በቅርቡ የለንደን ጦር ሙዚየም በእጁ የነበረውን የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላ (ጉንጉን ፀጉር) ለኢትዮጵያ ሰጥቷል፡፡ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) የተመራው ልዑክ፣ ባለፈው መጋቢት ወር በለንደን በመገኘት ሁለት ቁንዳላዎችን መረከቡ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ በዋናነት በለንደንና በኒው ዮርክ የሚሠራጨው ‹‹ዘ አርት ኒውስፔፐር›› (THE ART NEWSPAPER) ድረ ገጽ ኢትዮጵያ ቁንዳላዎቹን ስለ መረከቧ ከታሪካዊ ዳራው በመነሳት ሽፋን ሰጥቷል፡፡ የቁንዳላዎቹ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታን በተመለከተም ከልዑካን አባላት አንዱ የሆኑትን አቶ ኤፍሬም አማረን አነጋግሮ፣ ቋራ በሚገኘው የንጉሠ ነገሥቱ መካነ መቃብር ማኅበረ ሥላሴ ገዳም እንደሚቀበሩ ዘግቧል፡፡
ይህንን ዘገባ መነሻ በማድረግ ሪፖርተር መዘገቡ፣ እንዲሁም ልዑኩ ቁንዳላዎቹን ይዞ አዲስ አበባ ሲደርስ በተደረገለት አቀባበል ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) “የንጉሠ ነገሥቱ ቁንዳላ በጊዜያዊነት የሚቀመጠው ብሔራዊ ሙዚየም ሲሆን ቀጣይ ዕጣ ፈንታው በመመካከር ይፈጸማል፤” ማለታቸውን በመጋቢት 20 ዕትሙ መዘገቡም ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ ባለፈው ሳምንት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ለሪፖርተር ዘጋቢ ‹‹የአፄ ቴዎድሮስ የራስ ፀጉር አይቀበርም፡፡ የሚቀመጥበት ቦታም አልተወሰነም፣ ሚኒስቴሩ የአሠራር ሥርዓቱን ጠብቆ የሚቀመጥበትን ቦታ ያሳውቃል፤›› ብለውታል፡፡ የባህር ማዶው የዜና ምንጭ ያሠራጨውን ዜና እንደተላከላቸውም፣ ‹‹ለማንኛውም እንደማይቀበር ላረጋግጥልህና ማስተካከያ ይሰጥልን›› ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የልዑኩ አባልና የብሔራዊ ሙዚየም ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም አማረ፣ ‹‹ጋዜጠኛው [Martin Bailey] ያላልኩትን ነው የዘገበው፣ የንጉሠ ነገሥቱ መካነ ማቃብር ባለበት ቦታ በክብር ይቀመጣል ነው ያልኩት›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ዳግማዊ ቴዎድሮስ የአሥራ ሦስት ዓመት የንግሥና ዘመናቸው (1847-1860) ያበቃው በመቅደላ አምባ ከእንግሊዝ ሠራዊት ጋር በነበረው ጦርነት ፍጻሜ ላይ ‹‹እጄን አልሰጥም›› ብለው ራሳቸውን በጀግንነት ባጠፉበት ቅፅበት ነበር፡፡ በጄኔራል ናፒር ይመራ የነበረው ጦር የመቅደላ አምባን ሲወር ከዘረፋቸው ቅርሶች በተጨማሪ ከንጉሠ ነገሥቱ አስክሬን ላይ ቁንዳላቸውን (ጉንጉን ፀጉራቸውን) ቆርጦ መውሰዱ ይታወቃል፡፡
የታሪክ ሰነዶች እንደሚያሳዩት፣ ሁለቱን ቁንዳላ ቆርጦ የወሰደው መቶ አለቃ ፍራንክ ጀምስ ነው፡፡ ጀምስ ሠዓሊም በመሆኑ በቃሬዛ ላይ የነበሩትን አፄ ቴዎድሮስ ገጽታ በንድፍ በሚሥልበት ወቅት ነበር ቁንዳላቸውን ቆርጦ የወሰደው፡፡ የጀምስ ቤተሰብ ሁለቱን ቁንዳላዎች ከ100 ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1959 ለብሔራዊ የጦር ሙዚየም ሰጥቷል፡፡
በለንደን ከተማ ብሔራዊ ጦር ሙዚየም ለስድሳ ዓመታት የተቀመጠውን ሁለት ቁንዳላ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ፈቃደኛነቱን ያሳየው ሙዚየሙ መጋቢት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) ማስረከቡ ይታወሳል፡፡