የኢሕአዴግ ምክር ቤት ከሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ስብሰባ ላይ ነው፡፡ ከኢሕአዴግ አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች የተውጣጡት የምክር ቤት አባላት እየተሳተፉበት ያለው ይህ ስብሰባ፣ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሐሳብ ልዩነቶች የሰፉበት እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡
ሰሞኑን የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያወጣው መግለጫ በኢሕአዴግ ውስጥ ያለው ግንኙነት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለየ ገጽታ መያዙን አመላካች እንደሆነ ተስተውሎበታል፡፡ ሕወሓት ከሌሎቹ አባል ድርጅቶች በተለየ ሁኔታ የውህደት ዕቅዱን ያልተቀበለ ከመሆኑም በላይ፣ ኢሕአዴግ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት የለውም ሲል ደምድሟል፡፡
የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በሰሞኑ መግለጫው፣ ‹‹በመሠረቱ የፓርቲ ውህደት ጥያቄ በተለያዩ ጊዜያት ሲነሳ የነበረና በጥናት እንዲመለስ አቅጣጫ ተቀምጦ እንደነበር ግልጽ ነው። ይህ አቅጣጫ የተቀመጠው ደግሞ ኢሕአዴግ ጤናማ በነበረበት ወቅት፣ በመሠረታዊ የድርጅቱ እምነቶችና መስመር ላይ ጽኑ እምነት በነበረበትና ምንም መሸራረፎች ባልነበረበት ወቅት ነው። ይሁን እንጂ የደፈረሰና ጉራማይሌ አመለካከትና እምነት የያዘ ኢሕአዴግ አይደለም ለውህደት፣ ከዚህ ከቀደም ለነበረው አደረጃጀቱም የሚሆን የአስተሳሰብና ተግባር አንድነት የሌለው ኢሕአዴግ ነው አሁን ያለው። በሁሉም መሠረታዊ ጥያቄዎች የፕሮግራም፣ የስትራቴጂና የመለያ እምነቶች በእህት ድርጅቶች መካከል አንድ የሚያደርግ አመለካከትና እምነት በሌለበት፣ ሁሉም ወደ ተለያየ አቅጣጫዎች በሚላጋበት ውህድ አንድ ፓርቲ ሊታሰብ የሚችል አይደለም፤›› ብሏል።
በሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ መሠረት አንድ የሚያደርግ የጋራ አመለካከት በሌለበት ወቅት ድርጅት እንደ ድርጅት ህልውና ሊኖረው አይችልም። ‹‹አንድ የሚያደርግ አመለካከት በማይኖርበት ጊዜ ድርጅታዊ መበታተን እንጂ ውህደት ሊመጣ አይችልም። ስለዚህ ከውህደት በፊት፣ ለመዋሀድ የሚያዋህዱንን ነገሮች ልናስቀምጥ ይገባል፤›› ይላል፡፡
‹‹ከሁሉም በፊት ጽኑና ግልጽ መለያ መስመር አጥንተን ልንይዝ ይገባል፤›› የሚለው መግለጫው፣ ኢሕአዴግ እንዲበተን ከሚያደርጉ የተዛቡ አመለካከቶች የሚለይ አጥር በግልጽ አስቀምጦ ግልጽና ጽኑ ሥርዓት አስቀምጦ ብቻ ነው ስለውህደት መነጋገር የሚቻለው ሲል ያክላል።
የፓርቲዎች ውህደት በፍፁም ዴሞክራሲያዊ ሒደት ማለፍ ይኖርበታል የሚለው ሕወሓት፣ በሁሉም እህት ድርጅቶችና መላ አባላት ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች ሳይካሄዱ የሚፈጸም መሆን የለበትም በማለት፣ ‹‹ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ ኢሕአዴግ ስለውህደትና አንድ ፓርቲ መሆን ሊታሰብ የሚችል አይደለም። ከዚህ አግባብ ውጪ የሚኖር አማራጭ የተፈጠረው ችግር የሚያባብስ እንጂ መሠረታዊ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል በጽኑ እናምናለን፤›› በማለት መግለጫውን ያጠቃልላል።
በሌላ በኩል የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአጋር ድርጅቶችና የሲቪክ ማኅበራት ማስተባበሪያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ውህደቱ ከልብ በሚቀበሉት ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡
ኢሕአዴግ ውህደት ሊፈጽም ነው ሲባል አራቱ ፓርቲዎች ከግንባርነት ወደ አንድ ወጥ ፓርቲነት በመምጣት አጋሮችንም ያካትታሉ ማለት ነው ብለው ከዚያ በኋላ ኦዴፓ፣ አዴፓ፣ ሕወሓትና ደኢሕዴን የሚባል ነገር ቀርቶ አንድ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።
ሕወሓት ውህደቱን ባይቀበለውስ ተብሎ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ፍቃዱ፣ ‹‹ይህ ነገር ተደጋግሞ ይጠየቃል። ሆኖም ይህ ለውጥ በሚመጣበት ጊዜ የአራቱም ብሔራዊ ድርጅቶች ሥራ አስፈጻሚ ጥሩ ትግል አድርጓል። በኢሕአዴግ ምክር ቤትም በተመሳሳይ ትግል ተደርጎበታል። በመጨረሻም በጋራ ውሳኔ በ11ኛ ጉባዔ የተቀመጠ ነው። የጥናቱንም የመጀመርያ ምዕራፍ (ፌዝ) በጋራ ማየት ተችሏል። በዚህ ሁሉ ሒደትም ሕወሓት እንደ ድርጅት ከውህደቱ እወጣለሁ የሚል አቋም አላሳየም። በእኛም በዚህ ላይ የታየ ምንም አዲስ ግምገማ የለንም። ሆኖም የተለያዩ ግለሰቦችና አንዳንዶችም በፌስቡክ ሊጠይቁ ይችላሉ። ውህደቱ ደግሞ ለሕዝብ የሚበጅ እንደመሆኑ በስምምነት የሚፈጸም ነው። እስካሁንም የመጣነው የትኛውም ድርጅት ቢሆን ሙሉ በሙሉ በስምምነት ነው። ከአጋሮች ጋርም በዚያው አግባብ የሚካሄድ ነው። የሚታረምና የሚስተካከል ነገር ሲኖርም በውይይት ነው የሚሆነው። ያም ሆነ ይህ ግን ማንኛውም ድርጅት በውህደቱ አግባብ ላይ ነፃ ፍላጎቱ የሚጠየቅ እንደመሆኑ፤ መዋሀድም ሆነ አለመዋሀድ መብቱ ነው። ስለዚህ ውህደቱ ከልብ በሚቀበሉት ተግባራዊ ይሆናል። ሕወሓት ውህደቱን ላይቀበል ይችላል የሚል ግምገማ ላይ ያልተመሠረተ ግምት ከወዲሁ ማስቀመጥ ግን ትክክል ነው ብለን እናምንም፤›› ብለዋል።
ስለዚህ ውህደቱ ከአራቱ ድርጅቶች ባለፈ አጋር የነበሩትም በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲወስኑ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት አቶ ፍቃዱ፣ ‹‹ውህደቱ አሁን የምንለውን አገራዊ አንድነት ትርጉም ባለው መንገድ ለማምጣት ሁሉም በእኩልነት የሚሳተፉበትና የሚወስኑበትን ዕድል ለመፍጠር ነው። ይህ ደግሞ ኢሕአዴግ ቀድሞ የነበረውን አቅም ለማጠናከርና የአጋሮቹንም አቅም ጨምሮ የበለጠ እንዲጠናከር የሚያስችለው በመሆኑ የሚተገበር እንደመሆኑ፤ ዘላቂና በመተማመን ላይ የተመሠረተ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመፍጠር ሒደትም ነው በማለት አስረድተዋል።
ምክንያቱን ሲገልጹም አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠር ሒደቱ አንድ ጠንካራ አገር የመፍጠር ሥራ መሆኑን፣ ይኼንን ዕውን የማድረግ ተግባር ደግሞ አንድ ጠንካራ ፓርቲ ዕውን ከማድረግ መጀመር ስላለበት ነው ብለዋል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ በሁሉም አባል ድርጅቶች መካከል የሐሳብ አንድነት ተፈጥሮ ወደ ውህደት የማምራቱ ጉዳይ እንደማይሳካ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በተለይ አዴፓ፣ ኦዴፓና ደኢሕዴን ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ውህደቱን ቢያሳኩም፣ ሕወሓት ግን በዚህ አቋሙ የውህደቱ አካል እንደማይሆን ግምታቸውን ይገልጻሉ፡፡ የአቶ ፍቃዱን ውህደቱን ከልብ በሚቀበሉት ተግባራዊ ይሆናል የሚለው አባባል ሁኔታውን በሚገባ ይገልጸዋል ሲሉም ከግምት ከፍ ያለ መሆኑን ያክላሉ፡፡