በሔለን ተስፋዬ
የአካባቢው ፀጥታ መንፈስን ያድሳል፡፡ አየሩም ንፁህ ከምንም ነገር ጋር ያልተደባለቀ ነው፡፡ ቦታው እምብዛም ገጠር የሚባል እንዳልሆነ በቤቶች አሠራርና ባላቸው የኤሌክትሪክ ዝርጋታ መገመት አይከብድም፡፡ የነበርንበት መኪና መጓዙን ቀጥሏል፤ ተሳፋሪውም ስለቦታው ማውራቱን ተያይዞታል፡፡ መንገዱ ግን ጠጠር መሆኑ ጉዞውን አሰልቺና አድካሚ አድርጎታል፡፡ በጠጠር መንገድ ከተጓዝን በኋላ ጥቂት ደኑን ለሁለት ሰንጥቆ በሚያልፈው አስቸጋሪ አቀበታማ መንገድ ላይ ወጣን፡፡
ያገኙትን በጀርባቸው አዝለው አቀበቱን የሚያዘግሙ እናቶች፣ የታዘሉ ሕፃናት፣ በጭንቅላታቸው ውኃ የተሞላ ጀሪካን የተሸከሙ ጉብሎች ሲያልፉ ይታያል፡፡ ከሰዓታት ጉዞ በኋላ መናገሻ አምባ ማርያምና ጋራ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ደረስን፡፡
የጉብኝት ፕሮግራሙን ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ከኖርዌይ መንግሥት ጋር በመተባበር ነው፡፡
በኢትዮጵያ ገዳማት ዛፍ መትከል እንጂ መቁረጥ እንደ ነውር ይቆጠራል የሚሉት የኮሚሽኑ ዋና ዳይሬክተር አግደው ረዴ (ዶ/ር)፣ የጥንት አበውን አሰር በመከተል በመናገሻ አምባ ማርያምና ጋራ መድኃኔ ዓለም ገዳም ዛፍ በመትከል፣ ደን በመጠበቅ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት ከአካባቢው እንዳይጠፉ ከኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን ጋር እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹በወጣትነት ዘመኔ፣ ብዙ ዛፎች ስለነበሩ አውሬ እንዳይበላኝ እናትና አባቴ ተሸክመውኝ ነበር የሚያልፉት፤›› ያሉት አግደው (ዶ/ር) ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ አስጊ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር፣ የዓለም አቀፍ የአየር ንበረት ጠባይ ለውጥ ዋና ዳይሬክተር ጨምሮ ሌሎችም ስለ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተገኝተዋል፡፡
በመናገሻ አምባ ማርያምና ጋራ መድኃኔ ዓለም፣ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ሞገስ ኃይለማርያም እንደተናገሩት፣ ገዳሙ ለደኑ መጠበቅ ዋነኛ ነው፡፡ እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ ደኑ በገዳሙ ሥር እንደነበር አስታውሰው፣ በኋላም በጊዜው የነበሩት የገዳሙ አስተዳዳሪ የመንግሥትን ዕርዳታ ጠይቀው ደኑ እስካሁን እየተጠበቀ ይገኛል ብለዋል፡፡
የልማትና ክርስቲያን ተራድኦ ኮሚሽን ከያዛቸው ስድስት የደን ጥበቃ ፕሮጀክቶች አንዱ የመናገሻ አምባ ማርያምና ጋራ መድኃኔ ዓለም አንዱ መሆኑን ገልጸው፣ ኮሚሽኑ ደኑን አስመልክቶ ችግኝ በማፍላትና በመትከል እንዲሁም በመጠበቅ ለደኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡
‹‹የመናገሻ ደን ከ20 ጋሻ መሬት በላይ ሲሸፍን ለአካባቢው ነዋሪዎችም ሆነ ለሌሎች አካባቢ ሕይወት ነው፤›› የሚሉት አባ ሞገስ፣ ደኑ ለአዲስ አበባና አካባቢዋ የዝናብ ምንጭ ነው፡፡ ብዙ ተመራማሪዎች ወደ አካባቢው በመምጣትም ለመድኃኒትነት የሚጠቅማቸውን ወስደው እንደሚሄዱም አክለዋል፡፡
በደኑ ውስጥ ከ15 ያላነሱ ብርቅዬ እንስሳት ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አነር፣ ድኩላ፣ ሽኮኮ፣ ቆቅ፣ ዝንጀሮ፣ ጉሬዛና ሌሎችም የዱር እንስሳት በውስጡ አቅፏል፡፡ ከበርካታ ዓይነት አገር በቀልና የውጭ ዛፎች መካከል የሐበሻ ዛፍ፣ ወይራ፣ የፈረንጅ ፅድ፣ ባህር ዛፍ፣ ዝግባ፣ ጥቁር እንጨት፣ ግራር የመሳሰሉትን በውስጡ ይዟል፡፡
ቄስ ገበዝ ፀጋዬ ተክለ አረጋዊ ከልጅነታቸው ጀምሮ በገዳሙ እያገለገሉ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ስለ ደኑ ‹‹ደኑ ሕይወት ነው ለጤና ተስማሚ›› ነው ብለዋል፡፡
ቄስ ፀጋዬ እንዳሉት፣ በገዳሙ ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ ደኑን ይንከባከባሉ፣ ይተክላሉ፤ የወደቁትን ደግሞ ከጥቅም ያውሉታል፡፡ ደኑ ከዚህም ባለፈ ለገዳሙ ሞገስ ሰጥቶታል፣ የቦታው ታዋቂነትም በደኑ ምክንያት መሆኑን ቄስ ፀጋዬ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
የመናገሻ አምባ ማርያምና ጋራ መድኃኔ ዓለም ጥንታዊ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ በአካባቢው በተደረገ ቁፋሮ በርካታ ንዋየ ቅድሳት፣ ፅናዎች ተገኝተዋል፡፡ በቀድሞ ጊዜ ከክርስትና በፊት ይሰዋበት እንደነበረ፣ በ15ኛው ምዕት ዓመት በአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ግማደ መስቀሉ ወደ ግሸን ከመሄዱ በፊት ለሰባት ወር አርፎበት ከዚያም ወደ ግሸን አምባ እንደሄደ በታሪክ ይነገራል፡፡
በቤተ ክርስቲያን ያለው ደንም ከአፄ ዘርዐ ያዕቆብ በፊት እንደነበር፣ ከዚያም በኋላ የነበሩት ነገሥታት ደኑን በመጠበቅና በመንከባከብ ዛፍ ያስተክሉ እንደነበር የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪው አብራርተዋል፡፡ መናገሻ የተባለበትም ምክንያት ነገሥታቱ ቅብዓ ሜሮን የሚፈጽሙበት ስለሆነ ነው፡፡ መንግሥታቸው የፀና እንዲሆን፣ ለትውልድ ትውልድ ያስቀጥላል ተብሎ ስለሚታሰብ ቅብዓ ሜሮን በዚህ ቦታ ይፈጽማሉ ሲሉም አክለዋል፡፡
ከልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ከ70 ሺሕ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ 35 ሺሕ የሚሆኑት በደን የተሸፈኑ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከአንድ እስከ አራት ሺሕ ሄክታር የሚሸፍን ደን በውስጡ ሲይዝ የቤተ ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ፣ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚኖሩ ኅብረተሰቦች ደኑን በመጠበቅና በማስተዳደር ረዥም ታሪክ አላቸው፡፡
ኮሚሽኑ በ1964 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን ላለፉት 47 ዓመታት በምግብ ዋስትና በመልሶ ማቋቋም፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በጤና፣ በውኃ አቅርቦት፣ በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ብሎም ሌሎች ማኅበራዊ ኃላፊነቶች ላይ በስፋት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በተለይም ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ደን ልማትና የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች ላይ በሰፊው እየሠራ ሲሆን ለዚህም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ ግንዛቤ የማስጨበጥና ደኖችን የመንከባከብ ተግባር እየተከናወነ ነው፡፡
በዚህ ቅንጅታዊ ተግባራትም በ19 አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ጥብቅ ደኖች የመንከባከብና የሥነ ምኅዳር ጤና እንዲጠበቅ ለማድረግ ከሚመለከታቸው የመንግሥትና አጋዥ አካላት ጋር እየተሠራ ይገኛል፡፡
ከእነዚህም አካላት መካከል የኖርዌይ ቤተ ክርስቲያን ትገኝበታለች፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 16 ቀን 2018 በኢትዮጵያ የኖርዌይ ኤምባሲ አማካይነት የተመደበው 26.5 ሚሊዮን ብር በተመረጡ የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ለሚገኙ ደኖች ፕሮጀክት የሚውል ነው፡፡
ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ. ከ2018 እስከ 2021 ለሦስት ዓመታት የሚቀጥልና በቤተ ክርስቲያናቱና በገዳማት የሚገኙ በተመረጡ ስድስት የደን ቦታዎች ሲሆን በአማራና በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው መናገሻ ከተማን ያጠቃልላል፡፡
በ305 ሄክታር ደን መንከባከብና መጠበቅ የሚተገበረውም በሁለት ወረዳዎች ደን ውስጥ ሲሆን፣ እነሱም ጎንጨ ሲሶ አቢሴና ወልመራ በየደረጃው በፕሮጀክቱ ይሠራል፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ የሚገኘው ደን በአካባቢው የሚኖሩ ዘጠኝ ሺሕ ነዋሪዎች በቀጥታ ከደኑ ጥቅም ሲያገኙ 28 ሺሕ ደግሞ በተዘዋዋሪ ጥቅም ያገኛሉ፡፡
የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ የቤተ ክርስቲያን ደን ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም በሚያስችል መልኩ በተግባር ማሳየት ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የሁሉም ቤተ ክርስቲያናት ደኖች እንዳይመናመኑ ማኅበረሰቡ እንዲንከባከብ ግንዛቤ ማስጨበጥ ዓይነተኛ ተግባር ነው፡፡
‹‹የደን ደሴት››
ከዓመታት በፊት በተዘጋጀ ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሚና በአየር ንብረት ለውጥ›› የተሰኘ ጥናታዊ መድረክ ተከትሎ በወጣ አንድ ኅትመት ላይ እንደተገለጸው፣ በመድረኩ ጥናት ያቀረቡት የቅርስ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ አራጌ እንዳስረዱት፣ የቤተ ክርስቲያን ተፈጥሯዊ ደኖች አገር በቀል ዛፎች ለዘር ተርፈው የሚገኙባቸው “የደን ደሴት” ፈጥረዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ደኖችን መቁረጥ በቃለ ዐዋዲ የተከለከለና የተወገዘ ነው፡፡ ምእመኑ የቤተ ክርስቲያን ዐጸድን መቁረጥ የሚያስቀስፍ እንደሆነ ስለሚያምን አይደፍርም፤ እንሰሳትንም አያስገባም፡፡ ዐጸድ የሌለው ደብር ጽሕም የሌለው መምህር፣ ለሰው ጨርቅ ነው ልብሱ፤ ለቤተ ክርስቲያን ደን ነው ሞገሱ፣ ጥምጣም የሌለው ካህን፣ አጸደ የሌለው ቤተ ክርስቲያን፤ የሚሉት የማኅበረሰቡ ብሂሎች የቅዱሳን መጠለያና መጠጊያ ሆኖ ለኖረው የቤተ ክርስቲያን የተፈጥሮ ደን ምእመናን ያላቸውን አመለካከትና አክብሮት የሚያጠይቁ ናቸው፡፡
እንደ አቶ ተስፋዬ ማብራሪያ፣ ኦርቶዶክሳዊቷ ቤተ ክርስቲያን ያለውን አገር በቀል ዛፍ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን አዲስ ችግኞችን በመትከልና በመከባከብ የተፈጥሮ አካባቢን በመጠበቅ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተች ትገኛለች፡፡ በዚህ የተነሳ ቤተ ክርስቲያኗ የራስዋን ቅጥር በደን ከመሸፈን አልፋ ዛሬ በሰሜኑ ክፍል ለሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች መመሥረት ምክንያት እንደ ሆነች መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ የስሜን ብሔራዊ ፓርክ ለመመሥረቱ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች አንዱ የቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን በቦታው መኖሩ ነው፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን የደንቆሮ ደን ብሔራዊ ፓርክ መነሻው የምስካበ ቅዱሳን ማርያም ገዳም መሆኗ፣ እንዲሁም በጣና ደሴት ለሚገኘው የተፈጥሮ ደን ጥበቃ ዋነኛው የገዳማቱ መኖር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጥናት በተደረገባቸው የደቡብ ጎንደር ሦስት ወረዳዎች እንደታየው፣ እንደ ሊቦ ከምከም ጣራ ገዳምና በፋርጣ ወረዳ የሚገኘው የዓለም ሳጋ የመንግሥት ደኖችና በዳራ ወረዳ የመካነ ሰማዕት ገላውዴዎስም ከገዳማት ይዞታዎች የተወሰዱና ዛሬም ከገዳማቱ ጋራ የተቆራኙ ናቸው፡፡