Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየክልል አመራሮች ወደ ፌዴራል እንዲመጡ የተደረገው ለውጡን ተሻጋሪ ለማድረግ መሆኑ ተገለጸ

የክልል አመራሮች ወደ ፌዴራል እንዲመጡ የተደረገው ለውጡን ተሻጋሪ ለማድረግ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሐሙስ ሚያዝያ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. በካቢኔያቸው ባደረጉት ሹም ሽር ሁለት የክልል መንግሥታት አመራሮች በፌዴራል መንግሥት ኃላፊነቶች ላይ እንዲሾሙ የተደረገው፣ አገራዊ የፖለቲካ ለውጡን ተሻጋሪ ለማድረግ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በካቢኔያቸው ላይ ያደረጉትን መጠነኛ የአመራሮች ለውጥ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያፀድቅላቸው ባለፈው ሐሙስ የምክር ቤቱ አባል በሆኑት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ በኩል ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት መጠነኛ የካቢኔ ሹም ሽር የመከላከያ፣ የውጭ ጉዳይና የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴሮችን የሚመለከት ነው፡፡

በአገሪቱ ታሪክ የመጀመርያዋ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ከወራት በፊት ተሹመው የነበሩት ወ/ሮ አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር) ቀድሞ ወደነበሩበት የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስትር እንዲዘዋወሩ፣ እርሳቸው ለነበሩበት የመከላከያ ሚኒስቴር ደግሞ በአገሪቱ ለተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል የሚባሉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ለማ መገርሳ ዕጩ ተሿሚ መሆናቸውን፣ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ጫላ ለሜ ለምክር ቤቱ አስታውቀዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከወር በፊት በመሾማቸው ምክንያት የተፈጠረውን የሥልጣን ክፍተት ለመሙላት፣ በተመሳሳይ በአገሪቱ ለታየው የፖለቲካ ለውጥ ግንባር ቀዳሚ ሚና እንደነበራቸው የሚነገርላቸውና እስከ ቅርብ ጊዜ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ዕጩ ሆነው መቅረባቸውን የመንግሥት ረዳት ተጠሪው ገልጸዋል፡፡

 ይህንን የካቢኔ ሹም ሽር እንዲፀድቅ የቀረበለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሹም ሽሩን አመክንዮና ዕጩ ተሿሚዎች ለሚመደቡበት ኃላፊነት ብቁ የትምህርትና የልምድ ዝግጅት፣ እንዲሁም ሰብዕና በመመዘን የቀረበውን ሹመት የማፅደቅ ወይም ውድቅ የማድረግ ሕጋዊ ሥልጣን እንዳለው ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ የቀረበውን ሹም ሽር በተመለከተ ሦስት የምክር ቤት አባላት ብቻ አስተያየት የሰጡ ቢሆንም፣ ዕጩ ተሿሚዎቹ የሚመደቡበትን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል የትምህርትና የልምድ ዝግጅት ያላቸው መሆኑን ለመመዘን ያደረጉት ጥረት በእጅጉ አነስተኛ ነበር፡፡

ተሿሚዎቹን በተመለከተ አስተያየት ከሰጡት ሦስት የምክር ቤት አባላት መካከል አንዱ ብቻ የክልል አመራሮች ወደ ፌዴራል ኃላፊነት እንዲመጡ የተደረገበት ምክንያት እንዲገለጽላቸው፣ ሹም ሽር መብዛቱ የፌዴራል መንግሥት ካቢኔ የተረጋጋ እንዳይሆን እንዳደረገው በአሉታዊነት አውስተዋል፡፡ የተቀሩት ጠያቂዎች ደግሞ ለሹመት የቀረቡት ዕጩዎች አገራዊ የፖለቲካ ለውጡን በመምራት ረገድ ጉልህ ሚና የተወጡ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ለፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት መታጨታቸውን እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት ጥያቄና አስተያየት በመቀጠል ማብራሪያ የሰጡት ረዳት የመንግሥት ተጠሪው አቶ ጫላ፣ የክልል አመራሮች ወደ ፌዴራል መንግሥት እንዲመጡ የተደረገበትን ምክንያት በተመለከተ በቀረበው ጥያቄ ላይ በማተኮር፣ የፌዴራል መንግሥትን በማጠናከር አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ እነዚህ ዕጩ ተሿሚዎች በየክልሎቻቸው ከፍተኛውን ድርሻ መወጣታቸውን የተናገሩት ረዳት የመንግሥት ተጠሪው፣ ‹‹አገራዊ ለውጡ በተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኝና ተሻጋሪ እንዲሆን ለማድረግ የፌዴራል መንግሥትን በጠንካራ ሰዎች ለማጠናከር ታስቦ ነው ከክልል እንዲመጡ የተደረገው፤›› ብለዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ሕግ ማስከበርና አስፈላጊውን የአመራር ቁመና ይዞ መጠናከር እንዳለበት፣ በሕዝብ በኩል በቅሬታ መልክ እየተነሳ መሆኑንም አቶ ጫላ ገልጸዋል፡፡

ይህንን ቅሬታ ከግንዛቤ በማስገባትና በፌዴራል ደረጃ ያለውን የአመራር ስብስብ በጠንካራ ሰዎች በማደራጀት አገራዊ ለውጡ ሳይደናቀፍ እንዲሻገርና አገራዊ አንድነትን በሚፈጥር አግባብ ለመምራት፣ የእነዚህ ዕጩዎች ወደ ፌዴራል መምጣት አስፈላጊ እንዳደረገው ጠቁመዋል፡፡

አቶ ጫላ የሰጡትን ማብራሪያ ተከትሎ ምክር ቤቱ ሹመቱን በአንድ ተቃውሞና በአምስት ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ ለማ መገርሳ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የፈጠረውን የሥልጣን ክፍተት ለመሙላት፣ በተመሳሳይ ቀን ለአስቸኳይ ስብሰባ የተቀመጠው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) በእሳቸው ምትክ በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ክልሉን እንዲያስተዳድሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ጽሕፈት ኃላፊ የነበሩትን አቶ ሽመልስ አብዲሳን ሹሟል፡፡

አቶ ሽመልስ እጅግ ወጣት ከሚባሉት የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡

በትውልድ ቦታቸው በምዕራብ ሸዋ ጊንጪ ከተማ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአምቦ ከተማ አጠናቀዋል፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፍልስፍና ያጠናቀቁት በ2000 ዓ.ም. እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዚያ በኋላም ለትምህርት ትኩረት በመስጠት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሰብዓዊ መብት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሌላ ተጨማሪ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአመራር ሳይንስ ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡

በከፍተኛ አመራርነት ካገለገሉባቸው ኃላፊነቶች መካከል የኦሮሚያ ክልል የከተማና ቤቶች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ፣ በኋላም የኦሮሚያ ክልል የኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ፣ እንዲሁም ላለፉት ጥቂት ወራት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ (ቺፍ ኦፍ ስታፍ) ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል፡፡

አቶ ሽመልስ ሥልጣን በተረከቡ በማግሥቱ የመጀመርያ ጉብኝታቸው በቄለም ወለጋ ዞን ያደረጉ ሲሆን፣ በደምቢደሎ ከተማ ከነዋሪዎች ጋር ውይይት አድረገዋል፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲሠሩ፣ በክልሉ የሚታየውን የሰላም ዕጦት በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚተጉ ለነዋሪዎቹ መግለጻቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...