Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊድርቅ በእንስሳት ሀብት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ተጠቆመ

ድርቅ በእንስሳት ሀብት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ተጠቆመ

ቀን:

በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው ድርቅ እንደ ከዚህ ቀደሙ በእንስሳት ሀብት ላይ አደጋ እንዳያደርስ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

በተደጋጋሚ ጊዜ በድርቅ የሚጠቁ አርብቶ አደሮች የሚበዙባቸው አካባቢዎች በችግር ጊዜ የሚጠቀሙትን የከብት መኖ እንዲቆጥቡ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹አርብቶ አደሩ በባህላዊም መንገድ ቢሆን መኖ ቆጥቦ የሚያቆይበትን ዘዴ በስፋት እንዲጠቀም እያደረግን ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ የአገሪቱ የእንስሳት ሀብት በድርቅ እንዳይመናመን አስፈላጊው ሥልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለአርብቶ አደሮች የተመቻቸ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ ያላቸውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የበልግ ዝናብ ያላገኙ የተወሰኑ የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎች፣ እንዲሁም በተደጋጋሚ በድርቅ በሚመቱ የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰተው የድርቅ አደጋ ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች አስቸኳይ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በቅርቡ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያሳያል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 8.3 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የዕለት ደራሽ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ከእነዚህም ውስጥ 3.19 ሚሊዮን የሚሆኑት በየቦታው በተቀሰቀሱ ግጭቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆኑ፣ 5.5 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ በድርቅ የተጎዱ መሆናቸውን የድርጅቱ ሪፖርት ያሳያል፡፡ የዕርዳታ ድጋፍ ለማድረግም 1.3 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ መንግሥት 346 ሚሊዮን ዶላር እንደመደበ ከብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎችና ዕርዳታዎች በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል እየተሠራጩ መሆኑም ታውቋል፡፡

ዘንድሮ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የድርቅ አደጋ ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ከባድ አለመሆኑን፣ ‹‹ላሊና ሊከሰት ይችላል ተብሎ ትልቅ ሥጋት ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የሚታየው ሁኔታ እንደሚያሳየው ከባድ የድርቅ አደጋ አይኖርም፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅም ከአካባቢዎቹ አልፎ በአገር ደረጃ የሚያሠጋ አይሆንም፤›› ያሉት የግብርና ሚኒስትሩ ናቸው፡፡

ይህንን ያሉትም ከአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) ምክትል አስተዳዳሪ ቦኒ ግሊክ ጋር በጋራ ለመሥራት በጽሕፈት ቤታቸው የመግባቢያ ሰነድ በተፈራረሙበት ወቅት ነው፡፡ ፊርማው ላለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ሲሆን የቆየው ‹‹የፊድ ዘ ፊውቸር›› ፕሮግራም፣ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት እንዲቀጥል የተረጋገጠበት ነው፡፡

የአገሪቱን ኢኮኖሚ ዕድገት ሊያፋጥኑ የሚችሉ የልማት ሥራዎችን የመደገፍና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ሚና እንደሚኖረው የተነገረለት ፕሮግራሙ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል፣ በጣና ሐይቅ ዙሪያ፣ በደቡብ የአገሪቱ አካባቢ፣ በጅማ ዙሪያ፣ እንዲሁም አርብቶ አደሮች በሚኖሩባቸው ቆላማ የአገሪቱ ክፍሎች ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል፡፡

የግብርናውን ምርታማነት በማሳደግ፣ ለንግድ የተመቸ ከባቢን በመፍጠር፣ ለወጣቶች በተለይም ለሴቶች የሥራ ዕድልና ፈጠራ፣ የገበያ ትስስርን በመፍጠር ረገድ መንግሥት የሚያከናውናቸውን ሥራዎች እንደሚደግፍ ታውቋል፡፡ አሜሪካ ባለፉት አምስት ዓመታት አራት ቢሊዮን ዶላር ለልማትና ለሰብዓዊ ድጋፎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረጓን በወቅቱ ተገልጿል፡፡ በዚህኛው ‹ፊድ ዘ ፊውቸር› ፕሮግራም ምን ያህል በጀት እንደተያዘ ባይታወቅም፣ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ገንዘብ ኢንቨስት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

‹‹ስምምነቱ በተለይ በቆላማው የአገሪቱ አካባቢ በምግብ ዕጥረት ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል ነው፡፡ በጤና፣ በንግድ፣ በአጠቃላይ የሎጀስቲክ ሥርዓቱን ለማስተካከል፣ የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ድጋፍ ያደርጋል፤›› ያሉት አቶ ዑመር፣ የመግባቢያ ሰነዱ ፊርማ ለአገሪቱ የሚኖረውን ፋይዳ አስረድተዋል፡፡

በአሜሪካ መንግሥት ተግባራዊ የሚሆነው ‹ፊድ ዘ ፊውቸር› ፕሮግራም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ረሃብን ለማጥፋት፣ ሥርዓተ ምግብን ለማጠናከርና በአጠቃላይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገሮች የማይበገር ኢኮኖሚ ለመፍጠር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ይደግፋል ተብሏል፡፡ ፕሮግራሙ ተግባራዊ ከሚደረግባቸው 12 አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...