Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

በቀደም ጠዋት ከቤቴ ወጥቼ ወደ ጉዳዬ ሳመራ ሁለት እህትማማቾች መንገድ ላይ ይጨቃጨቃሉ፡፡ መንታ መሆናቸውን ወዲያው ነው የተረዳሁት፡፡ ሁለቱም ለመለየት የሚያስቸግር ገጽታና አለባበስ ሲኖራቸው፣ ለዓይን የሚያሳሳ የልጅነት ውበት አላቸው፡፡ ምን ይሆን የሚያጨቃጭቃቸው በማለት ጠጋ ስላቸው እንደ ማፈር እያሉ አቀረቀሩ፡፡ እኔም በአባትነት ቀረብ ብዬ ስጠይቃቸው ነገሩ ግልጽ ሆነልኝ፡፡ አንደኛዋ ፌስቡክ ላይ ጊዜዋን ስለምታባክን ሌላኛዋ ተይ እያለቻት ነው፡፡ እኔም አስፈላጊውን ምክር ሰጥቼ እንዲስማሙ አድርጌ ተለያየን፡፡ 

መገናኛ ደርሼ ወደ ሳሪስ አቦ የሚያመራውን መኪና ስፈልግ የአንድ ቅጥቅጥ አውቶቡስ ረዳት እየደጋገመ የጉዞውን አቅጣጫ እየተናገረ ሲጣራ ራመድ ብዬ ተሳፈርኩ፡፡ ከእኔ ቀጥሎ አንድ ጎልማሳና ለግላጋ ወጣት እየተጨቃጨቁ ገብተው ተሳፈሩ፡፡ እኔ ከተቀመጥኩበት ወንበር ከኋላ አረፍ እንዳሉ ከደጅ ይዘውት የመጡት ጭቅጭቅ ቀጥሏል፡፡ አንዳንዴ ተመሳሳይ ነገር ይገጥም የለ? የመንታዎቹ ዓይነት ነገር እዚህ እንደገና ሲገጥመኝ እየገረመኝ ጆሮዬን አቁሜ ማዳመጥ ጀመርኩ፡፡

‹‹ስልክህን ከኪስህ አውጥተህ ክፈተውና የጻፍከውን አሳየኝ፤›› የሚለው ጎልማሳው ሲሆን፣ ለግላጋው ወጣት ደግሞ፣ ‹‹አባዬ የምልህን ለምን አትሰማኝም? የጻፍኩት ለጓደኛዬ ነው፡፡ ጽሑፉም ጥናትን በተመለከተ ነው፤›› አለው፡፡ አሁን ገባኝ፡፡ አባትና ልጅ ናቸው፡፡ አባትየው ግንባሩ ላይ ያለው ደም ሥር ተገታትሯል፡፡ ዓይኖቹ ተጎልጉለው ወጥተው ያስፈራሉ፡፡ ልጅየው ደግሞ የአባቱን ሁኔታ በጨረፍታ እያየ መሬት መሬት ያያል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አባትየው የልጁ ትከሻ ላይ እጁን እያሳረፈ፣ ‹‹አየህ ልጄ እኔ ለአንተ ብዬ ነው፡፡ በፌስቡክ ላይ እየጻፍከው ያለውንና በሌሎች ሰዎች ላይ የምትሰጣቸው አስተያየቶችን ዓይቻለሁ፡፡ ጠዋት በጨረፍታ ያየሁት ግን አደገኛ ነው፡፡ እኔ አንተን ያለ እናት ሳሳድግህ በእንዲህ ዓይነት ባህሪ አይደለም፡፡ በጣም ፈሩን የሳተ ሁኔታ ላይ ነው ያለኸው፡፡ እየገባህበት ያለው ሁኔታ በጣም አስፈሪ ስለሆነ ለመተማመን ስልክህን ስጠኝና ልየው፡፡ ከዚያም እንወያይበት. . . ›› እያለው በለሆሳስ ሲነግረው ሰማሁ፡፡ ልጁ ግን በእንቢተኝነቱ ፀና፡፡

አውቶቡሱ ሞልቶ ጉዞ ወደ ሳሪስ ተጀመረ፡፡ ሾፌሩ የተለመደውን የማለዳ የስፖርት ትንተና የሚያውጀውን ጣቢያ በከፍተኛ ድምፅ ከፍቶ መደማመጥ ጠፋ፡፡ የአባትና የልጅ ጭቅጭቅ ግን ቀጥሏል፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን አጠገቤ ማን እንደተቀመጠ እንኳ ማየት አልቻልኩም ነበር፡፡ ዞር ብዬ ሳይ ግን አንዲት ውብ ወጣት ተሰይማለች፡፡ አካባቢዬን ረስቼ የአባትና የልጅን ሙግት ለመስማት ብፈልግም፣ ድምፃቸው በጣም ዝግ በማለቱ ይሁን፣ ወይም የእኔ የመስማት አቅም በማነሱ የሚባባሉት አይሰማኝም፡፡ ሁሉንም ትቼ ዓይኖቼን ወደ ውጭ በመስደድ በራሴ ሐሳብ ውስጥ ተዘፈቅኩ፡፡ የተለያዩ ነገሮችን እያነሳሁ ስጥል የቀድሞው ኢምፔሪያል ሆቴል አደባባይ ጋ ደርሰናል፡፡

‹‹ወይ ጉድ!›› ትላለች አጠገቤ የተቀመጠችው ቆንጆ፡፡ ዞር ብዬ ሳያት ሳቅ አለች፡፡ ‹‹በሰላም ነው?›› ስላት፣ ‹‹አይሰሙም እንዴ?›› አለችኝ፡፡ ግራ ገብቶኝ፣ ‹‹ምኑን?›› ማለት፡፡ ‹‹ከኋላ የሚባለውን ይስሙ በጣም ይገርማል፤›› ስትለኝ ገባኝ፡፡ የእኔ የደከመ ጆሮ የማይሰማውን ልጅቷ ጥርት አድርጋ እየሰማች ነው ለካ? ‹‹ምን እያሉ ነው?›› የሚል ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ጭንቅላቷን እየወዘወዘች፣ ‹‹አባትየው ያሳዝናል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ገና የጀመረ ልጁ አጉል ነገር ውስጥ ገብቶ እያንገበገበው ነው. . .›› እያለች የምሬት መልክ አሳየችኝ፡፡ ጉዳዩን የማወቅ ፍላጎቴ ናረ፡፡

‹‹ምንድነው የሚባባሉት?›› ስላት፣ ‹‹ልጅየው በተለያዩ የአገር ጉዳዮች ላይ የሚሰጣቸው አስተያየቶችና ስድቦች አባትየውን ናላውን አዙሮታል፡፡ በዚህ ላይ እሱ እንደሚለው ፖለቲካ ሳይገባው የሚሰነዝራቸው በኃይለ ቃልና በብልግና የታጀቡ አስተያየቶች እያሳበዱት ነው. . .›› እያለች ስትነግረኝ፣ ለአፍታ ያህል ዞር ብዬ ሳይ አባት የልጁን ሞባይል ስልክ ይዞ በሚያየው ጉድ እየተበሳጨ ነው፡፡ መበሳጨት ብቻ ሳይሆን እንባው ከዓይኖቹ ወደ ጉንጮቹ እየፈሰሰ ነው፡፡ ልጁ ደግሞ አንገቱን ደፍቶ ፀጥ ብሏል፡፡ የአባትና የልጅ ሁኔታ ሲታይ በዚህ ዘመን ወላጅ መሆን እንዴት ያለ ከባድ ነገር መሆኑን ይናገራል፡፡

እኔ ቦሌ ብራስ ሆስፒታል አጠገብ ወርጄ ወደ ጉዳዬ ሳመራ የአንድ እምነት ተከታዮች ሦስት ሆነው መደርደሪያ ቢጤ አቁመው፣ ለአላፊ አግዳሚው የሃይማኖት በራሪ ጽሑፎችንና መጻሕፍትን ይሰጣሉ፡፡ አንዱ ወደ ሰዎቹ እያመለከተ፣ ‹‹እነዚህን ነው እኮ በስሜ ሊያሳስቱ ይመጣሉ ያለው. . .›› እያለ ሲሳለቅ፣ አንዱ ደግሞ፣ ‹‹የእንዳንተ ዓይነቱን ትዕቢተኛ ልብ ለማብረድ የእነሱ መኖር ጥሩ ነው. . .›› ሲለው ድንገተኛ ፀብ ተፈጠረ፡፡ የመጀመሪያው እንዴት ትናገረኛለህ በሚል ስሜት አንዳች በሚያህል ሰፌድ እጁ ድንገት ሲያሳርፍበት ያኛው አስፋልቱ ላይ ዧ ብሎ ወደቀ፡፡ ሰዎች መሀል ገብተው ጠቡን ሲያበርዱና የወደቀውን ሲያነሱ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ንክ ቢጤ፣ ‹‹አባትና ልጅ የማይስማሙበት ዘመን፣ ወገን ከወገኑ የማይተዛዘንበት ጊዜ፣ የጠገበው ለራበው የማይሳሳበት ወቅት፣ መደማመጥ ጠፍቶ ሐሜትና አሉባልታ የገነኑበት አሰልቺ ትውልድ፣ ከትናንትና ይልቅ ዛሬን ማሳመር ሲገባቸው የበለጠ ለማበላሸት የሚክለፈለፉ ሰይጣኖች የበዙበት ጊዜ፣ በአጠቃላይ ሁኔታችን ሲታይ ለራሱ ለፈጣሪ ጭምር ግራ የሚያጋባ. . .›› እያለ በከፍተኛ ድምፅ ሲናገር ከእኛ እሱ እንደሚሻል ታሰበኝ፡፡

(አምሳሉ ነጋሽ፣ ከቀበና)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...