ዩኔስኮ እ.ኤ.አ. ከ1983 ጀምሮ አፕሪል 18 (ሚያዝያ 10 ቀን) የዓለም ቅርስ ቀን ብሎ በአባል አገሮቹ እያከበረው ይገኛል፡፡ የታሪክና የባህል አካል ስለሆኑት ሐውልቶችና ሌሎች ቦታዎች እንዲሁም ጥንታዊ ቤቶችን በተመለከተ ለሕዝብ ስለ ቅርስ ጥበቃና ክብካቤ ግንዛቤ ማስጨበጫ መሰናዶዎች፣ ጉብኝቶችና ተያያዥ ሥራዎች ይከናወንበታል፡፡ የዘንድሮው በዓል በዓለም ዙሪያ በባህልና ቅርስ ተኮር መንግሥታዊ ተቋማት አማካይነት ጭብጡን ገጠራዊ መልክዐ ምድር ላይ በማድረግ አክብረውታል፡፡ መካነ ቅርሶቻቸውንም አስተዋውቀውበታል፡፡
ጎረቤት ኬንያ የናይሮቢን ገጠራማ መልክዓ ምድር ውበት ነፍስ እንዝራበት፣ እናቅናው በማለት ስታከብረው፣ የዘንድሮ የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ሊቀመንበርነትን የያዘችው ግብፅ በጥንታዊ ቅርስ ሚኒስቴሯ አማካይነት በሉክሰር የአርኪዮሎጂ መካነ ቅርስ ከአዲስ ቅርስ ግኝት ጋር ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማዶብሊ በተገኙበት አክብራለች፡፡ አል ምስር አልዮም እንደዘገበው፣ በመዲናዋ ካይሮም የጨርቃ ጨርቅ ሙዚየሟ በሚገኝበት አል ሞዕዝ ጎዳና ከቅርስ ጥበቃ ጠቅላይ አስተዳደር ጋር በመሆን ያዘጋጀውን ክብረ በዓል ለአፍሪካውያን ቅርስ እንዲሆን ያወጀው ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ሊቀመንበር መሆናቸውን ተከትሎ ነው፡፡ በክብረ በዓሉ የዕደ ጥበብ ቅርሶች የታዩበት ዐውደ ርዕይ ከመዘጋጀቱም በተጨማሪ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሞሮኮ፣ቱኒዝያ፣ ኮሞሮስ፣ ናይጄርያ፣ ካሜሮን እና ማሊ፣ እንዲሁም በክብር እንግድነት ፍልስጤም ተገኝተዋል፡፡ በማዕከላዊ ካይሮም የግብፅ ልዩ መልክዓ ምድሮችንና የተፈጥሮ ውበትን የሚያሳዩ ፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይም ለዕይታ በቅቷል፡፡ በዩኔስኮ ዘጠኝ የሚዳሰሱ ቅርሶችን በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነችው ኢትዮጵያ መንግሥታዊ ተቋማት በዓሉን እንደ ሌሎች አገሮች ሲያከብሩ አልተሰሙም፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ፣ ‹‹እንኳን በሚያዝያ 10 ለሚከበረው የዓለም ቅርስ ቀን በሰላም አደረሳችሁ፤ ቅርሶቻችንን በመጠበቅ፣ በማልማትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እናሳድግ›› ከሚል መፈክር ባለፈ የተራመደበት ነገር አልተሰማም፡፡ ከዚህ በፊትም ጭምር፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርስ በየዓመቱ የዓለም ቱሪዝም ቀንን እያከበረ እንዴት የቅርስ ቀንን ለማክበርና ለማስከበር ሳይተጋ ቀረ የሚሉ ድምፆች ሚያዝያ በመጣ ቁጥር የሚሰሙ ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ያልሆነው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለ አደራ ዘንድሮ የዓለም ቅርስ ቀን በጽሕፈት ቤቱ ባዘጋጀው የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይ አሐዱ ብሏል፡፡ ዕለቱን ያሰበው ‹‹ኑ ታሪክን እንዘክር፣ ኑ ባህላችንን እናወድስ፣ ኑ ስለ ቅርሶቻችን እናውራ፣ ኑ ማንነታችንን እንጠብቅ፣ ኑ የቀደሙ አባቶቻችንን እናመስግን›› በማለት ነው፡፡ ፎቶው ዩኔስኮ በ1970 ዓ.ም. በዓለም ቅርስነት የመዘገበው የስሜን ብሔራዊ ፓርክ አንዱን ገጽታ ያሳያል፡