በድንገት ከኃላፊነታቸው የተነሱበት ምክንያት አልታወቀም
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን ለስምንት ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት የመሩት አቶ ዮናስ ደስታ ከሥልጣናቸው መነሳታቸው ታወቀ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለአቶ ዮናስ በጻፉት ደብዳቤ፣ ከሐምሌ 13 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ለአገር ላበረከቱት አስተዋጽኦ በማመስገን፣ ከሚያዝያ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸው እንዳነሷቸው አስታውቀዋቸዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ አቶ ዮናስ ከኃላፊነታቸው የተነሱበት ምክንያት አለመጠቀሱ ታውቋል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. የወጣው ደብዳቤ እንደ ደረሳቸው ለሪፖርተር የገለጹት አቶ ዮናስ፣ ‹‹ከሰባት ዓመታት በላይ ካገለገልኩበት ኃላፊነቴ እንድነሳ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የተወሰነውን ውሳኔ በአክብሮት ተቀብያለሁ፤›› ብለዋል፡፡
ወደ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በ28 ዓመታቸው የመጡት አቶ ዮናስ ገጸ ታሪካቸው እንደሚያሳየው፣ የኢትዮጵያ ቅርሶች ምዝገባና ቆጠራ ጥናትና ምርምር፣ እንክብካቤና ስትራቴጂካዊ ተከላ ላይ በመሪነት ሠርተዋል፡፡
በብሔራዊ ባህልና ቱሪዝም ፕሮጀክቶች መደብ (ፕላት ፎርም) በሊቀመንበርነት፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ቦርድ አባል፣ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ምሥራቅ አፍሪካን በመወከል በዓለም ቅርስ ኮሚቴ አባል በመሆን ለአራት ዓመታት፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ2016 የዩኔስኮ ኢንተር ገቨርንመንታል ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆነው ሠርተዋል፡፡
በዳይሬክተርነት ዘመናቸው ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ሦስት የማይዳሰሱ ቅርሶችን (መስቀል፣ ፊቼ ጫምባላላና የገዳ ሥርዓትን) በዩኔስኮ አስመዝግባለች፡፡ አምስት በሒደት ላይ ያሉም አሉ፡፡
አቶ ዮናስ ገዳን በማስመዝገባቸው የኦሮሞ አባገዳዎች ‹‹ኢፋ ገዳ›› የሚል ማዕረግ ሲሰጧቸው፣ ሲዳማዎችም ‹‹ካያሞ›› የሚል ማዕረግ ሰጥቷቸዋል፡፡
በቅርቡም የአፄ ዮሐንስ አራተኛ የሰውነት አካል ከሱዳን ለማስመለስ እንቅስቃሴ ጀምረው ነበር፡፡
የአቶ ዮናስ ከኃላፊነት መነሳታቸው ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራኑን ዶ/ር ሙሉጌታ ፍሰሐና አቶ አበባው አያሌውን በዋና እና በምክትል ዳይሬክተርነት መሾማቸው ታውቋል፡፡
አቶ አበባው የተተኩት፣ በግንቦት 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት ተሹመው ከወራት በኋላ ኃላፊነቱን በተውት አቶ ቃሲም ፌጤ ምትክ ነው፡፡
ስለቅርስ ጥናትና አጠባበቅ የወጣው አዋጅ ቁጥር 209/1992፣ ባለሥልጣኑ አንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብቻ እንደሚኖረው ቢደነግግም፣ ዓምና የተሰጠው የምክትል ዋና ዳይሬክተርነት ከአዋጁ ጋር እንደሚጋጭ አስተያየት ይሰጥበት እንደነበር ይታወሳል፡፡