Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አብዛኛው ተረጂ በድርቅ ምክንያት ለችግር የተጋለጠው ነው››  መሸሻ ሸዋረጋ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በኢትዮጵያ ከሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ከ80 ዓመታት በላይ ዜጎችን ሲያገለግል የቆየ ተቋም ሲሆን፣ በዓመት እስከ 500 ሚሊዮን ብር የሚገመት የሰብዓዊ ድጋፍ ያደርጋል፣ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችንም ያገለግላል፡፡ ማኅበሩ ከሚሠራቸው ዋና ዋና የሰብዓዊ ድጋፎች በተጨማሪ ከአጎራባች አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ከቤተሰቦቻቸው የተጠፋፉ ስደተኞችንም የማገናኘት ሥራ ይሠራል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች ተጎጂ የሆኑ ዜጎችን በመደገፍ ረገድ ጉልህ ሚናም እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማኅበሩ የሚሠራቸውን የሰብዓዊ ድጋፎች በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን ዋና ጸሐፊውን መሸሻ ሸዋረጋ (ዶ/ር)ን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ ማኅበሩ የትኞቹን መድረስ ችሏል? እንዲህ ያሉ አገራዊ ጉዳዮች መፈጠራቸውን በመገናኛ ተቋማት ጋር እስኪደርሱ ሳይጠብቅ ቀድሞ በመድረስ ምን ያህል የሰብዓዊ ዕርዳታ እያደረገ ይገኛል?

ዶ/ር መሸሻ፡- በአገራችን እዚህም እዚያም ግጭቶችና መፈናቀሎች አሉ፡፡ ይኼ ቅቡልነት ያለው ነገር አይደለም፡፡ እንደ ማኅበርም እንደ ዜጋ የሚያሳዝነን ነገር ነው፡፡ ጌዴኦ፣ ገደብ፣ ባሥኬቶ፣ ቴፒም አካባቢ የነበሩ ግጭቶችን አስቀድመን ነው የሰማነው፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ከመገለጻቸው በፊት እኛ አቅማችን በፈቀደ ምላሽ ለመስጠት ሞክረናል፡፡ እንደምታውቂው ቀይ መስቀል በዕቅድ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው፡፡ ከዕቅድ ውጭ በሆነ መንገድ ችግሮች ሲከሰቱ ሁኔታው የሚጠይቀውን ያህል ምላሽ ለመስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡ ማኅበሩ በአገሪቱ በቀበሌ ደረጃ ከ4000 በላይ የሚሆኑ ኮሚቴዎች አሉት፡፡ ማንኛውንም የተከሰቱ ነገሮች ከቀበሌ ወደ ወረዳ፣ ከዚያም ወደ ዞን ሪፖርት ያደርጋል፡፡ በዚህ መሠረት በደቡብ ክልል ያለው ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በአካባቢው ለተከሰተው ችግር ባለው አቅም ምላሽ ለመስጠት ሞክሯል፡፡ ከአቅሙ በላይ በሚሆንበት ጊዜ ወደእኛ አቤት ብሏል፡፡ እኛም ከ500 ሺሕ ብር በላይ የሚገመት የምግብ ድጋፍ አድርገናል፡፡ በዚህ 2734 ሰዎችን ረድተናል፡፡ ወደ 3919 የሚሆኑ ሕፃናትን የሚያጠቡ እናቶችን አንድ ሚሊዮን ገደማ ገንዘብ በመመደብም ገደብ ባስኬቶ፣ ሚዛን ቴፒ አካባቢ ድጋፍ አድርገናል፡፡ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችም 21,750 ለሚሆኑ ወገኖች ድጋፍ አድርገናል፡፡ በአጠቃላይ ደቡብ ክልል ላይ ወደ 28,405 ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ ሁለት ሚሊዮን ስድስት መቶ አሥራ አንድ ሺሕ ሰባት መቶ ሃያ አንድ ብር ወጪ አድርገናል፡፡ ይህንንም ወጪ ያደረግነው ከመጠባበቂያ በጀት ሳይሆን ለሌሎች ፕሮግራሞች ተመድበው የነበሩ ገንዘቦችን ወደዛ በማዞር ነው፡፡ በአማራ ክልል በምዕራብ፣ ምሥራቅና ማዕከላዊ ጎንደር ለተከሰተው ከፍተኛ ችግር በቻልነው መጠን ምላሽ ሰጥተናል፡፡ ወደ 12,250 ለሚሆኑ ተፈናቃዮች 3.7 ሚሊዮን ብር አካባቢ ወጪ በማድረግ የተለያዩ ቁሳቁሶች ረድተናል፡፡ ምግብም እየተጓጓዘ ይገኛል፡፡ ዋናው ነገር ለመሰል ክስተቶች ምላሽ ለመስጠት በሚዲያ ላይ እስኪነገር አንጠብቅም፡፡ የምናደርጋቸው ነገሮች ጥናት ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ማኅበሩ ታች ድረስ የወረዳ መዋቅር ስላለው ምንም የሚያመልጠው ነገር የለም፡፡ ሁሌ ደጋግመን እንደምንለው የመጀመርያውን ግብረ መልስ የሚሰጠው ታችኛው መዋቅር ነው፡፡ ከአቅሙ በላይ ሲሆን ነው የድረሱልን ጥሪ የሚያደረገው፡፡ እነዚህ በየቀበሌው የሚገኙ የቀይ መስቀል ኮሚቴዎች በጣም ጥሩ የመረጃ ምንጮች ሆነውም ያገለግሉናል፡፡ በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በደቡቡም፣ በኦሮሚያም፣ በሶማሌም፣ በአፋርም፣ በአማራም ክልል ተመሳሳይ ሥራዎች ሠርተናል፡፡ አዲስ አበባ አካባቢም እንዲሁ ተፈጥሮ በነበረው ችግር ለተፈናቀሉ ለዜጎች ድጋፍ አድርገናል፡፡ በአጠቃላይ ለ48,421 አባወራዎች ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ድጋፍ አድርገናል፡፡ ለዚህም ከ33.1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርገናል፡፡ የአዲስ አበባውን ብንመለከት 2700 አባወራዎች ወይም 13,500 በተለያዩ መንገዶች ችግር ያጋጠማቸው (ለገጣፎ አካባቢ ቤት የፈረሰባቸው በዋናነት) በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አማካይነት ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለለገጣፎ ተፈናቃዮች ማኅበሩ ምን ዓይነት ድጋፎችን ነው ያደረገው?

ዶ/ር መሸሻ፡- የመጀመርያው ድጋፍ መጠለያ የማቅረብ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ተፈናቃዮቹ በእምነት ተቋማት ተጠልለው በየሜዳው ወድቀውም ነበር፡፡ 13,500 ሰዎች አካባቢ ከለገጣፎ ሲፈናቀሉ በተለይ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንና ልጃገረዶች ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠው ነበር፡፡ እነዚህን ወገኖች በዘላቂነት መርዳት ያለበት እንግዲህ መንግሥት ነው፡፡ ጊዜያዊ መጠለያ፣ ምግብና የተለያዩ ድጋፎች እንዲያገኙ ግን አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ መጠለያዎች የሚገኙ የለገጣፎ ተፈናቃዮች ከቀይ መስቀል ማኅበር ያገኘነው ድጋፍ የለም፡፡ በመጠለያነት የሚያገለግል ድንኳን እንኳን ማግኘት አልቻልንም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ማኅበሩ ድጋፍ እንዲያደርግልን ጠይቀን ደብዳቤ አምጡ ተብለናል የሚሉ ቅሬታዎችን ያነሳሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ዶ/ር መሸሻ፡- እንዳልኩሽ ቀይ መስቀል በቻርተር የተቋቋመ ገለልተኛ አካል ነገር ግን የመንግሥትን የሰብዓዊ ሥራዎች እንዲደግፍ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ እኛ ጣልቃ ገብተን እንድንሠራ መንግሥት ከአቅሜ በላይ ነው ቀይ መስቀል ድጋፍ ያድርግ ማለት አለበት  አሠራሩ ይኼ ነው፡፡ ምክንያቱም በቂ የሆነ መረጃ ሳናገኝ ዘለን የምንገባበት አካሄድ የለም፡፡ ስለዚህ የአካባቢው መስተዳደር ከአቅሙ በላይ እንደሆነና ድጋፍ እንደሚፈልግ ሊገልጽልን ይገባል፡፡ ምክንያቱም የመንግሥት መዋቅር እንደሚታወቀው ቢሮክራቲክ ነው፡፡ በጀት አልተያዘ ይሆናል ወይም ሌሎችም ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ለዚህም እስኪወሰን ሊያስቸግር ይችላል፡፡ እኛ ደግሞ ለመጠባበቂያ ብለን የምናስቀምጣቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላል፡፡ በመርህ ደረጃ አንድ ችግር በተከሰተ በ72 ሰዓታት ውስጥ ዳሰሳዊ ጥናት ተደርጎ ለቀይ መስቀል መድረስ አለበት፡፡ በዚያ መሠረት ነው ቀይ መስቀል ገብቶ ድጋፍ መስጠት የሚችለው፡፡ መንግሥት ሌላ ፕሮግራም፣ አጀንዳ ኖሮት ወይም ዲዛይን እያደረገ ሳለ ጣልቃ ገብተን ድግፍ እናድርግ ብንል የመንግሥትን ሥራ ማፍረስ ነው፡፡ የሀብትም ብክነት ሊያጋጥም፣ ከመንግሥትም ጋር ወዳልተፈለገ መፋጠጥ ውስጥ ሊከተን ይችላል፡፡ በጥንቃቄ መደረግ ያለበት ከዚህ አኳያ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን በለገጣፎ ተፈናቃዮች ዙሪያ መሰመር ያለበት ነገር አለ፡፡ የአዲስ አበባ ቀይ መስቀል ጽሕፈት ቤት ፈጥኖ በመግባት ለተፈናቃዮቹ መጠለያ ድንኳን አቅርቧል፡፡ ይህንን በተመለከተ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊውን ማነጋገርም ይቻላል፡፡ ምናልባት አንቺ የምትይው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚጠቃለሉትን የለገጣፎ ተፈናቃዮችን ይሆናል፡፡ አንቺ ወዳልሽው እውነትም ሊጠጋ የሚችለውም የኦሮሚያው ነው፡፡ እዚህ ላይ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ ምክንያቱም ዕርዳታ የማያስፈልጋቸው ሰዎች ሁሉ ተቀላቅለው ዕርዳታ የሚፈልጉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይህንን በደንብ አጥንቶ፣ መንግሥት በራሱ መዋቅር ይህንን ነገር ተመልክቶ ቀይ መስቀልንም ጋብዞ፣ የቀይ መስቀል ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ግልጽ ደብዳቤ ሲጽፍልን በጋራ ሆነን የዳሰሳ ጥናት እንሠራለን፡፡ መንግሥት ይህንን የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ አሠራሩም በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የምንጠቀምበትና የተለመደ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ችግሩን እንደሰማን አጥኚ ቡድን ተቋቁሞ የዳሰሳ ጥናት እንዲያደርጉ ወደ ቦታው ድረስ ልከን ነበር፡፡ ነገር ግን በተለይ በእምነት ተቋማት ተጠልለዋል የተባሉትን ለማየት ሄደን አንድም ሰው አላገኘንም፡፡ አንዳንዴ በተለያየ አጋጣሚ ጎዳና ወጥቶ የነበረ ሰው እቺን አጋጣሚ መጠቀም ይፈልጋል፡፡ ግለሰባዊ መሻቶችን የሚያስተናግድ ሀብት የለም፡፡ አሠራሩም ቅድም እንዳስቀመጥኩት ነው፡፡ ቀይ መስቀል በዘላቂነት ድጋፍ ማድረግ አይችልም፡፡ ያጋጠመው ችግሮች ወደ ከፋ ጉዳት እንዳይደርሱ የማድረግ አቅም ብቻ ነው ያለው፡፡ እንደሚታወቀው ማኅበሩ በበጀት ሳይሆን ከተለያዩ አካላት ለምኖ በሚያመጣቸው ዕርዳታዎች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እነዚህ ዕርዳታዎችም በአንድ ጊዜ የሚመጡ አይደሉም፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአገራችን 8.8 ሚሊዮን ሕዝብ ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጧል፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ ስምንት ሚሊዮን አንድ መቶ ሰላሳ ሺሕ የሚጠጋ ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ደግሞ የአልሚ ምግቦች አቅርቦት ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ፍላጎቶች ናቸው ያሉት፡፡ ቀይ መስቀል ፍላጎት ስላለው ብቻ መሥራት አይችልም፡፡ ላድርግ እንኳን ቢል የገንዘብ እጥረት አለብን፡፡ መንግሥትም ቢሆን አቅሙ ውስን ነው፡፡ ምክንያቱም ለልማት የመደበው ገንዘብ ለምሳሌ የዘንድሮን ብንወስድ ወደ 600 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ መንግሥት ይህንን የልማት ገንዘብ ቅድም ላልኳቸው ችግሮች  ለማዋል እስኪገደድ ችግሩ አስከፊ ነው፡፡ ቀይ መስቀልም የሁሉ ነገር መፍትሔ ተደርጎ ሊታሰብ አይገባም፡፡ ይህንን የማድረግ አቅሙም የለውም፡፡ አቅሙ ቢኖረውም ዝም ብሎ ጣልቃ ገብቶ ድጋፍ ማድረግ አይቻልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ምን ይፈጠራል መሰለሽ ለምሳሌ አንድ ቦታ ላይ ሄደን መንግሥት ሳያውቅ መጠለያ ድንኳን ብንተክል ብዙ ነገር ሊበላሽ ይችላል፡፡ መንግሥት ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ያሰበበት መንገድ ሊኖር ይችላል፡፡ ድንኳኑን ስንጥል ለችግር ያልተጋለጡ ሰዎች መጠለያ ፍለጋ ይመጣሉ፡፡ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ጊዜያዊ መጠለያዎችን ወደ ቋሚ መጠለያነት ሊቀይሩ ይችላሉ፡፡ ይህ መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ያስቀመጠውን አቅጣጫ የሚያበላሽ፣ በመንግሥትና ዜጎች መካከልም ያልተፈለገ ውጥረት የሚፈጥር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ትኩረት ያላገኙና በቂ ድጋፍ የተነፈጋቸው የተፈናቃዮች መጠለያዎች አሉ?

ዶ/ር መሸሻ፡- በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያለው የተፈናቃዮች ሁኔታ አሁን ላይ በደንብ የሚታወቅ ነው፡፡ የተለያዩ ሥራዎችም እየተሠሩ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ እንደምናወራው ቀላል አይደለም፡፡ ‹‹ዕርዳታ በተፈለገው መጠንና ፍጥነት ማድረስ እጅግ በጣም ፈታኝ ነው፤›› እንዲህ ያለ ነገር ያጋጥማል ተብሎ በቂ ዝግጅት አልተደረገም፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ትኩረቱ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተበታትኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት እየተከሰቱ ያሉት ሰብዓዊ ቀውሶች ዋጋቸውም በጣም እየጨመረ ነው፡፡ በዓመት 1.4 ቢሊዮን ዶላር ለማውጣት የምንገደድበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ ለአምስት ዓመት ይዋጣ የነበረ ገንዘብ ነው አሁን በአንድ ዓመት ያስፈለገው፡፡ መዘንጋት የሌለበት ነገር ተፈናቅለው የነበሩ ወደ አካባቢያቸው የተመለሱ ግን ቤታቸው ያልገቡ ዜጎች መኖራቸው ነው፡፡ ወደ አካባቢያቸው ተመልሰዋል ይባላል ቤታቸው እንዳይገቡ ግን የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የሚደረገው ቅድሚያ መሠራት ያለባቸው ነገሮች ካለቁ በኋላ አይደለም ወይ?

ዶ/ር መሸሻ፡- መንግሥት ዜጎቹ የበለጠ ሊረዱ የሚችሉበትን መንገድ ያመቻቻል፡፡ በተለያዩ ነገሮች እየተወጠረ መሆኑን ደግሞ ማየት አለብን፡፡ በአንድ በኩል የልማት ሥራዎች እየሠራ፣ በሌላ በኩል ግጭቶች ከየአቅጣጫው ሲከሰቱ ሠራዊት እያሰማራ ለማስተካከል እየሞከረ ይኼ ደግሞ ሳያንስ ከድርቅ ጋር የተያያዙ የተፈጥሮ አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ አብዛኛው ተረጂ እኮ በድርቅ ምክንያት ለችግር የተጋለጠ ነው፡፡ በኦሮሚያ 3.8 ሚሊዮን ሕዝብ ድግፍ ይፈልጋል፡፡ በሶማሌ ክልል ደግሞ ለ1.8 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ በደቡብ ክልልም ወደ 800 ሺሕ ዜጎች እንዲሁ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ በሌሎችም በተደጋጋሚ ጊዜያት በድርቅ የሚጠቁ የአገሪቱ ክፍሎች እንዲሁ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ የተሻለ መሥራት እንዲችል ምን እያደረገ ነው?

ዶ/ር መሸሻ፡- ማኅበሩ ኃላፊነቱን ለመወጣት ራሱን እያደራጀ የተሻለ መሥራት የሚያስችለውን ስትራቴጂክ ፕላን እያወጣ ይገኛል፡፡ ስትራቴጂክ ፕላኑ ከቻርተሩ ጋር እንዲሰላሰል ተደርጎ እየተዘጋጀም ነው፡፡ እንዲሁም አገሪቱ ያወጣችውን ሁለተኛውን የምዕተ ዓመቱን ግብ ለማሳካት ቅድሚያ ሊሠራባቸው የሚገቡ ነገሮችን ለይተን እየሠራን ነው፡፡ እንደሚታወቀው ማኅበሩ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን አባል ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ያወጣውን ስትራቴጂክ ግምት ባስገባ መልኩ ነው ፕላኑ እየወጣ የሚገኘው፡፡ በአጠቃላይ ማኅበሩ የሚቀርጸው ፕላን የተለያዩ ዓለም አቀፍና ብሔራዊ ጉዳዮች ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም የተለያዩ የምንሠራቸው ፕሮግራሞች አሉ፡፡ በአገራችን ውስጥ ያለውና እያደር እየጨመረ የመጣውን ሰብዓዊ ድጋፍ ሁኔታን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ነው ስትራቴጂው እንደገና እየታየ ያለው፡፡ በአደጋ መከላከልና በግብረመልስ፣ እንደዚሁም የአደጋ ተጋላጭነትን የሚቀንሱ ሥራዎች፣ በዘላቂነት ራሳችንን፣ የአደጋ ተጋላጭነታችንንና መቋቋም የምንችልባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞች አሉን፡፡ ሌላው በተቋቋምንበት ቻርተር ላይ የተካተተ ነገር ግን ብዙ ያልሠራንበት ከሰላም ግንባታ አንጻር የምንሠራው ነገር ይኖራል፡፡ እንደሚታወቀው በአገራችን ውስጥ በተለይ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት አብዛኛውን የአገሪቱን ክፍል ያካተተ በግጭቶችና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ወደ 3.1 ሚሊዮን ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የነበረው የተፈናቃዮች ቁጥር 2.7 ሚሊዮን አካባቢ ነበር፡፡ 3.1 ሚሊዮን መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው በቅርቡ ይፋ ያደረገው፡፡ ይኼ ቁጥር በተለያዩ ቦታዎች ግጭቶች እየተነሱ ስለሆነ እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ በዜጎች መካከል መቻቻል፣ መደጋገፍ፣ መረዳዳት ተግባብቶ መኖር እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ የምትታወቅበት በሃይማኖት፣ በጎሳ የመቻቻል እሴቶች እያደሩ እየላሉ ነው፡፡ በተለይ በተለይ ደግሞ በወጣቶች መካከል ባልተለመደ ሁኔታ አለመግባባቶች እየተፈጠሩ፣ አለመግባባቶቹም ወደ ግጭት እያመሩ፣ ውሎ አድሮም የጎሳና የሃይማኖት ቅርፅ እየተላበሱ የሚመጡበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ስኬታማ ተሞክሮዎችን መሠረት ያደረገ ሰላም ላይ ያተኮረ ፕሮግራም እንዲኖረን እየሠራን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበረሰቡ ተቻችሎ ለዘመናት የኖረ ነው ይባላል፡፡ ተቻችሎ ስለመኖርም ብዙ ነገር ይባላል፡፡ ተቻችሎ መኖር ሲባል የአንዱን መኖር ባንፈልግም አብሮ ለመኖር ሲባል እንዲኖር መፍቀድ ዓይነት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ የአንዱን ስህተት ለሰላም ሲባል ችሎ በትዕግሥት ማለፍ ዓይነት ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ሰው እስከ መቼ ይቻቻላል? ትዕግሥቱም ቢሆን የሆነ ጊዜ ላይ መፈንዳቱ አይቀርም፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የአገሪቱ ሁኔታ በከፊልም ቢሆን የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ እንደገና ተቻችሎ እንዲኖር ከመሥራት ይልቅ ተከባብሮና አንዱ የአንዱን ግላዊና ማኅበራዊ ሕይወት በማይነካ መልኩ የራሱን ክልል ጠብቆ መኖር እንዲችል ማድረግ ላይ ለምን አይሠራም?

ዶ/ር መሸሻ፡- የቋንቋ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር መቻቻል Peace Full Coexistence ወይም በሰላም አብሮ መኖር ማለት ነው፡፡ ድሮም እኮ ልዩነት ሳይኖር ቀርቶ አይደለም፡፡ ያንቺ እምነት ለእኔ ትክክል አይደለም ብዬ ላስብ እችላለሁ፡፡ ነገር ግን የእኔ እምነት ላንቺ ትክክል ባይሆንም ለእኔ ትክክል መሆኑን ተቀብለሽ እኔም ላንቺ ትክክል መሆኑን አምኜ በሰላም መኖር ነው፡፡ በፖለቲካ ርዕዮትም አንዱ የሶሻሊዝም ተከታይ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ የሚያዋጣው ኒዮሊብራሊዝም ነው ሊል ይችላል፡፡ ሶሻል ዴሞክራስ ነው የሚያዋጣው የሚልም ይኖራል፡፡ ሦስቱ ርዕዮቶች የተለያዩ ትርጉም አላቸው፡፡ እንደ ደጋፊዎቻቸው ዕይታ ትክክል ሊሆኑ ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ መቻቻል ለእኔ እነዚህ ልዩነቶች የሐሳብ ፍጭቶች ብቻ ሆነው እንዲቀሩ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ሰው ማኅበራዊ እንስሳ ነው ይባላል ማኅበራዊ እንስሳ ደግሞ ፈርጀ ብዙ መሆናችን፣ አመለካከታችን፣ አስተዳደጋችን፣ የኋላ ታሪካችን መለያየታቸው አብሮ መኖርን አዳጋች ማድረግ የለበትም፡፡ እነዚህ ማኅበራዊ እሴቶች ያሉት ልዩነቶች የግጭት መንስኤ እንዳይሆኑ አድርገዋል፡፡ መቻቻል ግዴታ ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ ባልና ሚስት 80 በመቶ ሊግባቡ ይችላሉ፡፡ 20 በመቶ ግን አብሮ መኖራቸውን አዳጋች የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሊኖሩባቸው ይችላሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ከመቻቻል ባለፈ በምን ሊታለፍ ይችላል፡፡ ሐሳባችንን በነጻነት የመግለጽ፣ የፈለግነውን እምነት የመከተል የመሳሰሉ መብቶች ለድርድር የሚቀርቡ አይደሉም፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ ልዩነቶች የግጭቶች ምክንያት ሊሆኑ አይገባም፡፡ ደም አፋሳሽ የሆኑ ግጭቶች ከዘር መለያየት ወይም ከእምነት መነሳት የለባቸውም፡፡ በአገራችን ውስጥ 3.1 ሚሊዮን ዜጎች ከየት አካባቢዎች የተፈናቀሉ ናቸው የሚለውን ብንመለከት አንደኛ ከኦሮሚያ፣ ሁለተኛ ከሶማሌ ክልሎች ነው፡፡ ይኼ አሁን በሁለት ክልሎች የተፈጠረ ግጭት ሳይሆን በሁለቱ ጎሳዎች መካከል የተፈጠሩ ግጭቶች ናቸው ወደዚህ ያመሩት፡፡ በሁለቱ መካከል ለምንድነው ግጭቶች የተፈጠሩት ብለን ብንመለከት ለጎሳ ልዩነት የሰጠነው ትኩረት ከሚገባው በላይ እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ ነው፡፡ የፖለቲካ አውታሩ የተዋቀረበት ውቅር የዘር ልዩነት በመሆኑ ይህንን መሠረት አድርገው የተቋቋሙ የፖለቲካ ድርጅቶች እያራገቡና ፀንቶ የነበረውን አብሮ የመኖር እሴት ስለረበሹት የተፈጠረ ነው፡፡ የዘርና የሃይማኖት ልዩነትኮ ከዛሬ 3000 ዘመን ጀምሮ የነበረ ነገር ነው፡፡ እያልኩ ያለሁት የሰላም ባህል በአገራችን መጠናከር አለበት፡፡ ስለዚህም የመልካም ወጣትነትን ሥነ ምግባር ለመገንባት፣ አገራችን በሰላም ወደ ሥልጣኔ ማማ የምትወጣበት መንገድ ላይ አጥብቀን እንሠራለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...

ከጎዳና ከማንሳት ራስን እስከማስቻል የሚዘልቀው ድጋፍ

ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ባያገኝለትም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመለወጥ በሚሠሩ ሥራዎች ዕድሉን አግኝተው ራሳቸውን...