ቁጥራቸው 70 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ቀይ ባህርን አቋርጠው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያና የመን ለመሻገር ሲጓዙ፣ ጀልባ በመስጠሙ ሕይወታቸው ማለፉ ታወቀ፡፡ ሕይወታቸው ካለፈው ወጣቶች ውስጥ 60ዎቹ ከትግራይ ክልል አፅቢ ወንበርታ ወረዳ የተነሱ እንደሆኑ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ጀልባው የተገለበጠው ከሳምንት በፊት መጋቢት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. መሆኑን፣ 40 የሚሆኑት ሟቾች ቤተሰቦች መርዶውን መስማታቸውን የትግራይ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ባወጣው የሐዘን መግለጫ አረጋግጧል፡፡ ቀሪዎቹ አሥር ኢትዮጵያውያን ከየት አካባቢ እንደሆኑ አልታወቀም፡፡