Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለኢትዮጵያ ታዳጊዎች ተስፋን የሰነቀው የሦስት ዓመቱ የባየር ሙኒክ ፕሮጀክት

ለኢትዮጵያ ታዳጊዎች ተስፋን የሰነቀው የሦስት ዓመቱ የባየር ሙኒክ ፕሮጀክት

ቀን:

የጀርመን አንጋፋ የእግር ኳስ ክለብ ባየር ሙኒክ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ተስፋ የፈነጠቀ የምሥራች ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ክለቡ በኢትዮጵያ ተሰጥኦ ያላቸውን ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ታዳጊ ወጣቶች ለአገርና ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ብቻ ሳይሆን አግር ኳሱን ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ሊያመነጭ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የሚያስተዋውቅ ሥርዓት እንዲዘረጋ ትልቅ ጅምር ስለመሆኑ ጭምር እየተነገረለት ይገኛል፡፡

የባየር ሙኒክ እግር ኳስ ክለብ የቦርድ አባላትና የቴክኒክ ቡድን ከሚያዝያ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ፣ ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ታዳጊ ወጣቶች ላይ ለመሥራት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ከስፖርት ኮሚሽን ጋር  የሦስትዮሽ ስምምነት አድርገዋል፡፡ ለሦስት ዓመት በሚዘልቀው ስምምነት መሠረት ለፌዴሬሽኑ ሙያተኞች ቴክኒካዊና አስተዳደራዊ ሥልጠናዎችን በአገር ውስጥና እንደ አስፈላጊነቱ ከኢትዮጵያ ውጪ ይሰጣል፡፡

በእግር ኳስ የጥራት ደረጃ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም ካላቸው የአውሮፓ ክለቦች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት የጀርመኑ ባየር ሙኒክ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖረው ቆይታ ታዳጊዎቹ በእግር ኳስ ተሰጥኦና ችሎታቸው ተመልምለው ሳይንሳዊ ሥልጠና ማግኘት የሚችሉበትን የእግር ኳስ ማሠልጠኛ ማዕከል ለመክፈት ዕቅድ ይዟል፡፡ በስምምነቱ ሥነ ሥርዓት ላይ በኢትዮጵያ በኩል፣ የስፖርት ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳውና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ በባየር ሙኒክ በኩል የባቫሪያን ግዛት ሚኒስትር ዴኤታ ማርከስ ሶደርና የባየር ሙኒክ እግር ኳስ ክለብ ቦርድ ተወካይ ሚስተር ዮርግ ዎከር ተገኝተዋል፡፡

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የምሥረታ ዕድሜ እንዳለው የሚነገርለት የአትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውድድር ተኮር ካልሆነ፣ እንደነዚህ የመሰሉ በተለይ ታዳጊ ወጣቶች ላይ መሠረት ያደረጉ ማዕከላት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲንቀሳቀስ አይስተዋልም፡፡ አሁን ለሚታየው የእግር ኳስ ውድቀት አንዱና መሠረታዊ ጉዳይም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ጨምሮ በተዋረድ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የሚከተሉት ተመሳሳይ አካሄድ ለችግሩ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ይነገራል፡፡

ከባየር ሙኒክ እግር ኳስ ክለብ ጋር በአምባሳደርነት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የቀድሞ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ጂኦቫኒ ኤልበር፣ በአዲስ አበባ በነበረው ቆይታ የበርካታ ታዳጊ ተጨዋቾችን እንቅስቃሴ ሲያብራራ፣ ‹‹ብዙዎቹ ታዳጊዎች የተሰጥኦ ችግር አላስተዋልኩባቸውም፣ ነገር ግን እግር ኳስ ሒደት ነውና ልጆቹ ላይ በዕቅድ ላይ የተመሠረተ ሥራ መሥራት ስለሚጠይቅ በዚህ ረገድ በቂ ሥራ የተሠራባቸው አይመስለኝም፡፡ ከክለቡ ጋር በተለያዩ አገሮች በመዟዟር የታዳጊዎችን የእግር ኳስ ተሰጥኦ ተመልክቻለሁ፤ ኢትዮጵያውያኑ ላይ የተመለከትኩት ያልተሠራበት በተፈጥሮ ብቻ የተገኘ ተሰጥኦ ተመልክቻለሁ፡፡ ይህን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ደግሞ ትልቅ ሥራ ይጠይቃል፤›› ብሏል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ስምንት ቡድኖች ተመርጠው፣ እርስ በርስ እንዲጫወቱ በማድረግ በባየር ሙኒክ ክለብ ሙያተኞች እንዲታዩ ተደርጓል፡፡ ክለቡም በተመለከተው ደስተኛ መሆኑን ብራዚላዊውን ጂኦቫኒ ኤልበር ጨምሮ የክለቡ ኃላፊዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ከባየር ሙኒክ ጋር የተደረሰው የሦስት ዓመት ስምምነት ቀጣይነት እንዲኖረው ቢደረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስም ሆነ ባየር ሙኒክ የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሰፊ ዕድል ስለመኖሩ ጭምር ጂኦቫኒ ኤልበር ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ዋና አሠልጣኝ አብርሃም መብራህቱ ስምምነቱን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወደሚፈለገው ደረጃ ለማምጣት፣ ‹‹አሁን በእጃችን እየገባ ያለውን ዕድል አሟጠን መጠቀም ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡ የባየር ሙኒክ ክለብ አመራሮች በተመለከቱት ነገር እጅጉን መደሰታቸውን የገለጹት አሠልጣኙ፣ ‹‹ከእኛ የሚጠበቀው ሚዲያው ጭምር ፕሮጀክቱ ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን ሁኔታ በማመቻቸት መንቀሳቀስ ብቻ ነው፤›› ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡    

ፈዴሬሽኑ ከአንድ ወር በፊት በሁለቱም ጾታ ዕድሜያቸው ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች በሆኑ ታዳጊዎች ላይ ለመሥራት ከ15 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት የሦስትዮሽ ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...