በውብሸት ሙላት
ሕገ መንግሥታዊነት በበርካታ አገሮች አሁንም ቢሆን በአጣብቂኝ ውስጥ መላቀቅ እንደተሳነው ነው፡፡ አጣብቂኝ ውስጥ እየከተቱት ካሉት ምክንያቶች መካከል ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎችና ለውጦች፣ በሥልጣን ላይ የሚገኙ ፓርቲዎች ከሕገ መንግሥት ይልቅ ለፓርቲያቸው ታማኝ መሆን ይገኙበታል፡፡ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ደግሞ በጣም ይጎላሉ፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎቹም ይሁን ለፓርቲያዊ አሠራር ቅድምና ሰጥቶ የሚተላለፉት ውሳኔዎች ሕገ መንግሥትን ይጥሳሉ ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ ከእንዲህ ዓይነቶቹ ተግባራት አንዳንዶቹ አድራጎት ሕገ መንግሥታዊ ቢሆኑም ቀሪዎቹ ደግሞ አይደሉም፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓብይ ትኩረት ሕገ መንግሥታዊነት ምንነትንና ፋይዳውን፣ በመቀጠልም ሕገ መንግሥት እያለ፣ ተከብሮም ሥራ ላይ እየዋለ ሕገ መንግሥታዊነት የማይኖርበትን ሁኔታዎች ብሎም ሕገ መንግሥት ሳይከበር ወይም ተጥሶም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ የሚሆኑ አድራጎቶችን ማሳየት ነው፡፡ ሕገ መንግሥት ስንል ምክንያታዊ ከሆኑ መርሆች የሚመነጩ፣ ለሕዝብ ጥቅም የሚበጁ ደንቦች፣ ልማዶች፣ ተቋማትን ያካተተ የአንድ አገርን ጥቅል ሥርዓት የሚያስቀምጥ ብሎም ማኅበረሰቡም ትዳሩን በዚሁ መልክ ለማድረግ የተስማማበት ሕግ ነው ለማለት ነው፡፡ ስለሆነም በአንድ ድንበሯ በታወቀ አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ከመንግሥት ጋር የተዋዋሉት ማኅበራዊ ኪዳን ነው፡፡ ተዋዋይ ወገኖቹ በአንድ በኩል መንግሥት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዜጎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ሁለቱም የራሳቸው የሆነ ተነፃፃሪ ግዴታች አሉባቸው፡፡ የፖለቲካ ፈላስፎች፣ የሕገ መንግሥትን ማኅበራዊ ኪዳንነት (ውልነት) ይቀበሉና ልዩነታቸው የሚመጣው የተዋዋይ ወገኖቹ ተነፃፃሪ መብትና ግዴታዎቻቸው ላይ ነው፡፡
ሕገ መንግሥት የአንድን አገር ማንነትም ይወስናል፡፡ ድንበሯን ያስቀምጣል፣ ግቧን ይለያል፣ ሰብዓዊ መብቶችን ያካትታል፣ ሥልጣን እንደምን እንደሚገኝ ይደነግጋል ወዘተ፡፡ ግልጽ ለማድረግ ኢትዮጵያ ሲባል የት እንደምትገኝ ማለትም ማን እንደሚያዋስናት፣ ምን ዓይነት መንግሥት እንዳላት፣ ሕዝቦቿ ያላቸው መብቶችና ከመሳሰሉት ሁኔታዎች ተነጥላ ልትሳል አትችልም፡፡ ስለሆነም የአገሪቷን ማንነት የሚገልጽ ሰነድ ነው፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበረችው ኢትዮጵያ በደርግ ከነበረችው ትለያለች፤ በደርግ የነበረችው ደግሞ ከአሁኑ ትለያለች፡፡ በእነዚህ ዘመናት ኢትዮጵያን እንደ አገር የሚለይዋትም የሚያሳውቋትም ሁኔታዎች ይለያያሉ፡፡ በዋናነት ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ተመሥርቶ የመጣ ልዩነት ነው፡፡
ሕገ መንግሥት አንድም ከላይ የተገለጹትን መርሆች፣ ድንጋጌዎች፣ መብቶችና ግዴታዎች ወዘተ. የያዘ ሰነድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከሰነድነቱ የሚያልፉ፣ ማለትም ሰነዱ ባይኖርም እንኳን የማይቀሩ፣ አገራዊ ግቦችንም ይይዛል፡፡ የሕዝቡም የመንግሥትም ጥረትና ጉዞ ያንን ግብ ለማሳካት መሆን አለበት፡፡ ዜጎችም ለዚያ ግብ የሚሰጡት ዋጋ ከፍ ያለ መሆን አለበት ማለት ነው፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥታዊ ግብ እንከን የለሽ ኅብረት መፍጠር፣ ፍትሕ ማስፈንና አገራዊ ፀጥታን ማስፈን ወዘተ ናቸው፡፡
የአሁኑ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ዋና ግብ ‹‹አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር›› ሆኖ ይኽንን ግብ ለማሳካት የሚያግዙ ሌሎች ንዑሳን ግቦች አሉት፡፡ በቅድሚያ ሕዝቡ ይኼንን ግብ የእኔ ነው ብሎ ሊቀበለው ይገባል፤ ከተቀበለው በኋላ ስኬቱ የሚገመግመው ግቡን ለማሳካት በሚደረገው ጥረትና ውጤት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ግቦች ምን ያህል ሕዝባዊ ናቸው? እነሱንስ ለማሳካት እንደ አገር የተጓዘችባቸው መንገዶች የት አደረሱን? የሚለው ፍተሻ ያስፈልገዋል፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥት ስንል ከሰነድነቱ ባሻገር፣ ዜጎች ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጧቸው ዕሴቶችን የሚያመለክት ነው፡፡
የሕገ መንግሥት ዓብይ ፋይዳው የመንግሥትን አመል መግራት፣ ሥልጣኑን መገደብ ብሎም የዜጎችን ፍላጎቶች ዕውቅና በመስጠት ጥበቃ ማድረጊያ ሥልቶችን ማበጀት ነው፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ገና ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት፣ ጀምስ ማድሰን፣ አሌክሳንደር ሐሚልተንና ጆን ጃይ የተባሉ ምሁራን ከጻፏቸው ውስጥ፣ ፌዴራሊስት ቁጥር 52 ላይ አንድ ትልቅ ቁምነገር ተካቷል፡፡ ይኸውም ሕገ መንግሥት በመጀመርያ መንግሥት ተገዥዎችን (ሕዝቡን) ሊቆጣጠር የሚያስችለው ሕጋዊ አቅም እንዲኖረው ማስቻል ሲሆን፣ ቀጥሎ የሚመጣው ደግሞ መንግሥት ራሱን የሚቆጣጠርበት ሥልት ማበጀቱና መቻሉ ነው፡፡ ይኽንን ቁም ነገር ለማሳካትም እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አሁንም አገሮችን ያስቸገረው መንግሥት ሕዝብን እንዳሻው ይቆጣጠራል፡፡ ሕዝብ በተራው መንግሥትን የሚቆጣጠርበት ሥርዓት አለመኖር ወይም መድከምና ውጤታማ አለመሆናቸው ነው፡፡ እንዲህ እንዲሆንም የሚሠራው ደግሞ አንዱ ተዋዋይ የሆነው ይኼው መንግሥት ነው፡፡ አሁንም ኢትዮጵያን ያስቸገራት መንግሥትነትን በመዳፉ ያደረገው ገዥው ፓርቲ ራሱን የሚቆጣጠርበት ሥልት አለመሥራቱ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንም ይሁን ሌሎች ሕግጋትን ወደ ጎን በመተው የሚተላለፉት ውሳኔዎች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥትን የሥልጣን ሥዕሉን፣ ንድፉን ያስቀምጣል፤ ተቋማትንም ያቋቁማል፡፡ ይኼንን አምባገነን መንግሥትም ያደርጉታል፡፡ በመሆኑም ዴሞክራሲያዊነትን አያሳይም፡፡ ከመጀመርያው ፋይዳ ጋር መቀዳጀት አለበት ዴሞክራሲያዊነትን ለማስፈን፡፡ ዴሞክራሲያዊነትን ለማምጣት ከሥነ ሥርዓታዊ ይልቅ ለመሠረታዊ ለሆኑት ዕሴቶች ትኩረት ማድረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ከማድረግ በዘለለ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመደራጀት መብትን አለማጣበብ፣ የሕግ የበላይነትን ሥር የሰደደ ባህል እንዲሆን መሥራት፣ የፍርድ ቤቶች ነፃነትና ገለልተኛነትን ማረጋገጥና የመሳሰሉት መሠረታዊ የዴሞክራሲ ባህሪያት ናቸው፡፡ ሌላው የሕገ መንግሥት ዓላማ የታወቀና የተረጋጋ ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡ አንድ ሕገ መንግሥታዊ አስተዳደር የዴሞክራሲዊ ዕሴቶችና የሕዝቡ ፍላጎት ነፀብራቅ ከሆነ፣ ተቀባይነቱ ከጨመረ፣ ሕዝቡ የእኔነት ስሜት ካለ የተረጋጋ ሥርዓት መፍጠር አይገደውም፡፡ የሕገ መንግሥትን ምንነትና ፋይዳ በዚሁ እናቁመውና ወደ ሕገ መንግሥታዊነት እንለፍ፡፡
ሕገ መንግሥታዊነት በአጭሩ የመንግሥትን ሥልጣን ሊገደብ መቻሉንም፣ ሊደገብም እንደሚገባውም የሚያሳይ ሲሆን ሥልቶቹንም ጭምር የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ስለሆነም ዋናው ነጥቡ ያለው የሥልጣን ገደብ ላይ ነው፡፡ ለላዕላይ ሕጎች የመገዛት ቁርጠኝነት አንዱ የሕገ መንግሥታዊነት ክፍል ነው፡፡ መንበረ ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች ከሕግ በታች መሆናቸውን ከልብ በማመን፣ ለወጡት ሕጎች ተግባራዊነት በቁርጠኝነት መሥራትን ይጠይቃል፡፡ እንደ ዕውቁ አሜሪካዊ የፖለቲካ ፈላስፋ፣ ጆን ራውልስ አመለካከት ‹‹ሕጎች ሲወጡ ሰውንም ድርጅትንም ታሳቢ ያደረጉ መሆን የለባቸውም፡፡ ሕግ አውጭው ብሔርን፣ ፓርቲን፣ ሃይማኖትና ጾታን ወዘተ. ከሰው በመነጠል ሁሉንም እኩል አድርጎ በማየት ነው ሕግ መውጣት ያለበት፤›› ይላል፡፡ ይህ ሁኔታ ከሁሉም በላይ ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ መተግበር አለበት፡፡ የመንግሥትን ሥልጣን ወሰን ሲተለም፣ ሕገ መንግሥት አርቃቂዎችና አጽዳቂዎች ሥራ ላይ ሲውል ሊያገኙት የሚችሉት ጥቅም ማሰብ የለባቸውም፡፡ ሥልጣን ሊይዙ የሚችሉ አካላትንም ከግምት ማውጣት አለባቸው፡፡ ሕገ መንግሥታዊነት፣ በዚህ ሁኔታ አስቀድሞ የተተለመ የሥልጣን ወሰንና ሥርዓት እንዲኖር ታሳቢ ያደርጋል፡፡
ሕገ መንግሥታዊነት የሚያመለክተው በሕግ አውጭው፣ በአስፈጻሚውና በተርጓሚው መካከል የሥልጣን ክፍፍል መኖርን፣ የዳኝነት ነፃነት፣ በወንጀል የተከሰሱ ሰዎችን በተመለከተ ፍትሐዊና ሕጋዊ ሥርዓትን መከተል፣ የግለሰቦች መብት መከበርና የመሳሰሉት ሕገ መንግሥታዊ ሒደቶችና ሥነ ሥርዓቶችን ማስፈኛ ሥልትን መሆኑን ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊነት እንደ ጽንሰ ሐሳብም ይሁን እንደ ፖለቲካዊ ንድፈ ሐሳብ የሚያሟላቸው አላባውያን አሉት፡፡ ከእነዚህ መካከል የተወሰኑትን ብቻ በአጭሩ እናንሳ፡፡
በአንዲት አገር ውስጥ ሕገ መንግሥታዊነት አለ ወይም የለም ለማለት የመጀመርያው ነጥብ የሕግ የበላይነት መሥፈኑን ወይም ያለበትን ደረጃ የሚመለከት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ባልሰፈነበት ወይም የገዥዎች ፍላጎት በነገሠበት፣ ሥርዓት አልበኝነት በሰረፀበት ሁኔታ ሕገ መንግሥታዊነት አይኖርም፡፡ ሁለተኛው ነጥብ ሕገ መንግሥት፣ ከሁሉም ሕጎች የላቀ ቦታ መያዝን፣ በውስጡ የተካተቱት ጉዳዮችም እንዲሁ የላቀ ዋጋ ያላቸው መሆኑን ይመለከታል፡፡ ሌሎች ደግሞ ከዚያ በታች እንደሆኑ መረዳትና ዋና ግባቸውን ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱትን ለማሳካት እንደሆነ አመኔታ መኖርንና በተግባር የሚፈጸመውም ይኼው መሆንን ይጠይቃል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ግቦችንና ድንጋጌዎችን የሚያስፈጽሙ ተቋማት የመኖራቸው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም የሥልጣንን ክፍፍል ያለው መንግሥት፣ ነፃ የዳኝነት ተቋም፣ የሰብዓዊ መብትን ለማስጠበቅ የሚረዱ እንደ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ ያሉ አካላት መኖራቸውን ታሳቢ ያደርጋል፡፡
የመጨረሻው ነጥብ ለሰብዓዊ መብት ከሚሰጠው ዕውቅናና ጥበቃ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እነዚህ መብቶች በማይከበሩባቸው አገሮች ሕገ መንግሥታዊነት ሰፍኗል ማለት አይቻልም፡፡ እነዚህ ከላይ የተገለጹት አራቱ ጉዳዮች የሕገ መንግሥታዊነትን ህልውና ከሚያሳዩት መሥፈርቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥታዊ አባት ከሚባሉት አንዱ የሆነው ሐሚልተን፣ ደግሞ በዋናነት ሕገ መንግሥታዊነት ስንል ‹‹ሥርዓት ያለውና ሥርዓቱን ብቻ ጠብቆ በመጓዝ የሚያስተዳድር መንግሥት ማቆምን፣ የሥልጣን ድካውን ለይቶ ማስፈርንና ይህ ሥርዓት በሕዝብ ታማኝ ማድረግ ነው፤›› ይላል፡፡ በዓለማችን ላይ አንድ ዓይነት ሕገ መንግሥታት የሉም፤ እንደ አገሮቹ ብዛት ይለያያሉ፡፡ ሕገ መንግሥታዊነት ግን የሕገ መንግሥትን ያህል ብዛት የለውም፡፡ ይሁን እንጂ እሱም ቢሆን የራሱ የሆኑ ልዩነቶች አሉት፡፡ ለአብነት የሚከተሉትን እንይ፡፡ አንዳንድ አገሮች ሕገ መንግሥታዊነትን የሚመዝኑት በዚያች አገር ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች ባላቸው ዕሴት ላይ ተመሥርተው ነው፡፡ ሲወርድ ሲዋረድ ይዘውት የመጡት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እንዲሁም ባህላዊ ዕሴቶችን መነሻ በማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም የተለዩ መለኪያዎች ሊኖሩት ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ በርካታ አገሮች የሚያስተሳስር የሕገ መንግሥታዊነት እሳቤም አለ፡፡ ለምሳሌ ኮንትኔታል (ከታላቋ ብርቴን ውጭ ያሉ የአውሮፓ አገሮች) በዚህ ረገድ ብዙ ነገር ይጋራሉ፡፡
በሌላ መልኩ ደግሞ ሁሉንም ሰው ልጆች የሚያስተሳስሩ በሕገ ልቦና የሚታወቁ መርሆችም ስላሉ ሁሉን አቀፍ ባህሪያትም አሉት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ በሃይማኖታዊ ድንጋጌዎች አማካይነት የሚለኩም አሉ፡፡ በርካታ የዓረብ አገሮች ለዚህ አስረጂ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ በተለየ ሁኔታ ደግሞ በአመክንዮ ላይ የተመሠረቱ መሥፈርቶችንም ሲወሰድ እየተስተዋለ ነው፡፡ ይኼ ርዕዮተ ዓለማዊም ሊሆን ይችላል፡፡ ሶሻሊዝምና ካፒታሊዝም ወዘተ. ሕገ መንግሥታዊነት ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ከላይ የተገለጹት ሁኔታዎች ዓይነቱን ይወስኑታል፡፡
ሕገ መንግሥታዊነት የሕገ መንግሥት ቅርፁ፣ ይዘቱም ቅቡልነቱም ይፈተሽበታል፣ ይገመገምበታል፡፡ ወይም መፈተሻና መገምገሚያ መሥፈርትም በመሆን ያገለግላል፡፡ የሕገ መንግሥቱን ዓይነት ያሳያል፡፡ ሕገ መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ቅቡል መሆንን ይሻል፡፡ ይህንን የቅቡልነት ምርኩዝ ከሌለው ወይም ቀድሞውንም ከሌለው በመንግሥት (በገዥው) እና በሕዝብ (በተገዥው) መካከል ቅራኔ መኖሩ ስለማይቀር ሕገ መንግሥቱ የይስሙላ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ በውስጡ የተካተቱት መርሆች፣ ድንጋጌዎች፣ አስተዳደራዊ መዋቅሮችና ሌሎችም ጉዳዩች ተፈጻሚ ሳይሆኑ ይቀራሉ፡፡ ውሎ አድሮም በገቢር እየተዘነጉ ስለሚሄዱ የመንግሥትም ይሁን የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ተቀባይነት ተኖ ያልቃል፡፡
ሕገ መንግሥታዊነት ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በየአገሮቹ የወጡ ሕገ መንግሥቶች ማክበር ወይም ማስፈጸም ብቻ የሕገ መንግሥታዊነትን መኖርን አያሳይም፡፡ አሁን አሁን ሉላዊ (ግሎባል) ሕገ መንግሥታዊነት የሚለው ጽንሰ ሐሳብም በዓለም አቀፍ ሕግ እየዳበረ መጥቷል፡፡ እንግዲህ ዓለም አቀፋዊ ሕገ መንግሥት የሚባል ሰነድም ሳይኖር ሉላዊ ሕገ መንግሥታዊነት ያደገበት፣ ከሕገ መንግሥት የዘለለ፣ በዋናነትም ጽንሰ ሐሳብ ስለሆነ ነው ማለት ነው፡፡ በሕገ መንግሥታዊ ንድፈ ሐሳብ ውስጥ ጎላ ብለው ከሚታዩት ጥያቄዎች አንዱ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከሥጋትና ከአደጋ ሕገ መንግሥት እንዴት ሊታደግ ይችላል? የሚለው ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በተለያዩ ምክንያቶችና አጋጣሚዎች ሥጋትና አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ሕገ መንግሥት ደግሞ እንደ አንድ ጥሩ ዕቅድ አስቀደሞ ሥጋቶችን በመገመት መፍትሔዎችን ሊዘረጋ ይገባል፡፡ የጀርመንና የቱርክ ሕገ መንግሥቶች ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡ ሒትለርና ፓርቲው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሥልጣን ያዙ፡፡ ከዚያም የሆነውን ሁሉ ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ ጀርመን ከናዚ አረመኔያዊ ድርጊት በመማር በሕገ መንግሥቷ የተለያዩ መፍትሔ አስቀመጠች፡፡
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን አደጋ ላይ የሚጥል ፓርቲ ሥልጣን መያዝ እንዳይችል የሚያደርጉ አንቀጾች በሕገ መንግሥቱ ተካተቱ፡፡ እነዚህ አንቀጾች ደግሞ ዝንተ ዓለማዊ እንዲሆኑ በማሰብ መቼም ቢሆን መሻሻል እንዳይችሉ ወሰነች፡፡ ይህንን የሚያስፈጽም ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤትም አቋቋመች፡፡ ለሕገ መንግሥታዊነት ታላቅ እንቅፋት በመሆን ካስቸገሩት አድራጎት መካከል ሕገ መንግሥትን ማሻሻልና መለወጥ ዋናዎቹ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ መንግሥታዊ ሥርዓታቸው ፕሬዚዳንታዊ በሆኑ አገሮች የበለጠ ተለምዷል፡፡ በፕሬዚዳንት የሚተዳደሩ አገሮች የሥልጣን ዘመናቸውን አስቀድመው በሕገ መንግሥት ይወስናሉ፡፡ ይሁን እንጂ የመንበረ ፕሬዚዳንት ዘመኑ ሊያልቅ ሲል ሕገ መንግሥት ማሻሻል ትዝ ይላቸዋል፡፡ በተለይ ከሰሃራ በታች ያሉ አፍሪካ አገሮችና በላቲን አሜሪካ ልማድነቱ አልቀረም፡፡ በቅርቡ እንኳን በቡሩንዲ የሆነው ይኼው ነው፤ ሩዋንዳም ተመሳሳይ ጥያቄ መነሳቱ ይታወቃል፡፡ ሕገ መንግሥትን ለግል ጥቅም በማዋል ለሕገ መንግሥታዊነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዳተኛ ከመሆን የሚመነጭ ነው፡፡
በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተቀመጠውን አሠራር ተከትሎ የሚከናውን ማሻሻያና ለውጥ ሕገ መንግሥታዊ ነው ብንልም በዋናነት ዴሞክራሲን ማዳከሚያ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ተግባር ሕገ መንግሥታዊ ቢሆንም ፀረ ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ስለሆነም ሕገ መንግሥታዊ የሆነ ሁሉ ዴሞክራሲያዊ አለመሆኑን ያጤኗል፡፡ በተወሰኑ አገሮች የሚገኙ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንታዊ የሥልጣን ዘመንን ለማራዘም ሲባል ሕገ መንግሥትን ማሻሻል ኢሕገ መንግሥታዊ አድራጎት እንደሆነ በመቁጠር እንዳይሻሻል ወስነዋል፡፡ አፍሪካንና ሌሎች ታዳጊ ዴሞክራሲዎችን ሕገ መንግሥታዊነት በመገዳደር ላይ የሚገኘው የፓርቲዎች አምባገነንነት ነው፡፡ ገዥ ፓርቲዎች ምርጫ ከመከናወኑ በፊት ሕግ በማውጣትና የመንግሥት ተቋማትን በመጠቀም ተቃዋሚ ፓርዎችን ያሳድዳሉ፣ ይከፋፍላሉ፣ በተለያዩ ወንጀሎች ይከስሳሉ፣ መራጩም ተቃዋሚን እንዳይመርጡ ያስፈራራሉ፡፡ አዝማሚያውን በመመልከት የምርጫ ውጤቱንም ሊያጭበረብሩ ይችላሉ፡፡
ይህ እንግዲህ በፓርቲ ደረጃ የሚፈጸም ሕገወጥ ድርጊት ብሎም ሕገ መንግሥታዊነትን እንዳይሰርጽ የሚያደርግ እንቅፋት ነው፡፡ ለፓርቲ አምባገነንነት ምቹ ከመሆናቸው ባለፈው የዳኝነትና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትን ፓርቲው እንዳሻው ስለሚያዛቸው መላው ሥርዓቱ ይነቅዛል፡፡ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱና በፓርቲው መካከል ልዩነት እንዳይኖርም ያደርጋል፡፡ ውሎ አድሮም ሕዝባዊ አመጽ እንዲነሳ ማበረታቻ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ መፍትሔው፣ ሕገ መንግሥታዊነትን በማስፈን ፓርቲውንና የፓርቲው አይነኬ ሰዎችን ከሕገ መንግሥት በታች እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡ የእኛው አገርም ችግርም ይኼው ነው፡፡ ለአብነትም በፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሆኑ ተመራጮችን ባልተመረጡበት፣ የምርጫ ቦርድም ምንም ዓይነት ተሳትፎ ሳያደርግበት፣ የተመረጡበት ምክር ቤትም ሳይወስን ወደ ክልል በመውሰድ ፓርቲዎች የመሾም አካሄዳቸውን ቀጥለውበታል፡፡ ሙስና የፈጸሙ ሰዎች ተጠያቂ የሚሆኑት በዘመቻ ነው፡፡ በዘመቻ ማሰር በዘመቻ መፍታት ልማድ እንደሆነ ነው፡፡ ቀደም ሲል የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት በአገር ውስጥ በሰቀቀን ይንቀሳቀሱ እንደነበር ቢታወቅም አሁን ላይ ደግሞ ዝቅተኛውን የመመዝገብ ቅድመ ሁኔታ እንኳን ሳያሟሉ እንደ ፓርቲ መንቀሳቀስ ደግሞ ሕጋዊ እንደሆነ የተቆጠረ ይመስላል፡፡
ከየቦታው የሚፈጸመው የዜጎች መፈናቀል ሕጋዊ የሆነ ያህል መፍትሔ ሲሰጠው አይስተዋልም፡፡ ፓርላማው የባለሥልጣናት ሀብት ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን የሚያስገድድ ሕግ ቢያወጣም፣ ባለሥልጣናቱን ከሕግ በታች ማድረግ ስላልተቻለ ይኼው እስካሁን ድረስ የበላው ጅብ አልጮኸም፡፡ ተቃዋሚዎችንና ግለሰቦችን የሚመለከት ሕግ ቢሆን ኖሮ ግን በማግስቱ ወይም እንዳስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ ሕዝቡ ስለመታወጁ ከመስማቱ በፊትም ጀምሮ ቢሆን ሥራ ላይ ይውል ነበር፡፡
አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡