Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት በህዳሴ ግድብ ላይ የተለየ አቋም የለኝም አለ

የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት በህዳሴ ግድብ ላይ የተለየ አቋም የለኝም አለ

ቀን:

ሱዳንን ለ30 ዓመታት ከመሩት ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር ላይ ሰሞኑን  ሥልጣን የተረከበው ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት፣ ከዚህ ቀደም የሱዳን መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ያደረጋቸውን ስምምነቶች እንደሚያከብር በማስታወቅ በተለይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የተለየ አቋም እንደሌለው ተገልጿል፡፡

ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በጄኔራል ጋላለዲን አል ሼክ የተመራ የልዑካን ቡድን አባላት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በሱዳን በተከናወነው የመንግሥት ለውጥና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም ከኢጋድና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ተነጋግረዋል፡፡

በተለይ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ባላት የጠበቀ ግንኙነት ምክንያት የልዑካን ቡድኑ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝቶ ተወያይቷል፡፡ የወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት አባል ጄኔራል ጋላለዲን በሱዳን ኤምባሲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የህዳሴ ግድቡን ጨምሮ ከዚህ ቀደም ሁለቱ ወገኖች ባላቸው ግንኙነት ላይ አንዳችም ዓይነት የተለየ አቋም እንደማይኖር አስታውቀዋል፡፡

- Advertisement -

ጄኔራሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተደረገላቸውን ትብብር አውስተው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የመንግሥት ለውጡን አስመልክተው ለሱዳን ሕዝብ ያስተላለፉት መልዕክት አዎንታዊና ገንቢ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በሱዳን የተከናወነውን የመንግሥት ለውጥ አስመልክተው፣ ‹‹ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ለውጡን መምራቱንና የሱዳን ሕዝብን ጥያቄ መስማቱን አደንቃለሁ፤›› ሲሉ በመልዕክታቸው ገልጸዋል፡፡

ከልዑካን ቡድኑ ጋር ተገናኝተው የተወያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ መንግሥታቸው ለሱዳን ሕዝብ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥልና ይህም በመከባበር ላይ የተመሠረተና ሉዓላዊነትን አክብሮ ጣልቃ ገብነትን ባስወገደ መንገድ ይሆናል ብለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የፕሬዚዳንት አልበሽር መንግሥት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተወገደ በኋላ፣ የወታደራዊ ምክር ቤት አባላት የመጀመርያውን የውጭ ጉዞ ያደረጉት ወደ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በአካባቢ ያላትን ተፅዕኖ እንደሚያመለክት የሚገልጹ አንድ ታዋቂ የፖለቲካ ተንታኝ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባላቸው ተሰሚነት ለወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤቱ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ ለማስገኘት እንዲቻል የታለመ ጉብኝት እንደሆነ ያምናሉ፡፡

ኢትዮጵያም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ወደ ግዛቷ የሚጎርፉ የጦር መሣሪያዎችን ለማስቆም፣ እንዲሁም ለሰላሟ ጠንቅ ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች የደኅንነት ሥጋቶችን ለመቅረፍ ልትጠቀምበት ትችላለች ሲሉ ግምታቸውን ያስረዳሉ፡፡ ወታደሮቹ ከየትኛውም አገር በፊት ሮጠው እዚህ ሲመጡ ጥቅምን በሚገባ ማሥላት ይገባል ሲሉም ያክላሉ፡፡ ምንም እንኳን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትን መደገፍ የማይገባ ቢሆንም፣ አንዴ ከሆነ በኋላ ግን በአካባቢው ትርምስ እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

ለሁለት ዓመታት ይቆያል የተባለው የሱዳን የሽግግር መንግሥት ከተለያዩ የፖለቲካና የሲቪል ማኅበራት ጋር ተከታታይ ውይይቶችን እንደሚያደርግ፣ በእነዚህም ውይይቶች ይመሠረታል የተባለውን የሲቪል መንግሥት ለማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች ይከናወናሉ ሲሉ ጄኔራል ጋላለዲን አስረድተዋል፡፡

ጄኔራሉ ይህን ይበሉ እንጂ በሱዳን ካርቱም ጎዳናዎች የሕዝብ ተቃውሞዎች የቀጠሉ ሲሆን፣ ወታደራዊ የሽግግር መንግሥቱ ሥልጣኑን ለሲቪል መንግሥት በአስቸኳይ እንዲያስተላልፍ እየጠየቁ ነው፡፡

የሽግግር መንግሥቱ ከተለያዩ አገሮች ድጋፎችን ያገኘ ቢመስልም፣ የአፍሪካ ኅብረት ግን ጠንካራ የሆነ ተቃውሞውን ገልጿል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፣ ወታደራዊ የሽግግር መንግሥቱ በሁለት ሳምንት ውስጥ የያዘውን ሥልጣን ለሲቪል መንግሥት እንዲያስተላልፍ፣ ይህን ማድረግ ካልቻለ ግን ሱዳንን ከአፍሪካ ኅብረት አባልነት እንደሚሰርዝ ከቀናት በፊት አስታውቋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...