Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርበኃይሌ ጋርመንት አካባቢ ነዋሪዎችን ያስጨነቀው የመብራት ዕጦት

በኃይሌ ጋርመንት አካባቢ ነዋሪዎችን ያስጨነቀው የመብራት ዕጦት

ቀን:

አዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ‹‹ኃይሌ ጋርመንት›› እየተባለ በሚጠራውና ‹‹ፔፕሲ መንደር›› በሚባለው አካባቢ የሚገኙ በግምት 300 ከሚሆኑ ቤቶች መካከል የተወሰኑት የኤሌክትሪክ ኃይል ከተቋረጠባቸው አራት ቀናት እንዳለፋቸው ከአካባቢው ነዋሪዎች መረዳት ተችሏል፡፡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ አባወራ ይህንን ጉዳይ ለሪፖርተር ጋዜጣ ላቀረበው ሰው ስለ ችግሩ እንደሚከተለው አስረድተውታል፡፡

ከ15 ዓመታት ወዲህ በተለይ በበዓል ቀናት መብራት ከምናገኝበት የማናገኝበት ቀን ይበዛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለይቶልን ኑሯችን ዳፍንት ወርሶታል፡፡ ለሻማና ለጋዝ ጭስ ተዳርገን ፍዳችንን እያየን ነው፡፡ አንዳንዴ በተከታታይ ከሣምንትና ከ15 ቀናት በላይ አጥፍተው ያቁዩብንና ለተወሰነ ጊዜ ብልጭ አድርገው እንደገና ያጠፉታል፡፡ ሄደን ስንጠይቅ ‹ይመጣላችኋል፤ እዛው ጠብቁ› ይሉናል፡፡ የምናደርገው ግራ ገብቶን፣ ጨንቆናል፡፡

ችግሩ ሲባዛብን ሰሞኑን ተሰባስበን ወደ ቢሯቸው ሄድን፡፡ ስንሄድ ‹‹ቢሮው ወደ ለቡ ተዛውሯል›› ተባልን፡፡ እዚያም ሄደን ኃላፊውን ስንጠየቅ ‹‹ችግሩ ፊውዝ ነው››  አለን፡፡ ‹‹ታዲያ ምን ተሻለን?›› ብለን ስንጠይቀው ‹‹በውጭ ምንዛሪ ዕጦት ምክንያት ለጊዜው ፊውዝ የለም፤ ገንዘብ እንደተገኘ ይገዛል፡፡ እስከዚያው ተመዝገቡና ተራችሁን ጠብቁ፡፡ ከሰባት እስከ ስምንት ወር ሊፈጅ ይችላል፡፡ ለማንኛውም በትዕግስት ጠብቁ ወይም እናንተ ራሳችሁ ግዙና እንግጠምላችሁ›› አለን፡፡ ‹‹ለስምንት ወር ካለመብራት ልንቆይ?›› ብለን ስንጠይቀው ኃላፊው ምንም ሳይመስለው በማሾፍ መልክ ‹‹ሌላ ምን ምርጫ አላችሁ?›› ብሎ ቀለደብን፡፡ ከፊቱ የሚነበበው ‹‹ገንዘብ አምጡና አሁኑኑ እንግጠምላችሁ›› የሚል ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ያንዱን ለመጠገን ሲሄዱ የሌላውን ሆን ብለው በማበላሸት በሙስና የተጨመላለቀ አሠራር ውስጥ እንደተዘፈቁ በስፋት ይታወቃል፡፡ እንዲያውም አንዱ የመብራት ኃይል ሠራተኛ አንድ ጊዜ የተበላሸ መብራት ጠግኖ ሊመለስ ሲል ሌላውን አበላሽቶ ከምሰሶው ሲወርድ ወጣቶች ደርሰው ሊደበድቡት ሲሉ ‹‹እባካችሁ አትንኩኝ፤ አሁኑኑ አስተካክዬ እወርዳለሁ›› በማለቱ ምረውታል፡፡

በሌላ በኩል ግን የኛ ጎረቤት የሆኑ 200 የማይሞሉ ነዋሪዎችን የሚያገለግሉ ስምንት ወፍጮ ቤቶች መብራት መቼም ቢሆን አይቋረጥባቸውም፡፡ እነዚህ ወፍጮ ቤቶች ወፍጮውን ሲተክሉ ጀምሮ ብዙ ገንዘብ በጉቦ መልክ ለመብራት ኃይል የሥራ ኃላፊዎች እንደሚሰጡ እንሰማለን፡፡ የኛን የሚያጠፉትም ለእነሱ ኃይል ለማብዛት እንደሆነ  ይነገራል፡፡

ከነዋሪዎቹ መረዳት እንደተቻለው የአካባቢው ወጣቶች በእነዚህ የመብራት ኃይል የሥራ ኃላፊዎች በሙስና የተጨመላለቀ ብልሹ አሠራር በመበሳጨት በሰዎቹ ላይ ጉዳት ሊያደርሱባቸው እየዛቱ መሆኑንና የአካባቢው ወላጆች ግን ችግሩን ለመቅረፍ በሕግና በሕግ ብቻ ለመፍታት እንደሚንቀሳቀሱ ለወጣቶቹ በማስረዳት እንዲታገሱ በመምከር ላይ መሆናቸውን የመረጃ ምንጫችን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ችግሩ ሳይቀረፍ ቀርቶ ወጣቶቹም ሆኑ ማንም ተበደልኩ የሚል አካል በእነዚህ ተለይተው በሚታወቁ በሙስና የሚታሙ የሥራ ክፍሉ ኃላፊና ምድብ ሠራተኞች ላይ አንዳች ነገር ቢደርስ ተጠያቂዎቹ ራሳቸው መሆናቸውን ሊያውቁ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ ይህን ማለት ያስቻለን ችግር ፈጣሪዎቹ ሠራተኞች በሕዝብ ይታወቁ ዘንድ ፎቶግራፋቸው ተባዝቶ በመንደሩ ውስጥ እየተበተነ ስለሚገኝ የዚህ ነገር መቋጫ ደግሞ ከግምት ባለፈ ምን ሊሆን እንሚችል በግልጽ መረዳት ስለማይቻል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር መናገር የሚቻለው ሌላው ማሰረጃ ወጣቶቹ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እየተመካከሩ በነበረበት ወቅት ጉዳዩን በቅርብ የተከታተሉ እናቶች ‹‹ልጆቻችን ችግር ከሚያስከትሉና ከሚያስወቅሱን፣ እነሱም ወንጀል ውስጥ ከሚገቡብን እኛው ሄደን የመብራት ኃይል ሠራተኞችን ብንለምናቸው መፍትሔ ይገኝ ይሆናል›› ከሚል ተስፋ ሄደው መማጸናቸውና ልፋትና ድካማቸው ዋጋ አጥቶ መቅረቱ ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ ከባድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ጉዳዩ የሚመለከተው የኢትየጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የበላይ አካል ይህን በዜጎች ላይ የሚፈጸም ደባና ተንኮል ተከታትሎ ለችግሩ አወንታዊ መፍትሔ እንዲሰጥ የዚህ መረጃ ጠቋሚ ማሳሰብ ይፈልጋል፡፡ ብሶት ሲጠራቀም የሚፈጠረው ነገር ከግምት በላይ በመሆኑ የሥልጣኔ ማዕከል በሆነች የአገር ዋና ከተማ ውስጥ ያለ መብራት መኖር የሚታሰብ አይደለምና ችግሩ ለነገ የሚተው አለመሆኑን ሁሉም ወገን ተገንዝቦ፣ የተፈጠረው ሰው ሠራሽ ችግር ዕልባት እንዲያገኝ መረባረብ ይገባዋል፡፡

(ምሕረት ዘገዬ፤ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...