Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየትምህርትና የዲፕሎማሲ ባለሙያ ኃይለ ገብርኤል ዳኜ መታሰቢያ

የትምህርትና የዲፕሎማሲ ባለሙያ ኃይለ ገብርኤል ዳኜ መታሰቢያ

ቀን:

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማንዴላ ሕንፃ ፊት ለፊት ባሉት ክፍት ቦታዎች ላይ ከወትሮው በተለየ መልኩ በርካታ ተሽከርካሪዎች ቆመዋል፡፡ ወደ ሕንፃው ሲዘልቁ ደግሞ በየኮሪደሩ ቄጤማ ተነስንሷል፡፡ ብዙ የቡና መጠጫ ስኒዎችን የያዘው ረከቦት ተቀምጧል፡፡ የጀበና ቡናም በከሰል እሳት ላይ ተጥዷል፡፡ ለቁርስ የሚሆን ፈንዲሻም ተዘጋጅቷል፡፡ በትልቅ የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይም የኃይለ ገብርኤል ዳኜ (ዶ/ር) በርካታ ፎቶግራፎች ለዕይታ በሚያመች መልኩ ተለጥፈዋል፡፡

ይህን ሁሉ ታልፎ ወደ አዳራሽ ሲገባ በስተቀኝ ክንፍ ያሉት መቀመጫዎች በሙሉ በታዳሚዎች ተይዘዋል፡፡ ፊት ለፊት ባለው መድረክ ላይ በግራና በቀኝ በበራ ሻማ የተከበበ፣ ዙሪያው በተለያዩ አበባዎች ያጌጠ፣ ወይም የተዋበ የኃይለ ገብርኤል ዳኜ (ዶ/ር) ፎቶግራፍ ተቀምጧል፡፡ የዚህ ሁሉ ዝግጅት ዋነኛ ዓላማው የዶክተሩን የአንደኛ ዓመት ዕረፍት መታሰቢያ ለመዘከር ነው፡፡

በዚህም ዝክረ በዓል ላይ የትምህርትና ዲፕሎማሲ ባለሙያው ኃይለ ገብርኤል ዳኜ (ዶ/ር) አጭር የመታሰቢያ ቪዲዮ የታየ ሲሆን፣ ከቀድሞ የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ከአብሮ አደግ ጓደኞቻቸው፣ በቅርብና በሩቅ ከሚያውቋቸው ወዳጃቸው አጠር ያሉ ትውስታዎች ተንፀባርቀዋል፡፡ በእነዚህም ትውስታዎች ላይ ዶክተሩ አገራቸውንና ሕዝባቸውን በጣም ይወዱና በሥራቸውም ላይ ምን ያህል ትጉህና ታታሪ እንደነበሩ ተጠቁሟል፡፡

ከተንፀባረቁትም ትውስታዎች መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ሁለት መጻሕፍትን በማሳተም በፕሬሱ ታሪክ የመጀመርያው ሰው መሆናቸው ተነግሯል፡፡ ከመጻሕፍቱም መካከል፣ ‹‹ባህልና ትምህርት በኢትዮጵያ›› የሚለው እንደሚገኝበት፣ መጽሐፉ 359 ገጾች እንዳሉት፣ ስድስት በእንግሊዝኛና ሌላ አምስት ደግሞ በአማርኛ የተጻፉ አርቲክሎችን እንደያዘ ተገልጿል፡፡

ከዚህም ሌላ በቅርቡ ይታተማል ተብሎ የሚጠበቀው ‹‹ሶሻል ፋውንዴሽን ኦፍ ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ጽሑፍ ማዘጋጀታቸውንም ተገልጿል፡፡ ለኅትመት ዝግጁ የሆነው ይህ ዓይነቱ ጽሑፋቸው በተለይም የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ የደርግና የአሁኗ ኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓቶች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑንም ከተሰነዘሩት ትውስታዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

በመድረኩ እንደተወሳው፣ አዲስ አበባ ውስጥ በሥነ ተዋልዶ ጤና የወጣቶች ሊደርሺፕ ፕሮግራም ላይ በፈቃደኝነት በመሳተፍ ለወጣቶች እጅግ ጠቃሚ የሆነ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በአሜሪካ በ2000 ዓ.ም. ‹‹የኢትዮጵያውያን የወል መረጃ ማዕከል›› በማቋቋም ለኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ታላላቅ ሰዎች ታሪክ በማዕከሉ እንዲቀመጥና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መረጃውን ያለምንም ችግር በቀላሉ እንዲያገኙ በማድረግ እጅግ ጠቃሚ ሥራም አከናውነዋል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ተወካይም፣ ኃይለ ገብርኤል (ዶ/ር) የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሆነው ባገለገሉባቸው ዓመታት ውስጥ የማኅበሩ የ40 ዓመታት ታሪክን የሚዳስስ መረጃን የመምህራን ድምፅ በተሰኘው የማኅበሩ ኅትመት ላይ በማሳተም ወደር የማይገኝለት አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ወዳጆቻቸው መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር አግደው ረዴ (ዶ/ር) በተለይ  እንደገለጹት፣ ኃይለ ገብርኤል (ዶ/ር) በቋንቋና በሥነ ትምህርት (ፔዳጎጂ) የታወቁ ነበሩ፡፡

በጀርመን ትምህርታቸውን በተከታተሉባቸው ዓመታት ውስጥ በአውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ወጣቶች በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ሥር የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ነፃነታቸውን እንዲቀዳጁ በመጠየቅ በቅኝ አገዛዝ ላይ ከፍተኛ የሆነ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ያደረጉ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ሁልጊዜ ቅዳሜ በኢትዮጵያ ወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ) በቅኝ አገዛዝ እንቅስቃሴ ዙሪያ ንግግር የሚያደርጉበት ፕሮግራም እንደነበራቸው አስታውሰዋል፡፡

ከተንፀባረቁት ትውስታዎች፣ ከቀረቡትም ኅትመቶች ለመገንዘብ እንደተቻለው ኃይለ ገብርኤል ዳኜ (ዶ/ር) ከእናታቸው ከወ/ሮ ወርቅነሽ ራስ ወርቅና ከአባታቸው ከቀኛዝማች ዳኜ ኃይሌ መስከረም 10 ቀን 1923 ዓ.ም. በቀድሞ አጠራር በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በወበራ አውራጃ እንደተወለዱ፣ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ፊደል ቆጥረው ዳዊት እንደደገሙ፣ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትም ዘመናዊ ትምህርት እንደጀመሩ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚያው እንዳጠናቀቁ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዚህም ሌላ በ1943 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመግባት ለአንድ ዓመት ከተማሩ በኋላ ወደ ግሪክ በማቅናት በአቴንስ ዩኒቨርሲቲ በሥነ መለኮት ትምህርት የመጀመርያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ ከዚያም አገራቸው በመመለስ ሐረር ከተማ በሚገኘው መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በርዕሰ መምህርነት አገልግለዋል፡፡ ወደ ጀርመን በማቅናትም ፍሪ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ በርሊን በመግባት በኢዱኬሽን የትምህርት ዘርፍ፣ እንዲሁም በታሪክና በማኅበረሰብ ሳይንስ ጥናት በ1959 ዓ.ም. በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ በጀርመን በነበሩበት ወቅት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ኅብረትን ከመሠረቱ መካከል አንዱ ናቸው፡፡

ኃይለ ገብርኤል ዳኜ (ዶ/ር) በቀድሞ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ትምህርት ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት አስተምረዋል፡፡ በዚህም ሙያቸው አያሌ ምሁራንን ያፈሩ ሲሆን፣ ከ1966 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ዓመታት የትምህርት ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበርን ከ1979 ዓ.ም. እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ማለትም ለአምስት ዓመታት ያህል በፕሬዚዳንትነት መርተዋል፡፡ ከ1960ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ለሰባት ዓመታት ያህል በምዕራብ ጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው መሥራታቸው ይታወሳል፡፡

ከጀርመን ከተመለሱ በኋላ ከ1976 ዓ.ም. እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማርና ልዩ ልዩ የምርምር ሥራዎች ላይ በማተኮር ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆነው ነበር፡፡ በዚህ ወቅትም የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ሠርተዋል፡፡  በዚህ የአገልግሎት ዘመናቸው ተማሪዎች ለተቃውሞ ሲወጡ በወታደሮች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከተማሪዎቹ ፊት በመሆን ያረጋጉ እንደነበር ይነገራል፡፡ የአፓርታይድ አገዛዝን በመቃወም በተለያዩ የዓለም አገሮችና በኢትዮጵያ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች እየተዘዋወሩ ፀረ አፓርታይድ ቅስቀሳና ግንዛቤ ለወጣቱ ይፈጥሩ ነበር፡፡

ጊዜያቸውንም በጥናትና ምርምር ሥራ በማሳለፋቸው በርካታ የምርምር ውጤቶች በአገር ውስጥና በውጭ ኅትመቶች ማሳተም ችለዋል፡፡ ዶ/ር ኃይለ ገብርኤል በ1963 ዓ.ም. ከወ/ሮ መቅደስ ዓለሙ ትዳር መሥርተው ሁለት ሴት ልጆች አፍርተዋል፡፡        

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...