Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየጥላቻ ንግግርን በመከልከል ሌላ ጥላቻን መሸመት

የጥላቻ ንግግርን በመከልከል ሌላ ጥላቻን መሸመት

ቀን:

ውብሸት ሙላት

ይህ ጽሑፍ የጥላቻ ንግግርንና የሐሰት መረጃ ማሠራጨትን ለመከላከል በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ የሚመለከት ነው፡፡  የዚህ ጽሑፍ መንፈስም የጥላቻ ንግግርን የሚከለክል ሕግ መውጣቱን በመደገፍ ነገር ግን ረቂቅ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ የማይጻረር፣ ኢትዮጵያ ተቀብላ ካፀደቀቻቸውና ዓለም አቀፍ ልማዳዊ ሕግ ደረጃ ከደረሱት የሰብዓዊ መብት ሰነዶች፣ እንዲሁም እንዲያሳካ የሚታሰበውን ግብ ስቶ በተቃራኒው የዜጎችን መብት ለማፈንና ለመጨፍለቅ በሚመች መልኩ የመንግሥት የአፈና መሣሪያ እንዳይሆን መፈተሽ ነው፡፡ በመሆኑም ከመግቢያው በመጀመር የተወሰኑ ጎላ ጎላ ያሉ ነጥቦችን በመምረጥ ቀረበ ነው፡፡

መግቢያውና ዓላማዎቹ

መግቢያው አጭር የሚባል ነው፡፡ የጥላቻንም ይሁን ሐሰተኛ ንግግሮችን ለመከልከል ያስፈለገበትን ምክንያቶች አሳማኝ በሆኑ መልኩ ይዟል የሚያሰኝ አይደለም፡፡ የመጀመርያውን የመግቢያ ሐረግ ብንመለከት ‹‹ሰብዓዊ ክብርን የሚገረስሱና ሆን ተብሎ የሚሠራጩ ሐሰተኛ ንግግሮችን በሕግ መከልከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤›› የሚል ነው፡፡  ይህ ሐረግ ስለ ሐሰተኛ ንግግር ነው፣ የጥላቻ ንግግርን አልያዘም፡፡ ከዚህ የምንረዳው የክልከላው መለኪያ የሆኑት ሐሰተኛ ንግግር መሆኑ፣ ሆን ተብሎ መሠራጨቱ፣ እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚጥስ መሆኑ ነው፡፡

 ከመለኪያነትም አልፎ የክልክል ሕግ ለማውጣት ምክንያት ሆነዋል ማለት ይቻላል፡፡ ሆን ተብሎ የሚነገሩ ሐሰተኛ ንግግሮች ሰብዓዊ ክብርን እንዳይገረስሱ ጥበቃ ለማድረግ ሲባል ነው ከዚህ ሐረግ እንደምንረዳው ሕግ ማውጣት ያስፈለገው፡፡  ሐሰተኛ ንግግር በመሆኑ ብቻ ለመከልከል ሳይሆን ሆን ተብሎ ሰብዓዊ ክብርን የሚገረስሰውን ነው መከልከል የተፈለገው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው የጻፈው ወይም የተናገረው ነገር ሐሰት በመሆኑ ብቻ መከልከል አልተፈለገም፡፡

ሁለተኛው የመግቢያ ሐረግ ደግሞ ‹‹የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት የሚያስከትሉት ግጭትና ጉዳት ለእኩልነት፣ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለሕዝቦች አንድነት ትልቅ ጠንቅ በመሆኑ፤›› የሚል ነው፡፡ ይህ አገላለጽ በራሱ ችግር የለበትም፡፡ ይሁን እንጂ፣ ንግግር ቢደረግ የሐሰት መረጃ ቢሠራጭ ግጭትና ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል በሚል ምክንያት ንግግርን ማቀብ ይቻላል ወይ? ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 (6) ይስማማል ወይ? ይኼ ደግሞ ወደ ቀጣዩ ሦስተኛው መግቢያዊ ሐረግን እንድንመለከት ያንደረድረናል፡፡

ሦስተኛው የመግቢያው ሐረግ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹መሠረታዊ መብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች በሕግ የተደነገጉ፣ በዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ተቀባይነት ያለውን ዓላማ ለማስፈጸም የሚወጡና ተመጣጣኝ መሆን እንዳለባቸው በመገንዘብ፤›› ነው ይላል፡፡

ይህ አገላለጽ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ የሚኖሩ ገደቦችን ብቻ ሳይሆን፣ በጥቅሉ መሠረታዊ የሚባሉ መብቶች ላይ እንዴት ገደብ ሊጣል እንደሚችል መርሖቹን ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረታዊ (ሰብዓዊ) መብቶች ላይ ሊኖሩ የሚችሉ ገደቦችን አንድ ወጥ መርህ በማስቀመጥ መገደብን አልመረጠም፡፡

ይልቁንም፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተዘረዘሩ መብቶችን ለእያንዳንዳቸው በምን ሁኔታ ሊገደቡ እንደሚችሉ ለይቶ ማስቀመጥን ተከትሏል፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 26 ላይ የተገለጸው የግል ሕይወት መከበርና መጠበቅ መብት ገደብ ሊደረግ የሚችለው ‹‹አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩና ብሔራዊ ደኅንነትን፣ የሕዝብን ሰላም፣ ወንጀልን በመከላከል፣ ጤናንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ ለመጠበቅ ወይም የሌሎችን መብትና ነፃነት የማስከበር ዓላማዎች ላይ የተመሠረቱ ዝርዝር ሕጎች መሠረት ካልሆነ በስተቀር የእነዚህ መብቶች አጠቃቀም ሊገደብ አይችልም፤›› በማለት ገደቦቹን በተናጠል አስቀምጧል፡፡ 

አንቀጽ 27 ላይ ዋስትና የተሰጠው የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት ሊገደብ የሚችለው በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ አምስት ላይ በተገለጸው አኳኋን ነው፡፡ እነዚህም፣ ‹‹የሕዝብን ደኅንነት፣ ሰላምን፣ ጤናን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታ፣ የሌሎች ዜጎችን መሠረታዊ መብቶች፣ ነፃነቶችና መንግሥት ከሃይማኖት ነፃ  መሆኑን ለማረጋገጥ በሚወጡ ሕጎች ይሆናል፤›› በማለት በአንቀጽ 26 ላይ ከተገለጹት ገደቦችን በመጠኑ ለየት ባለ መልኩ ተገልጾ እናገኘዋለን፡፡

በአንፃሩ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ላይ ጥበቃ የተሰጠው የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት ገደብ ሊኖረው የሚችለው ‹‹የወጣቶችን ደኅንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ፣ የጦርነት ቅስቀሳዎች  እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ለመከላከል ሲባል በሚወጡ ሕጎችን›› መሠረት በማድረግ እንደሚሆን በማያሻማ ቋንቋ ተገልጾ እናገኘዋለን፡፡

ከላይ እንደቀረቡት ሦስቱ አንቀጾች ሁሉ አንቀጽ 29 ላይ ዋስትና የተሰጠው አመለካከትና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት የሚገደብባቸው ሁኔታዎችም በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ስድስት ላይ ተዘርዝረዋል፡፡ እነዚህም የወጣቶችን ደኅንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ፣ የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ለመከላከል ሲባል በሚወጡ ሕጎች አማካይነት ካልሆነ በስተቀር በሌላ ምክንያት ክልከላ አይደረግም የሚሉት ናቸው፡፡

ከእነዚህ አንቀጾች የምንረዳው በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡ እያንዳቸው መብቶች በምን ሁኔታ ሊገደቡ እንደሚችሉ በተናጠል ማስቀመጥን የመረጠ መሆኑን ነው፡፡

መግቢያው ላይ ከተቀመጠው በተጨማሪም አዋጁ ማሳካት የፈለጋቸውን ዓላማዎች አንቀጽ ሦስት ላይ እናገኛቸዋለን፡፡ እነዚህም ‹‹ሰዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሰብዓዊ ክብርን፣ የሌሎችን ደኅንነትና ሰላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር እንዲቆጠቡ ማስቻል፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ እኩልነት እንዲሰፍን፣ መከባበር እንዲኖርና መግባባትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲጎለብት ማድረግ፣  ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አደጋ የሆኑ የጥላቻ አመለካከትና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን መስፋፋትንና ተያያዥ ወንጀሎችን መከላከልና መቀነስ ናቸው፤›› በማለት በሦስት ንዑሳን አንቀጾች ለይቶ አስቀምጧቸዋል፡፡ እነዚህ ዓላማዎችም ይሁኑ ከላይ በመግቢያው ላይ የተገለጹት ሕገ መንግሥታዊነታቸውን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ከሕገ መንግሥቱ መንፈስም ቃልም ጋር የማይጋጭ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

በረቂቅ አዋጁ መግቢያ ላይ መብቶች ላይ የሚኖሩ ገደቦች አስቀድመው በሕግ መታወቅ ያለባቸው መሆኑን እንደ ደጋፊ ምክንያት ማቅረቡ ከላይ ባየናቸው ምሳሌዎችም ላይ ቢሆን በሕግ መሠረት ብቻ ሊገደቡ እንደሚችሉ ስለተገለጸ በዚህ ረገድ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ረቂቅ አዋጁ የተከተለው የገደብ ፍኖት ሕገ መንግሥቱ ከጅምሩም አልተከተለውም፣ አልመረጠውም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የተወውን በጅምላ ለሁሉም መብቶች ገደብ የሚጣልበትን ሁኔታ ነው ረቂቅ አዋጁ የመረጠው፡፡ ይህ ዓይነቱ የገደብ ፍኖት በአውሮፓውያን ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ ተግባራዊ ያደረጉትም ይኼንኑ ነው፡፡

እዚህ ላይ አንድ ሊነሳ የሚችል መከራከሪያን መገመት ይቻላል፡፡ ይኸውም፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13 (2) ላይ የተገለጸውን መነሻ በማድረግ የሚቀርብ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተገለጹት የሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ ተቀብላ ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ጋር የተጣጣመ ሁኔታ መሆን እንዳለበት ስለተገለጸ፣ በእነዚህ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ላይ የተቀመጡትን የመገደቢያ አካሄዶችን መከተል እንደሚገባ የሚቀርብ ክርክር ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ከእነዚህ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች በተሻለ ሁኔታ የሰብዓዊ መብቶችን ጥበቃ የሚያደርግ በሚሆንበት ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆነው የሚሻለውን እንጂ መብት የሚያጣብበው ሊሆን አይችልም፡፡

 ሕገ መንግሥቱ ላይ የአመለካከትና ሐሳብን የመግለጽ መብትና ነፃነት የሚገደቡበት ሁኔታ ተዘርዝረው በተቀመጡበት፣ እንደውም ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶቹ ጋር የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ የማያጣብብም የማይጋጭም ስለሆነ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች በመተው ሌሎች ግቦችንና የሚገደቡባቸው ሁኔታዎችን መውሰዱ ተገቢነትም አሳማኝነትም አይኖረውም፡፡

ንግግር፣ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ

ረቂቅ አዋጁ ውስጥ የተካተቱ ሦስት ቁልፍ ጽንሰ ሐሳቦች አሉ፡፡ እነዚህም ‘ንግግር’፣ ‘የጥላቻ ንግግር’ እና ‘ሐሰተኛ መረጃ’ የሚሉት ናቸው፡፡ ንግግር የሚለው ቃል ከተለምዷዊ ትርጉሙ የሰፋ ሐሳብን በመያዝ “በቃል፣ በጽሑፍ፣ በምሥልና ሥዕል፣ በቅርፃ ቅርጽና በሌሎች ተመሳሳይ መንገዶች መልዕክትን የማስተላለፍ ተግባር  እንደሆነ ብያኔ ተሰጥቶታል፡፡ በመሆኑም፣ በቃል ብቻ ሐሳብ መግለጽ ላይ ሳይወሰን በጽሑፍም በምሥልና ቅርፃ ቅርጽም ጭምር የሚተላለፍ መልዕክት በሙሉ ንግግር ነው ማለት ነው፡፡

 ንግግር ይህን ትርጓሜ በመያዝ  የጥላቻ የሚሆንበትንም እንዲሁ ረቂቁ አዋጁ ሁለተኛ ብያኔ አስቀምጧል፡፡ የተሰጠው ብያኔም እንደሚከተለው ነው፡፡ ‹‹የጥላቻ ንግግር›› ማለት የሌላን ግለሰብን፣ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማኅበረሰብን ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ ፆታን፣ አካል ጉዳተኝነትን፣ ዜግነትን፣ ስደተኝነትን፣ ቋንቋን፣ ውጪያዊ ገጽታን፣ መሠረት በማድረግ፣ ሆነ ብሎ እኩይ አድርጎ የሚስል፣ የሚያንኳስስ፣ የሚያስፈራራ፣ መድልዎ እንዲፈጸም፣ ወይም ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ንግግር ነው።

ይህ ብያኔ ለብዙ ትችት የተጋለጠ፣ ውሎ አድሮም ከታሰበለት ዓላማ ውጭ ጥቅም ላይ ለማዋል ደረቱን ገልጦ የሰጠ አንቀጽ ነው፡፡ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰተ ያለውና የዜጎችንም መብትና የተለያዩ ማኅበራዊ መደብ ያላቸውን ቡድኖች ጉዳት ላይ በመጣል የአገሪቱንም ሕልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ዐውድን ነቅሶ ማውጣት ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች እየበዙና ዜጎችንም ብሔራቸውንና ሃይማኖታቸውን መሠረት በማድረግ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በተለይ ብሔርን መሠረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች ከእለት ወደ እለት እየጨመሩ ጥላቻ ወለድ ወንጀሎችም ተበራክተዋል፡፡

በዚህ ብያኔ ላይ ንግግሩ፣ ፆታን መሠረት ያደረገ የጥላቻ ንግግር ለአገሪቱ አደጋ ነው ወይ? ወንድን የምትጠላ ሴት ‹እናንተ ወንዶች እንዲህ ናችሁ› በማለት ባሏን ወይም የወንድ ጓደኛዋን ብትሳደብ፣ ወይም በተቃራኒው አንድ ወንድ አንዲትን ሴት በዚህ መልኩ ቢናገር ሴቶችና ወንዶችን በሁለት ጎራ አለያይቶ የአገርን ሰላም ያውካል፣ ጥቃት እንዲፈጸም ያነሳሳል የሚለው ተጠየቃዊ ነው ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡

ልክ እንደዚሁ ሁሉ፣ አካል ጉዳተኝነትን፣ ውጫዊ የአካል ገጽታን ዜግነትን መሠረት አድርጎ የሚደረጉ ስድብና የሚያዋርዱ ንግግሮች ጉዳት ደረሰብኝ በሚለው ሰው አመልካችነት በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አማካይነት የሚታይ ቢሆን የተሻለ ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንድ አገሮች (ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ) ከእነዚህም የበለጡ ሌሎች ማኅበራዊ አቋሞችን መሠረት አድርጎ የሚፈጸሙ ንግግሮችን የጥላቻ ሊሆኑ እንደሚችሉ ደንግገዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ትኩረታቸው ንግግሩ ላይ ብቻ ሳይገደብ በተጨባጭ ወንጀል ሲፈጸም መቅጣትንም ይጨምራል፡፡

የጥላቻ ንግግርን ብያኔ ከእንደገና በረቂቁ አንቀጽ 4 ላይ በማስቀመጥ ንግግሩ የሚተላለፍባቸውን የመገናኛ ወይም የማሠራጫ ዘዴዎች ጨምሯል፡፡ ክልከላውንም በግልጽ አስቀምጧል፡፡ የጥላቻ ንግግሮች የያዙ መልዕክቶችን መናገር፣ ጽሑፍ መጻፍ፣ የኪነ ጥበብና ሥነ ጥበብ ወጤቶችን መሥራት፣ እነዚህን ድርጊቶች በድምፅ ወይም በምስል አዘጋጅቶ ማሳተም ወይም ማሠራጨትንም ይይዛል፡፡ እነዚህ አንቀጽ 4(1) ከፊደል ‘ሀ’ እስከ ‘መ’ ድረስ የተዘረዘሩት ናቸው፡፡

እነዚህ ድንጋጌዎች እንዳሉ አሁን ባሉበት ሁኔታ ከፀደቁ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ የማይኖራቸው ሥልጣን መኖሩ በራሱ አጠራጣሪ ነው፡፡ የተከለከለው በጽሑፍ አዘጋጅቶ ማሠራጨት ሳይሆን፣ መጻፍም ጭምር ነው፡፡ አንድ ሰው በድንገት የማስታወሻ ደብተሩ ላይ በማናቸውም አጋጣሚ የጻፈውን ጽሑፍ፣ ማሠራጨት ባይፈልግም እንኳን ሊያስቀጣው ይችላል፡፡ አንድ ሠዓሊ በግል ቤቱ የሚያስቀምጠው አንድ ሥዕል ሠርቶ ቢገኝና ፖሊስ ቢደርስበት በዚህ ድንጋጌ መሠረት ይቀጣል፡፡

በተለይ ከ ‘ሀ’ እስከ ‘ሐ’ ድረስ ያሉትን በማናቸውም መንገድ ማሠራጨትን ወይም ሌላ ሰው ጋር መድረሳቸውን በቅድመ ሁኔታነት አላስቀመጠም፡፡ እንደውም ይኼንን አቋም አጠናክሮ፣ ይሔው አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ሁለት ላይ ‹‹ለሦስተኛ ወገን ወይም ለማኅበረሰቡ እንዲደርስ በማሰብ ይዞ መገኘት›› ክልክል እንደሆነ ገልጿል፡፡

ይህ አገላለጽ ለትርጉም እጅግ ሰፊ ዕድል ስለሚሰጥ ግላዊነትንም (Privacy) ለከፋ አደጋ ያጋልጣል፡፡ አንድ ሰው ሞባይል ስልክ ቀፎውን እንደ ማስታወሻ ቢጠቀም፣ እዚያ ላይ የጻፈው ነገር በሙሉ እየተበረበረ ምን ጽሑፍ አስፍረሃል ሊባል ነው፡፡ የጻፈው ነገር በማስታወሻነትም ይሁን በግላዊ ባሕርይ ምክንያት ጽፎ በግሉ የያዘው ሁሉ ለማሰራጨት አስቦ ነው ሞባይሉ ወይም ኮምፒተሩ ላይ የጻፈው የመባል ዕድሉ እጅግ በጣም ሰፊ ነው፡፡ በዚያ ላይ ‘ለማሰራጨት አስቦ ነው’ ወይም ‘ለማሰራጨት አስቤ አይደለም’ የጻፍኩት የሚለውን ማስረዳት ለፖሊስም ለተከሳሽም እጅግ አዳጋች ነው፡፡

በዚሁ አንቀጽ 4(1) (ሠ እና ረ) ላይ መልዕክቶችን በብሮድካስት (በቴሌቪዥንና ሬዲዮ) እና በማኅበራዊ ሚዲያ ማሠራጨትን ለይቶ ከልክሏል፡፡ እንደውም በማናቸውም ሌላ ዘዴ ለሕዝብ እንዲደርስ ማድረግንም ጨምሮ አስቀምጧል፡፡ በእነዚህ ሁለት ንዑስ አንቀጾች ላይ የተቀመጠው አገላለጽ ከላይ የቀረበውን፣ ሳይሰራጩም ጭምር፣ ሊስቀጡ እንደሚችሉ የበለጠ ያጠናክራል፡፡ ማሰራጨትን በሚመለከት፣ ተሠራጭቷል ለመባል በመጀመርያ ‘ሕዝብ’ የሚለው ስንት ሰው እንደሆነም አይታወቅም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በስልክ አጭር መልዕክት ለአንድ ሰው ላከ፡፡ ወይንም በፌስቡክ የውስጥ መልዕክት መላኪያ በመጠቀም ለአንድ ወይም ሁለት ሰው መልዕክት ላከ፡፡ እነዚህ ለሕዝብ እንደ ደረሱ ይቆጠራልን? ለአንድ ሰው የተላከ መልዕክት ኖሮ፣ መልዕክቱ የደረሰው ሰው ለሕዝብ ቢያደርሰው የሚጠየቀው የትኛው ሰው ነው?

ሦስተኛው ብያኔ የተሰጠው ሐረግ ‹‹ሐስተኛ መረጃ›› የሚለው ነው፡፡ ብያኔውም ‹‹የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ ውሸት የሆነና ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ ዕድሉ ግልጽ በሆነ መልኩ ክፍ ያለ ንግግር ነው፤›› የሚል ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ለፖሊስም፣ ለዓቃቤ ሕግም ለዳኞችም ሰፊ ሥልጣን የሰጠ ነው፡፡ ‘የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ’ የሚለው አገላለጽ በንግግሩ ውስጥ የተካተተውን የሐሰትነት መጠን ወደ መሆን ይወስደዋል፡፡ በዚያ ላይ አመለካከትና ጥሬ መረጃን የለየ አይደለም፡፡ በተጨማሪም ሁከትና ግጭት የማስነሳት ዕድሉ ከፍ ያለ ነው ወይስ አይደለም የሚለውም እንዲሁ ወደተፈለገበት አቅጣጫ ተጠምዛዥ ነው፡፡

ይኼንን ሐሰተኛ መረጃ የማሠራጨት ተግባርን በግልጽ የከለከለው አንቀጽ አምስት ነው፡፡ በማናቸውም መልኩ ለሕዝብ እንዲደርስ ማድረግ ወንጀል ነው፡፡ የሐሰት መረጃ ያሠራጨ ሰው እስከ አንድ ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት ሊቀጣ ይችላል፡፡ አሠራጩ ሰው በማኅበራዊ ሚዲያ ከአምስት ሺሕ ሰው በላይ ተከታይ ካለው፣ በብሮድካስት ወይም በየጊዜው በሚወጣ ኅትመት (ጋዜጣ፣ መጽሔት ወዘተ) ከሆነ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት፣ ወይም እስከ አሥር ሺሕ ብር የሚደርስ መቀጮ ይቀጣል፡፡ በሐሰተኛ መረጃው ምክንያት ተነሳስቶ ጥቃት ከተፈጸመ ደግሞ እስከ አምስት ዓመት የሚደረስ ፅኑ እስራት ያስቀጣል፡፡  የሐሰት መረጃ ማሰራጨት፣ በዚህ መልኩ በሦስት ምድብ የተከፋፈሉ ቅጣቶችን ያስከትላል፡፡

የጥላቻ ወንጀልን ጥሎ ንግግርን አንጠልጥሎ

ከዚህ ባለፈ ግን የጥላቻ ንግግርን ወንጀል አድርጎ፣ በጥላቻ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን ወንጀል አለማድረግም ሌላው የዚህ ረቂቅ ጉድለት ነው፡፡ አንድን ሰው የሆነ ብሔር ተወላጅ በመሆኑ ብቻ አንድ የሌላ ብሔር ተወላጅ በጥላቻ ተነሳስቶ የአካል ጉዳት ቢያደርስበት ወይንም ቢገድለው ከጥላቻ ንግግሩ በከፋ ሁኔታ ማኅበራዊ ሰላምን የሚነፍግ ብሎም የብሔር ግጭት እንደሚፈጥር እሙን ነው፡፡

ንግግርን ከተራ ስድብነት ወይንም ስም የማጥፋት ወንጀል ለይቶ የወንጀል ቅጣቱ ከፍ እንዲል ከተደረገ በተመሳሳይና እንደውም የበለጠ አሳማኝ የሚሆነው በጥላቻ ተነሳስቶ መድልኦ የፈጸመ፣ ጥቃት ያደረሰ ሰው በተለየ ሁኔታ ከፍ ያለ ቅጣት ሊቀመጥለት ይገባል፡፡ ስለሆነም የጥላቻ ንግግር በባሕርይው ወንጀል እንዲፈጸም ስለሚያነሳሳ ነው ወንጀል የተደረገው፡፡ በንግግሩ ተነሳስቶ ወይንም በንግግሩ ምትክ ሌላ ወንጀል ሲፈጸም የበለጠ የሚስቀጣ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

በተጸውኦ ስም መጻፍ እንደ ወንጀል

የፌስቡክ (ቲውተር፣ ሊንክድኢን ወዘተ) አካውንት (ስም) በትክክለኛ መጠሪያ ስምና አድራሻ የማይጽፍ ሰውን በሚመለከት ምንም ዓይነት ድንጋጌ የለውም፡፡ ማንነቱ ሳይገለጽ በሌላ ስም በመጠቀም የጥላቻ ንግግር የሚያስተላልፍ ሰው ቢኖር፣ የፌስቡክ አድራሻው (አካውንቱ) ሊዘጋበት ነው ወይስ ምን ሊደረግ ነው? ረቂቅ ሕጉ ተፈጻሚ ሊሆን የሚችለው በስማቸው ለሚጽፉ ሰዎች ብቻ ስለሚሆን፣ ከተጠያቂነት ለመሸሽ ሰዎች ትክክለኛ ስማቸውን ከመጠቀም ይልቅ ሌላ ስም መጠቀምን እንዲመርጡ ያበረታታል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ መንግሥት በትክክለኛ የተጸውኦ ስም የማይጠቀሙትን በመዝጋት ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ በማድረግ ሥራ ይጠመዳል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ይኼን እውን ማድረግ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በአጭሩ ተፈጻሚነቱ በተጸውኦ ስም የማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ ሰዎችን ላይ እንጂ በሌላ ስም የሚጠቀሙትን አይጨምርም፡፡

ከኢትዮጵያ ውጭ ሆነው የሚናገሩትንስ/ የሚጽፉትንስ?

የጥላቻ ንግግርንና የሐሰት መረጃ ማሠራጨትን ወንጀል ለማድረግ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ከኢትዮጵያ ውጪ ሆነው የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰት መረጃ የሚያሠራጭ ሰዎችን በምን መንገድ ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚቻል ድንጋጌ የለውም፡፡ ስለሆነም፣ በጥላቻ ንግግርም ይሁን በሐሰት መረጃ በወንጀል ሊከሰሱ የሚችሉት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ብቻ መሆናቸው ነው፡፡ በመሆኑም፣ እንዲህ ዓይነት ንግግሮች የመሆን ዕድል ያላቸውን ጽሑፎች አንድም በግል ስማቸው ለማይጠቀሙ፣ ሁለትም ከኢትዮጵያ ውጭ በሚኖሩ ሰዎች አማካይነት መሠራጨትን ያበረታታል እንጂ ዓላማውን ማሳካት አይችልም፡፡ በተጨማሪም አድሏዊ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ መጻፍ ብቻ ያስቀጣል፡፡ ጉዳያቸው በሌሉበት የሚታይ ወንጀልም አይደለም፣ ምክንያቱም በሌሉበት ለመታየት ቅጣቱ ከአሥራ ሁለት ዓመት በላይ የሚያሳስር መሆን ስላለበት ነው፡፡

በሥርጭት ላይ ያሉትስ?

የጥላቻ ንግግርንና የሐሰት መረጃ ማሠራጨትን ለመቆጣጠር የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ  ከአሁን በፊት ተዘጋጅተው የተሠራጩና በሥራ ላይ ያሉ ወይም ተደራሽ የሆኑ ሰነዶች፣ ካሴቶች ወዘተ ላይ የሚገኙ የጥላቻ ንግግሮችና የሐሰት መረጃዎችን በሚመለከት ዕጣ ፋንታቸው ምን እንደሚሆን የሚገልጸው ነገር የለም፡፡ 

የመንግሥት የፖሊሲ ሰነዶች፣ የተማሪ መማሪያ መጽሐፍት፣ ግለሰቦች ያሳተሟቸው መጽሐፍት፣ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ ካሴቶች፣ በዩቲዩብና መሠል ማሠራጫ ላይ የሚገኙ የጥላቻ ንግግሮችን በሚመለከት የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ሥርጭታቸው ይቀጥላል፡፡

ቀድሞ ስለተገለጸ ወይም ስለተጻፈ ወይም ስለተሠራጨ ተብሎ አሁንም ሥርጭቱ ይቀጥላልን? ወይስ ይቋረጣልን? ያስቀጣልን  ከዚሁ ጋር ተያያዞ፣ እንዲህ ዓይነቱን የጥላቻ ንግግር የሚቆጣጠረው አካል (ብሮድካስት ባለሥልጣን) የሚታተሙ መጽሐፍትን ጋዜጣን፣ መጽሔትን፣ በኢንተርኔት የሚለቀቁ ንግግሮችን ሁሉ የማንበብ አቅምና ችሎታ እንዴት ሊኖረው ይችላል? ወይንስ ደግሞ፣ ቢያንስ ለመጽሐፍ፣ መጽሔት፣ ወዘተ. ሲሆን ቅድመ ኅትመት ምርመራና ፈቃድ (ሳንሱር) ሊኖር ነውን? 

የፍርድ ቤት ሥልጣን…

የኢንተርኔት መከሰት የስም ማጥፋት ሕግን ሲበዛ ውስብስብ አድርጎታል፡፡ አንድ አገር ላይ ተሁኖ የተለቀቀን ጽሑፍ፣ የድምፅ ወይም የምስል መልዕክት ኢንተርኔት ባለበት አገሮች ሁሉ ይገኛል፡፡ የጥላቻ ንግግሩም ይባል የሐሰት መረጃው መነሻ የሆነው ድርጊት የሆነ አገር ላይ ይለቀቃል፡፡ ጉዳቱ ደግሞ ድርጊቱ ከተፈጸመበት በተጨማሪ ሌሎች አገርም ላይ ይፈጸማል፡፡

አሜሪካ ሆኖ ስለ አንድ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖርን ሰው ስም የሚያጠፋ ጽሑፍ በማኅበራዊ ሚዲያም ይሁን በሌላ ዓይነት መደብ ሲለቀቅ ይኼንን ስም አጥፊውን ጽሑፍ፣ ንግግር፣ ምስል ወዘተ በመላው ዓለም የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ወይም ሌላ ሰው ጭምር ሊያየው ይችላል፡፡

እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ጉዳት የደረሰበት ሰው መብቱን ለማስከበር የሚጠቀማቸው አማራጮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰቡና አዳጋች እየሆኑ ነው፡፡  እየተወሳሰበ የመጣው፣ ኢንተርኔት ድንበር ስለማያውቅ፣ መብትና ግዴታን የሚወስኑት ደግሞ በድንበር የተገደቡ አገሮች በመሆናቸው ነው፡፡

በአንዱ አገር ስም የሚያጠፋ ነው የሚያሰኝ ጽሑፍ ወይም ንግግር በሌላ አገር ሕግ የተፈቀደ ይሆናል፡፡ ድርጊቱ በራሱ ስም የሚጠፋ ነው ወይስ አይደለም የሚለውም እንደየማኅበረሰቡ ሲለያይ፣ ኢንተርኔት አገር ስለሌለው የተለየ ማኅበረስብ የለውም፡፡ ስለሆነም በየትኛው ማኅበረሰብ አኳያ ጽሑፉ ወይም ንግግሩ ለመልካም ስም ተቃራኒ ነው ይባል?

በኢንተርኔት ዓለም የፍርድ ቤት ሥልጣን የሰከነ የሕግ ሥርዓት ላይ አልደረሰም፡፡ አይደለም በተለያዩ አገሮች መካከል ስለሚኖረው ይቅርና በፌደራል ሥርዓት የሚመሩ አገሮችም ከፈተና አልተላቀቁም፡፡

በተለይ ደግሞ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን በሚመለከት ሕግ የማውጣት ሥልጣኑ ለክልሎች ከሆነ የውስብስብነት ደረጃው ይጨምራል፡፡ የኢትዮጵያን በምሳሌነት እናንሳ፡፡ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን በሚመለከት ሕግ የማውጣት ችሎታ/ሥልጣን ለክልሎች የተተወ ነው፡፡ ጉዳዩን የማየት ሥልጣን የየትኛው ፍርድ ቤት ነው የግዛት የዳኝነት ሥልጣን የሚባል አለ ወይ?

በግል አመልካችነት ወይስ በክስ?

በጥላቻ ንግግር የሚቀርብ የወንጀል ክስ የግል ተበዳይ የሆነ ሰው ሲያመለክት (Upon Complaint) ነው ክስ የሚመሠረት ወይስ ደግሞ የሕዝብ ጥቅምን እንደሚፃረር እንደ ማንኛውም ሌላ ወንጀል የግል ተበዳይ አቤቱታ ባያቀርብም (Upon Accusation) ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማድረግ ይችላልን? ይሄም ሊመለስ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ ሰው በማኅበራዊ ሚዲያም ይሁን በሌላ የመገናኛ ዘዴ የጥላቻ ንግግር የሆነ ስድብ ወይም የሚያዋርድ ንግግር ቢፈጸምበትም እንኳን፣ ክስ ማቅረብ የማይፈልግ ይኖራል፡፡

በዚህን ጊዜ የግለሰቦቹ ምርጫን በማክበር የወንጀል ተግባሩን ምርመራ እንዳይጀመር ይደረጋልን? በሌላ መልኩ ደግሞ ቀጥታ ንግግሩ ያተኮረው አንድ ሰው ላይ ቢሆንም እንኳን ሌሎች ሰዎችን በማነሳስት የበለጠ ንትርክ ውስጥ በመክተት በብሔር መካከል ጥላቻ እንዲበረታ የሚያደርግ ቢሆንስ? ለማንኛውም እንዲህ ዓይነቶቹ ጉዳዮች የፖሊሲ አማራጮች ስለሆኑ ጥልቅ ፍተሻ በማድረግ የተሻለውን አማራጭ መከተል የመንግሥት ሥልጣን ነው፡፡

ለማጠቃለል ያህል፣ ረቂቅ አዋጁ በመግቢያው ላይ ከያዛቸው መነሻዎች ጀምሮ ዓላማውንም ጭምር ከእንደገና በጥልቀት መፈተሽ አስፈላጊ ነው፡፡ በተጨማሪም ስለ ጥላቻ ንግግርም ይሁን ሐሰተኛ መረጃ መያዝና ማሠራጨት ወንጀል የሚሆኑትን መሆን ከሌለባቸው ከእንደገና አጥርቶ የመለየት ሥራ ማከናወንን ይጠይቃል፡፡ እንዲሁም፣ ያላለቁ ጉዳዮች ስላሉትና ደንብ በማውጣት የማይሸፈኑ ስለሆኑ ድጋሜ ማጤን ተገቢ ነው፡፡ ከላይ የቀረቡት በጣም ጥቂት የሚባሉት ነጥቦች እንጂ፣ በዝርዝር ቢታይስ ብዙ ነገር አለው፡፡ ሰው የመሰለውን ሐሳብ በግላዊ ቁሳቁሶቹ ላይ ማስቀመጥን ሳይቀር ወንጀል ማድረግ ሕጉንም አውጪውንም መጥላት ነው ትርፉ የሚሆነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...