የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ የገንዘብ ኢንዱስትሪ ውስጥ በማገልገል ጉምቱ ከሚባሉ የፋይናንስ ባለሙያዎች መካከል አንዱ በሆኑት በአቶ ለይኩን ብርሃኑ ስም የሚሰየም ቅርንጫፍ ሊከፍት ነው፡፡
ባንኩ በአቶ ለይኩን ስም የሚከፍተው ቅርንጫፍ ከእስካሁኑ የባንኩ ሒደት የሚለይ አገልግሎት በሴቶች ሠራተኞቹ በኩል ይፋ ያደርጋል፡፡ ሴቶች ሠራተኞች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡበት ይህ ቅርንጫፍ፣ በአቶ ለይኩን ስም እንዲጠራ ተወስኗል፡፡
ቦሌ አትላስ ሆቴል አካባቢ አሌክሳንድርያ ሆቴል ግቢ ውስጥ ለአገልግሎት ይበቃል የተባለው ‹‹ለይኩን ብርሃኑ ቅርንጫፍ›› ሰኞ፣ ሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ተመርቆ ሥራ እንደሚጀምር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
አቶ ለይኩን ብርሃኑ በኢትዮጵያ የገንዘብ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ43 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በሥራ አስኪያጅነት ስለመምራታቸውም የታሪክ ማኅደራቸው ይገልጻል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በመሆን ካገለገሉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ለይኩን፣ አዋሽ ባንክ ከተቋቋመ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በመቀላቀል የባንኩ የመጀመርያው ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ እንደቆዩና ከፕሬዚዳንትነት እስከተሰናበቱበት ጊዜ ድረስም በዚሁ ባንክ ውስጥ ማገልገላቸው ይታወሳል፡፡