Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሦስት ዓመት የፈጀው የመንገድ ግንባታ ቁጣ ቀሰቀሰ

ሦስት ዓመት የፈጀው የመንገድ ግንባታ ቁጣ ቀሰቀሰ

ቀን:

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የወረዳ 5 ነዋሪዎች በፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ዝርጋታ ስም የተቆፈረ መንገድ ወቅቱን ጠብቆ ባለመገንባቱ፣ ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸውን ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በተቃውሞ ሠልፍ ገለጹ፡፡

የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ለመዘርጋት መንገዱ ከተቆፈረ ሦስት ዓመታት መቆጠራቸውን የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪ አቶ ተሾመ እሸቱ፣ መንገዱን ወደ ነበረበት ለመመለስ ይኼንን ያህል ጊዜ መፍጀቱ የአካባቢውን ነዋሪዎች ለተለያዩ ችግሮች እንዳጋለጠ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

መንገዱ የተቆፈረው የአካባቢው ነዋሪዎች ገንዘብ አዋጥተው መንገድ በኮብልስቶን አሠርተው ብዙም ሳይገለገሉበት እንደሆነም ተገልጿል፡፡ መንገዱን  በኮብልስቶን ለማሠራት የአካባቢው ነዋሪዎች ከአራት ሺሕ እስከ ሰባት ሺሕ ብር ድረስ ማዋጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

መንገዱ ከተቆፈረ ሦስት ዓመታት አልፈዋል ያሉት አቶ ተሾመ፣ በተለይ ለአካባቢው ነዋሪዎች ትልቅ ሥጋት የሆነው ወደ ታች እስከ ዘጠኝ ሜትር ጠልቆ የተቆፈረውና አፉን ከፍቶ የቀረው ሰፊ ጉድጓድ ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በጉድጓዱ ውስጥ ሦስት አቅመ ደካሞችና አንድ ሕፃን ልጅ ወድቀው ለጉዳት መዳረጋቸውንና በሰዎች ርብርብ መትረፋቸውን አስታውቀው፣ እንደ ውሻና ድመት ያሉ የቤት እንስሳትም ብዙ ጊዜ ጉድጓዱ ውስጥ እንደሚወድቁም አክለው ገልጸዋል፡፡ መንገዱን የሚጠቀሙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሆናቸውንና በአካባቢው ከ300 በላይ አባወራዎች እንደሚኖሩ ታውቋል፡፡

በመቆፈሩ ምክንያት በአካል ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ የመንደሩ ነዋሪዎች ቤት ውስጥ እንዲቀሩ መደረጉን፣ ከመንገዱ በታች በኩል የሚኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎችም በተደጋጋሚ ጊዜ ቤታቸው በጎርፍ እንደተጠቃ ከተቆፈረው መንገድ ፊት ለፊት ሱቅ ከፍተው የሚሠሩት ወ/ሮ አየለች ደበላ ገልጸዋል፡፡

‹‹አዲስ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ በኮብልስቶን ካሠራን አራት ዓመት ቢሆነው ነው፡፡ እንደተሠራ ነበር መንገዱ የፍሳሽ ማስወገጃ ፒቪሲ ለመቅበር ተብሎ የተቆፈረው፡፡ ነገር ግን እንደምታዩት ኮብልስቶን የተነጠፈበት መንገድ አይመስልም፡፡ በሙሉ ፈራርሷል፡፡ አፍርሰን ጠግነናል ያሉት ሁሉ በአግባቡ ባለመሠራቱ ገደል እየሆነ ነው፡፡ መኪና ማሳለፍ አይችሉም፤›› ያሉት አቶ ተሾመ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ኮሚቴ አቋቁመው ግንባታውን በወቅቱ እንዲጨረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን፣ ነገር ግን ምላሽ አለማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ኮንትራክተሩን በተለያዩ ጊዜያት አግኝተው የመንገዱ ግንባታ ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ ቢያነጋግሩትም፣ ነገ ዛሬ እያለ ማዋላወሉን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ ሲያነጋግሩት ጀመር አድርጎ መልሶ እንደሚተወው የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት ሥራ ጀምሮ እንደነበር፣ በወቅቱም ወደ መኖሪያ ቤቶች ውኃ የሚተላለፍባቸውን የውኃ መስመሮች መስበሩንና ነዋሪዎች ለ16 ቀናት ውኃ ጠፍቶ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡

በግንባታ ወቅት የተቆረጠው ዋና የውኃ ማስተላለፊያ መስመሮችም አካባቢው በጎርፍ እንዲጥለቀለቅ ማድረጉን ወ/ሮ አየለች ገልጸዋል፡፡ ሪፖርተር ሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በቦታው ተገኝቶ እንዳረጋገጠው ተሰበረ በተባለው የውኃ ማስተላለፊያ መስመር ውኃ ይፈስ ነበር፡፡ ወደ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች የሚገቡ ስድስት የውኃ መስመሮችም መቆራረጣቸውን ለማየት ተችሏል፡፡

‹‹ኮንትራክተሩ ሠርቶ ማስረከብ የሚችልበት አቅም አጥቶ ሳይሆን ኅብረተሰቡን እየዋሸ ነው፡፡ የተበታተኑ ሌሎች ፕሮጀክቶች እንዳሉት ይሰማል፡፡ ሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ አተኩሮ የእኛን ችላ ብሏል፤›› ብለዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች መጪው ክረምት እንደመሆኑ አፋጣኝ መፍትሔ እንሻለን ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

‹‹የዚህ አካባቢ ችግር መሬቱ ውኃ ማፍለቁ ነው፤›› የሚሉት የኮንትራክተሩ ተወካይ አቶ ዮሴፍ አምባዬ፣ ጥልቀት ያለው ጉድጓድ ሲቆፈር ሦስት ሜትር ያህል ወደ ታች እንደተቆፈረ ውኃ መፍለቁ ግንባታውን እንዲደናቀፍ አድርጓል ብለዋል፡፡ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ወቅቱን ጠብቀው አለመቅረባቸውም ሌላው ችግር እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ከሦስት ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት እየሠራ የሚገኘው ኒውፒክ ኮንስትራክሽን የተባለው ሥራ ተቋራጭ ፕሮጀክቱን ከተረከበው ዓመት እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ጊዜ የሥራችን 95 በመቶ ተጠናቋል፤›› የሚሉት ተወካዩ፣ በግንባታ ወቅት የተበላሹ መሠረተ ልማቶችን ወደ ነበሩበት የመመለስ ሥራ እናከናውናለን ብለዋል፡፡ የተሰጠው የግንባታ ጊዜ ለመጠናቀቅ አሥር ቀናት እንደቀሩ፣ ግንባታውን ክረምት ከመግባቱ በፊት አጠናቀው እንደሚያስረክቡም አስረድዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...