የኢሕአዴግ አራቱ ብሔራዊ ድርጀቶች የምክር ቤት አባላት በዝግ የሚያደርጉትን ስብሰባ ቀጥለዋል፡፡ ኢሕአዴጎች እንደተለመደው በአንድነት መክረውና ዘክረው የሚያጠናቅቁት ስብሰባ እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ መገንዘብ ያለባቸው ጉዳይ፣ አሁንም በአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ከየትኛውም ስብስብ በላይ መሆኑን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ልዩነቶቻቸውን አጥብበው፣ ኢትዮጵያ እጃቸው ላይ እንዳትፈረካከስና የታሪክ ተጠያቂ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ ‹‹የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል›› እንደሚባለው፣ በመሀላቸው በሚስተዋለው ሽኩቻና ትንቅንቅ የአገር ህልውና ሥጋት ላይ እንዳይወድቅ የብዙዎች ፍርኃት ነው፡፡ ይህንን ፍርኃት ተጋርቶ የታሪክ ተጠያቂ አለመሆን ይመረጣል፡፡
እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ቁምነገር፣ ኢሕአዴግ የተጀመረው ሽግግር ሳይሳካ በየፊናው ተበታተነ ወይም ግንባሩን አፍርሶ ተለያየ ማለት ቀውስ መፍጠር እንጂ ዕርባና እንደማይኖር ነው፡፡ በበርካታ ችግሮች ምክንያት በሁሉም ጉዳዮች መስማማት ላይኖር ቢችልም፣ ዋና ዋና በሚባሉ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ግን የጋራ አቋም መያዝ የግድ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ለአገር ዘላቂ ሰላምና ህልውና ሲባል፡፡ የአገርን ህልውና ከድርጅት ፍላጎት በታች በማድረግ ዘራፍ ማለት በሕዝብ ላይ መቆመር ነው፡፡ አሁን የሚያዋጣው ምክንያታዊ ሆኖ ስሜትን መቆጣጠር ነው፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚወስዳት ጎዳና ድረስ ተባብሮ ማድረስ ዋና ዓላማ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለ ፍላጎት አገርን ማጥ ውስጥ ከመክተት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ጎረቤት አገሮችን በማስተባበር አካባቢውን ከግጭት ነፃ በማድረግ ወደ ዕድገትና ብልፅግና መጓዝ ሲገባት፣ በችግር ላይ ተጨማሪ ችግሮችን እየደራረቡ የቀውስ የስበት ማዕከል ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ የሶማሊያና የደቡብ ሱዳን ትርምስ አልበቃ ብሎ ጎረቤት ሱዳን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እየተከናወነባት፣ እንደ አገርና ሕዝብ አንድ ሆኖ መቆም አለመቻል የማይወጡት አደጋ ውስጥ ይከታል፡፡ ከኢሕአዴግ ውስጣዊ ችግሮች በተጨማሪ ሌሎች አካላትም ለሰላም መደፍረስ ጠንቅ እየሆኑ፣ በንፁኃን ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው ሰቆቃ ይታወቃል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚያዝበትን ሥልጡን ጎዳና በመተው፣ ሁሉንም ነገር በስሜታዊነት የፀብና የግጭት ምንጭ ማድረግ መቆም አለበት፡፡ ኢሕአዴግ ከሥልጣንም ሆነ ከክብርና ከዝና በላይ የሆነች አገር እንዳለች ማመን አለበት፡፡ ዘመን ያለፈባቸውን ጎሰኝነትና ነውጠኛ ድርጊቶችን በመተው፣ ሙሉ ትኩረቱን አገር ለማዳን መረባረብ አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻለ የታሪክ ተጠያቂ ይሆናል፡፡
ኢሕአዴግ ላለፉት 28 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየ ዕድሜ ጠገብ ድርጅት ነው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የሠራቸው መልካም ነገሮች ያሉትን ያህል፣ በከፍተኛ ደረጃ የፈጸማቸው በደሎችና ስህተቶች ደግሞ የገዘፉ ናቸው፡፡ ከውስጡ የወጡ የለውጥ ኃይሎች አመራር መስጠት ሲጀምሩ ሕዝብ ከፍተኛ ድጋፍ የሰጣቸው፣ በእነሱ አሸጋጋሪነት ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትገባለች በሚል እምነት ነው፡፡ ‹‹የፈሰሰ ውኃ አይታፈስም›› እንደሚባለው፣ ካሁን በኋላ ወደኋላ የሚያስመልስ ምንም የቀረ ጉዳይ ስለሌለ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የሚሳተፍበትና በእኩልነት ተጠቃሚ የሚሆንበት ሥርዓት መገንባት ነው የሚያዋጣው፡፡ በአፍ ወለምታም ሆነ ወይም ሆን ተብሎ የተፈጸመ ስህተት ካለም በመተራረም፣ ለአገር ዘላቂ ሰላምና ህልውና ሲባል ከዚህ ስብሰባ ተስፋ ሰጪ ነገር ይዞ መውጣት ይጠቅማል፡፡ ‹‹የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል›› እንደሚባለው በሐሰት ተሸነጋግለው ከስብሰባ አዳራሽ ከወጡ በኋላ፣ ሕዝቡ ውስጥ ግጭት በመቀስቀስ የንፁኃን ደም ማፍሰስ ነውር ነው፡፡ ሕዝብ ይህ ዓይነቱ አሳፋሪ ሒሳብ ማወራረድ ሰልችቶታል፡፡
በሌላ በኩል ኢሕአዴግ እርስ በርሱ ሲተራመስ እናተርፋለን ብለው የሚያስቡ ካሉም ተሳስተዋል፡፡ በአጋጣሚ የወደቀ ሥልጣን እጃችን ይገባል በማለት በተለያዩ መንገዶች የሚያደቡ፣ ይህንን በሚገባ ቢያስቡበት ይበጃል፡፡ ኢትዮጵያ ሥልጣን ከአንዱ ወደ ሌላው በኃይል ወይም በአጋጣሚ የሚተላለፍባት ከሆነች፣ ያለ ምንም ጥርጥር ወደለየለት ሥርዓተ አልበኝነት ነው የሚገባው፡፡ የፖለቲካ ቁማርተኝነት ካርድ መምዘዝ የሚፈልጉም ይጠንቀቁ፡፡ የፖለቲካ ቁማር አሸናፊም ተሸናፊም አይኖርበትም፡፡ ሁሉንም ነገር በስሜታዊነት መደገፍም ሆነ መቃወም መታወቂያቸው የሆኑ ወገኖችም ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ስሜታዊነት ደመነፍሳዊ እንጂ ህሊናዊ ባለመሆኑ አገርን ለጉዳት ይዳርጋል፡፡ የአገርን ህልውና እንደ ዘበት በማየት የወደቀ ሥልጣን ለማግኘት የሚያንዣብቡትን ማጀብም ትርፉ ፀፀት ነው፡፡ የተገኘውን ነገር ሁሉ የፖለቲካ ቅመም እያደረጉ በነገር መቋሰልም ሆነ፣ ጠብ ያለህ እያሉ አገሪቱን መነታረኪያ ማድረግ ጤነኝነት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የጋራ የሆነ ጉዳይ የሌለ ይመስል በሁሉም ነገር መጋጨት መዘዙ የከፋ ነው፡፡ ይልቁንም ኢሕአዴግ መስመር ይዞ አገሪቱን ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲያሲዛት ድጋፍ ማድረግ፣ ለአገር ትልቅ ውለታ እንደመዋል ይቆጠራል፡፡ ከአገር በላይ ምንም የለምና፡፡
ከኢሕአዴግ ሠፈር እንደሚሰማው በአሁኑ ጊዜ ትልቁ የሥርዓቱ አደጋ፣ ጽንፈኛ ብሔርተኝነትና የወጣቶች ሥራ አጥነት ነው፡፡ የብሔር ጽንፈኝነት የአገር ደኅንነት አደጋ መሆኑ ከታወቀ ሰነባብቷል፡፡ ከዚህ ችግር ውስጥ ለመውጣት ግን ብልኃት ያስፈልጋል፡፡ ብልኃት የሚገኘው ደግሞ ሲተባበሩ ብቻ ነው፡፡ በአፍ ሌላ በልብ ሌላ ከሆኑ ግን የተለመደው የሴረኝነት አዙሪት ውስጥ ይገባል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን በማስተካከል ሁሉንም የሚያግባባ ዓውድ መፍጠር የግድ ይሆናል፡፡ ይህ ዓውድ አገሪቱንም ሕዝቧንም ወደ ትክክለኛው መስመር የሚያስገባ፣ እኩልነት፣ ፍትሕና ነፃነት የሚያጣጥሙበት ሥርዓት በጋራ ለመገንባት የሚያስችልና ሰላማዊ መሆን ይኖርበታል፡፡ የአንድ ወገን የበላይነት ሳይሆን፣ በመከባበርና በእኩልነት የሚኖሩበት ሥርዓት ለመፍጠር መንገዱን መያዝ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ተነሳሽነቱ ሲኖር እንኳን ለኢትዮጵያ ወጣቶች፣ ለጎረቤት አገሮች ጭምር ሥራ መፍጠር ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያን በሥርዓት መምራት ከተቻለ ተዓምር መሥራት የሚችል ቅን፣ ትጉህ፣ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ አለ፡፡ ይህን ታሪካዊ ሕዝብ ችግር ውስጥ መጣል ግን የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ኢሕአዴግ መጠንቀቅ ያለበት ከታሪክ ተጠያቂነት ነው፡፡