Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበቅዠት የሚናውዙ ግለሰቦችና ቡድኖች ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ ይታገዙ

በቅዠት የሚናውዙ ግለሰቦችና ቡድኖች ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ ይታገዙ

ቀን:

በልዑል አልጀበል

1990ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ይመስለኛል የሦስት አገር ጋዜጠኞች መላውን ኢትዮጵያውያንን ያስቆጣ፣ ያስፎከረ፣ ያሳዘነና ያስደነገጠ ጽሑፍ በጋዜጣ ላይ አውጥተው ነበር፡፡ ጋዜጠኞቹም የኬንያ፣ የናይጄሪያና የጃፓን ዜጎች ሲሆኑ፣ ጽሑፎቻቸውን ያስነበቡትም በየአገሮቻቸው ጋዜጦች ላይ በማውጣት ነበር፡፡ እነዚህ ደፋርና ወጥ ረገጥ ጋዜጠኞች ስለኢትዮጵያውያን ያቀረቡት አስተያየት ለእኛ ጆሮ የደረሰው ግን፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሑድ ጠዋት የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጆች በኩል እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የጋዜጠኞቹን አስተያየት ያዳመጠ ሁሉ ሐሳባቸው መሠረተ ቢስ መሆኑን የሚያሳይና የሚያፈርስ፣ የጋዜጠኞቹ ታዕታይ ምስቅልቅል (Inferiority Complex) የፈጠረው የተሳሳተ ሐሳብ መሆኑንና ኢትዮጵያውያንን የሚያፅናና ምላሽ ሲሰጡ ነበር ያረፈዱት፡፡ በእውነት እላችኋለሁ የሚችለውን ሁሉ አስተያየት ያልሰጠ አድማጭ አልነበረም ምን አለፋችሁ የዚያን ዕለቱ የሬዲዮ ፕሮግራም መልኩን ቀይሮ የቁጭትና የእሮሮ ማሰሚያ መድረክና የብሶት መግለጫ ሆኖ ነበር ያረፈደው፡፡

በዕለቱ ከታዩና ከተሰሙ ሁኔታዎች መካከል በእጅጉ የሚያስገርመው ደግሞ፣ እያንዳንዱ ተደፈርን ባይ አስተያት ሰጪ ሐሳቡን የገለጸው በእልህና በቁጭት መሆኑ ነበር፡፡ የአንዳንዶቹ አስተያየቶች ይዘትም ቢሆን ከማስገረም አልፎ የሚያስቅም ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ አንዳንዶቹ አስተያየቶች ታሪክ ቀመስ ከመሆናቸውም በላይ፣ ከጋዜጠኞቹ ሐሳብ ጋር ፍፁም የማይገናኙ እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ አንዳንዶቹ አስተያየቶች ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምረው በላሊባላና በፋሲለደስ የሥነ ሕንፃ ጥበብ አልፈው እስከ ዓድዋ ጦርነትና ታሪካዊ ድል ድረስ ያሉትን እሴቶች በመጠቃቀስ፣ ኢትዮጵያውያን የአምስት ሚሊኒየም ሥልጣኔ ባለቤት መሆናችንን ለማስረዳት የሚሞክሩ ነበሩ፡፡ ከጃፓኑ ጋዜጠኛ አስተያየት ጋር የተዛመደ ሐሳብ የሰጡ አድማጮች ደግሞ፣ እንደ ዛሬው አያድርገውና 60 ዓመታት በፊት ጃፓን በአደጋ በተመታችበት ወቅት ኢትዮጵያ ዕርዳታ መላኳን በማስታወስ፣የቀን እንጂ የሰው ጀግና የለውም› በማለት ቁጭታቸውን ይገልጹ ነበር፡፡

በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚ ልማት ባንታወቅም በጀግንነታችን በዓለም የምንታወቅና የማንደፈር ኩሩ ሕዝቦች መሆናችንን ለመግለጽ፣ ከዶጋሊ ጦርነት ጀምሮ በተለያዩ ሰሜናዊ የአገራችን አካባቢዎች የተካሄዱ ጦርነቶችንና ድሎችን በኩራት በመጥቀስ ሐሳባቸውን ከገለጹ ወገኖች በተጨማሪ፣ ተራራ ያንቀጠቀጠ ትውልድ የተፈጠረባት አገር መሆኗንም በሰፊው ያነሱ ነበሩ፡፡ 27 ዓመታት ያህል የጭቆና ቀንበር ስላሸከመንና  በወቅቱ አገር ይገዛ ስለነበረው ታላቅ መሪ ተብየው የደፈጣ ተዋጊዎች መሪ አንባቢነትና አስተዋይነት እያነሱ ማስረጃ ማቅረብ ባይችሉም፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ከማንም የበለጠ ማሰብ የምንችል መሆኑን ለማስረዳት ያልተፍጨረጨረ አድማጭ አልነበረም፡፡

ለጋዜጠኞቹ አስተያየት ማናቸውንም ምላሽ የሰጡ ኢትዮጵያውያን ‹የአቅሙን ያህል የወረወረ ፈሪ አይባልም› እንዲሉ፣ ሁሉም ምላሽ የሰጡ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ናቸውና ሊመሠገኑ ይገባል እላለሁ፡፡ የእኔ ጽሑፍ መነሻም እነዚያን ጋዜጠኞች የወረድንባቸው አላግባብ ነበር ወይም ለምን ተነካን በሚል ስሜት ተነሳስተን ነው የሚል አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ግን አንድ ጉዳይ መታየት እንደነበረበት ለማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ ጋዜጠኞቹ ስለኢትዮጵያውያን የተዛባና ብዙዎቻችንን የማይወክል አስተያየት ለምን አቀረቡ? የትኞቹን ኢትዮጵያውያን መነሻ አድርገው ነው ለመጻፍ የደፈሩት? በእርግጥስ ጋዜጠኞቹ ያቀረቡትን ሐሳብ የሚወክሉ ጥቂት ሰዎች የሉም ወይ? በወቅቱ መንግሥት ይከተለውነበረውና ሰምና ወርቅ ያለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ሥርዓት ጋዜጠኞቹን እንደዚያ ባለ ጥቅል መደምደሚያ ላይ ሊያደርሳቸው አይችልም ወይ? ብለን ማሰብና ስለወቅቱ ሁኔታ መመርመር የነበረብን ይመስለኛል፡፡

በወቅቱ ሁሉን ፈጣሪና አድራጊ ከነበሩ ከአንዳንድ ባለጊዜ ሰዎች ድርጊትና ሰብዕና ጋር አጣምረን ለማየት ለምን አልሞከርንም? በወቅቱ በሥልጣን ላይ የነበሩና ከባለሥልጣናት ጋር ቅርበት የነበራቸው ወይም በባንዳነት ያደሩ ግለሰቦች አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ አስነዋሪ ተግባር ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ፣ መሬት ቆርሰው ለጎረቤት አገር ሲሰጡና የአገር ታሪክ ሲበርዙም ሲሰርዙም ዓይተውና ሰምተው ይሆን እንዴ ለምን አላልንም? የሞቱትም አሁን ያሉትም ሆኑ በደጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲቀልዱ፣ ሀብቱን ሲዘርፉና አገር በታኝ ሴራ ሲጎነጉኑ የኖሩትን ባለጊዜዎች ዓይተውና ታዝበው የጻፉት ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁም ሐሳብ ለአንዳችን እንኳ እንዴት ብልጭ አላለንም? የሚል ነው የጽሑፌ መነሻ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ እስቲ ትንሽ ልጫጭርበት ብዬ የተነሳሁትና ትዝብቴን ለመግለጽ የከጀልኩትም፣ በእርግጥም ጋዜጠኞቹ የገለጹትን ሐሳብ የሚወክሉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ስላረጋገጥኩ ነው፡፡ እነዚያ የኬንያ፣ የናይጄሪያና የጃፓን ጋዜጠኞች ለዓለም ሕዝብ ያስነበቡት አስተያየት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን የማይወክልና ጫፍ የወጣ አስተሳሰብ ቢሆንም፣ የጋዜጠኞቹን ሐሳብ በትክክል የሚያረጋግጥና ዕውቀት የራቀው ድርጊት የሚፈጽሙ በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች በዘመናችንም ያሉ መሆኑን መናገር ግን እውነት እውነት የማይሸት ነው ሊባል አይችልም፡፡ እኔም ጋዜጠኛ ያላየውንና መረጃ የማይመዝበትን ጉዳይ አይጽፍምአይናገርም የሚለውን ሳይንሳዊ እውነታ ያረጋገጥኩትም ከጥቂት ዓመታት በፊትና በአሁኑ ወቅት በጥቂት ግለሰቦች የተሠሩና እየተሠሩ ያሉ አስገራሚ ተግባራትን በመመልከቴ ነው፡፡ ምክንያቱም ጋዜጠኞቹ ስለእኛ እንደዚያ ለማለት የደፈሩት፣ በእነማንና በየትኞቹ ግለሰቦች ቁና ሰፍረውን እንደሆነ በግልጽ የገባኝም ግን ዛሬ ነው፡፡

የጋዜጠኞቹን ሐሳብ ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ አሳፋሪ ተግባራትን የፈጸሙና የሚያስፈጽሙ ጥቂት ግለሰቦችን የሚመለከቱ ድርጊቶችን፣ አሠራሮችንና ተግባራትን በማስረጃነት እያነሳሁ ሐሳቤን ለማስረዳት ስለምሞክር፣ ብዙዎቻችንን ስላበሳጨን የጋዜጠኞቹ አስተያየትና ለጽሑፌ ርዕስ ስላደረኩት ጉዳይ ላውጋችሁ፡፡ መላው ኢትዮጵያውያን የተንጫጫንበትንና ሦስቱ ጋዜጠኞች የጻፉት ሐሳብ ምን የሚል መሰላችሁ? የማቀርብላችሁም የጋዜጠኞቹን ጠቅላላ ጽሑፍ ሳይሆን የጻፉባቸውን ርዕሶች ብቻ ነውና ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

እንደነገርኳችሁ ጊዜው 1990ዎቹ መጨረሻ ሲሆን፣ ጋዜጠኞቹ በአገሮቻቸው ጋዜጦች ላይ የጻፉትም በተለያዩ ወራት መሆኑን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ፡፡ የኬንያው ጋዜጠኛ ‹‹ኢትዮጵያውያን በትክክል ማሰባቸውን እጠራጠራለሁ›› ብሎ ሲጽፍ፣ የናይጄሪያው ጋዜጠኛ ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያውያን የሚስቡትና የሚኖሩት 19ኛው ክፍለ ዘመን ልክ ነው›› በሚል ርዕስ በወቅቱ እየተገበርነው ያለውን የፌዴራሊዝምና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ሥርዓት የሚመለከት ጽሑፍ አስነብቦ ነበር፡፡ የጃፓኑም ‹‹ኢትዮጵያውያን እንደ ሰው የሚያስቡ አይመስለኝም›› በሚል ርዕስ በጃፓን ውስጥ ሰፊ ሽፋን ባለው ጋዜጣ ላይ ጽፎ ነበር፡፡ ይህም ጋዜጠኛ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ወቅታዊ ሁኔታዎችን የሚመለከቱ ማስረጃዎችን በማጣቀስና በማቀናበር ሊያስተላልፍ የፈለገውን አስተያየት ተንትኖ ነበር፡፡

የጋዜጠኞቹ ጽሑፎች ርዕሶች በመጠኑም ቢሆን የተለያዩ ቢመስሉም፣ የጽሑፎቹ የጋራ ሐሳባቸውና መልዕክታቸው ግን ‹‹ከኢትዮጵያውያን ማሰብ አይችሉም›› በሚለው የሚጠቃለል መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡ ያኔ በኢትዮጵያውያን በኩል ሲሰጡ የነበሩ ምላሾችም እኛ ኢትዮጵያውያን እንዴት ማሰብ አትችሉም እንባላለን የሚል መልዕክት ያላቸው ስለነበሩ፣ በጠቀስኩት የጋዜጠኞቹ ጽሑፍ የጋራ ይዘት የምንስማማ ከሆነ በእርግጥም ማሰብ የማይችሉ ጥቂት ግለሰቦች አሉ ያልኩበትን ምክንያት ላስረዳ፡፡ በርዕስ ደረጃ ወዳስቀመጥኩት ዋና ጉዳዬ ከመግባቴ በፊት ግን ማሰብ አለመቻልና ማሰብ መቻል ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚያግባባ አጭር ትርጉም መስጠት ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ ማሰብ አለመቻልና ማሰብ መቻል የሚሉት ስማዊ ሐረጎች ብያኔ ወይም የሚያስተላልፉት መልዕክት በእጅጉ የተራራቀና ተቃራኒም ይዘት ያለው ነው፡፡

ማሰብ አለመቻል የሚለው ስማዊ ሐረግ ሲነገርም ሆነ ሲነሳም ግርታ ሊፈጥር እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ ምክንያቱም አዕምሮ ያለው ሰው እንዴት ማሰብ አይችልም የሚል ጥያቄ ማስነሳቱም እንደማይቀር እገምታለሁ፡፡ የሥነ ትምህርት ጥናትፔዳጎጂ› የሙያ ዘርፍ የሰው ደደብ የለውም የሚል ማጠቃለያ ስለሚሰጥ፣ በእርግጥም ማሰብ የማይችል ግለሰብ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ በእኔ በኩል ግን በቅዠት ሰክሮ መራወጥና ከብዙ ዓመታት በፊት ከቆሙበት ቦታ አንድ ስንዝር እንኳ ለመራመድ አለመፈለግ ወይም አለመቻል ማሰብ መቻል አይመስለኝም፡፡

ማሰብ አለመቻል ማለት በአጭሩ ከሰውነት ይልቅ የስግብግብነትና የአውሬነት ባህሪይ የተጠናወተው ይመስለኛል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታትና ዛሬም በተወሰኑ ግለሰቦችና ቡድኖችም እየተፈጸመ ያለው እኮ ይኼው የአውሬነት ፀባይና ተግባር ነው ማሰብ መቻል የሚለው ሐረግ ግን መልካም ሥነ ምግባር የሚገለጽበትና የትክክለኛ ሰብዓዊ ፍጡርን መለኪያ የሚያሟሉ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ግለሰቦችብዕና የሚንፀባረቅበት ነው፡፡ በአጠቃላይ አነጋገር አዎንታዊና መልካም አመለካከት ያላቸውና የፈጣሪ ህሊና የሚባለውን ታላቅ ስጦታ የቸራቸው እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ እንደ አቶ ለማ መገርሳ፣ እንደ አቶ ደመቀ መኮንንና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ወዘተ. ለአገርና ለሕዝብ ታላቅነት፣ ለአንድነትና ለፍቅር መሠረት የሚሆኑ ሥራዎችን የሚሠሩ ዜጎች መገለጫ ይመስለኛል፡፡

የሦስቱ አገሮች ጋዜጠኞች ድፍረትና ዘጠና በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የማይወክል የተዛባ አስተያየት ማቅረባቸው እኔን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያንን የሚያበሳጭ ቢሆንም፣ የጋዜጠኞቹን ሐሳብ ትክክለኛነት የሚያረጋግጡና ቀደም ብዬ ከጠቀስኳቸው መገለጫዎች ጋር የሚገናኙ ተግባራትን ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የኖሩ ዛሬም አጠገባችን የሚገኙ ግለሰቦችን በማስረጃነት ማቅረብ ከባድ አይደለም፡፡ ማስረጃዬን ወደ ኋላ ሄጄ ስጀምር ‹ባንዲራ ጨርቅ ነው፣ እንኳንም ከናንተ ተወለድን፣ አክሱም ለወላይታው ምኑ ነው፣ ሌብነት ሥራ ነው›፣ ወዘተ. ዓይነት ንግግር በአደባባይ መናገር ማሰብ አለመቻል የፈጠረው አላዋቂነት አይመስላችሁም ወገኖቼ? በተነባበረ የአለት ክምችት የተሞላ አካባቢ ይዘው ከሌሎች አካባቢዎች ለመዝረፍ ባቀዱትና በተገበሩት ድብቅ ተልዕኮ ተስፋ በማድረግ፣ ሪፐብሊክ እንመሠርታለን ብለው ካርታ መንደፍም እኮ መነሻው ቅዠት ወይም ማሰብ መቻል ነው፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት በተሸከምነው የጭቆና፣ የሰቆቃና የመከራ ዘመን በኢትዮጵያውያን የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች የተካሄዱትም፣ እንደ ሰው በሚያስቡ ፍጡራን ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም፡፡ ከየብሔረሰቦቹ የተመለመሉና በባንዳነት ሲያገለግሉ፣ ወገኖቻቸውን ጌቶቻቸው በገነቡት የጨለማ እስር ቤት እየከረቸሙ  አካላቸው እንዲጎድል አሳልፈው ሲሰጡ የኖሩ፣ ዛሬም ራሳቸውን እንደ እባብ ቆዳ ሸልቅቀው ወደ ለውጡ አካል በማስጠጋትከደሙ ንፁህ ነኝ› ብለው በሥልጣን የቀጠሉ ግለሰቦችም ሆድ እንጂ ህሊና ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ይህ ማስረጃ የሚያረጋግጠው ከዛሬ 27 ዓመታት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ማሰብ የማይችሉ ጥቂት ግለሰቦች የሠሯቸውን ሥራዎች ነው ቢባል ስህተት የሚሆን አይመስለኝም፡፡

ያው ማሰብ አለመቻል የሚገለጸው በንግግር ወይም በተግባር ስለሆነ ለሐሳቤ ማጠናከሪያ የሚሆኑ ቅዠት ወይም ቀቢፀ ተስፋ የወለዳቸውንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲነገሩ የሰማኋቸውን አስገራሚ ንግግሮችን ልጨምር፡፡ የተነባበሩ የድንጋይ አለቶች የታጎሩበትንና ለሦስት ወራት እንኳ የማይበቃ ቀለብ በማይመረትበት አካባቢ እንደሚኖሩ እየታወቀ፣ በየአደባባዩ የመገንጠል ድቤ መደለቅ ህሊና ያለው ሰው ያደርገዋል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ምናልባት ቅዠታቸውን ሊነግሩን ወይም ሊያስፈራሩን ከሆነም ማሰብ አለመቻላቸውን የበለጠ ከመረዳት ውጪ፣ ንግግራቸው የማያስደነግጠን መሆኑን ልነግራቸው እፈልግለሁ፡፡ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን እንቅስቃሴ በተደረገ ቁጥር  ከሕገ መንግሥት ይከበር የሚል ቁጭት ወለድ ነጠላ ዜማ ማላዘንም ማሰብ አለመቻል ውጤት መሆኑን አልጠራጠርም፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥት ማክበር ማለት የወገኖቻችንን አካል ያስቆረጠ፣ ለጅብ የሰጠና መሰል አሰቃቂ ኢሰብዓዊ ተግባራትን ሲፈጽምና ሲያስፈጽም የኖረን ወንጀለኛ አሳልፎ አለመስጠት መሆኑን ሊረዱበት የሚያስችላቸው ህሊና የላቸውምና ልፈርድባቸው አልችልም፡፡

ለብሔሮችና ብሔረሰቦች ነፃነትና መብት፣ ለሃይማኖት እኩልነት ታግያለሁ፣ መስዋዕትነት ከፍያለሁ እያለ ሲያቅራራብን፣ ሲፎክርብንና ሲያደነቁረን የኖረ ቡድን የአክሱም ሙስሊሞች መስጊድ እንዳይገነቡ ሲከለከሉ ጆሮ ዳባ ማለቱ ማሰብ ባለመቻሉ መሆኑን መናገር ስህተት አይመስለኝም፡፡ የወልቃይትንና የራያን ሕዝቦች የማንነት ጥያቄ በጠመንጃ ለማፈን መሞከርና መብታቸውን የጠየቁ ዜጎችን በየእስር ቤቶች እያጎሩ ማሰቃየት፣ የአዋጁን በጆሮ ዓይነት በለመደው የሐሰት ፕሮፓጋንዳው የዜጎችን ጥያቄ አቅጣጫ ለማስቀየር መንደፋደፍም፣ ማሰብ ከሚችል ግለሰብም ሆነ የቡድን አባላት የሚጠበቅ ነው አያሰኝም፡፡

እነዚያ ሲያንጫጩን ያረፈዱ ጋዜጠኞች ከኢትዮጵያውያን ማሰብ አይችሉም ያሉት ከምንም ተነስተው አልነበረም ለማለት ያስቻሉኝ ሌሎች ተግባራት ደግሞ፣ በዚህ የለውጥ ዘመን በየአካባቢው የተከሰቱና የታዘብኳቸው ሁኔታዎች ናቸው፡፡ ይህን እውነታ የሚያረጋግጡልኝም በተለያዩ የአገራችን አካባበቢዎች የተፈጸሙ ድርጊቶችና በተለያዩ ሚዲያዎች የተሰጡ መግለጫዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያውም ማረጋገጫ በተወካዮች ክር ቤት የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመመለስ የሚያስችል አዋጅ በሚፀድቅበት ጊዜ የተመለከትኩት ግብ ግብ ነው፡፡ ምክንያቱም አዋጁ እንዳይፀድቅ የአንገታቸው ጅማት እስኪበጠስ ድረስ ሲቃወሙና ሲወተውቱ የነበሩ 33 የምክር ቤት አባላት እንደዚያ ሲናገሩ የነበረው በሉ የተባሉትን ለማለትና ጌቶቻቸውን ለማስደሰት ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች የምክር ቤት አባላትን እናሳምናለን ወይም እንዳለፉት 27 ዓመታት የገዥነት መብታችን እኛ ያልነው ነው የሚፈጸመው ብለው ከሆነ ያስፈራሩን ማሰብ የሚችሉ ናቸው ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ምክንያቱም አንዱ የማሰብ አለመቻል ማረጋገጫ ወቅትን አለመረዳትና ትናንት በቆሙበት ቦታ መገኘት ነው፡፡

ከእነዚህ የምክር ቤት አባላት የባሰምአዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጋጫል፣ ሌላ ችግር ይፈጥራል፣ ተግባራዊ ከሆነም እንከሳለን› እያሉ ሲያላዝኑና ሲያስፈራሩን የነበሩት አንዳንድ ጎጠኛ የሕግ ባለሙያዎችና ዩኒቨርሲቲ ፖለቲከኛ ተብዬዎች የሰጡት ጭፍን አስተያየትም፣ ማሰብ የማይችሉ ወይም ህሊና አልባ ጥቂት ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ በሚዲያ በቀረበ ቁጥርለውጡን ያመጣነው እኛ ነን፣ የትግራይ የበላይነት አልነበረም› እያለ የአዋጁን በጆሮ ሊነግረን የሚሞክረውና የወገኖቹን የመብትና የነፃነት ጥያቄ በሆዱ የለወጠው ፖለቲከኛም፣ የጋዜጠኞቹን አስተያየት የሚያረጋግጥ መሆኑን የሚክድ የለም፡፡ ከዚህ የበለጠም ህሊናቸውን ያኔ ጫካ ውስጥ ጥለው ነው እንዴ የመጡት የሚያሰኝ ሌላ ጉድ ልናገር፡፡

ግለሰቧ የፖለቲካ ቡድን አባል ናቸው፡፡ ከስድስት ወራት በፊት ይመስለኛልኢሕአዴግ ወደ ድሮው ማንነቱና አቋሙ መመለስ አለበት› በማለት ፀፀታቸውንና ፍላጎታቸውን ገለጹልን፡፡ በቅርብ ጊዜ ደግሞሕወሓት የሚያሸማቅቅ ታሪክ የለውም› ብለው አረፉ፡፡ በእውነት የሚገርም አስተያየት ነው፡፡ ለመሆኑ ኢሕአዴግ ወደ ዱሮው ማንነቱና አቋሙ መመለስ አለበት ማለት ምን ማለት እንደሆነ አውቀው ነው? ወይስ የዘረፋና የጭቆና ዕቅዳቸውን አለመጨረሳቸው ቆጭቷቸው ነው የተናገሩት? ምክንያቱም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ‹ኢሕአዴግ ወደ ዱሮው ማንነቱና አቋሙ ይመለስ› ማለት የሚሰጠን ትርጉም እኮ ልንቀበለው ቀርቶ፣ ልናስበው የምንፈልገው እጅግ ዘግናኝ አባባል ነው፡፡ የንግግሩ ባለቤትም ማሰብ ቢችሉና ዕውቀት ያራቃቸው ቢሆኑ ኖሮማ 27 ዓመታቱን ወያኔ መራሽ ኢሕአዴግ ይመለስ አይሉም ነበር፡፡ በባለሥልጣኗ አባባል መሠረት የዱሮው ኢሕአዴግ ይመለስ ማለት ለእኛ የሚሰጠን ትርጉም እኮ ያለፈው የሩብ ምዕተ ዓመት የወያኔ ቅኝ ግዛት ሥርዓት፣ የሌብነትና የዘረፋ ተግባራት፣ በዜጎች ላይ ይፈጸም የነበረው የእስራት፣ አካል የመቁረጥና የመግደል፣ የሥቃይና የጭቆና ዘመን ይደገም የሚል ነው፡፡ ታዲያ ይህ አነጋገር ማሰብ ከሚችል ግለሰብ አንደበት እንዴት ሊወጣ ይችላል ወገኖቼ?

ማሰብ የሚችሉ ቢሆኑና እንደ መልዓክ የሚቆጥሩት መሰሪ መሪያቸው በነገራቸውና መቼም ቢሆን ተግባራዊ የማይሆን ሪፐብሊክ የመመሥረት ቅዠት ሌት ተቀን ባይናውዙ ኖሮማ፣ የሚያሸማቅቅ ታሪክ እንደሌላቸው አይነግሩንም ነበር፡፡ የሚገርም ነው እኮ እናንተዬ፡፡ መብታቸውን የጠየቁ ዜጎችን በድብቅ ጨለማ እስር ቤቶች እያጎሩ ማሰቃየት፣ እግርና እጅ መቁረጥ፣ ጥፍር መንቀል፣ በአፍንጫ ቀዳዳ እስኪሪቢቶ እየሰነቀሩ ማሰቃየት፣ በብልት ላይ ኮዳ እያንጠለጠሉ ማኮላሸት፣ ሰውን ያህል ክቡር ፍጡር በአስፋልት ላይ አጋድሞ በኦራል መኪና መጨፍለቅ፣ ዜጎችን ከአውሬ ጋር ማሰርና በአውሬ ማስበላት እንዴት የሚያሸማቅቅ ታሪክ ሊሆን አይችልም? ምክንያቱም በየትኛውም ዓለም ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ዘግናኝና ኢሰብዓዊ ድርጊት፣ በዜጎች ላይ መፈጸም የማያሸማቅቀው ማሰብ የማይችል ሰው ብቻ ነውና፡፡ የራሱ የጭፍጨፋ ተግባር አልበቃው ብሎ እንደ ፋሽስቱ ቅኝ ገዥ ጣሊያን ወይም እንደ 19ኛው ክፍለ ዘመን ጨካኝ ቅኝ ገዥዎች በማሰብ ተከባብሮና ተቻችሎ የኖረን ሕዝብ በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል ደም ያፋሰሰና ያፈናቀለ፣ የአማራን ብሔር ለማጥፋት ማኒፌስቶ አዘጋጅቶ ሲንቀሳቀስ የኖረ ቡድን መሸማቀቅ የለበትም ብሎ በድፍረት መናገር፣ የማሰብ አለመቻል ውጤት ነው ማለት ስህተት ሊሆን አይችልም፡፡ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ከሚገፉ ደሃ ኢትዮጵያውያን ጉሮሮ ተነጥቆ ለፕሮጀክቶች ማሠሪያ የተሰበሰበን ገንዘብ መዝረፍ፣ አውሮፕላንና መርከብ መስረቅ ወይም እንዲሰርቁ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ካላሸማቀቀ ሌላ ምን የሚያሸማቅቅ ተግባር ሊኖር ይችላል? የጥፋት ኃይሎችን በማደራጀትና በዘረፉት ገንዘብ ስፖንሰር በማድረግ ዜጎችን ደም ማቃባትና ከቦታቸው በማፈናቀል ለዕልቂትና ለሰቆቃ ኑሮ መዳረግ የሚያሸማቅቅ ታሪክ የማይሆነውም ማሰብ ለማይችሉ ግለሰቦች ብቻ ነው፡፡

ለነገሩ ማሰብ የማይችሉት የጠቀስኳቸው ጥቂት ግለሰቦች ብቻ አይደሉም፡፡ ከለውጡ በፊትና በኋላም በሌሎች አካባቢዎችም የሚገኙ ጥቂት ግለሰቦች የሚናገሩት፣ የፈጸሟቸውና እየፈጸሟቸው ያሉት ተግባራትም ማሰብ የማይችሉ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ለእዚህ አባባል ማስረጃ ከሚሆኑት ተግባራት ፈጻሚዎች መካከል በግንባር ቀደም የሚጠቀሱትም አንዳንድ የሶሻል ሚዲያ አርበኞችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህን በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦችን ማሰብ አይችሉም የሚያሰኛቸውም፣ ከሚዲያ ባለሙያነትና ከተማረ ሰው መለኪያ አኳያ ሲመዘኑ ነው፡፡ ጥንት የነበሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አንባቢዎችና አዳዲስ ሐሳብ አፍላቂዎች ከመሆናቸውም በላይ፣ አገራቸውንና መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚወዱ ነበሩ፡፡ በሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎችን እንደ እህት ወንድማቸው የሚወዱ፣ ለአገራቸው አንድነትና ለሕዝቦቿ ታላቅነት የሚታገሉ ነበሩ፡፡ የብሔርተኝነት ስሜትም ሆነ የጥላቻ አመለካከት የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ አስተሳሰብ የተጎናፀፉና ማንም ተነስቶ የተዛባ አመለካከቱን የማይጭንባቸው፣ የጠማማ አስተሳሰብ ሰለባና ምርኮኛ የማይሆኑ፣ የራሳቸው አቋም ያላቸው ምርጥ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡

1983 .. ወዲህ ባሉት ዓመታት በዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ በአንዳንድ ተማሪዎች አማካይነት የተከሰቱ ሁኔታዎች ግን፣ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚጠበቁ ብቻ ሳይሆኑ በእጅጉ አሳፋሪም ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡ እንዲህ ለማለት የደፈርኩትም 27 ዓመታት የሌብነትና የውንብድና ሥርዓት ከዘረፉት ገንዘብ በሚያንጠባጥቡላቸው ምፅዋት ሆዳቸውን እየሞሉ፣ አብረዋቸው በሚማሩ ጓደኞቻቸው (ተማሪዎች) ላይ ቢለዋ የሚመዙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አሳፋሪ ድርጊት ሲፈጸም በማየቴና በመስማቴ ነው፡፡ በጣም ጥቂት ቢሆኑም በዚህ በሠለጠነ ዘመን የሌሎች ግለሰቦችና ቡድኖች አስተሳሰብ የተጫነባቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማየት በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ለህሊናቸው ሳይሆን ለሆዳቸው ያደሩ የፌስቡክ አርበኞችም ቢሆኑ የሚሠሩት ሥራ ህሊና ካለውና ከተማረ ዜጋ የሚጠበቅ ነው ብሎ ለማሰብ ይከብዳል፡፡ የጥቂት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ሆነ የሶሻል ሚዲያ አበጋዞች ድርጊት ዕውቀት ያጠረው ነው የሚያሰኘውም፣ በእነሱ ጫጫታና ግርግር ለውጡ ይቀለበሳል ብለው መቃዠታቸው ነው፡፡ ወገኖቹንና ደጋፊዎቹን በጨለማ እስር ቤት እያጎረ ሲገርፍ፣ አካላቸውን ሲቆርጥና ሲገድል፣ የአሸባሪነት አዋጅ አውጥቶና በአሸባሪነት ፈርጆ ሲያሳድደው ከኖረ ቡድን ጋር ግንባር ገጥሞ አሸሸ ገዳሜ የሚል የፖለቲካ ድርጅትም ማሰብ ይችላል ለማለት አይቻልም፡፡

በግፍ የተገደሉ ወገኖቹንና ደጋፊዎቹን በከንቱ የፈሰሰ ደም ዋጋ ነስቶና አሳዳጆቹ በመሸጉበት ከተማ የሬዲዮ ጣቢያ አቋቁሞ፣ የፈጠራና የቅዠት ዲስኩር መቀባጠርም ማሰብ ከሚችል ፖለቲከኛ የሚጠበቅ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ቃለ መጠይቅ በተደረገላቸው ቁጥር የድርጅታችን ግብ በክልላችን የብሔራችንን የበላይነት ማረጋገጥ ነው የሚል የቅዠት ወግ መጠረቅም፣ ማሰብ ከሚችል 21ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲከኛ አንደበት ሊወጣ የሚችል አይደለም፡፡ በግለሰብ የፌስቡክ ጥሪ በመነዳት በየጎዳናው የሚግተለተሉ ወጣቶችም ምኞታቸውን የሠለጠነው ዘመን የማይፈቅደው ስለሆነ፣ እኔም ለጽሑፌ መነሻ እንደሆኑኝ ጋዜጠኞች እነዚህ ግለሰቦች ማሰብ መቻላቸውን እጠራጠራለሁ፡፡

ሁሉም ዜሮ ዜሮ ብሎ ሲያላዝን የኖረ አዝማሪ ለሆዱ ተገዝቶ ሲቃወመው ለነበረ ጎጠኛ ቡድን ማጎብደዱ ግለሰቡ ማሰብ የማይችል መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ ራሱም በፍጡራን መለኪያ የማይመዘን ዜሮ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህ ዜሮ ግለሰብ አሳፋሪ ማንነት ጋር የሚመሳሰል ሰብዕና ያላቸው ደግሞ፣ የቅማንትን ማኅበረሰብ የረጅም ዘመን ታሪክ የሚያረክስ አሳፋሪ ተግባር እየፈጸሙ የሚገኙና በወያኔ የተገዙ ባንዳዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም የቅማንት ማኅበረሰብ የራስን በራስ የማስተዳደር መብት በሚል ሰበብ ጌቶቻቸው የነገሯቸውንና ደጋግመው ያሠለጠኗቸውን አፍራሽ ተልዕኮ ለማስፈጸም፣  ለአምስት ሚሊኒየም አብሯቸው የኖረው የአማራ ብሔር ጠላት ከሆነ ከፋፋይና ጎጠኛ የፖለቲካ ድርጅት ጋር ወግነው የብጥብጥና የዕልቂት ነጋሪት መጎሰማቸው ማሰብ ይችላሉ የሚያሰኝ አይደለም፡፡ናልባት ድርጊታቸው ጌቶቻቸውን ያስደስት እንደሆነ እንጂ እንኳን የቅማንትን ሕዝብ ራሳቸውንም የሚጠቅም አይደለም፡፡ ቅዠታቸው የህልም እንጀራ ሆኖ ይቀራል እንጂ የምፅዓት ቀን ሲቃረብ እንኳ በምኞታቸው አፋፍ ቢደርሱ፣ በወገኖቻቸው ላይ ሲፈጽሙት እንደኖሩት ደባ በማጅራታቸው እንደሚያራምዷቸው መናገር ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡ እነዚያ ጋዜጠኞች ማሰብ አይችሉም ብለው ገመናችንን ለዓለም ሕዝብ የገለጹትም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ እኔም ከአንዳንድ ድርጊቶችና ሁኔታዎች በመነሳት ጥቂትም ቢሆኑ ማሰብ የማይችሉ ኢትዮጵያውያን አሉ ለማለት የደፈርኩትም ማሰብ ባለመቻል የሚፈጸሙ ድርጊቶች፣ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ብቻ ሳይሆን ማሰብ ለማይችሉትም ቢሆን የማይጠቅሙ መሆናቸውን ለማስረዳት ነው፡፡ አንባቢያንም ሆኑ የጽሑፌ መልዕክት የደረሳቸው ወገኖቼ ታዲያ የሚበጀውና የሚያዛልቀው የቱ ነው? ብለው በስህተት ጎዳና የሚንከላወሱ ወገኖቻችንን ወደ ትክክለኛውና ሁላችንንም ወደሚጠቅም አቅጣጫ የሚመለሱበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማሳሰብ ነው፡፡ መልዕክቴን የምቋጨውም የጽሑፌን ዓላማ እንደገና በማስታወስና ከመላው ኢትዮጵያውያን የምጠብቀውን ተግባር በመግለጽ ነው፡፡

በመጀመሪያ ለማሳሰብ የምፈልገውም ማሰብ አለመቻል የሰው ወይም የሰብዓዊ ፍጡር መለኪያ አለመሆኑን ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም ህሊና ቢስ መሆንና ደመ ነፍሳዊ የእንስሳ ፀባይ ማሳየትም ሆነ የአውሬ ተግባር መፈጸም፣ ለሰው ልጅ የተፈቀደ አለመሆኑን መረዳት በራሱ ትልቁ ዕርምጃ ነው፡፡ ሰብዓዊ ፍጡር ማለት በተለይም 21ኛው ክፍለ ዘመን ሰው የሚባለው ፍጡር ተግባራዊ በማይሆን ቅዠት ተወጥሮ፣ ለምሳሌ ለውጡን ቀልብሶና እንዳለፉት ዓመታት በኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ የጭቆና ቀንበር በመጫንና የአገር ሀብት በመዝረፍላም አለኝ በሰማይ› ዓይነቷን ሪፐብሊክ ለማቋቋም መሥራት አለብኝ ከሚል የጫካ ህልም ወጥቶ፣ ወደ ዕውኑ ዓለም ለመመለስ ያስችለዋል፡፡ በዚህ ዘመን ሊሆን ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል ጭካኔ የተሞላበት የእንስሳ ተግባር በመፈጸም የሕዝብ ጠላት መሆን አክሳሪ እንጂ አትራፊ አለመሆኑን በመገንዘብ፣ ራስን ማንቃትና ከዘመኑ ጋር መራመድ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛው መልዕክቴ ማሰብ አለመቻል የሚጎዳው ሁሉንም የሰው ልጆች ነው የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን ማሰብ ባለመቻሉ በሚፈጽማቸው እኩይ ተግባራት የሚጎዳው የተወሰነ አካል ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ ድርጊቱን ያስፈጸመውም የፈጸመውም ግለሰብና ቡድን መሆኑን ከሌሎች አገሮች ታሪክ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

መፍትሔ የሚሆነውም ማሰብ የሚችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ግለሰቦች ሁሉም ዜጋ የአመለካከት ለውጥ የሚያመጡበትን ጥረት ማድረግ ነው፡፡ በቅዠት የሚናውዙ ግለሰቦችና ቡድኖች ወደ ቀልባቸው የሚመለሱበትን ድጋፍ በማድረግና መልካሙን ሁሉ በማሳየት ከጥፋታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ማሰብ የማይችሉ ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች እኩይ ዓላማና ተግባር አስፈጻሚ አለመሆንም ዋናው መፍትሔ መሆኑ መታወቅ ያለበት መሆኑን እየገለጽኩ፣ ማሰብ አለመቻል የሕዝብና የአገር መልካም ገጽታ የሚያበላሽ፣ ወገን የሚያዋርድ አደገኛ በሽታ ስለሆነ ፈጣሪ ማሰብ እንዲችሉ ያደርጋቸው ዘንድ እፀልይላቸዋለሁ፡፡ አሜን፡፡

   ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...