Saturday, December 2, 2023

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከማቋቋም ባሻገር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ታላቅ ተስፋ አጭሮ የነበረው ምርጫ 97 የአገሪቱን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደት አንድ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል በማለት ብዙዎች የጠበቁት ጅማሮው መልካም ስለነበረ ነው፡፡ ነገር ግን ፍፃሜው በእስርና በግድያ ከመጠናቀቁም በላይ፣ አጠቃላይ የአገሪቱን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ጭራሹን ቁልቁል የሰደደና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴን ቅርቃር ውስጥ የከተተ በመሆን አልፏል፡፡

የምርጫው ዋዜማ ላይ የነበሩ ውይይቶች፣ ክርክሮችና የምረጡኝ ቅስቀሳዎች የብዙዎችን ቀልብ ከመሳብ ባለፈ ለብዙዎች የተስፋ ስንቅ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የምርጫውን መጠናቀቅን ተከትሎ የተፈጠሩት ሁከቶች፣ ግድያዎችና እስራቶች ተስፋውን በማጨለም ወደ ቀቢፀ ተስፋነት ቀይረውታል፡፡

ምርጫ 97 በዚህ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ተከርችሞ ስለነበረ፣ የተቃውሞ ጎራው የፖለቲካ ፓርቲዎች ገዥውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ለመፎካከር አይደለም፣ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን እንኳን በቅጡ ማከናወን አለመቻላቸው የአደባባይ ሚስጥር ነበር፡፡

ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ ወደ መድረክ ከመጡት በርካታ አዋጆች፣ ሕጎችና አሠራሮች መካከል የሚጠቀሰው ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥነ ምግባር ደንብ ሲሆን፣ ደንቡን ተከትሎ የሚቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጉዳይ ነበር፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥነ ምግባር ከወጣ በኋላ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ እንዲሁም የኢዴፓ፣ የመኢአድና የመሳሰሉት ፓርቲዎች አመራሮች ሰነዱን ከኢሕአዴግ ጋር ለሚኖር ግንኙነት፣ ውይይትና ድርድር ሊጠቅም ይችላል በማለት ፈርመውት ነበር፡፡ በወቅቱ ከምርጫ 97 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የመኢአድ ሊቀመንበር የነበሩትና ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት አቶ ኃይሉ ሻውል (ኢንጂነር) ከአቶ መለስ ጋር በአንድ መድረክ ተገናኝተው ከተፈራረሙ በኋላ መጨባበጣቸው መነጋገሪያ ነበር፡፡

በተቃራኒው መድረክና ሌሎች ፓርቲዎች ደግሞ ከኢሕአዴግ ጋር ለሚኖር የድርድርም ይሁን የክርክር ወይም የውይይት ሒደትን በሚመለከት፣ የቀረበው ደንብ አፋኝ ነው በማለት ተቃውሞ በማሰማት ሰነዱን አልፈረሙም ሰነድ ነበር፡፡

ወደኋላ ላይ መመልከት እንደተቻለው የሥነ ምግባር ሰነዱን መፈረም በተቋቋመው የጋራ ምክር ቤት ውስጥ ለመሳተፍና ከኢሕአዴግ ጋር በማንኛውም ጉዳይ ለመወያየት እንደ ቅድመ ሁኔታ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ ኢሕአዴግ ከመድረክና መሰል ሰነዱን ካልፈረሙ ፓርቲዎች የእንወያይ ጥያቄዎች ሲቀርብለት መጀመርያ ሰነዱን ፈርሙ የሚል ምላሽ ይሰጥ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፣ በተለይ መድረክ ደግሞ በጉዳዩ ላይ ያለውን ልዩነት የሚገልጹ በርካታ መግለጫዎችን ያወጣ እንደነበርም እንዲሁ ይታወሳል፡፡

ወደ ቅርብ ጊዜው ትዝታ መለስ ሲባል ደግሞ የዛሬ ዓመት ወደ ሥልጣን በመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር አማካይነት አፋኝ የተባሉ አዋጆችንና አሠራሮችን ለማሻሻል እየተሠራ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ የተለያዩ ሕጎች መሻሻል አለባቸው ተብለው ከተለዩት መካከል የሚጠቀስ ሲሆን፣ የምርጫ ቦርድ ማሻሻያ አዋጅም ለተወካዮቾች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ቦርዱም አዲስ ሰብሳቢ ተሹሞለት በፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች የሚያርቁ ደንቦችን እያወጣ ነው፡፡

የፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማረቅ የምርጫ ቦርድ ኃላፊነቱን ከመውሰዱ አስቀድሞ ግን በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ ወደ አገር ቤት የገቡትንም፣ አገር ውስጥ ከሰነበቱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የግማሽ ቀን ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከሁሉም አስቀድሞ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚደረጉ ቀጣይ ውይይቶች፣ ድርድሮች፣ እንዲሁም ንግግሮች የሚመሩበት ሥነ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊነት መሆኑን በአጽንኦት ተናግረው ነበር፡፡

ይህንንም እንዲያስፈጽምና እንዲያመቻች ለምርጫ ቦርድ ኃላፊነቱንና የቤት ሥራውን ሰጥተው ነበር፡፡ ስለሆነም በወቅቱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችና አመራሮች አሉን የሚሏቸውን ጥያቄዎችና ቀጣይ ግንኙነታቸው እንዴት መመራት እንደሚኖርበት የሚያትት ሐሳባቸውን ለቦርዱ በጽሑፍ ለማቅረብ ተስማምተው ነበር፡፡

በዚህ ሒደት ውስጥ ያለፈው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የገዥው ፓርቲና የምርጫ ቦርድ ቀጣይ አቅጣጫን የሚመራው ‹‹በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት፣ እንዲሁም በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሠራር ሥርዓት ቃል ኪዳን›› ሰነድን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ከአንድ ወር በፊት ተፈራርመዋል፡፡

ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኅዳር ወር የፓርቲዎቹን ቀጣይ ግንኙነት የሚመራ የሥነ ሥርዓት ደንብ ያስፈልጋል ሲሉ፣ የፓርቲዎች ቁጥር 80 አካባቢ የነበረ ቢሆንም የቃል ኪዳን ሰነዱን የፈረሙ ፓርቲዎች ቁጥር ግን ወደ 107 አሻቅቧል፡፡

የዚህ የቃል ኪዳን ሰነድ መፈረምን ተከትሎ ደግሞ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ስብሰባ ያካሄዱት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና የምርጫ ቦርድ አመራሮች ደግሞ፣ የጋራ ምክር ቤት ለማቋቋም የሚያስችለውን ደንብ አፅድቀዋል፡፡

ይህ ደንብ በቀጣይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማረቅ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል የተባለ ሲሆን፣ ፓርቲዎችም ለሚገጥማቸው ችግር በጋራ በመወያየት፣ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥና ለመተለም እንደሚረዳም ታምኖበታል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጋራ ምክር ቤትና የሥነ ምግባር ደንብ መታጠፍ አሊያም ደግሞ አዲስ በተቋቋመው የጋራ ምክር ቤት መተካቱ ይፋ ባይደርግም፣ አዲሱ ምክር ቤት የቃል ኪዳን ሰነዱን አተገባበር ከመከታተል ጀምሮ በፓርቲዎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን የመፍታት ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ዓርብና ቅዳሜ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የተሰበሰቡት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና የቦርዱ አመራሮች፣ የጋራ ምክር ቤቱ ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ በመወያየት አፅድቀውታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢን መርጠዋል፡፡

በዚህም መሠረት የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሙሳ አደም የፓርቲዎቹ የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል፡፡ በዚህም መሠረት በቃል ኪዳን ሰነዱ ክፍል ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሚለው ድንጋጌ አንቀጽ 14(4) መሠረት፣ ሰብሳቢው ለመጪዎቹ ስድስት ወራት የጋራ ምክር ቤቱን በስብሳቢነት ይመራሉ፡፡

ከጋራ ምክር ቤቱ ምሥረታ አስቀድሞ በ107 ፓርቲዎች አማካይነት የተፈረመው የቃል ኪዳነ ሰነድ የጋራ ምክር ቤቱ ዓላማን በተመለከተ በአንቀጽ 15 እና 16 የጋራ ምክር ቤቱን ዓላማ፣ ተግባርና ኃላፊነትን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡

በዚህም መሠረት የጋራ ምክር ቤት ዓላማን በተመለከተ፣ ‹‹በአገራችን የተጀመረውን የዴሞክራሲ ግንባታ ሪፎርም ለማጠናከርና የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለባቸውን ሕጋዊ ኃላፊነት በዚህ የቃል ኪዳን መሠረት ለማስፈጸም ተቋማዊ አካል ሆኖ ማገልገልና በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲዎችና በመንግሥት መካከል አለመግባባቶች ሲከሰቱ በውይይትና በመግባባት ለመፍታት የሚያስችል ውይይትና የምክክር አካል ሆኖ ማገልገል፣ እንደሁም በፈራሚዎች መሀል የተፈጠሩ ግጭቶች በዚህ ሰነድ አግባብ ውሳኔ  መስጠት፤›› መሆኑን ያመላክታል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ተግባርና ኃላፊነትን በሚመለከት ደግሞ፣ ‹‹ለዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ፓርቲዎች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ያበረታታል፣ ይደግፋል፣ በፓርቲዎች መካከል በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በሚነሱ አለመግባባቶችና ጥያቄዎች ላይ በመወያየት ችግሮችን የሚፈታ መድረክ ሆኖ ያገለግላል፣ የቃል ኪዳን ሰነዱን ይዘት አስመልክቶ ፓርቲዎች ለአባሎቻቸውና ለደጋፊዎቻቸው ትምህርት መስጠታቸውን ያረጋግጣል፣ የቃል ኪዳኑ ሰነዱ በሁሉም ፈራሚዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፈጻሚ መሆኑን ይከታተላል፣ ያረጋግጣል፣ ወዘተ›› የሚሉትን ያካተተ ነው፡፡

እነዚህ ከላይ የተመለከቱት የጋራ ምክር ቤቱ ዓላማ፣ ተግባርና ኃላፊነትን የሚመለከቱ ጉዳዮች በ2002 ዓ.ም. ከወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ሥነ ምግባር ለመደንገግ በወጣው አዋጅ መሠረት ከሚቋቋመው የጋራ ምክር ቤት ዓላማ፣ ተግባርና ኃላፊነት ጋር በአብዛኛው ተመሳሳይ እንደሆኑ ሁለቱን በማነፃፀር መረዳት ይቻላል፡፡

ከዚህ አንፃር የጋራ ምክር ቤት ከማቋቋምን የተለያዩ ሰነዶችን ከመፈራረም  በዘለለ መንግሥትም ሆነ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአገሪቱን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ለማሳለጥ በሚያስፈልጉና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ሌሎች ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ ውይይት መኖር እንደሚገባ የሚጠቁሙ አሉ፡፡        

የቃል ኪዳን ሰነዱም ሆነ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ማቋቋም ጉዳይ በተለይ አገሪቱ እየሠራችባቸው ያሉ የተለያዩ ሕጎች፣ አዋጆችና ደንቦች የማሻሻል እንቅስቃሴና በተለያዩ ቡድኖች ጥናት እየተደረጉ ያሉ ሥራዎችን ከግምት በማስገባት፣ እንዲሁም የተወሰኑት እንዲሻሻሉ እየቀረቡ ባሉበት ወቅት አጠቃላይ የሕግ ማዕቀፉን በመከተል ሊደረጉ የሚገባቸው ጉዳዮች እንደሆነ የሚጠቀሙም አሉ፡፡

ይህን የጋራ ምክር ቤት ለማቋቋም በሚያስችለው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የጋራ ምክር ቤቱ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ያልተመዘገቡ ፓርቲዎችን ሊያቅፍ አይገባም የሚለው ሐሳብ፣ እንዲህ ላሉ ሙግቶች የማጠናከሪያ ሐሳብ ይሰጣል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ላይ የተደነገጉ ክልከላዎች ይነሳሉ? ወይስ እንደነበሩ ይቀጥላሉ? አገር ቤት የገቡ ፓርቲዎች በቦርዱ ሳይመዘገቡ እንዴት ነው የፖለቲካ ሥራ የሚሠሩትና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው አዋጅ ሲስተካከል ብቻ ነው፡፡

በዚህ መሠረት ቦርዱ በፖለቲካ ፓርቲነት ያልመዘገባቸውን ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነዱን ፈርመዋል በሚል ብቻ የጋራ ምክር ቤቱ አባል ማድረጉ፣ በአዋጁ መሠረት ለሚመጡ ሕጋዊ ኃላፊነቶች በምን መሥፈርት ነው የሚያስተዳድራቸው? የሚል ጥያቄም ይነሳል፡፡

እነዚህን ጥያቄዎችና ሥጋቶች በጊዜ ምላሽ መስጠት በቃል ኪዳን ሰነዱ መግቢያ ላይ የሠፈረውን ጠንካራና ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት ከመሆኑ አንፃር፣ በሰፊው የጋራ ምክር ቤት ማቋቋምም ሆነ ሌሎች አሠራሮች በቅድሚያ ውስጥ ቢካተቱ መልካም መሆኑን የሚያሳስቡ በርካቶች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -