ከአገሪቱ አጠቃላይ የባንክ ገበያ ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ ድርሻ የያዙት ሁለቱ የመንግሥት ባንኮች ጤናማነት እንዲጠና፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቅጣጫ መሰጠቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክንና የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ጤነኝነት ማጥናትና ማረጋገጥ፣ እንዲሁም በጥናት ውጤቱ ላይ የተመሠረቱ የማስተካከያ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ አቅጣጫ መሰጠቱ ተመልክቷል፡፡ ይህም የሁለቱ ባንኮችን ሚና ቀጣይነት ከማረጋገጥ ባለፈ በገበያው ውስጥ ካላቸው ከፍተኛ ድርሻ አንፃር፣ የባንክ ዘርፉን ጤነማነትና ዘለቄታዊነት ለማስቀጠል እንደሚረዳ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ለሪፖርተር አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለበትን ሁኔታ ጤናማነት ለማጥናት ደረጃውን የጠበቀ ኦዲት እንደሚደረግ፣ ይህም ኦዲት የባንኩን ብድሮች ስብጥር ሥጋት (Portifolio Concentration Risk) እና የሀብትና ዕዳ መጣጣምን እንደሚያካትት ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅት የሚሰጠው የባንክ አገልግሎት ጤናማ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ ከሰጣቸው ብድሮች ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የረጅም ጊዜ ብድር ለጥቂት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በተለይም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተሰጠ በመሆኑ የብድር ስብጥሩ ሥጋት የሚፈጥር ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ።
የሁሉም የአገሪቱ ባንኮች ጠቅላላ የብድር ክምችት ባለፈው ወር 792.5 ቢሊዮን ብር የደረሰ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል።
ከዚህ ውስጥ 57 በመቶ ወይም 452 ቢሊዮን ብር ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ በዋናነትም ለኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ተብሎ ለኤሌክትሪክ ኃይል የተፈቀደ ነው። ይህ ብድር ከሞላ ጎደል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመንግሥት የዋስትና ሰነድ የተወሰደ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው 18ቱ የአገሪቱ ባንኮች አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በየካቲት ወር 2011 ዓ.ም. 816.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከዚህ ተቀማጭ የገንዘብ መጠን ውስጥ 496.9 ቢሊዮን ብር የሚሆነው በመንግሥት ባንኮች እንደሆነ፣ ነገር ግን ልማት ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ ስለማይሰበስብ የተጠቀሰው ተቀማጭ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑን ለመረዳት ይቻላል።
በሌላ በኩል ባንኩ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሰጣቸው ብድሮች በረጅም ጊዜ የሚመለሱ መሆናቸውና የብድሩ ማስያዣም የመንግሥት ሰነድ በመሆኑ፣ ብድሩ እስኪመለስ ድረስ ባንኩ ለቀጣይ የባንክ አገልግሎቶቹ የሀብት መጠን ዕጥረት ሊገጥመው ይችል እንደሆነ ኦዲቱ እንደሚገመግም ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዋናነት የገጠመው ችግር ባንኩ ከሰጣቸው ብድሮች ውስጥ 40 በመቶ መመለስ የማይችልና አጠራጣሪ መሆኑ በመታወቁ፣ ባንኩ ጤናማ እንዳልሆነ ከወዲሁ መረጋገጡ ይነገራል፡፡
ከብሔራዊ ባንክ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው የልማት ባንክ አጠቃላይ የብድር ክምችት 46.2 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 39.5 በመቶ የማይመለስና አጠራጣሪ ነው።
በመሆኑም ይህንን ባንክ ለማስተካከል ጥልቅ ግምገማ እንዲከናወንና አዲስ የአሠራርና የብድር አሰጣጥ ማስተካከያ እንዲበጅ ተወስኖ፣ ኃላፊነቱ ለብሔራዊ ባንክና ለገንዘብ ሚኒስቴር መሰጠቱ ታውቋል።