Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትካፍ እና ኢትዮጵያ በቻን ሻምፒዮና ዝግጅት መንታ መንገድ ላይ

ካፍ እና ኢትዮጵያ በቻን ሻምፒዮና ዝግጅት መንታ መንገድ ላይ

ቀን:

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት መርሐ ግብር በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይፋ ባደረገው መመሪያ አንዳንድ ክልሎች ያለ ፌዴሬሽኑ ይሁንታ ለሊጉ የሚሰጡትን የቀጥታ ሚዲያ ሽፋን እንዲያቆሙ ክልከላ ማድረጉ ሰሞነኛ መነጋገሪያ መሆኑ አልቀረም፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ የተላለፈው መመሪያ ክልከላ ሳይሆን፣ በተለይም ከተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የክልል ጨዋታዎችን ጨምሮ ለሊጉ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን እሰጣለሁ የሚል አካል ተጠያቂነትንና ኃላፊነት የመውሰድና ያለመውሰድ ጉዳይ ነው ይላል፡፡ እንደ ፌዴሬሽኑ ከሆነ ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ በአገሪቱ በተለያየ ደረጃ በመከናወን ላይ የሚገኙ ውድድሮች የክለብ ደጋፊነትን ሽፋን በማድረግ የሚታዩ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደሎች ቅርፅና ይዘታቸው እየተለዋወጠ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደር ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ አንፃራዊ ሰላም እየታየ ባለበት በአሁኑ ወቅት ለጨዋታዎች ቀጥታ ሥርጭት የሚሰጡ የሚዲያ ተቋማት በሥርጭቱ ምክንያት ችግሮች ቢከሰቱ ኃላፊነት ስላለባቸው፣ ይህንኑ ውድድሮችን በበላይነት ከሚያስተዳድረው ተቋም ጋር ውል እንዲያደርጉ ማድረግ ክልከላ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት ጭምር ፌዴሬሽኑ ያምናል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በ2020 የሚያዘጋጀውን በአፍሪካ አገሮች የውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን ብቻ በሚያሳትፈው የቻን ዋንጫ ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ ዕድል መስጠቱ አይዘነጋም፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ካፍ ዓምና በተለይም ከእግር ኳስ መሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ አገሪቱ በምን ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የሚያጠና ቡድን ልኮ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ከሳምንት በፊትም የዚያ ተመሳሳይ የቴክኒክ ቡድን በኢትዮጵያ ተገኝቶ ጨዋታዎቹ የሚደረጉባቸውን ሜዳዎችና ሌሎች ተያያዥ መሠረተ ልማቶችን ገምግሞ ተመልሷል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ምንም ያለው ነገር ባይኖርም፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በስፖርቱ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አማካይነት እንደተነገረው ከሆነ፣ ሻምፒዮናውን ለማስተናገድ ከ300,000 ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳለ፣ ከዚያም በላይ ሻምፒዮናው በሚከናወንበት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረግ ምርጫ በመኖሩና በሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች ኢትዮጵያ ዝግጅቱን ለማስተናገድ እንደምትቸገር መገለጹ ተሰምቷል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራን ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን ከሚሰጡ ሚዲያዎች መካከል የአማራና የትግራይ ክልል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በከተሞቻቸው የሚደረጉ ጨዋታዎችን ማስተላለፍ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ይሁንና ከሰሞኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክልሎቹ እንዳያስተላልፉ በመመሪያ የከለከላቸው መሆኑ ተሰምቷል፣ ምክንያቱ ምንድነው?

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አቶ ኢሳያስ፡- ክልከላ የሚባለው ነገር ውሸት ነው፣ የተደረገው ሕግ ይቀመጥለት ነው፣ ይህ ደግሞ ጥቅሙም ሆነ ጉዳቱ ለሁላችንም ነው፡፡ እንደሚታወቀው እስካሁን በነበረው ግለሰብ በእጅ ሞባይል ሳይቀር ጨዋታዎችን በመቅረፅ በሬዲዮ የሚያስተላልፍበት ሁኔታ መኖሩ የሚካድ አይደለም፡፡ በሥርጭቱ በርካታ አሉታዊም አዎንታዊም ነገሮች ሲተላለፉ ቆይቷል፣ ቀጥሏልም፡፡ የቀጥታ ሥርጭቶች ደግሞ በባህሪያቸው ጥንቃቄና ኃላፊነትን መውሰድ የሚፈልጉ ነገሮች መሆናቸው ይታመናል፡፡ በዚህ ረገድ አሉታዊ ጎናቸው እያመዘነ ብዙ ጥፋቶች እንዲከሰቱ ምክንያት መሆናቸው ጭምር ተረጋግጧል፡፡ በነበረው ሁኔታ ለችግሩ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት አልነበረም፣ አሁን ሊደረግ የታሰበውም ተጠያቂነት እንዲኖር ካልሆነ በቀር ክልከላ የሚባለው ነገር ውሸት ነው፡፡ በነበረው ሁኔታ በተለይም በአማራና በትግራይ ክልሎች ጨዋታዎች ሲደረጉ ጥቂት ነገሮች ሲከሰቱ እኛ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ኅብረተሰቡን ወደ አላስፈላጊ ነገር ውስጥ እንዲገባ እያጋነኑ በማቅረብ ችግሮች ሲፈጠሩ ቆይቷል፡፡ ቡድኖቹ በተራቸው ወደ ሌላው ሜዳ ሲሄዱ የበቀል አዝማሚያ እንዲኖር ቀጥታ ሥርጭቶች የነበራቸው ሚና ቀላል አልነበረም፣ በሰውና በንብረት ላይ ከፍ ያለ ዋጋ ሲያስከፍል ቆይቷል፡፡ ስለሆነም ሚዲያው ጨዋታውን ለማስተላለፍ ከክለቡ ጋር የተፈራረመውን ውል ከፌዴሬሽኑም ጋር መዋዋል ይኖርበታል ነው፡፡ በሕግ ፊት ሚዲያው፣ ክለቦችና ፌዴሬሽኑ መውሰድ የሚኖርባቸው ነገሮች ስላሉ እነዚያን ዕውን ማድረግ ይቻል ዘንድ ነው፣ መመሪያው ያስፈለገው፡፡ ፌዴሬሽኑም ያለው ፈርሙና አስተላልፉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፌዴሬሽኑ እንደነዚህ የመሰሉ መመሪያዎች ወደ ሚመለከታቸው አካላት ከመወርወራቸው አስቀድሞ የግንዛቤ ሥራዎችን ማከናወን አልነበረበትም ብለው ያምናሉ?

አቶ ኢሳያስ፡- ፌዴሬሽኑ በዚህ ላይ ጠንካራ መመሪያ ለማውጣት በጥናት ላይ ነው፣ እስከዚያው ግን ኃላፊነት የተሞላበት እንዲሆን ኑና ፈርሙ ነው የተባለው፡፡ እንደሚነገረው ክልከላ ቢሆን የአማራና የትግራይ ክልሎች ሚዲያዎች ማስተላለፍ ከጀመሩ ቆይተዋል፣ ለምን ዝም ተባሉ? የውድድሮቹ ባለቤት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ነው፣ የመከልከል ፍላጎት ቢኖረው ከጅምሩ መከልከል ይችል ነበር፡፡ የሚገርመው ክልከላ የሚለው ተጋኖ ወጣ እንጅ ፌዴሬሽኑ ያለው ለጊዜው በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ሥርጭቶች መጠንና ዓይነት ጭምር ተለይቶ ነው መመሪያው የተላለፈው፡፡ ጨዋታዎችን ቀጥታ ለማስተላለፍ ጥያቄ ያቀረበው የፋሲል እግር ኳስ ክለብ ነው፣ ክለቡ ያንን ሲያደርግ በቅድመ ሁኔታዎች ላይ ከፌዴሬሽኑ ጋር ተስማምቶና ፈርሞ ነው፡፡ ሌሎችስ ግዴታቸውን ከመወጣት ይልቅ ወደ አሉባልታና ክርክር ገቡ፣ ሕጋዊ ማዕቀፍን ተከትሎ መሥራት ችግሩ ምንድነው? በግሌ ሰዎች የፈለኩትን ተናግሬ ልግባ ካልሆነ መብትና ግዴታን አውቆ መንቀሳቀስ ችግር ያለው አይመስለኝም፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን መመሪያ ያወጣው ክልሎቹ ለጨዋታዎቹ በሰጡት ቀጥታ ሥርጭት ገንዘብ አገኙ ከሚል መነሻ እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል፣ በሕግ አግባብ የመጠቀም መብት ያለው መሆኑ እንደተጠበቀ ግን ደግሞ ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ የሚለው ነው በዋናነት መወሰድ ያለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሪሚየር ሊጉ ሲጀምር ዋልታና ሌሎችም የሚዲያ ተቋማት ጨዋታዎችን ለማስተላለፍ ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት እንዳላገኙ፣ በሌላ በኩል ግን በትግራይና በአማራ ቀጥታ ሥርጭት ሲያደርጉ ወራትን ማስቆጠራቸው ከምን የመነጨ ነው ሲሉ የሚጠይቁ አሉ?

አቶ ኢሳያስ፡- የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ኃላፊነት ከተቀበልኩበት ጊዜ ጀምሮ በዚህ የሕግ አግባብ ከፌዴሬሽኑ ጋር ሕጋዊ ውል ፈጽሞ የተከለከለ ካለ እጠየቃለሁ፣ በተጨባጭ ያለው ነገር እንደለመድኩት መቀጠል አለብኝ፣ የለብህም ነው፡፡ እኔ እስከ ማውቀው ድረስ በተቋሙ ሕግና ሥርዓት አክብሮ የተከለከለ አካል የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከመመሪያ በፊት ውይይት መቅደም እንዳለበት ቀደም ሲል ለቀረበልዎ ጥያቄ በቂ ማብራሪያ አልሰጡም፣ መድረክ ፈጥሮ መነጋገር ለምን አልተቻለም?

አቶ ኢሳያስ፡- ትክክል ነው ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ለተቋሙ ሲባል ሁሉን ነገር ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መነጋገር የማያስፈልግበት አሠራር ይኖራል፡፡ እንደተባለው መወያየት በጣም ጥሩ ነው፣ ግን ደግሞ ሕግና ሥርዓትን አክብር ብሎ ማለት ክፋቱ ምንድነው? እንዲያም ሆኖ በስፖንሰር የምታስተላልፍ ከሆነ ይህን ያህል፣ በራስ ከሆነ ደግሞ ይህን ያህል፣ ኃላፊነትህን በተመለከተ ደግሞ እነዚህ እነዚህ ነገሮች ናቸው ብሎ መነጋገር የሠለጠነ አካሄድ እንጂ በግሌ ክፋቱ አይታየኝም፡፡ በነገራችን አንዳንዶች ሊጉን የሚሸጥ አድርገው የሚወስዱ አሉ፣ እንዲታወቅ የምፈልገው ሊግ የመሸጥና ያለመሸጥ የክለቦች ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሊጉ ከተሠራበት መሸጥ እንደሚችል በአማራና በትግራይ ክለቦች ታይቷል፣ ከዚህ በመነሳት ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ምን ያሰበው ነገር አለ?

አቶ ኢሳያስ፡- እውነቱን ለመናገር አመራሩ ኃላፊነቱም ከተረከበ ጀምሮ ሲሠራ የነበረው እሳት የማጥፋት ሥራ ነው፣ ሁሉም እንደሚያውቀው በፌዴሬሽኑ ሲንከባለሉ የመጡ በርካታ ችግሮችና ክፍተቶች አሉ፣ ከምርጫ ጀምሮ የነበረው ሽኩቻና እሰጣ ገባ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በስፖርት ማዘውተሪያዎች የነበሩ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች በአጠቃላይ እንዲህና እንዲያ በማለት ከኃላፊነት መሸሽ እንዳይመስል እንጂ ስለዚህ የልማት ጉዳይ የምናስብበት ወቅት አልነበረም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ክለቦች ውድድራቸውን እንዲያስተዳድሩ ኮሚቴ ከተዋቀረ በኋላ ዕድሉ ሲሰጣቸው ከጥቂት ክለቦች በስተቀር ብዙዎቹ አፈገፈጉ፣ እንዲያውም ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን ራሱ ሠርቶና አደራጅቶ እንዲሰጣቸው የጠየቁ አሉ፡፡ በመሆኑም የልማት ጉዳይ የእኛም ጉዳይ ነው፣ እንደተባለው ለጊዜው ብንቸገርም በሒደት ግን የምሄድበት መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ጎረቤቶቻችን ኡጋንዳና ታንዛኒያ ሊጎቻቸው የሚተላለፉት መብት ባለው ሚዲያ ነው፡፡ እኛም ወደ እዚህ አሠራር መሄድ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ የሚገርመው እያንዳንዳቸው የሊግ ካምፓኒያቸውን ያቋቋሙት ከፍለው ነው፣ ባገራችን የሠፈር ዕድር እንኳን ለመግባት ከፍለን አይደለም እንዴ? በእኛ ክለቦች እንደ አለመታደል ሆኖ አንዱ ሌላውን ይጠራጠራል፣ ምን ዓይነት በሽታ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ክለቦቻችን ለአንድ የውድድር ዓመት 40 እና 50 ሚሊዮን ብር እያወጡ ባለበት የሊጉን ደረጃና አሠራር አሻሽሎ ተጠቃሚ መሆን ካልቻሉ የህልውናቸው ጉዳይ በራሱ አጠያያቂ ነው፡፡ ሰፊ የደጋፊ ቁጥር ያላቸው ክለቦች አሉን፣ በክልሎችም ቢሆን ቀላል የማይባል የደጋፊ ቁጥር እየመጣ ነው፣ ይህን ወደ ገንዘብ ለመለወጥ ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ክለቦች አልሠሩም ብሎ ዝም ብሎ አልተቀመጠም፣ ሊጉን ገቢ ተኮር ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ለምን ፈጥናችሁ አልገባችሁም? ማነቆው በመብዛቱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢትዮጵያ በ2020  እንድታሰናዳ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የተሰጣትን የአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) እንደማትቀበል አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም በላይ ካፍ ይህን የሚያጠና የቴክኒክ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ መጥቶ በተለይ ሻምፒዮናውን ማድረግ የሚያስችል መሠረተ ልማት እንዳልተሟላ ምክረ ሐሳብ ለካፍ ማቅረቡ ጭምር እየተነገረ ይገኛል፡፡ ምን አስተያየት አለዎት?

አቶ ኢሳያስ፡- ችግሩ ግልጽ ነው፤ ይህ ሲባል ግን የመስተንግዶ አይደለም፡፡ ነገር ግን የቻንን ፕሮግራም ለማዘጋጀት ቀድሞውኑ ያለጥናት የተሄደበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ እንደተባለው የካፍ ቴክኒካል ቡድን ከዓመት በፊትና ከወር በፊት ሁለት ጊዜ መጥቶ ገምግሞናል፤ ቡድኖቹ መጥተው ሲገመግሙ ምንም የተለወጠ ነገር እንደሌለ ነው በምክረ ሐሳብ ደረጃ ያረጋገጡልን፤ ይህንኑ ለካፍ ሪፖርት እንደሚያደርጉ ጭምር ነው የነገሩን፡፡ የቴክኒክ ቡድኑ ከታንዛኒያና ከኡጋንዳ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡የስታድየሞቹ መሠረተ ልማት አለመሟላት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ግን ደግሞ በአገሪቱ ካለው ወቅታዊ ሁኔታና የበጀት ጉዳይ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታው መግለጫም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ይመስላል?

አቶ ኢሳያስ፡- እውነት ነው እንደነዚህ የመሰሉ ዝግጅቶች የመንግሥትን ቁርጠኝነትና በጀት የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት በትንሹ ከ300 ሺሕ ዶላር በላይ ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብቻ ቀርቶ የክልል መስተዳድሮችን ተሳትፎ ጭምር የሚጠይቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነትዎ ውሳኔው ለኢትዮጵያ የሚያመጣውን ፋይዳ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ኢሳያስ፡- ለዚህ ጥያቄ እንደ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ሳይሆን የግል አመለካከቴ፣ የመስተንግዶው ዓርማው ሲወሰድ በመንግሥት ደረጃ ነው፡፡ ይሁንና እንደነዚህ ዓይነት መስተንግዶዎች ሲወሰዱ የማያሳፍሩ መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ፣ ክልሎቻችንን በበጀት ራሳቸውን አደራጅተውና ስታዲየሞቻቸውን ብቁ አድርገው ሲገኙ ቢሆን ነው የሚሻለው፡፡ ባለው ሁኔታ አገሪቱ ወደ ቅጣት እንዳትሄድ የካፍ ሰዎችን በማነጋገር የ2020 ዝግጅት በ2022 ለሚያዘጋጀው አገር እንዲሰጥ ቢደረግና ኢትዮጵያ የ2022ን እንድታዘጋጅ ቢደረግ ነው የሚበጀው፡፡ ይህን የምልበት ዋናው ምክንያት ምንም እንኳ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሁንታ ቢሰጡትም፣ የአሁኑ እስከ አሁን ምንም ያሉት ነገር የለም፡፡ ሌላው ኢትዮጵያ ይህን ዝግጅት ለማስተናገድ ካፍ ሰነዱን ቢልክም፣ ኢትዮጵያ ግን ተቀብላ አልፈረመችም፡፡ ካፍ ኢትዮጵያ ላይ በዚህ ምክንያት ቅጣት እንዳያስተላልፍ መሥራት የሁላችንም ድርሻ ሊሆን ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ የሚገርመው የካፍ ሰዎች የግል አስተያየታቸውን ሲሰጡን በክልል የሚገኙ ስታዲየሞቻችን 50 እና 60 ሺሕ የሚይዙ ተደርገው ከሚገነቡ መለስተኛ ተደርገው ቢገነቡ አሁን የገጠመን ዓይነት ችግር እንደማይኖር ጭምር ነው የነገሩን፡፡                                                         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...