋይ ውስጥ ቅርጽ አለየቀራጩም ሥራ ይህንን ቅርጽ ከታፈነበት ድንጋይ ነፃ ማውጣት ነውበማለት ነበር።

15ኛው ክፍለ ዘመን የገድለ ላሊበላ ደራሲም በተመሳሳይ መልኩ የላሊበላ ቤተ ክርስቲያናትን ቅርጽ አሠራር ሲገልጽ እንዲህ ይላል፣

በላሊበላ እጅ እኒህ አብያተ ክርስቲያናት ከምድር ልብ ወጥተው የሚሠሩበት ጊዜ ደረሰምድርን ከፈጠረ ጀምሮ ተሠውሮ የነበረውን ሕንፃ እንዲገልጥ እግዚአብሔር ወዷልና።

ወደ ቤተ ክርስቲያናቱ አሠራር ስንሄድ፣ የላሊበላ ገድል በድጋሚ እንዲህ ይላል፣

ገብረ መስቀልም (ላሊበላ) ልዩ ልዩ የሆኑ የብረት መሣሪያዎችን አሠራ። ለመጥረብም የተሠራ አለ። ለመፈንቀልም የተበጀ ብረት አለ። ለመፈልፈልም የተሠራ አለ። እነዚህን ቋጥኝ ድንጊያ የመቅደስ ሕንፃ የሚፈጸምባቸውን አሠራ። ገብረ መስቀልም ከዚያን ጊዜ ወዲህ ምድራዊ ሐሳብን፣ ሚስቱንም ደስ ለማሰኘት ፈቃድ ቢሆንም አላሰበም። ሁሉንም በሙሉ መንፈስ ስለ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት አሰበ እንጂ።

የላሊበላ ገድል እንደሚያሳየው ሕንፃዎቹ በተለያዩ የእጅ መሣሪያዎች (የብረት መጥረቢያ፣ መፈንቀያ፣ መፈልፈያ) እንደተሠሩ ይገልጻል። አፄ ላሊበላም እራሱ ሥራውን ይከታተል እንደነበረ ይናገራል።

በአገራችን የድንጋይ ፍልፍል ሕንፃዎች ታሪክ ላሊበላ የመጀመሪያው አይደለም። በተለይም በትግራይ አካባቢ ከላሊበላ በፊት የተሠሩ በርካታ ውቅር ቤተ ክርስቲያኖች ይገኛሉ። ታዲያ ላሊበላን ከሌሎቹ የሚለየው ምንድን ነው? የላሊበላ ውቅር ቤተ ክርስቲያናት በተለይ የሚታወቁት በአንድ አካባቢ እና ተቀራራቢ ጊዜ ከአስር የሚበልጡ ፍልፍል ሕንፃዎች በመሠራታቸው ነው። እንዲሁም ደግሞ ከሌሎቹ በተለየ ጥበብ የፈሰሰባቸው ስለሆነ ነውየአሠራሩ ጥራት፣ የሕንፃዎቹ ግዝፈት፣ እንዲሁም የጌጥ አወጣጣቸው ብስለት ነው። ከቀራጮቹ ችሎታም በተጨማሪ ይህንን ማድረግ የቻሉት የላስታ አካባቢ ድንጋይ ለሥራው ተባብሯቸው ይመስላል።

ሁለቱን የድንጋዮቹን ዓይነት አጥንቶ የነበረው የሥነ ቅርስ ተማራማሪው David Phillipson እንዲህ ይላል፦

በላስታ አካባቢ የተሠሩት ውቅር ቤተ ክርስትያናት በትግራይ ከተሠሩት ጓደኞቻቸው እጅግ ይለያሉ። በትግራይ የሚሠሩት hard sandstone ከተባለ በአካባቢው የሚገኝ ድንጋይ ሲሆን በላስታ የሚገኘው ድንጋይ ደግሞ ለስለስ የሚል volcanic tuff ነው። በትግራይ የሚገኘው ድንጋይ ለመቅረጽ ትንሽ ጠንከር ያለ ስለሆነ ብዙ ጌጦችን ለማውጣት እንዲሁም መስኮቶችን በትክክል ለማውጣት ስለማይመች፣ መስኮቶቹን በእንጨት ለመሥራት ይገደዳሉ። በላስታ የሚገኘው የድንጋይ ዓይነት ግን ለስላሳና ለመቅረጽ የሚመች በመሆኑ ለተለያዩ ጌጦችና ቅርጾች የተመቸ ነበር። በአንጻሩ በትግራይ ያሉት ውቅር ቤተ ክርስቲያናት በድንጋያቸው ጥንካሬ የተነሳ ቅርጻቸውን በሚገባ ጠብቀው ለመቆየት ሲችሉ፣ በላስታ የሚገኙት ግን በውጭው አየር ዝናብና ንፋስ ለመበላሸት የተጋለጡ ናቸው።

የላሊበላ ቤተ ክርስቲያናት ለምን ከአንድ ድንጋይ ተወቅረው ተሠሩ?

አንድ ሕንፃን ከድንጋይ ፈልፍሎ ማውጣት እጅግ ከባድ ሥራ እንደሆነ ግልጽ ነው። እንኳንስ አሥር ትላልቅ ቤተ ክርስቲያናት ይቅርና አንድን ሙቀጫ ከድንጋይ ፈልፍሎ ማውጣት ምን ያህል እንደሚከብድ የሞከረው ያውቀዋል። ታዲያ አባቶቻችን ይህንን እልህ አስጨራሽ ሥራ ለመሥራት ምን አነሳሳቸው ብለን መጠየቃችን አይቀርም። ስለምን ከመሬት በታች? ስለምን ከአንድ ድንጋይ? ሕንፃ በድንጋይ አነባብሮ መገንባት አይቀልም ነበር?

አንድም ሕንፃዎቹን ዘላለማዊ ለማድረግ መፈለግ ይመስለኛል። ይህም በመጠኑ የተሳካ ይመስላል። ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ እኛም የእጅ ሥራቸውን ለማድነቅ እነሱም የኛን ዘመን ሰው ለማስደመም በቅተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ አስደናቂ ነገር በመሥራት ለአምላካቸው ክብር፣ ታላቅነትን ለማሳየት ሊሆን ይችላል። ሰዎች እምነታቸውን ለአምላካቸው ለማሳየት የማይቻለውን አድርገው፣ የማይሞከረውን ሞክረው ይሠራሉ። ይህም አንድም ለቀጣዩ ዓለም ክብርን ለመሰብሰብ አንድም ደግሞ ለራሳቸው ውስጣዊ ደስታ እና ለአምላካቸው ክብር የሚያደርጉት ነው። ላሊበላና የጊዜው የሕንፃ ጥበበኞች እምነታቸው ጠንካራ መንፈሳቸው ገራራ እንደሆነ ከሥራቸው ለማየት እንችላለን።

አንድም ደግሞ ከመሬት በታች ቤተ ክርስቲያኖችን መሥራት ከጠላት እይታ ለመሸሸግ ሊሆን ይችላል። ከመሬት በላይ ከተሠራ ማንኛውም ሕንፃ ይልቅ ከመሬት በታች የሆነውን ጦረኛ ቢመጣ በቀላሉ እንደማያገኘው አስበው ይሆን? በጊዜው ጦርነቶች የተፋፋሙበት ዘመን እንደመሆኑ፣ ቤተ ክርስቲያናቱን ከእይታ ውጪ የማድረግን አስፈላጊነት አስበው እንደሆነ እገምታለሁ።

የላሊበላ ቤተ ክርስቲያናት በማን ?

እስከዛሬ የላሊበላን ውቅር ቤተ ክርስቲያናት ማን እንደሠራቸው በመገመት በተለያዩ ጊዜያት ብዙ መላምቶች ተሰጥተዋል። እስቲ ያለንን የጽሑፍ መረጃ ከኋላ ወደፊት እንይ።

ገድለ ላሊበላበንጉሥ ላሊበላ አዛዥነት በአገሬው ሰዎች እና በአማልክት እገዛ እንደተሠራ ይነግረናል፤

ሕዝቡን ሁሉ ወደ እርሱ እንዲሰበሰቡ አዘዛቸው። በተሰበሰቡም ጊዜ በአብያተ ክርስቲያናቱ ሕንፃ ሥራ የምትረዱኝ ሁላችሁም የምትቀበሉትን ደሞዛችሁን ተናገሩ አላቸው፣ እግዚአብሔር እንድሠራ አዞኛልና። እናንተም በአንደበታችሁ ደመወዛችሁን እንዴት እንደምትቀበሉ ተናገሩ። በጠራቢነትም ሥራ የሚረዳ፣ ጥራቢውንም በማውጣት የሚረዳ ሁላችሁም በአንደበታችሁ ተናገሩ። እንደ አላችሁኝ እሰጣችኋለሁና። ያለ ፈቃዳችን አስገደደን እንዳትሉኝ። በአጉረመረማችሁ ጊዜ ድካማችሁ ብላሽ እንዳይሆን።

ሁላቸውም ልባቸው እንዳሳሰባቸው ነገሩት። እሱም ስጦታቸውን ሳያጓድል እንዳሉት ሰጣቸው። የአብያተ ክርስቲያናቱን ሕንፃ ሥራ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ እስከ ፈጸመ ድረስ ለሚፈለፍልም ሆነ ለሚጠርብ የቤተ ክርስቲያኑን ጥራቢ ለሚያወጣም ሆነ  ደሞዛቸውን በጊዜው ይሠጣቸው ነበር።

16ኛው ክፍለ ዘመን ጊዜ ወደ ላሊበላ ተጉዞ ስለ ቤተ ክርስቲያኖቹ ጽፎ የነበረው አልቫሬዝ እንዲህ ይላል፤

የእነዚህ ቤተ ክርስቲያኖች ሥራ ሃያ አራት ዓመታት ፈጅቷል፤ ይህም ተጽፎ ይገኛል ብለው ነግረውኛል እናም የተሠራው በግብጾች እንደሆነም። ግብጾች ማለታቸውም ነጮች ማለታቸው ነው። ኢትዮጵያዊ ወሬ ነጋሪዎቼ ራሳቸው ይህንን አስደናቂ የጥበብ ሥራ በዚህ ጥራት መሥራት እንደማይችሉ ጠንቅቀው ያውቁታል።

ምናልባትም አልቫሬዝ አንድ አፍሪካዊ ሕዝብ ይህንን መሥራት ችሏል ብሎ ማመን የፈለገ አይመስልም። እንኳንና እሱ፣ የአገራችንም ሰዎች በጊዜው ማመን ስላቃታቸው የጥበቡን ባለቤትነት ለግብጾች ያስታቀፏቸው ይመስላል።

19ኛው ክፍለ ዘመን የመጡት ተጓዦች (Gehrard Rohlfs Raffray እና Simon) ሥራው ሙሉ ለሙሉ በውጭ አገር ሰዎች እንደተሠራ ማመናቸውን ጽፈዋል። የአገሬው ሰው በምንም መንገድ ይህንን ዓይነት ሥራ መሥራት የሚችል ጥበብ እንዳላካበተ አምነው ተቀብለዋል።

አልቫሬዝሀያ አራት ዓመታት ፈጅቷል ይህም ተጽፎ ይገኛልብሎ የገለጸልን ጽሑፍ እስካሁን አልተገኘም። ምናልባትም በዘመን ሒደት ከጠፉት ብራናዎች መካከል አንዱ ሊሆን ይችላል።

ይሁን እንጂ ከአልቫሬዝ ጽሑፍ 400 ዓመታት በኋላ 1951 .ም. ተጽፎ የታተመውዜና ላል ይበላልየተባለው መጽሐፍ የተለያዩ የጽሑፍ መረጃዎችና አፈ ታሪኮችን ሲጠቅስ ፍንጭ ይሰጣል። ደራሲው ደጃዝማች ብርሃነ መስቀል ደስታ የተጠቀሙት የጽሑፍ መረጃዎች ግን እስካሁን ስላልተገኙ ስለ መረጃው እውነትነት ማረጋገጫ አላገኘንም። መጽሐፉ የላሊበላ ሕንፃዎች በማን እንደተሠሩ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፣

“[ላልይበላ] በነገሠ 10 ዓመቱ መራ ከተባለው አጠገብ የነበረውን ቤተ መንግሥት ወደ ሌላ ለማዛወር አስቦ ቀይት ከተባለችው ባላባት ከሚዳቋ ገደል በላይ ከመካልት በመለስ ከጉሮ በታች ከገጠርጌ አፋፍ በላይ ያለውን ቦታ በአርባ ጊደር ገዝቶ ቤተ መንግሥቱን መካነ ልዕልት ብሎ እሰየመው ቦታ ላይ ሠራና በዚያው አቅራቢያ ታላላቅ ቋጥኝ ደንጊያዎች መኖራቸውን ስላረጋገጠ በግዛቱ የሚገኙትን ዜጋዎቹን አዞ ሕንፃ ቤት ክርስቲያኖቹን ማነጽ ጀመረ።

የሥራው መሪ ምንም ራሱ ቢሆን በዘመኑ የነበሩ ዜጎቹ ሁሉ ጥበብ ተገልጾላቸው በፈቃደ እግዚአብሔር እየተረዱ ሥራውን እያፋጠኑ ይሠሩ ነበር። እርሱም የሥራ መሪነቱ ብቻ ሳይሆን እንደ ሕዝቡ ሁሉ በጉልበቱ ይሠራ ስለነበርጥንታዊው ጽሑፍ ሥራው 23 ዓመት እንደፈጀበት ሲናገር የቦታውም ስም ለተወለደበት ስፍራ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ሮሐ አለው ይላል።

ይህም ጽሑፍ ሥራው ስለፈጀው ጊዜ አልቫሬዝ ከጻፈው ጋር ተቀራራቢ የጊዜ መስፈሪያ ተጠቅሟል። ስለ መሬቱ ስሪትም ሌላ ቦታ ያልተገኙ መረጃዎችን አካቷል።  ነገር ግን ደጃዝማች ብርሃነ መስቀል ይህንን መረጃ ከየት እንዳገኙት የሚገልጽ ነገር የለም።ጥንታዊው ጽሑፍብለው የጠቀሱትም በየት እንዳለ እስካሁን አይታወቅም።

በሌላ በኩል 1960ዎቹ አባ ገብረመስቀል ተስፋዬ የተሰኙ የላስታ ገነተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አለቃ ከዋሻ አግኝቼ ተርጉሜዋለሁ ብለውዜና ላሊበላየተባለ ጽሑፍ ለቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አቅርበው ነበር። ኦሪጅናሌው ግዕዝ ጽሑፍ እስካሁን ባለመገኘቱ ትክክለኛ መረጃነቱን ማረጋገጥ ባይቻልም አባ ገብረመስቀል ያቀረቡት የአማርኛ ዜና መዋዕል እንዲህ ይላል፤

ከመንግሥቱ ሕዝብ መካከል የሕንፃ ሥራ የሚችሉትን ጠበብት መረጠ አንድ መቶ ጠበብት አገኘ። ሕንፃውንም ለማነፅ መሣሪያ፣ የአፈሩ መዛቂያ አካፋ፣ መጥረቢያ፣ መዶሻ፣ መቆርቆሪያ፣ የሕንፃው ማለስለሻ ምሳር መሮ ተርዳ፣ መሰላል ሠረገላ ከብረታ ብረት አሰራ አዘጋጀ። የአሥሩን ቤተመቅደስ ሥራ ወርዱን ቁመቱን ጐኑን ወለሉን ለክቶ ሥራውን ጀመረ። በመጀመሪያ ቅጽሩን ለየ ከዚህ ቀጥሎ መስኮቱን ደጃፉን ለየ …”

እስከ 1950ዎቹ ድረስ በውጭው ዓለም እንዲሁም በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን የላሊበላ ሕንፃዎች በውጭ አገር ሰዎች የመሠራቱ ታሪክ ለረጅም ጊዜ ታምኖ ቆይቶ ነበር። ነገር ግን አገር ውስጥ የተገኙት ጽሑፎች በአገሬው እንደተሠሩ ደጋግመው ይናገራሉ። የውጭ አገር አጥኚዎችም 1960ዎቹ ከብዙ ጥናት በኋላ በአገር በቀል ጥበበኞች ሊሠሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ይህም ከላሊበላ በፊት የተሠሩ እንደሆነ የሚታመኑ ከአንድ ድንጋይ የተፈለፈሉ ውቅር ቤተ ክርስቲያኖች በላስታ አካባቢ እንዲሁም በሌሎች የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍሎች (ለምሳሌ ገርአልታ) በመገኘታቸው ነው። ይህ የውቅር ሕንፃ ጥበብ ለብዙ መቶ ዓመታት ከላሊበላ በፊት ሲሠራበት የኖረ በመሆኑ፣ ጥበቡ ከየትም ሳይሆን አገር በቀል ለመሆኑ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የላሊበላ ሕንፃዎችን በቅርበት ስናያቸው ብዙ የሥነ ሕንጻ ባህሪዮቹ ከአክሱም ጀምሮ ሲጠቀሙበት እንደነበረ፣ እያንዳንዱ የሕንጻውን ክፍሎች፣ ከጌጥ አወጣጥና የክፍሎች አወቃቀርን ጨምሮ ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲሠራባቸው የኖረ ጥበብ እንደሆነ እናያለን። ቀድሞ ከነበሩት የሕንፃ ሥራ ጥበቦች በተጨማሪ አንዳንድ አዳዲስ ጥበቦች በላሊበላ ስለሚታዩ ምናልባትም አንዳንድ የውጭ አገር ሰዎች በሥራው ተሳታፊ ሆነው ሊሆኑ እንደሚችሉ መላምቱን ክፍት እተወዋለሁ።

ላሊበላ በዓለማችን ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍለው ከተሠሩት ሕንፃዎች የመጀመሪያውም የመጨረሻውም አይደለም። በግብጽ ምድር ከላሊበላ ሕንፃዎች ሦስት ሺህ ዓመታት በፊት ንግሥት ሐትሸፕሱት ታላቅ ተራራ አስፈልፍላ ቤተ መቃብሯን አሠርታ ነበር። ከሷም በኋላ ብዙ ኀያላን ለራሳቸውም ሆነ ለሚያምኑበት ታላቅ አምላክ ተራራ ገምሰው ቋጥኝ ደርምሰው ሕንፃዎችን አሠርተዋል።

ለምሳሌ በህንድ አገር የሚገኘውን ከዓለማችን ትልቁን ውቅር የቡድሂስት ቤተ መቅደስ (Khailasa Temple) እንዲሁም በሀገረ ጆርዳን የሚገኘውን ካዝነህ ቤተ መቅደስን (AlKhazneh Temple) መጥቀስ ይቻላል።

በኢትዮጵያም ከአክሱም ጊዜ ጀምሮ ሕንፃዎችን ከአንድ ድንጋይ ፈልፍሎ መሥራት የተለመደ ጥበብ ነበር። ላሊበላ ግን አስደናቂ የጥበብ እመርታ አሳይቶናል። በውቅር ሕንፃ ሥራ ጥበብ ብዙ እርምጃዎች ወደፊት መራመድ እንደሚቻል ያሳየበት ምርጥ የጥበብ ሥራ ነው።

የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ጥናት እንዳደረገው፣ በኢትዮጵያ የውቅር ቤተ ክርስቲያናት ሥራ አሁንም አልቆመም። ባለፉት አሠርት ዓመታት ሰዎች እንደ አቅማቸው አሁንም መሮ እና ዶማ ይዘው ተራራ እየፈለፈሉ ቤተ ክርስቲያኖች በመሥራት የእምነታቸውን ጥንካሬ ለማሳየት ይጥራሉ። እነዚህ አዳዲስ ቤተ ክርስቲያናትም በቅርቡ እየተገኙ እንደሆነ ዩኒቨርሲቲው አሳውቋል።

ወደፊትስ ላሊበላን የሚወዳደር ውቅር ሕንፃ በአገራችን ተሠርቶ እናይ ይሆን?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊ አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ፎቶዎቹና መጣጥፉ በአንድምታ ይሁንታ የተገኙ ናቸው፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles