Friday, May 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የከተማ ፕላንና የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ህልምና ቅዠቶች

በብሩክ ሽመልስ

‹‹ዘ ማስተር ቢልደር›› ይሉታል በቅፅል ስሙ ሲጠሩት፡፡ በሚገባ የሚስማማው መጠሪያ ይመስላል፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ዓለማችን ካየቻቸው እጅግ ተፅዕኗቸው ጎልቶ ከሚታይ የከተማ ፕላነሮችና የሥራ መሪዎች ዋነኛው ነው፡፡ በአሜሪካ ኒውዮርክ ሜትሮፖሊታን አካባቢ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ በዘለቀው የሥራ ዘመኑ የኒውዮርክ ከተማን በግል ሐሳብና በራዕዩ ልክ ገልብጦ ሠርቷታል ብንል ጭራሽ እያጋነንን አይደለም፡፡

ሮበርት ሞስስ በሕዝብ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ ፖለቲከኛ አልነበረም፤ የመንግሥት ተቀጣሪ ሲቪል ሰርቫንት እንጂ፡፡ ከ1920ዎቹ እስከ 7ዐዎቹ አጋማሽ በዘለቀው ኒውዮርክ ዳግም እንደ አዲስ በተገነባችበት ረዥሙ የሥራ ዘመኑ እጅግ በርካታ የመንግሥት ቢሮዎችንና ፕሮጀክቶችን በመምራት በከተማዋ ከ650 በላይ የመጫወቻ ሥፍራዎችን፣ ከ416 ማይልስ የማያንስ በዛፍ የተከበቡ ጎዳናዎችን /Parkways/፣ የኒውዮርክን ኢኮኖሚ የቀየሩ 12 ታላላቅ ድልድዮችን፣ በአንድ ጊዜ ከ66 ሺሕ ሰው በላይ ማስተናገድ የሚችሉ አሥር ግዙፍ የመዋኛ ገንዳዎችን፣ እጅግ በርካታ ሕንፃዎችን፣ የከተማ ፓርኮችን፣ ወዘተ ፍፁም የግል ሐሳቡንና ፍልስፍናውን በሚያንፀባርቅ መንገድ ገንብቷል፡፡ ይህንን ሁሉ ሲፈጽም ግን መንገዱ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ላለማውም ሆነ ላጠፋው በርካታ ነገር ሞሰስ በአወዛጋቢ ሰብዕናው እስከ ዛሬ ይወሳል፡፡

ምክንያታዊነትና የከተማ ፕላን

ምክንያታዊነት (Rationalism) በሰዎች ሐሳብ ውስጥ እንደ ፍልስፍና መቀንቀን የጀመረው ከቅድመ ታሪክ ጀምሮ ነው፡፡ ምክንያታዊነትን ማቀንቀን ከጀመሩ የምዕራቡ ዓለም ፈላስፎች መካከል ፓይታጎረስ ከቀዳሚዎቹ ይጠቀሳል፡፡ እንደ ሒሳብ አዋቂነቱ ለቁጥር ማድላቱ ያመዘነ አሳቢ መሆኑን በሚያሳብቅ መንገድ ህላዌ ሙሉ በሙሉ በቁጥር ሊገለጽ እንደሚችል ለመግለጥ ‹‹ሁሉም ነገር ቁጥር ነው›› (All is Number) በሚለው ሐሳቡም ይታወሳል፡፡ ፕሌቶና አሪስቶትልን ጨምሮ ቀረብ እስካሉት ዴካርት፣ ስፒኖዛና አማኑኤል ካንት ድረስ የራሽናሊዝም ጽንሰ ሐሳብ በተለያየ ቅርፅና መጠን ከሰው ልጅ ታሪክ ጋር አብሮ የኖረ ነባር ፍልስፍና ነው፡፡

የእሳቤው መሠታዊ ትርክት የእውነት ምንጭ ስሜት ወይም ተሞክሮ (Sense or Empirical Evidence) ሳይሆን ምክንያት (Reason) ነው የሚል ነው፡፡ የዕውቀት ሁሉ ምንጭ ምክንያትና ምክንያት ብቻ ነች ይላል፡፡ የገሃዳዊውን ዓለም ስንክሳር ሁሉ በምክንያት መተንተንና መረዳት ይቻላል፡፡ ሌላ የዕውቀት ምንጭ ከቶ የለም ነው ጉዳዩ፡፡

እዚህ ጋር የተሳሳተ ሥዕል ላለመስጠት የኢማኑኤል ካንትን ሐሳብ ትንሽ ማብራራት ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ በእርግጥ ካንት ምክንያት የሞራል ምንጭ ነው ብሎ የሚያምን ፈላስፋ ነው፡፡ ሆኖም “The Critique of Pure Reason” በሚለው ሥራው በምክንያታዊውም ሆነ ልማዳዊው (Empiricist) እምነት ላይ ያለውን ተቃርኖ ገልጿል፡፡

ምክንያታዊዎቹን ሲተች ከምክንያታዊው ዓለም ውጪ ያሉ ምክንያት ዝንተ ዓለም የማይደርስባቸው እንደ ‹‹የእግዜር ህልውና›› እና ‹‹ከሞት በኋላ ሕይወት›› ዓይነት ነገሮችን (The Thing) በዚህ ዓውድ ሲገለጹ ወይም ሊታወቁ አለመቻሉን ያነሳል፡፡ ልማዳዊዎቹን ሲተች ደግሞ ልማድ ለዕውቀት አስፈላጊ መሠረታዊ ግብዓት ቢሆንም ያ ልማድ ወደ ወጥ ሐሳብነት የሚያድገው በምክንያት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ስለዚህ ልማድም፣ ምክንያትም የውቀት መሠረቶች ናቸው ይላል፡፡

እንግዲህ ይህ የምክንያታዊነት የፍልስፍና እሳቤ ያልነካው የሕይወት ዘርፍ ባለመኖሩ በከተማና በከተማ ፕላን ላይም በተለይ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰፊና ከባድ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ የትኛውም አስፈላጊና ትርጉም ያለው የሰው ልጅ ተግባር በበቂ ሁኔታ አስቀድሞ በታሰበ ረቂቅ መርህና ሕግ ሊገለጽ ይችላል ብለው የሚያምኑ፣ ታላላቅ ኃይልና ሥልጣን የጨበጡ፣ ተፅዕኗቸው ትውልድና ድንበር ተሻጋሪ የከተማ ፕላነሮች ብቅ አሉ፡፡ በእነዚህ ግለሰቦች ሐሳብ መሠረት ‹‹ትክክለኛውንና ጠቃሚውን›› ነገር ለመሥራት የሚያስፈልገው ብቸኛ ነገር ነገሩን መጀመርያ በትክክለኛው ኋልዮታዊ ቅርፅ (Theoretical Model) ማስቀመጥ ነው፡፡ በኋለኛው ዘመን የመጡ እሳቤዎች ኋልዮታዊ ግንዛቤዎች ከተግባራዊ ዕውቀት ላይ የሚበቅሉ ውጤቶች እንጂ የተግባር ምንጭ ወይም መሪዎች አይደሉም ብለው ቢከራከሩም ለአይዲያሊስቶቹ ምክንያታዊያን የከተማ መሪዎች ሥዕሉ ፍፁም የተገላቢጦሽ ነበረ፡፡

ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ አንስቶ እስከ አጋማሹ በዓለም ታላላቅ ከተሞች የተነሱ የከተማ ፕላነሮችና ህልቆ መሳፍርት ያልነበራቸው የሐሳባቸው ተከታይ አርኪቴክቶች፣ መሐንዲሶችና ከንቲባዎች የከተማ መንደሮችንና በአጠቃላይ ከተሞችን ሲያዩ የሚመለከቱት በሥርዓት ዲዛይን ያልተደረገ ምስቅልቅል (Chaos) ብቻ ነበር፡፡ እናም አብዛኞቹ ከተሞች በክፍለ ዘመናት በረቀቀ የሰዎች መስተጋብር ላበጁት ልዩ ከባቢ ፍፁም ትዕግሥት አልነበራቸውም፡፡ የከተሞች ታሪክን ያጠኑ አንዳንድ ጸሐፍት ሊኮቡዚዬ (Le Corbusier) የተባለው ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ተፅዕኖ ፈጣሪ አይዲያሊስት አርክቴክቶች አንዱ ዕድሉን ቢያገኝ ኖሮ ፓሪስን ‹‹ባማረና ሥርዓት በጠበቀ መንገድ›› እንደገና ይፈጥራት ነበር ይላሉ፡፡ በርግጥ ይህንን ለማድረግ ፍፁም አምባገነን መሆን ይጠይቅ ይሆናል፡፡ እዚህ ጋ ግን አምባገነኑ ዙፋኑ ላይ የተቀመጠ ንጉሥ አይደለም፡፡ የከተማው ፕላን እንጂ! ፍፁማዊ፣ ትክክለኛና እውነተኛ ፕላን!

ብራዚሊያ

በታኅሳስ ወር እ.ኤ.አ. 2012  ኦስካር ኔሜየር የተባለ አርክቴክት በ104 ዓመቱ ሲሞት ቢቢሲ አንድ ዘገባ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡ ኔሜየር በ1950ዎቹ መጨረሻ የብራዚል ዋና ከተማ የሆነችው ብራዚሊያ በጠፍ መሬት ላይ ከምንም ተነስታ ስትገነባ ዋና አርክቴክት በመሆን የተሳተፈ ሰው ነው፡፡ ዕቅዱ ቀላልና ግልጽ ነበር፡፡ የብራዚልን የኢኮኖሚ ዕድገት የምታፈጥን፣ አሮጌዋንና በችግር የተሞላችውን ሪዮ ዴጀኔሮን የምታስረሳ፣ ከቅኝ አገዛዝ ምልክቶች ነፃ የሆነች፣ በድህነት የተሞሉ ሠፈሮች (Slums) አልባ ከተማ መገንባት ነበር፡፡ ህልሙ ሰዎች በእግር ሳይሆን በተሽከርካሪ ብቻ የሚዘዋወሩባት፣ በፅዱ አውራ ጎዳናዎችና በሥርዓት የተሰደሩ መንደሮች የተሞላች ውብ ከተማ መፍጠር ነበር፡፡

በርግጥ ብራዚሊያ በሕንፃዎቿ ውበት ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የመዘገባት ሥፍራ ነች፡፡ ውብና ባለግርማ የሆኑ ሕንፃዎች!

‹‹ችግሩ ግን ብራዚሊያ ከተማ አይደለችም፣ ጉዳዩ የዚህን ያህል ቀላልና ግልጽ ነው›› ይላል በዘገባው የተጠቀሰው አንድ ባለሙያ፣ ‹‹ጥሩ ከተማ ወይም መጥፎ ከተማ ሳይሆን ብራዚሊያ ጭራሽ ከተማ አይደለችም፡፡ ከተማን ከተማ የሚያደርገው ግብዓት የላትም፡፡ ነዋሪዎቿ በየሳምንቱ መጨረሻ ሕይወት ወዳላቸው የአቅራቢያዋ ከተሞች ሳኦፖሎና ሪዮ ይተማሉ፡፡ በብራዚሊያ ሥራ የምትሄድበት፣ የምትገበያይበት ዞን አለ፡፡ ባለሥልጣናት የሚኖሩበትም ሠፈር ለብቻው አለ፡፡ ሁሉም ቦታውን ይዞ እንዲኖር ስለታቀደ የተለመደውን የከተማ ማኅበራዊ መስተጋብር መፍጠር ባለመቻሉ መንገዶቿ ሕይወት አልባ ናቸው፡፡”

ብራዚሊያ በተቀናጀና ዝርዝር የከተማ ፕላን ከምንም ተነስታ ተገነባች፡፡ የሥራ፣ የመኖሪያ፣ የመዝናኛ ሠፈሮቿ በሥርዓት ተሰደሩ፡፡ በራሽናሊስት ፕላነሮቿ ህልም ብራዚሊያ የወደፊቱ ዘመን ድንቅ ከተማ ነበረች፡፡ የህልም ዓለም ከተማ፡፡ ከብራዚላዊያን እሴትም ሆነ ከብራዚል ከተሞች ታሪክ የወረሰችው አንዳችም ነገር አልነበረም፡፡

ብራዚሊያ ግን ገና ከመነሻው ፕላነሮቿ የተመኙላትን መሆን እንደተሳናት ለሁሉም ታዛቢ ግልጽ ነበረ፡፡ በ1980ዎቹ መጨረሻ 75 በመቶ ነዋሪዎቿ በተከተማዋ ዕቅድ ውስጥ ፈፅሞ ባልታሰቡና ባልተፈለጉ መንደሮች ውስጥ በዘፈቀደ የሚኖሩ ዜጎች ነበሩ፡፡ በዚሁ ዘመን በዕቅድ የተነባችው ከተማ ግን ይኖራታል ተብሎ ከተጠበቀው የነዋሪዎች ቁጥር ግማሹን እንኳን አታኖርም ነበር፡፡ የከተሞች ምሳሌ ትሆናለች ተብሎ ሲጠበቅ ፍፁም በከፋ ማኅበራዊ ከፍፍል (Spacial Segregation) የምትታወቅ ጉደኛ ሥፍራ ሆና አረፈችው፡፡

ከተማ ግን ምንድነው? የጄን ጃኮብስ ሕመም

ጄን ጃኮብስ አስደናቂ ሴት ናት፡፡ አሜሪካዊ ደራሲት፣ ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች ነች፡፡ ከመደበኛ የትምህርት ተቋም ገብታ ያገኘችው ይህ ነው ተብሎ የሚቆጠር ዲግሪ የላትም፡፡ የሐሳቧ ተቀናቃኞችም ይህንን ቀዳዳ እንደ ደካማ ጎን በመቁጠር ድንቅ ሐሳቦቿን ለማጣጣል ሲጠቀሙበት ኖረዋል፡፡

በ1961 ዓ.ም. The Death And Life Of Great American Cities በሚል ርዕስ ዘመኑን በተቆጣጠሩ ራሽናሊስት የከተማ ፕላነሮች ላይ የተሰነዘረ በትር የሆነውን እስከ ዛሬ ድረስ በዓለም ላይ በከተማ ፕላን፣ ዕቅድና ተግባር ላይ ተፅዕኖው እጅግ የበረታ መጽሐፏን ይዛ መጣች፡፡

“This Book Is an Attack on Current City Planning And Rebuilding” ይላል መጽሐፉ ገና ሲጀምር፡፡ ‹‹አሁን ባለው የከተማ ፕላንና መልሶ ግንባታ አሠራር ላይ የተሰነዘረ ጡጫ ነው›› እንደ ማለት ነው፡፡

ጄን ከተሞች በዕቅድና በፕላን አይመሩ አትልም፣ ፈፅሞ፡፡ ለከተሞች የምንነድፈው ፕላን ከተሞችን የተረዳ፣ ከተማ እንዴት እንደሚሠራ የተገነዘበና ለዚህ የከተማ ልዩ ባህርይ ፍፁም ክብር ያለው ይሁን ነው ክርክሯ፡፡ ይህንንም ለማድረግ ከተሞች ሕይወታቸውን እንዴት እንደሚመሩ አበክሮ ማጤን እንጂ፣ ይህንን ሕይወት በሌላ ህልም የሚተካ ኋልዮታዊ ዕቅድ ማምጣት ከጥቅሙ ጉዳቱ እጅግ እንደሚገዝፍ ትመክራለች፡፡ ማንም ሰው አንድ ከተማ ምን መሆንና እንዴት መሥራት እንዳለበት ከመወሰኑ በፊት ‹‹ከተማ ምንድነው? እንዴትስ ይሠራል?” የሚሉትን ጥያቄዎች መረዳትና መመለስ ይኖርበታል ብላ ታምናለች፡፡   

ጃኮብስ በዘመኗ ሌ ኮቡዚዬና ሮበርት ሞስስን የመሳሰሉ በራሽናሊስት አስተሳሰብ የተሞሉ ግለሰቦችን ዕቅድና ተግባር፣ እንዲሁም አመክንዮ በሚገባ አጥንታ ሕይወቷን ሙሉ የተዋጋች ጀግና ነች፡፡ ጃኮብስ እንደተገነዘበችው በዓለም ያሉ ታላላቅ ከተሞች ሁሉ መልስ የሚሰጡት አንድ መሠረታዊ ችግር በጣም በርካታ ቁጥር ያላቸው የተለያየ እምነት፣ ባህል፣ ምርጫና የዕውቀት ደረጃ ያላቸው ግለሰቦች እንዴት በጋራ በሰላም መኖር እንደሚችሉ ነው፡፡ ይህ ያለ ምንም ማዕከላዊ አመራርና ዕቅድ ተፈጥሯዊ በሆነ ሒደት እንዴት እንደሚቻል በሚገባ ታብራራለች፡፡

ደኅንነቱ የተጠበቀና ደስ የሚል የከተማ ኑሮ በአመዛኙ በነዋሪዎች የአደባባይ ላይ ግንኙነት የሚፈጠር ያልታቀደ ውጤት ነው፡፡ በጤናማ ከተሞች ነዋሪዎች አደባባዮችን፣ የእግር መንገዶችንና የመገናኛ ሥራፍራዎችን ቀንም ሆነ ማታ አብዝተው ይጠቀማሉ፡፡ ምክንያቱም ሁሌም እነዚህን ሥፍራዎች የሚያይ ዓይን (Eyes on the Street) አለና ነው፡፡ እነዚህ ደስ የሚሉና ደኅንነታቸው የተጠበቀ የከተማ ሥፍራዎች የበለጠ ሰው እየሳቡ በመሄድ ከተማነት ይሳለጣል፣ ከተማው ይደምቃል፡፡

እነኚህ በከተማ ሥፍራዎች የሚገናኙ ሰዎች በዕውቀትም ሆነ በፍላጎትና ምርጫ በጣም የተለያዩና ለኢመደበኛ ግንኙነት የተመቹ እየሆኑ በመጡ ቁጥር ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የሐሳብና የቁስ ገበያ ይፈጠራል፡፡ ይህ በርካታ ቁጥር ያለው መቼም ሊገናኝ ይችል ያልነበረ ፀጉረ ልውጥ በአንድ የከተማ መንደር ውስጥ እንዲገናኝ ያስቻለው፣ በየመንደሩ በተፈጥሯዊ ሒደት የመጣው ማኅበራዊ ትስስር (Social Network) ነው፡፡ ጂኮብስ ይህንን ግለሰባዊ እሴት የሚጨምር፣ የነዋሪዎችን የእርስ በርስ መተማመን የሚያዳብር፣ እንግዶች ፍፁም ምቾት እንዲሰማቸው የሚያደርግ፣  የሰዎች የአደባባይ ግንኙነት ማኅበራዊ እሴት (Social Capital) ብላ ትጠራዋለች፡፡ ይህ ጉዳይ በተለይ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል የህልውናው መሠረት የሆነ እጅግ አስፈላጊ እሴት ነው፡፡

ሌላው ነጥብ ከተማ ማደስን ይመለከታል፡፡ ያረጁና የተጎሳቆሉ መንደሮች ከአንድ ከተማ እንዴት ነው መወገድ ያለባቸው የሚለው እስከ ዛሬ የዘለቀ ከባድ የከተማ ፕላን አጀንዳ ነው፡፡ ለራሽናሊስት ፕላነሮች በተጎሳቆሉ መንደሮች የሚኖሩ ዜጎች በሕዝብ በተጠቀጠቀ ሠፈር የሚኖሩ፣ ልጆቻቸው በጎዳና ላይ የሚጫወቱ፣ ንፁህ አየር፣ ፀጥታ፣ አረንጓዴ ሥፍራና አንዳንዴም የፀሐይ ብርሃን የተነፈጉ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከሀብታሞቹ መንደሮች ጋር የሚመሳሰል ህልም አለሙላቸው፡፡ ችግሩ ግን ህልሙ እነዚህ መንደሮች እንዴት እንደሚሠሩና በሕይወት እንደሚሰነብቱ ያገናዘበ አለመሆኑ ላይ ነው፡፡

በከተማ ዳርቻ ያሉ የባለፀጋ መንደሮች በተሻለ ሀብት፣ በተሽከርካሪዎች ባለቤትነት፣ ዝቅተኛ ቁጥር ባለው ነዋሪ፣ ብዙም ፀጉረ ልውጥ በማይጎበኛቸው ጎዳናዎች፣ በግል ቤት ጠባቂ ዘበኞች፣… ወዘተ የተዋቀረ ሕይወት የሚኖርባቸው ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ለተጎሳቆሉት ሠፈሮች የቀረበው ዕቅድ ሠፈሮችን ደምስሶ ነዋሪውን ባስ ሲል ሌላ ሥፍራ፣ ሻል ሲል ደግሞ እዚያው መንደሩ ላይ በተገነቡ ኮንዶሚኒየሞች ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንደያዙ ማስፈር ነው፡፡ በተለያዩ የዓለም አገሮች አሁን የተሻለ ስብጥር ለመፈጠር ቢሞከርም በመጀመርያ ይህ ፕሮግራም ተፈጥሯዊውን የተቀየጠ የመኖሪያና የንግድ አሠፋፈር የዘነጋና በዚያም ምክንያት ለከተሞች እጅግ አስፈላጊውን የነዋሪዎች ዓይን (Eyes on the Street) የተባለ እሴት ችላ ያለ ነበረ፡፡ ‹‹ምክንያታዊውና ዘመናዊው›› እሳቤ ያስተዋወቀው አገልግሎቶችን በዞን መወሰን ከሠፈር ያጠፋቸው የአጥቢያ መጠጥ ቤቶች እንኳን የሠፈሩ ጎዳናዎች እስከ እኩለ ለሊት ተመልካች እንዳያጡ የሚያስችሉ ነበሩ፡፡

የሕንፃዎቹ ቁመት በረዘመና የመጫወቻው ሥፍራ በራቀ ቁጥር ደግሞ ልጆችን ወደ እነዚህ የመጫወቻ ቦታዎች መላክ በወላጆችና በልጆች መካከል በማንኛውም ሰዓት ሊኖር የሚገባውን ተነፃፃሪ ርቀት በጣም ስለሚጨምረው ወላጆች ልጆቻቸው ከቤት እንዳይወጡ መከልከል ይጀምሩና መንደሩ ይሞታል፡፡ ሕይወት ያለበት የከተማ ሠፈር አልመስል ይላል፡፡

እንግዲህ ይህንን መሠረታዊ እውነት ከግምት ያላስገቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ የመዋኛ ገንዳዎች፣ መናፈሻዎችና የከተማ ፓርኮች በበርካታ የዓለም ከተሞች እጅግ ከፍተኛ ሀብት እየፈሰሰባቸው ከተገነቡ በኋላ ሰው የማይጎበኛቸው የተረሱ ቦታዎች ለምን ሆኑ ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡

በርግጥ የከተማ ፕላነሮች ይህንን የሚያደርጉት በክፋት ወይም መጥፎ ዓላማ ስላላቸው አይደለም፡፡ የችግሩ ዋነኛ ምክንያት ፕላኑን ለማዘጋጀት የተከተሉት መንገድ በከተሞች ያለውን የረቀቀ ማኅበራዊ መዋቅርና ውስብስብ ግንኙነት ያልተረዳና ከአንድ ውብ ግን የማይጨበጥ ምናባዊ ህልም የሚመነጭ መሆኑ ላይ ነው፡፡

የከተማ ፓርክ

አብዛኛውን ጊዜ የከተማ ፓርኮችና የመጫወቻ ሥፍራዎች አስፈላጊነት የሚገለጸው ሕፃናትና ወጣቶች በማኅበረሰቡ እንዳይዘነጉ በሚል መልካም ሐሳብ ነው፡፡ የሚሄዱበት ቦታ ከሰጠናቸው ከአልባሌ ሥፍራ፣ ከጎዳናና ከጎጂ ልማድ ይርቃሉ ነው ነጥቡ፡፡ ችግሩ ግን ልጆቹ ሠፈር ውስጥ ካለ ጎዳና ወደ ከተማ ፓርክ ሲሄዱ ከብዙ በከተማ ፓርኮች ዲዛይን ላይ በብዙ ዓይኖች እየራቁ ወደ ተገለሉና ለአደጋ የተጋለጡ ሥፍራዎች እየገቡ የመሄዳቸው ነገር ነው፡፡

በከተማ ፓርኮች ዲዛይን ላይ በብዙ የዓለም ከተሞች የታየ ሌላው ችግር ደግሞ በግልና በጋራ ይዞታ መካከል መኖር የሚገባው የመሸጋገሪያ ቦታ (Transitional Space) አለመኖር ነው፡፡ በፕላኑ የተቀመጠው የቦታ አጠቃቀም የአገልግሎት ዓይነት ሙሉ በሙሉ የግል ወይም ሙሉ በሙሉ የሕዝብ በሚል ፍፁማዊ ምርጫ የተቀረፀ ይሆንና ጃኮብስ ባዶ ድንበር (Boarder Vacuum) ብላ የምትጠራው ችግር ይከሰታል፡፡ ይህም ፓርኮቹን በከተማ ውስጥም ቢሆኑ ያለምንም መሸጋገሪያ በባዶ ድንበር ተከልለው ከተገነቡ ለአገልግሎት የማይመቹ የቅርብ ሩቅ ሥፍራዎች ያደርጋቸዋል ማለት ነው፡፡

‹‹ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ››

ጠቅላይ ሚኒስትሩ 56 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ከሰሜን ወደ ደቡብ አዲስ አበባን አቋርጠው የሚያልፉ ሁለት ወንዞች ዳርቻን ተከትሎ የሚገነባ በጣም ግዙፍ የከተማ ፓርክ ሊገነቡ ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ አሁን እንደ አገር ካለንበት ምጥና ከተራራ የገዘፉ ችግሮች አንፃር ይኼንን ፕሮጀክት ለመገንባት ጊዜው ነው? አይደለም? የሚለውን የፕራዮሪቲ ክርክር ለጊዜው እናቆየው፡፡ እንግዲህ ይህንን ፕሮጀክት በግዝፈቱ፣ በሚፈስበት ሀብትም ሆነ በከተማዋና በነዋሪዎቿ ላይ በሚኖረው ትልቅ ተፅዕኖ ምክንያት መላው የኅብረተሰብ ክፍልና በተለይ ደግሞ ዕውቀቱ ያላቸው ባለሙያዎች ጊዜው ሳይረፍድ ዝርዝር ፕላኑን ሊያውቁት፣ ሊረዱት፣ ሊተቹትና ሊያሻሽሉት እንደሚገባ ማሳሰብ የሁላችንም ግዴታ ይመስለኛል፡፡

የፕሮጀክቱን ዲዛይንና ትግበራ በዚህ ጽሑፍ ከተነሱ ዋና ዋና ሐሳቦችና የዓለም ከተሞች ተመሳሳይ ተሞክሮም ሆነ ከሌላ ሰፊና ተጨማሪ ዕውቀት በመነሳት ማየት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በውስን የኢኮኖሚ አቅማችን ላይ ሀብትና ጊዜያችንን አፍሰንም በተሳሳተ ፕላን ጥቅሙንም አጥተን ሌላ ያላሰብነውን ችግር እንዳንጎትት ከአሁኑ ቆም ብሎ ማሰብ ብልህነት ነው፡፡

አዲስ አበባ በተሳሳቱ የከተማ ፕላኖች ብዙ የምትታማ ከተማ ናት፡፡ የቅርብ ጊዜዎቹን ተሞክሮዎች ብንመለከት እንኳን ከቀለበት መንገድ ግንባታ ጀምሮ እስከ ቀላል ባቡር ዝርጋታ፣ ከከተማ ማደስ ፕሮግራም እስከ ግዙፍ የጋራ የመኖሪያ ቤት መንደሮች ምሥረታ የከተማዋን ማኅበራዊ ድር የበጣጠሱ፣ የታለመላቸውን ግብ ያልመቱ ብዙ ፕሮጀክቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ሁሉንም የሚያመሳስላቸው አንድ የጋራ ነገር በዝርዝር የተተቸና በደንብ የታሰበበት ፕላን ይዘው ወደ ሥራ አለመግባታቸው ነው፡፡

የከተማ ፓርክን በተመለከተ እንኳን አዲስ አበባ አንድ የቅርብ ተሞክሮ አላት፡፡ የጉለሌ የዕፀዋት ማዕከል! ክቡር ከንቲባው በቅርቡ ለሕዝብ ክፍት አድርገውት በአንዳንድ ጎብኚዎች እየታየ የሚገኝ የእንጦጦን ተራራ ተንተርሶ በሰሜናዊው የከተማዋ ጫፍ የተመሠረተና በአገር በቀል ዛፎች የተሞላ ፓርክ ነው፡፡

ግን ፓርኩን ተመልክተን በዚህ ጽሑፍ ከተጠቃቀሱ አንዳንድ ችግሮች ነፃ እንዳልሆነ ለመገንዘብ ብዙ ማሰብ የሚጠይቅ አይደለም፡፡ የመጀመርያው ፓርኩ የተመሠረተበት ቦታ ነው፡፡ በእርግጥ የጉለሌ የዕፀዋት ማዕከል (Botanic Garden) ስሙ እንደሚያመለክተው ዋነኛ ላማው አገር በቀል ዕፀዋትን መሰብሰብና መጠበቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር ካየነው ሙሉ በሙሉ እንደ ከተማ ፓርክ ወስዶ መተቸት ተገቢ ላይሆን ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ፓርኩ የተመሠረተበት ቦታ ፓርኩን ከከተማው  ሕይወት ሙሉ በሙሉ የነጠለ፣ በዙሪያው ለአጠቃቀም ምቹ እንዲሆን ያግዙ የነበሩ የመሸጋገሪያ ሥፍራዎች (Transitional Spaces) የሌሉት፣ ተጓዳኝ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በሁሉም የፓርኩ ሥፍራ ተሰባጥረው የማይገኙበት፣ ብዙ የጎደለው ፓርክ ነው፡፡

ሌላው እዚህ ፓርክ ውስጥ በጉልህ የሚታይ ነገር አንዳንድ የፓርኩ አካላት ያለባቸው መሠረታዊ የሲቪል ዎርክ ዲዛይን ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ በፓርኩ መካከል የተገነባውን የውኃ ግድብ (Reservoir) መመልከት ይቻላል፡፡ ከአቀማመጡ ለመገመት እንደሚቻለው የከርሰ ምድርና የምድር ውኃን (Ground And Surface Water) በማቆር ለፓርኩ አገልግሎት ለማዋል የታሰበ ይመስላል፡፡ በግድቡ ጫፍ የምትገኘውን የተፈጥሮ ምንጭ በማጎልበትና ከተራራው ቁልቁል የሚወርደውን ወቅቱን ጠብቆ የሚመጣ የጎርፍ ውኃ በመጠቀም ግድቡን መሙላት ታሳቢ ያደረገ ከሆነ ቢያንስ የምንጩን ውኃ ለመጠቀም ግድቡ ከምንጩ የውኃ ልክ (Water Level) ዝቅ ብሎ መገንባት ነበረበት፡፡ ያ ባልሆነበት ከምንጩ የሚገኘውን ውኃ ማቆር የሚቻለው አሁን ምንጩ እስከሚፈልቅበት ነጥብ ድረስ ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ያ ማለት ደግሞ አሁን በተሠራው ግድብ ላይ ከውኃ መውጫው ከፍታ (Outlet Pipe) በታች ነው፡፡ ሌላው በዓይን የሚታይ ነገር ከአካባቢው ጂኦሎጂ ጋር የተያያዘ በግድቡ ውኃን አቁሮ የማቆየት ችግርም እንዳለ በሚያመላክት ሁኔታ ውስጣዊውን የግድቡን ክፍል በላስቲክ ለመሸፈንም ተሞክሯል፡፡

እንግዲህ ይህንን ሁሉ ያነሳሁት በአንድ ፓርክ ደረጃ እንኳን በደንብ ያልተሠራና ያልተገመገመ ዲዛይን ይህንን ሁሉ ችግር ካስከተለ ከተማ አቋርጦ የሚያልፍ ግዙፍ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ደግሞ ምን ያህል ፈታኝና አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ፈፅሞ ከባድ እንደማይሆን ለማሳየት ነው፡፡ ስለዚህ በግልጽ የመመካከሪያውና የመደማመጫው ወቅት አሁን ይመስለኛል፡፡ ነገር ከተበላሸ በኋላ ጣትን ከመቀሰር ሁላችንም ገጣሚው እንዳለው፣

“. . . ውርውር የእጅህን ዘገር፣

በትር ያሻራህን ዘር

ይዘኸው እንዳትቀበር፡፡›› የምንባባልበት ጊዜ ላይ ቆመናል፡፡ ውብና ትንግርት የሆነች አዲስ አበባን ለማየት ያብቃን፡፡ ጨረስኩ!    

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡    

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles