የሲቪክ ማኅበራትን ገድቦና ሰንጎ እንደቆየ የሚነገርለት አዋጅ በአዲስ ተተክቷል፡፡ አዲሱ አዋጅ ነባር ተፅዕኖዎችን በማንሳት ማኅበራት ሥራቸውን በነፃነት እንዲተገብሩ ዕድል ይሰጣቸዋል የሚል እምነት አሳድሯል፡፡
የሲቪክ ማኅበራት በመጪው አገር አቀፍ የፖለቲካ ምርጫ ላይ ተሳትፏቸው እንደሚጎላ ስለሚታመን፣ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ምክክር መጀመሩም የሲቪክ ማኅበራትን ሚናና አስፈላጊነት ሊያመላክት ይችላል፡፡
እስካሁን በነበረው አዋጅ ሲሠሩ የቆዩ በርካታ ማኅበራት እንዳሉ ሆነው፣ አዳዲስ የሲቪክ ማኅበራትም እንደሚፈጠሩ ይጠበቃል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ለመሥራት የሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ተቋማትና ማኅበራት ሕዝብ በማንቃትና ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ የሚጠብቃቸው ሥራ የተበራከተ እንደሚሆን ዕሙን ነው፡፡ አዲሱ አዋጅ ሲወጣም ታሳቢ ያደረገው ዜጎችን ለማነፅና መልካም ትውልድ ለማፍራት ሲቪክ ማኅበራት ያለባቸውን ኃላፊነት ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶች ለሲቪክ ማኅበራት የትኩረት አቅጣጫ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ የግጭት መንስዔዎች የተባሉ ጉዳዮችን በመለየትና ለዜጎች ግንዛቤ በማስጨበጥ፣ ተመሳሳይ ድርጊት ቢቻል ዳግም እንዳይፈጸም ለመከላል የሚያስችል የሥነ ምግባርና የባህርይ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎችን የማከናወን ኃላፊነት የሚሸከሙ ናቸው፡፡ የሲቪክና የበጎ አድራጎ ድርጅቶችና ማኅበራት ጉዳት የደረሰባቸውን የመደገፍ፣ ጨዋ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር የማስተማር፣ መልካም አስተዳደር እንዲዳብር የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ተመን አይወጣለትም፡፡ የሙያ ማኅበራትም የሚወክሉትን የሙያ ዘርፍ ከማጎልበትና በሥራቸው የሚወከሉ አባላትን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር፣ ጎልቶ መታየት ያለበት በተደራጁበት የሙያ ዘርፍ በሥነ ምግባር የታነፀ ባለሙያ ማፍራትና ሥነ ምግባራዊና ሙያዊ ግዴታዎችን ተከትለው የድርሻቸውን የሚወጡ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው ቅን ዜጎችን ማብዛትም የሥራ ድርሻቸው ሊሆን ይገባል፡፡
በአሁን ወቅት ከምናየውም ከምንሰማውም መረዳት የሚቻለው በየአካባቢው ለሚነሱ ግጭቶች፣ በየጊዜው የምንታዘባቸው ሕገወጥ ተግባራትና ፅንፈኛ አመለካከቶች ምንጩን በማጤን፣ ከገንዘብና ቁሳዊ ሀብት ይልቅ ለአገርና ሕዝብ ብልጽግናና ደኅንነት ቅድሚያ የሚሰጥ ትልውድ አለመፈጠሩ ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ ይህ ጉዳይ መላ ካልተዘየደለትና መፍሰሻው ካልተቃና ለአገር ውድቀት ዋናው መነሻ ይሆናልና አዳዲስ የሲቪክ ማኅበራት ይህንን ጉዳይ ከግምት ያስገባ ሥራ እንዲሠሩ ማበረታታት ይገባል፡፡
ለጥፋት የሚቀሰቀሰው ተከታይና አጥፊ እንዳለው ሁሉ ለመልካም የሚያሰማራ፣ ለበጎነት የሚያበረታና የሚያነሳሳ አካል መኖር አለበት፡፡ ይህ አካል ክፋትንና ጥፋትን የሚሰብኩትን በልጦና ደፍቆ በመልካም ልባሞች ኢትዮጵያን መሸፈን መቻል አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የሲቪክ ማኅበራት መወጣጫ መሰላል ናቸው፡፡
ከወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ አንፃር በተሳሳቱ መረጃዎችና በስሜት በመነዳት የሚፈጸሙ ዘግናኝ ድርጊቶች ደርቀው እንዲቀሩ ሊያደርጉ በሚችሉ ሥራዎች ላይ ማኅበራቱ ያላቸው አገራዊ ፋይዳ ትልቅ ይሆናል፡፡ ለአገር መረጋጋት የሚሠሩ፣ ብሔራዊ ስሜትን የሚያጎሉ የሲቪክ ማኅበራት በጨዋነት እንዲሠሩ ማድረግ ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡ የቱንም ያህል የተጠራቀሙ ችግሮች የወለዷቸው ቢሆኑም፣ የትኞቹም ጥያቄዎች ከህልውና በላይ መሆን የለባቸውም፡፡ በአግባብና በሥርዓት እንዲስተናገዱ ለማድረግም ኅብረተሰቡን ስለሕግ፣ ስለማኅበራዊ ተሳትፎና በአጠቃላይ ስለ መብትና ግዴታዎች ዜጎች እንዲያውቁ፣ መከባበርና መተባበርን አንድነትና ኅብርን በሚያጠናክሩ ሥራዎች ውስጥ የሲቪክ ማኅበራትና ድርጅቶች በድርሻቸው ከፍ፣ ጎላ ብለው መታየት አለባቸው፡፡ የሲቪክ ማኅበራት አዋጅ ሲሻሻል፣ ጠንካራ ሆነው እንዲወጡና በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ሲደረግ፣ አገራዊ ጠቀሜታቸው ታስቦ ነው፡፡ ከእነርሱም የሚጠበቀው ውጤት ያለው የተግባር ሥራ ነው፡፡
ሥርዓት አልበኝነት የዚህች አገር ፈተና መሆኑ ሲታሰብ ችግሩ በኢኮኖሚው ውስጥም እንደተንሰራፋ ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚፈጠሩት የሲቪክ ማኅበራት ኢኮኖሚውን ሊያሳድጉ በሚችሉ ሥራዎች ውስጥ በመሳተፍ ኅብረተሰቡ የንግድና የግብይት ባህሉን እንዲያዳብር፣ ሕጋዊ ግብይትን እንዲያጎለብት በሚያደርጉ ሥራዎች ውስጥም እንድናያቸው እንሻለን፡፡
ሕገወጥ ንግድ ለአገር አደጋ መሆኑ እየታየ እንዲሁ መታለፍና ዝም መባል የለበትም፡፡ ዜጎች ከሕገወጥ ንግድ ራሳቸውን እንዲያርቁ፣ ሕገወጥ ንግድ በአገርና በግለሰብ ደረጃ ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት የሚያሳስቡ ማኅበራት ሊኖሩን ይገባል፡፡ በሕገወጥነት ሰበብ የሕዝብ ጤናና ደኅንነት አደጋ ላይ ሲወድቅ ይህንን በሚያደርጉት ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰብንና መንግሥትንም ማስገደድ አለባቸው፡፡ ጉዳይ ለማስፈጸም ጉቦ ካልተሰጠ የማይቻልበት አገር ውስጥ እንገኛለን፡፡ ከመሥሪያ ቤት ዘበኛ ጀምሮ እስከ የበላይ ኃላፊ ያለ ‹‹ሻይ መጠጫ›› የማይሠሩ፣ እንደ ሕዝብ ስልክ ሳንቲም ካልጎረሱ የማይሠሩ ሰዎችን አደብ ማስገዛትና አመለካከታቸውንም መቀየር ያስፈልጋል፡፡ አገልግሎት ማግኘት መብቱ መሆኑን እያወቀ ገና ለገና በሚገጥመው ውጣ ውረድ ሳቢያ ጉቦ ሰጥቶ መገላገል የሚመርጠው በርካታ ነው፡፡
ከዚህ ይልቅ ዋጋ በመክፈል ለእሱ ባይሆንለት እንኳ ሌሎች መሰሎቹና የነገ ልጆቹ ከዚህ ዓይነቱ ውጣውረድ እንዲድኑ መስዋዕትነት መክፈል እንደሚጠበቅበት ማስተማር ይገባል፡፡ ትራፊክ እንዳይቀጣው ጉቦ ይከፍላል፡፡ መታወቂያ ለማሳደስ ሔዶ ማኅተም የለም፣ ወረቀት አልቋል እያሉ ኪሱን የሚቀላውጡ ለማዳ ጉቦ በሎችን፣ የተፈቀደለትና የተመራለትን ደብዳቤ አግተው ‹‹በእጅህ ና፣ በእግር ብቻ አትምጣ›› የሚሉ ዓይናውጣዎችን ለመቆንጠጥና ለማረቅ የሚቻለው እምቢ ባይ፣ ዋጋ ከፋይ ሕዝብ ሲኖር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በማኅበራት ጉትጎታና ትምህርት ጭምር የሚመጣ የባህርይ ለውጥና ለዚህ ይበርቱ፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች ዜጎች መብትና ግዴታቸውን አደበላለቀው የሕግ የበላይነትን ለመፈታተን የሚሄዱበት መንገድ አግባብ አለመሆኑን የሚያመላክቱ ግንዛቤ ማስጨበጨዎችን በጥንቃቄና አግባብ ባለው መልኩ እንዲሠሩ ማድረግን አጀንዳቸው የሚያደርጉ ተቋማት ያሻሉ፡፡ ሕግ ከምንም በላይ መሆኑን ማስተማር ካልተቻለ ‹‹በሕግ አምላክ›› ሲባል የሚደነግጥ ሰው መፍጠር አይቻልም፡፡
የአንድ አገር መኖር ምሰሶው ኢኮኖሚው ነውና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ኅብረተሰቡ ሚና ምን መሆን እንዳለበት የሚያስተምሩ ተቋማት ከሌሉን ችግራችን ይበዛል፡፡
ዜጎች ግብር የመክፈል ባህላቸውን እንዲያዳብሩ ከተፈለገ፣ በዚህ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማኅበራት ወሳኝ ሚና ሊኖራቸው ይችላል፡፡
ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠርና በሕግና በሥርዓት የሚሠራ የንግድ ኅብረተሰብ እንዲኖርን በማድረጉ ረገድ ሲቪክ ማኅበራት መሥራት ያለባቸው ሥራ ይኖራል፡፡ የሸማቾች ችግር ዘርፈ ብዙ የመሆኑን ያህል ያለውን ችግር በደንብ በማሳየት የመፍትሔ አቅጣጫ ሊጠቁሙ የሚችሉ ማኅበራት ኖረው ማገዝ እስካልቻሉ ሕገወጥ ንግድን በዘመቻ ብቻ ለማስቆም አይቻልም፡፡
የዜጎች መብት ምን ድረስ እንደሆነ፣ መብቱን በምን አግባብ መጠቀም እንዳለበት፣ ከሕግ ውጪ ሲሆን በሕግ ሊወሰድበት የሚችለውን ዕርምጃ ማመላከት የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነውና ስለመልካም ዜጋ ማፍራት ስናወራ ኃላፊነት ከሚጣልባቸው አካላት መካከል የሲቪክ ማኅበራት ተጠቃሾች ይሆናሉ፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ነገር ሲታሰብ ሲቪክ ማኅበራት ራሳቸውን ችለው ለመንቀሳቀስ የኅብረተሰቡ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከልብ መሥራታቸውም ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ቀደም በአንዳንድ ሲቪክ ማኅበራት ይታይ እንደነበረው እንዲሠሩ ከተፈቀደላቸው ውጪ በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ማኅበራቱን ለሚፈልጉት ዓላማ ሊያውሉ ከሚችሉ አካላት ራሳቸውን መጠበቅ ግድ ይላቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ጨዋ ተቋማት እንዲሆኑ ያስፈልጋል፡፡ ከቀደሙ ልምዶች መታዘብ እንደምንችለው አንዳንድ የሲቪክ ተቋማት የሚያገኙትን ገንዘብ ለግል መጠቀሚያ በማድረግ ተቋማቱን እንደ ጥቅም ማግኛ አለማድረጋቸውን ማረጋገጫ ሊሰጡ ይገባል፡፡ የሲቪክ ማኅበራት የግለሰቦች መጠቀሚያ አለመሆናቸውን መፈተሽም ግድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ዛሬ እንደ አገር ለገጠመን ችግር አንዱና ቁልፉ ነገር በሥነ ምግባር የታነፀ ዜጋ ለመፍጠር የተሠሩ ሥራዎች አለመኖራቸው ነውና ይህንን ክፍተት ለማጥበብ አሁን በሁሉም ዘርፍ ጠንከር ያለ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ዜጎች ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ሕግ ለማስከበር የሚወስደው ዕርምጃ ጭምር የት ድረስ ሊሄድ እንደሚችል ሁሉም እንዲያውቅ ሲቪክ ማኅበራት ሊኖሩን ይገባል፡፡ ምክንያቱም መልካም ዜጋ ለመፍጠር መንግሥት ብቻውን ሊወጣው የማይችል በመሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ኃላፊነት አለባቸው የምንላቸው ሲቪክ ማኅበራት ግን ለሌሎች ለመትረፍ እነርሱም ጨዋ አገልጋይና ንፁህ እጅ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በእርግጥም ያለውን ችግር ተገንዝበው አግዛለሁ ብለው የሚያምኑ እንጂ ሕዝብን በማስተማር ስም የሚባልጉ መሆን እንደሌለባቸው ግን መታወቅ አለበት፡፡ በተለይ በጠባብ አመለካከት የከሸፉ እንዳይሆኑ መጠንቀቅም ይገባል፡፡