Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትድሮ’ኮ ወርቁ ቢጠፋ ቢያንስ ‘ሚዛኑ’ ነበር

ድሮ’ኮ ወርቁ ቢጠፋ ቢያንስ ‘ሚዛኑ’ ነበር

ቀን:

በገነት ዓለሙ

አንድ ዓመት የሞላውና በተለያየ ስሜት በመከበርና በመዘከር ላይ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ መንግሥት የሚመራው ለውጥ ብዙ ዓይነት የማይናቁ ተጠናዋቾች ቢኖሩትም፣ ‹ሀ› ብሎ ሥራውን የጀመረው የጠላትነት ፖለቲካን እናፍርስ፣ ለየትኛውም ቡድንና ወገን የማያገለግል፣ ከቡድናዊ ቁጥጥር፣ ወገናዊነትና ታማኝነት የተላቀቀ፣ ለፓርቲም ሆነ ለብሔርተኛ ማንኛውም አድልኦ የማይበገር፣ ዓይኑ የተጋረደ ሆኖ የሁሉም የጋራ አለኝታ ተደርጎ ለመታየት የበቃ አውታረ መንግሥት እንገንባ ብሎ ነው፡፡ ይህ በራሱ ትልቅ ግኝት፣ ትልቅ ዕውቀት፣ ትልቅ ጅምር ነው፡፡ በርካታ ተከታታይ ለውጦችን አግተልትሎ ማስከተል የሚችል አዲስ ለውጥ ነው፡፡ የአገራችን የዚህ ዘርፍ ችግር ሲበዛ እጅግ በጣም የተወሳሰበ በመሆኑ፣ በለውጡ አንደኛው ዓመት ‹‹በዓል›› ጊዜ ላይ መጠየቅ ያለበት የታለ ገለልተኛው ፍርድ ቤት፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ሲቪል ሰርቪስ፣ ወዘተ ተብሎ ሳይሆን፣ እንዳያያዛችን ገለልተኛ አውታረ መንግሥት የመገንባትና የማጠናከር የዓብይ ህልምና ራዕይ በሕይወት መኖሩ በራሱ ታላቅ ነገር ነው፡፡

በኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረው የለውጥ ኃይል የራሱን የኢሕአዴግን ያለቀላቸውንና ያበቃላቸውን ክስረቶችን ተቀብሎ፣ ከራሱ ውጪ የሌሎች ወገኖችን ድምፅ የመስማት ለውጥ አድርጎ፣ የኢትዮጵያን ዕድገት ህልውና ከራሱ መስመርና ዕቅድ ጋር አንድ አድርጎ ከማየት ጉድጓዱ ወጥቶ፣ ከሁሉም በላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ዳግም ዋናው የመንግሥት ሥራው አድርጎ ከተዘፈቀበት፣ ሥልጣንን ከመከላከልና ከተቃውሞ ጋር ከመተናነቅ ተግባሩ እላቀቃለሁ ብሎ ስለአውታረ መንግሥት ግንባታ ‹‹መታወጁ›› እንዳይቀለበስ የሚታገሉለት ድል ነው፡፡

ይህን መነሻ በማድረግ ገለልተኛ ተቋማትን፣ ማለትም ከየትኛውም ፓርቲ ሆነ መንግሥት ድልና ተልዕኮ፣ እንዲሁም ዕድሜ ጋር የማይጣበቁ፣ የማይታሙ ገለልተኛ ተቋማትን የመገንባትና የማነፁ ተግባርና ጅምር ጉልቶ እየወጣ፣ እየተነገረ፣ እየተመረመረ ካልታገዘ በስተቀር እንደ አያያዛችን፣ እንደ ‹‹ተቃዋሚ ብቻ›› ብዛት፣ እንደ ባህላችንና ኋላቀርነታችን ክፋት ነገርየው ከእነ ወሬው ሊቀለበስ፣ ሊጠፋና ሊረሳ ይችላል፡፡

እንኳንስ ገልተኛ የመንግሥት አውታራትን የመገንባት ሥራ መጀመሩ፣ ጅምሩም አዋጅ እስከ ማሻሻል ድረስ መሄዱ ወሬው ራሱ መነሳቱና የተነሳውም በለውጡ እንድርድሪት ውስጥ መሆኑ በአገራችን ተነስቶ የማያውቅ፣ ስለመኖሩም ጨርሶ የማይታወቅ ጥያቄ እንዲነሳና እንዲሰማ አድርጓል፡፡

ለምሳሌ የአገሪቱ የመረጃና የደኅንነት የሥልጣን አካላት ሕግ የማስበር (Law Enforcement Power) ሥልጣን አላቸው? ማለትም የመያዝ፣ የማሰር፣ የመፈተሽ መብት አላቸው? እነዚህ የማሰር፣ የመያዝ፣ የመፈተሽ፣ ወዘተ ሥልጣኖችን አጠቃቀምስ በበላይነት የሚቆጣጠርና ሕጋዊነታቸውን የሚያረጋግጥ፣ በአስፈጻሚው አካል ውስጥ፣ በዳኝነት አካሉ ወይም በፓርላማው የሚያይ የበላይ አለ ወይ? ብሎ ዓይነት ጥያቄ በተለይ ደግሞ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ማዕቀፍና መዋቅር ውስጥ የሚነሳና እያንዳንዱ መንግሥት መልስ ሊሰጥበት፣ ሪፖርት ሊያደርግበት የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ ኢትዮጵ መልስ ሰጠች፣ መልሴም ይህ ነው አለች ሲባል ሰምተን አናውቅም፡፡ የደኅንነት መሥሪያ ቤት የማሰር፣ ይዞ የማቆየት፣ የመፈተሽና የመበርበር ሥልጣን አለው ብሎ ጥያቄ እንኳንስ ተራው ዜጋ ውስጥ ፓርላማው ውስጥ፣ ሕግ ትምህርት ቤቶቻችን ላይ ተነሳ ተብሎ ወሬ ሲነገር አልሰማንም፡፡

ይህ ጥያቄና የጥያቄውም ትርጉምና አንድምታ ግን ከለውጡ በኋላ ባልተለደ ሁኔታ ሲጠየቅ፣ ሲነገር ምናልባትም መከላከያ ሆኖ ሲቀርብ ሰምተናል፡፡ ለምሳሌ መጋቢት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ‹‹በፀጥታ  በመረጃና በደኅንነት ተቋማት ላይ የተደረገው ሪፎርም›› ምን እንደሚመስል ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ላይ አዲስ ነገር ሆኖ ሲነሳ ሰምተናል፡፡ ከጋዜጠኞች መካከልም እነዚህን ጉዳዮች ያመሳከረ ጥያቄ በቁም ነገር ሲያነሱ አድምጠናል፡፡ ከዚህም አማካይነት በትንሹ በሰው ንቃትና ግንዛቤ ውስጥ ያልነበረና የማይጠየቅ የለውጥ ጥንስስ ተጀምሯል፡፡ የመረጃና የደኅንነት ተቋማትን ሥልጣን ከመያዝና ማሰር ለይቶ ማየት፣ እንዲህ ያለ ሥልጣን አላቸው ወይ ብሎ መጠየቅ በራሱ ቀላል ጅምር አይደለም፡፡ መንግሥት ሳይገረሰስ የመጣ ‹‹አብዮት›› ነው፡፡  

ገለልተኛ ተቋማትን መቼምና ምን ጊዜም የማይታሙና የማይበገሩ፣ መንግሥት በወጣ በወረዳ ቁጥር የማይገረስሷቸውና የማያበራዩዋቸው የሁሉም አለኝታ የሆኑ የመንግሥት አውታራትን የመገንባት ተግባር በተለይ በአገራችን፣ በተለይም በቅርብ ጊዜው የመንግሥት ታሪክ ውስጥ በተለይም በሕግና በዳኝነት ተቋማት ላይ ጎልቶና ሲበዛ መርሮ ይታያል፣ ይታወቃልም፡፡ ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ እሳቸው የሚመሩት ለውጥ አንደኛ ዓመት ሲከበር ባደረጉት ንግግር/ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹ . . ለዚህ ሲባል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታችን አይተኬ ሚና የሚጫወተውን የምርጫ ቦርድ ስናደራጅ፣ ከአንዴም ሁለቴ ታስራ ለፍትሕ የታገለችውን፣ በጀግንነት ለመላው ኢትዮጵያውያን አርዓያ የሆነችውን ብርቱካን ሚደቅሳን ያመጣነው፣ የፍትሕ ዕጦት ኢትዮጵያውያንን እንዳንገሸገሸ ስለምናውቅ እናት፣ እህት፣ ሚስት ሆና ፍትሕ የሚሸቅጡትን በመለየት፣ በማስተማር፣ ለማንም ዝቅ ሳትል በሕግና ሕግ ብቻ ፍትሕን ለኢትዮጵያ እንድታመጣ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን ለፍትሕ ሥርዓት . . . ›› የመረጥነው ያሉትና እዚህን ተቋማት በግንባር ቀደምትነት የጠቀሱት፡፡

እውነት ነው ብርቱካን በዚያ ቀውጢ ጊዜ በሕውሓት መሰንጠቅ በሐሳብና በተግባር ከአሸናፊው ሕወሓት ቡድን ለተለየው የሕወሓት አንጃ እንኳን እጅግ በጣም አስቸጋሪ በነበረው በዚያ ክፉ ጊዜ ውስጥ፣ ጀግንነትና ዳኝነት ያስመዘገበች ዜጋ ነች፡፡ ይህ ምስክርነት የተሰጠው ገና ዛሬ አይደለም፡፡ ያን ጊዜም በወቅቱ፣ ከዚያ በኋላ እንዳመቸ ‹‹ለባለ ጊዜ አፍና ዱላ ሆኖ ኑሮን ማቃናት የማያስነውር ተግባር ሆኖ በተለመደበት ወቅት ባሳየችው ዳኝነት፣ በኢትዮጵያ ምድር በፖለቲካ እስረኞች ላይ ታይቶ የማይታወቀውን ለገዥዎች ፍላጎት ሳያጎበድዱ በሕግና በህሊና ተመርቶ የመፍረድን ጀግንነት ደፍራ ሞክራለች፡፡ ይህ ተግባሯ በሐሰት እየኖሩ፣ በሐሰት እየፈረዱ፣ እያሳሰሩና እያስገደሉ በዕንባና በደም የተፈተፈተ እንጀራ የሚባሉ ግፈኞች ማሳፈሪያ ሐውልት ሆኖ ይኖራል፤›› ተብሏል፡፡

ዛሬ ደግሞ ‹‹ሽብርተኞች››፣ ‹‹አሸባሪዎች›› ሲፈቱ፣ ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ ሞት የተፈረደባቸው ከእስር ቤት በነፃነት ሲወጡና የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሲቀላቀሉ፣ ከእሷ ጀግንነት ይልቅ ይበልጥ ይበልጥ ጉልቶ የሚታየውና የሚሰማው፣ እንዲሁም የሚሰነፍገው ዳኝነት ሥርዓቱ ውስጥ ዛሬም ድረስ የተከመረው ቆሻሻ ነው፡፡ የለውጡ ፀሐይ የመታው የቆሻሻው ጠረን ነው፡፡ በውስጡ የነበሩ የዳኛ ተብዬዎችና የመሪዎች ኃፍረትና አለማፈር ጭምር ነው፡፡

በዚህ መለኪያና ብርቱካን ለምርጫ ቦርድ መመደቧ፣ ለየትኛውም የፖለቲካ ቡድንና ፖለቲከኛ ድርጅታዊ ቀረቤታ ያልነበራትና የሌላት መዓዛም የዳኝነቱን ዘርፍ እንድትመራ መመረጧ አዲስና ጥሩ ነገር ነው፡፡ የለውጡን በጎ እልህ የሚያሳይ ዕርምጃ ነው፡፡

ይህ ማለት ግን ዛሬም ቢሆን አሿሿሙ (ከሹመኞቹ ይልቅ አሿሿሙ) እንከን የማይወጣለት ነበር የሚባል አይደለም፡፡ ዓብይ አህመድ በዚህ ታሪክ ባስመዘገቡበት በወዳጅም፣ ወዳጅ ባልሆነም ‹‹ከዓይን ያውጣህ!›› በተባሉበት በዚሁ አሿሿማቸውም ማዕቀፍ ውስጥ፣ ማለትም ነባር ሕግ ማሻሻልና አዲስ ሕግ ማውጣት ሳያስፈልጋቸው የአሿሿሙን ሒደት ታይቶ የማይታወቅ፣ አገር አሳታፊና አገር አንቀጥቅጥ ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡ ብርቱካን ሚደቅሳ ለምርጫ ቦርድ፣ መዓዛ አሸናፊ ለፌዴራል ፍርድ ቤት መሪነት አትሆንህም፣ አትሆነንም የምትለኝ ለምሳሌ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ምክንያትህን ላክልን/ላክብኝ፣ ለሰውም ንገር፣ ተነጋገር፡፡ የሕዝብ ተወካዮችም ይህን የመሰለ እንከን ነውር አለ የምትለውን ይዘህ ቅረብ ማለት የመሰለ ነገር ሹመቱ ይጎድለዋል፡፡ ወደፊት መደገም የሌለበት ‹‹ክፍተት›› ነው፡፡

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ዛሬም የተቋማትን ገለልተኛነት ከየአቅጣጫው ከሚታገሉትና ከሚያንገላቱት ተፅዕኖዎች ከሚመስሉ ሁሉ ለመጠበቅ የሚያስችል መከላከያና ዝግጁነት የለንም፡፡ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከፍ ሲል የተጠቀሰውንና ስለ ‹‹እናት፣ እህት፣ ሚስት›› ሲናገሩ ቴሌቪዥኑም ወ/ሮ መዓዛን፣ ወ/ሮ መዓዛም ስሜታቸውን መደበቅ አልቻሉም፡፡ ጥያቄውና ችግሩ ዶ/ር ዓብይ ለምን ያንን አሉ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅን ልቦና የሚሰማቸውን ተናግረዋል፡፡ እምነታቸውንና ለውጡ የደረሰበትን ደረጃና ያስመዘገበውን ድል ከልባቸው ‹‹ሪፖርት›› አድርገዋል፡፡ ወ/ሮ መዓዛም ከዚያ በላይ ስሜታቸውን መደበቅ አልችል ቢሉ የእሳቸው ጥፋትና ስህተት አይደለም፡፡ ስህተቱና ጥፋቱ እንደዚያ ያለ ቦታ ላይ መገኘት (ግብዣ፣ አቀባበል፣ ስብሰባ ቅብርጦሽ) የነፃው ፍርድ ቤት መሪም ሆነ ሌሎች ዳኞች ወግም ፕሮቶኮልም አለመሆኑን ዛሬም ማናችንም አለመረዳታችን ነው፡፡ መደፋፈር የሚጀምረው መከባበር የሚቀረው እንዲያ እንዲያ እየተባለ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የፌዴራል ዳኝነት ሥርዓት የበላይ ኃላፊ ቃልና ድምፅ መስማት መልካቸውንና ገጽታቸውንም በአደባባይ ማየት ያለብን የያዙት መዝገብ ውስጥና ችሎት ላይ ብቻ ነው፡፡ እንዲህ እንዲህ ያለው ነገር ቀስ እያልን ማስተካከል የምንችለው፣ ዳኞቻችንንም ውስጥ ለውስጥ አጉል ከ‹‹ሚያሳስባቸው›› የፕሮቶኮል ጣጣ የምናወጣው ሥራቸውንና ሥራቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ‹‹ነፃ የምናወጣቸው›› ሕገወጡን ከሕገ ገቡ እንዲለዩ ብቻ ሳይሆን፣ ነፃው ፍርድ ቤት አቋሙንና ተግባሩን በሕግ ከተደነገገው ቁመናው ጋር እንዲያርቅ ማድረግ እንዲችል ስናግዘው ጭምር ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቻችን በሕዝብ ዘንድ ለመታመን የሚበቁትና የሕዝብን ተቀባይነት ማግኘት የሚችሉት፣ ይህንንም ጠብቀው የሚዘልቁት ከዋና ዋና የሕግ ጥበቃዎች ጋር ይህን በመሳሰሉ ጥቃቅን በሚመስሉ ‹‹ጠጠሮች›› ዋናውን ‹‹ጋን›› ደግፈው ሲይዙ ብቻ ነው፡፡

ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ለተሰጠው የዳኝነት ነፃነት ደምና መቅኒን ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱና ምናልባትም ‹‹ትንሹ›› የዳኞች ‹‹ያለ መከሰስ መብት›› የሚባለውና በአማርኛ ሲወራና ሲደነገግ፣ በሕግም ሲደነገግ ‹‹የሚጎረብጥ›› መልክና ስሜት ያለው የነፃነቱ ፍጥርጥር አካል የሆነው ጉዳይ ነው፡፡ አማርኛው ‹‹ያለ መከሰስ መብት›› የሚለውን ነገር እንግሊዝኛው ኢሚዩኒቲ ይለዋል፡፡ ይህንን መብት ዳኞች ብቻ እሱ ካልኖረን ‹‹ሞቼ እገኛለሁ›› ያሉት ነገርና ጉድ አይደለም፡፡ ሲጀመርም ለእሱ ተብሎ የተሰጠ መብት አይደለም፡፡ ለዳኝነቱ ለሥራው ነው፡፡ አስፈላጊ ሲሆን ሥልጣን በተሰጠው አካል የሚነሳና ሌላው ቀርቶ መብቱ በተጠበቀለት በራሱ በሰውየው ትቼዋለሁ የማይባል የነፃነት መጠበቂያ ነው፡፡

ከላይ እንደተመለከተው ይህ በባለመብቱ በራሱ የማይነሳ ያለ መከሰስ መብት የዳኛ ብቻ አይደለም፡፡ ዲፕሎማቶች፣ እንደራሴዎች፣ በተለየ ሁኔታ ደግሞ ጋዜጠኞች ጭምር ያለ መከሰስ መብት አላቸው፡፡ ማናቸውም የምክር ቤት አባል፣ ወይም መብቱ ፈቅዶለት የቀረበ ወይም ምክር ቤቱ ጥሪ ያደረገለት ማናቸውም ሚኒስትር ምክር ቤቱ በሚያደርገው በማናቸውም ስብሰባ ወይም ምክር ቤቶቹ በአንድ ላይ በሚያደርጉት ስብሰባ፣ ወይም የምክር ቤቱ ማናቸውም ኮሚቴ በሚያደርገው ስብሰባ ላይ ባቀረበው የጽሑፍ ማስረጃ፣ ወይም በተናገረው ቃል ምክንያት አይከሰስም፣ አይወነጀልም ማለት የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ያህል ዕድሜ ያለው ሕግና ድንጋጌ ነው፡፡

ደርግ እንኳን የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ካገደ በኋላ፣ ‹‹ጊዜያዊ ብሔራዊ የአማካሪ ጉባዔ ባቋቋመበት አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 12/1967 ታኅሳስ 1967) በማናቸውም የጉባዔው አባል በጠቅላላ ወይም በኮሚቴ ስብሰባ ላይ በሚሰጠው አስተያየት፣ ወይም ባቀረበው በማናቸውም ማስረጃ ምክንያት አይከሰስም፣ አይወነጀልም ማለትን የመሰለ የተቋቋመ ወግ አላፈረሰም ነበር፡፡ የ1980 ዓ.ም. የኢሕዲሪ ሕገ መንግሥትም ‹‹አንድ የሕዝብ እንደራሴ ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተገኘ በስተቀር፣ ያለ ብሔራዊ ሸንጎ ወይም ሸንጎ ባልተሰበሰበበት ጊዜ ያለ መንግሥት ምክር ቤት ፈቃድ አይያዝም በወንጀልም አይከሰስም ብሎ በ‹‹ወጉ›› ቀጠለ፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥትም በዚያው ‹‹ባህል›› ቀጠለ፡፡ በአንቀጽ 54 ንዑስ አንቀጽ 5 እና 6 ማንኛውም የምክር ቤት አባል በምክር ቤቱ ውስጥ በሚሰጠው ድምፅ ወይም አስተያየት ምክንያት አይከሰስም፣ አስተዳደራዊ ዕርምጃም አይወሰድበትም፣ እንዲሁም ከባድ ወንጀል ሲፈጸም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤት ፈቃድ አይያዝም፣ በወንጀልም አይከሰሱም አለ፣ የተለመደውን ወግ እየዘመረ!!

በእነዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ላይ በመመሥረትም የ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 47 (በጽሑፍ ጉዳይ የማይደፈር መብት) እና የ1996 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 47 (የማይደፈር መብት) ድንጋጌዎች በተለያየ ቋንቋ እንደሚደነግጉት ‹‹. . . የሕግ አውጪ፣ የአስተዳደር ወይም የፍርድ ባለሥልጣኖች የእውነተኛና የትክክለኛ ክርክሮች ወይም ውሳኔዎች ጸሐፊ፣ አሳታሚ ወይም በሕዝብ መገናኛ ዘዴ አቅራቢ የሆነው ሰው በወንጀል ተጠያቂ አይሆንም›› ይላል፡፡ ትርጉሙ በፓርላማ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤትና በአስፈጻሚ አካል፣ እንዲሁም በፍርድ ቤቶች ውስጥ የተሰሙትን የተባሉትን እንዳለ ያቀረበ ጋዜጠኛ አይጠየቅም፡፡ የማይደፈር መብት አለው ማለት ነው፡፡

በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን መጨረሻ አካባቢ መውጣት የጀመሩ የዳኝነት አስተዳደር ሕጎች የዳኞች አስተዳደርን ለዳኞች አስተዳደር ጉባዔ መስጠት ቢጀምሩም፣ ዛሬም ሌሎች ሠራተኞችን የማያቅፈውንና በዚህ ረገድ አሁንም ሳንካላና ሕመምተኛ ሆኖ የቀጠለው የዳኞች አስተዳደር ጉዳይ ሬጂስትራሮችን ጭምር በማካተት ማስፋት የጀመረው የደርግ መንግሥት ነው፡፡ የምንነጋገረው ስለተጻፈ ሕግ ነው፡፡ አሁንም በተጻፈ ሕግ ደረጃ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በአዋጅ ቁጥር ዘጠኝ፣ አሥርና በከፍተኛ ፍርድ ቤት አዋጆች ማናቸውም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ የወታደራዊ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ ወዘተ ብሎ ‹‹ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተገኘ በስተቀር ብሔራዊ ሽንጎ ወይም ሸንጎ ባልተሰበሰቡት ጊዜ የመንግሥት ምክር ቤት ሳይፈቅድ አይያዝም በወንጀልም አይከሰስም፤›› ብሎ ደነገገ፡፡

ደርግ ወደቀ፡፡ ሄደ፡፡ ኢሕአዴግ መጣ፡፡ የሽግግሩ መንግሥት ‹‹የፍትሕ አስተዳደርን ከማንኛውም ዓይነት ተፅዕኖ ነፃ ለማድረግ›› ባወጣው አዋጅ መግቢያ ላይ የሙዚቃ ኖታ ብቻ በቀረው ከዚያ በኋላ፣ በየካድሬውና በየባለሥልጣኑ ንግግር በሚያርበደብደው ውግዘቱ ያለፉትን ተከታታይ መንግሥታት በሙሉ ‹‹ጥንብ እርኩሳቸውን›› አወጣ፣ ዘፈነባቸው፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝቦች ባለፉት የታሪክ ዘመናቸው፣ እንዲሁም በቅርቡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥትና ቀጥሎም በደርግ/ኢሠፓ መንግሥት ፍትሕና ዳኝነት በተጓደለበት ሥርዓት ተጨፍልቀው በመገዛትና በመተዳደራቸው ምክንያት ከፍተኛ ቅሬታና ቅራኔ በዳኞች ውሳኔ አሰጣጥና በፍርድ ቤቶች አደረጃጀት ላይ መኖሩን በመገንዘብ፣ በተለይ ባለፉት አሥራ ሰባት ዓመታት የደርግ/ኢሠፓ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመጣስ፣ በመድፈር ከሕግና ከፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓት ውጪ በሆነ መንገድ ልዩ ልዩ ፍርድ ቤቶችን በመፍጠርና የፖለቲካ ሰዎችን በዳኝነት ሥራ በመመደብ በመንግሥት የአስተዳደር ተፅዕኖና በቀጥታ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ትዕዛዝ ዳኞች ውሳኔ እንዲሰጡ በማድረግ ፍትሕ የተጓደለበት የዳኝነት አሰጣጥ መፈጠሩን በማወቅ›› ብሎ፣ በአዋጁ ዋና ይዘት ውስጥ ደግሞ ከሌሎች መካከል የዳኞች አስተዳደር ሽፋንን ማለትም የተፈጻሚነት ወሰንን አሰፋ ሲባል፣ እንዲያውም ቀነሰ፡፡ በዚህ አዋጅ ቁጥር 23/84 ‹‹ማንኛውም ዳኛ ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ጉባዔው ሳይፈቅድ አይያዝም፣ በወንጀልም አይከሰስም›› በማለት ደርግም ቢሆን ቀፈፈኝ ሳይል የጻፈውን፣ እንዲያውም ደርግ ራሱ ለመጀመርያ ጊዜ ያስተዋወቀውን ድንጋጌ ‹‹ይለፍ›› ብሎ አፀደቀ፡፡

ከአዋጅ ቁጥር 24/1988 በሥራ ላይ መዋል ማለትም ከየካቲት 7 ቀን 1988 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ ድንጋጌ የዳኞች ልዩ መብት፣ ‹‹ያለ መከሰስ መብት›› የማይፈር መብት ከኢትዮጵያ የዳኝነት አስተዳደር ታሪክና ህልውና ውስጥ ተሸንቀጥሮ ተደፋ፡፡ በኢሕአዴግ፡፡

በዚህ ምክንያት የዳኞች ልዩ መብት ጉዳይ ይህን ያህል ጊዜ ተዳፍኖ የቆየው ከኢሕአዴግ ወይም ከሪፐብሊኩ የፖሊሲ ምርጫ ይልቅ፣ እጅግ በጣም ዘርፉን ተጭኖ እስከ ዛሬ ድረስ ‹‹. . . ውሾን ያነሳ . . . ›› ዓይነትና የዚያ ልክ የማይናገር ጉዳይ ሆኖ የቆየው በዳኞችና በፍርድ ቤቶች ካድሬዎች ጥናትና ‹‹ታማኝነት›› ምክንያት መሆኑ ብዙ ሳይቆፈር ሊጋለጥ የሚችል ደባ ነው፡፡

ይህ ጉዳይ ዛሬ አደባባይ ወጥቶ መነጋገርያ ሊሆን የቻለው በቅርቡ በወ/ሮ መዓዛ መሪነት እየተካሄደ ባለው የፍርድ ቤቶች ሕጎች ማሻሻያ መድረክ ይልቅ፣ ሪፖርተር ጋዜጣ በመጋቢት 25 ቀን 2011 ዓ.ም. (የረቡዕ) ዕትሙ ‹‹በፖሊስ ላይ የቅጣት ውሳኔ በመስጠታቸው የታሰሩት [የአማራ ክልል የሞጣው ወረዳ] ዳኛ ጉዳይ ዳኞችን ሥጋት ውስጥ ከትቷል››፣ በአማራ ክልል ዳኞች ያለ መከሰስ መብት የላቸውም የሚለው ዜና በመውጣቱ ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው፡፡ በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከየትኛውም ተፅዕኖ ነፃ ነው ይላል፡፡ እንዲያም ሆኖ የዛሬ ዓመት 25 ዓመት የሚሞላውን ‹‹የወርቅ ኢዮቤልዩ›› ውን የሚያከብረውን ሪፐብሊክ ያቋቋመው ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ በዋለበት በዚያን ያህል ዘመን፣ ከፍርድ ቤት ጋር ክፉ ቀን ያገጣጠማቸው ሰዎች በምሬት እንደሚመሰክሩት፣ ባለፈው አንድ ዓመት የመጀመርያዎቹ አስገራሚ ወራትም እንዳረጋገጡት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ፍርድ ቤቶች ይህን የመሰለ የውርደት አዘቅት ውስጥ ገብተው አያውቁም፡፡ እንዲህ ያለ የአገር ማፈሪያም ሆነው አልታዩም፡፡

ማንኛውም ዳኛ ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ጉባዔው ሳይፈቅድ አይያዝም፣ በወንጀልም አይከሰስም የሚለው ድንጋጌ፣ ከኢትዮጵያ የሕግ መጽሐፍ ውስጥ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ (እስካሁን ድረስ) በመውጣቱ፣ የእንደራሴዎችን ማለትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ያለ መከሰስ መብት በቀላሉና እንደ ቀልድ ማንሳት የማይሳነውን መንግሥት›› አቅምና ከሕግ በላይ የመሆን ችሎታ ላየ ኖረ አልኖረ ልዩነት የለውም ሊያሰኝ ይችላል፡፡ ላይ ላዩን ሲታይ እንዲያ ቢመስልም ዳኞችንና የዳኝነት ሥርዓቱን ‹‹የማስመሰል ችሎታ›› እንኳን ያዋረደ አንደኛው መሣሪያ ይኼው ነበር፡፡ የዳኞችን ነፍስ/ህሊና በማስመሰል ሥለት የገዘገዘው፣ ሽባ ያደረገው፣ ከሽባነትም በላይ የመንግሥት የፓርቲ የቅርብ አለቃ ንብረት ያደረገው፣ በመዝገብ ላይ በችሎት ውስጥ የሕጉንና የሥርዓቱን ፊት ለፊት ተናግሮ የመኖር ክብርን የገፈፈው የዳኞችን የዝምታ፣ የምንተዳዬና የማረጥረጥ ኑሮ ውስጥ የዘፈቀው፣ ከሌሎች መካከል እንዲህ ያሉ ድንጋጌዎችን መፋቅ የመቻል የፖለቲካው ተፅዕኖና ተራ ንቀት ነው፡፡

ጉዳዬን ከመቋጨቴ በፊት ከ34 ዓመት ጀምሮ በየአጋጣሚው፣ አጋጣሚውን ሁሉ እየፈለግሁ ስለው የነበረውን፣ እያነሳሁ እየጣልኩ በምሳሌነት የማቀርበውን፣ አንድ የአገራችንን ‹‹የነፃ ፍርድ ቤት›› የተጻፈ ሕግ ምሳሌ ደግሞ ላንሳ፡፡

አገራችን የመጀመርያውን ‹‹ዕርዳታና ማቋቋሚያ ኮሚሽን›› ሕግ ስታወጣ ለኮሚሽኑ አደጋውን፣ ዕልቂቱን፣ ድንገተኛነቱን፣ አስቸኳይነቱን ይመጥናል የተባለ ከፍተኛና ልዩ ሥልጣን ሰጠች፡፡ ኮሚሽኑ ችግሩ የደረሰበትና ጉዳዩ የሚመለከተው ክፍለ አገር/የአገር ክፍል አደጋ የደረሰበት (Disaster Area) ተብሎ እንዲታወጅ ለመንግሥት ሐሳብ የማቅረብ ሥልጣን ተሰጠው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ይህንን ክፍለ አገር በቀጥታ የማስተዳደር፣ እንዲሁም ማናቸውም ተቃራኒ ሕግ ቢኖርም እንኳን ተግባሩን ለማከናወን አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በማናቸውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ንብረት፣ በጀትና ማናቸውም መሣሪያ የመጠቀምና አስፈላጊ ሲሆን² በእነዚህ ሠራተኞች ላይ የሥነ ሥርዓት ዕርምጃ መውሰድ ሥልጣን ሁሉ የኮሚሽኑ ሆነ፡፡

የሚገርመው ይህ አይደለም፡፡ የሚገርመው በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን መጨረሻ ላይ፣ ነገር ግን በዚሁ የንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ‹‹የፍትሕ ህዋስ›› ማዕቀፍ ውስጥ በወጣው በዚህ ሕግ መሠረት፣ ‹‹የመንግሥት መሥሪያ ቤት›› የማለት ትርጉም ግን በጭራሽ፣ በጭራሽ ፍርድ ቤቶቻችን አይጨምርም ተብሎ በአዋጅ ተነገረ፡፡ የወሎ ጠቅላይ ግዛት የተፈጥሮ አደጋ የደረሰበት ክፍለ አገር መሆኑን ለማሳወቅ በወጣው አዋጅ ጭምር፡፡

እና ድሮ ድሮ ፍርድ ቤቶች ከእነ በጀታቸው፣ ከእነ ሠራተኞቸው፣ ከእነ መሥሪያዎቻቸው ይህን ያህል ክብር፣ ወግና ማዕረግ ነበራቸው፡፡ ግፋ ቢል ወርቁ ይጠፋል እንጂ፣ ‹‹ሚዛኑ››ስ በተለይ በሕግ ደረጃ ተዘንግቶ፣ ጠፍቶ አያውቅም፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡.

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...