በሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)
የ1960ዎቹ የብሔር ትግል አቀንቃኝ ተማሪዎች ቁንጽል የማርክሲስት ሌኒኒስት ግንዛቤ አበርክቶ ያለፈው ‹‹ያልጠራ የብሔር/ብሔረሰብ ትርጉምና ትንታኔ፤›› አለ፡፡ ይህን ከባዕድ የተወሰደ የተንሻፈፈ አፋጅ ትርጉም መርሳት ከተሳነው የዋህ ሰው፣ ወይም ‹‹አሞራዋን ጅግራ ናት›› በማለት ሐሳቡን ለጠባብ ቡድን ኪራይ መሰብሰቢያነት ለማዋል ‹‹ጥቂት ቆሎ ይዞ ከአሻሮ ከተጠጋ›› የፖለቲካ ልሂቅ በስተቀር፣ ‹‹ብሔር›› ማለት በአጭሩ ‹‹ሀገር ወይም ሕዝብ›› ማለት እንደሆነ፣ ‹‹ብሔረሰብ›› ማለት ደግሞ ‹‹የዚያ ሀገር ሰው›› ወይም ‹‹ከዚያ ሕዝብ የወጣ ሰው›› ማለት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ላለፈው ረዥም ዘመን ሰዎች የተወለዱበትን አካባቢ ወይም የወጡበትን ሕዝብ ለመግለጽ ‹‹ዘ ብሔረ ወሎ፣ ዘ ብሔረ አድዋ፣ ዘ ብሔረ ቡልጋ ወዘተ›› ይሉ እንደነበረ ለሚያውቅ ሰው ይህ ትርጉም እንግዳ ነገር አይሆንበትም፡፡
የብሔር/ብሔረሰብ ትርጉም በዘር ላይ ከተመሠረተው ነገድ/ጎሳ ትርጉም እንደሚለይ፣ ‹‹ሕዝቦች›› የሕዝብ የብዜት ስም እንደማይሆን፣ የማርክሲስት ሌኒኒስት የብሔር/ብሔረሰብ ታሪካዊ ቁስ አካልነት ትንታኔ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተፈጥሯዊ፣ ማኅበራዊና ታሪካዊ ዳራ እንደማይመጥን መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ከባዕድ ቋንቋ ተወስዶ በፖለቲካ የተመረዘው ‹‹ያልጠራ ትርጉምና ትንታኔ›› ከዚህ ሀገር በቀል ትርጉም ጋር አይስማማም፡፡ ሀገር በቀል የብሔር/ብሔረሰብ ትርጉም ከላይ የተገለጸው የአበው ትርጉም ነው፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አገራችን የምትታመስበትን ‹‹ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች›› ድርብ ድብልቅ ቃል ለመተንተን ሳይሆን፣ የገዥ መደቦች በሚፈጥሩት የሀገር አስተዳደር አወቃቀር ችግር ሀገርና ሕዝብ እንዴት እንደሚታመስ ወሎንና የወሎን ሕዝብ በምሳሌነት ወስዶ በማስቃኘት የመፍትሔ ሐሳብ ለመጠቆም ነው፡፡ ስለወሎ የሚተነትነው ጉዳይ የተቀሩትን የአገራችን ክፍሎች ሁኔታ ጭምር ስለሚያንፀባርቅ የዚህን ጽሑፍ አንባቢ ጉዳዩን ሰፋ ካለ አገራዊ ማዕዘን ተነስቶ ማጤን ያስችለዋል፡፡
ባለፉት አምስት አሥርት ዓመታት የተቀያየረው የአንድ ሦስት ስድስት የሀገር አስተዳደር አወቃቀር ዓላማው፣ የወሎን ሕዝብ በየወቅቱ ወደ ሥልጣን መንበር ለመጡት የገዥ መደቦች አገዛዝ ማመቻቸት ነበር፡፡ ሥዩመ እግዚአብሔር ነኝ ይሉ በነበሩት የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ (1884 እስከ 1967 ዓ.ም.) ከ14ቱ ጠቅላይ ግዛቶች አንዱ የነበረው ወሎ 12 አውራጃዎች፣ 38 ወረዳዎች ውስጥ የጋራ ማንነት አለን ብለው የሚያምኑ ስድስት ነገዶች (አማራ፣ ኦሮሞ፣ አገው፣ አፋር፣ አርጎባ፣ ትግሬ) በዋናነት የሚኖሩበት ጠቅላይ ግዛት ነበር፡፡ ከኢሕአዴግ በፊት የሀገር የውስጥ አስተዳደር የሚዋቀረው በአስተዳደር አመቺነት፣ ታሪክ፣ የጋራ ሥነ ልቦናና መልክዓ ምድር ነበር፡፡
በመፈንቅለ መንግሥት ንጉሡን በተካው የደርግ መንግሥት ወሎ ክፍለ ሀገር በተደጋጋሚ ተከልሏል፡፡ ከ1976 እስከ 1980 ዓ.ም. የአገሪቱን የልማት ዕቅድ ለማሳለጥ በሚል 14ቱን ክፍለ ሀገሮች በሰባት ቀጣናዎች ዙሪያ ሲያዋቅር ጥንት የወሎ ክፍለ ሀገር አካል የነበረውን የአሰብ አውራጃና የትግራይ ምሥራቃዊ ክፍልን በማካተት፣ የሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ ቀጣና በማለት የቀጣናውን ጽሕፈት ቤት ደሴ ከተማ አደረገ፡፡ በ1981 ዓ.ም. 14ቱን ክፍለ ሀገሮች (ከአዲስ አበባ በስተቀር) ለ31 የአስተዳደር፣ ልዩ ራስ ገዝና ራስ ገዝ አካባቢዎች በመከፋፈል የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ሲዋቀር የወሎ ክፍለ ሀገር ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎና የአሰብ ራስ ገዝ ተብሎ ተከፈለ፡፡ ‹‹የአስተዳደር ክፍፍሉ ዓምዳዊ እርከን ለማሳጠርና ጎናዊ እርከንን ለማስፋት በሕዝቡና በመስተዳደሩ የበላይ አካላት መካከል ያለውን ርቀት ለማጥበብ›› በሚል ዓላማ ላይ በመመሥረት፣ አውራጃ የመጨረሻው መንግሥታዊ አስተዳደር ሆኖ ወረዳዎች ታጥፈው በእያንዳንዱ አውራጃ ውስጥ በርካታ የቀበሌ ገበሬ ማኅበራትና ከነማዎች ተዋቀሩ፡፡
የቀድሞዎቹን የወሎ 12 አውራጃዎች በመከለስና ወረዳዎችን በማዋሀድ በሰሜን ወሎ ስምንት፣ በደቡብ ወሎ ዘጠኝ አውራጃዎችን መሠረተ፡፡ ማዕከሉን አሰብ ባደረገው ልዩ ራስ ገዝ የአውሳ፣ የአሰብ ዙሪያና የቀይ ባህር አውራጃዎች ተካተቱ፡፡ አዳዲሶቹን የአስተዳደር አካባቢ፣ ልዩ ራስ ገዝ፣ ራስ ገዝ አካባቢዎችን በማዋለድ ኢሕዲሪ ከተመሠረተ በኋላ ሰባቱ የቀጣና ፕላን ጽሕፈት ቤቶች ታጥፈው፣ በየአስተዳደር አካባቢ ጽሕፈት ቤቶች ሥር በመምሪያ ደረጃ ተዋቀሩ፡፡ የቀጣና ፕላን ጽሕፈት ቤቶቹ የተቋቋሙት የገዥ መደቡን ዕድሜ የሚያራዝም አዲስ የሀገር አስተዳደር ለማዋቀር እንዲቻል ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ነበር ተባለ፡፡ የተፈጠረውን ውጥረት በማስተንፈስ ዕድሜውን ያራዘመ ቢመስለውም፣ ነፍጥ አንስተው በበረሃ የሚታገሉትን ባለተራዎቹን ገዥ መደቦች የልብ ልብ የሰጠና ለሚፈልጉት ዓላማ ስኬት የመንጠላጠያ ድንጋይ ያቆመ ታላቅ ስህተት ፈጸመ፡፡ በወረዳ አስተዳደራዊ መዋቅር መታጠፍ ምክንያት ሕዝቡ ጭራሽ ከማዕከላዊ መንግሥት ግንኙነት በመራቁና ለአስተዳደርና ፀጥታ ሥራ ባለመመቸቱ ደርግ የራሱን ውድቀት አፋጠነ፡፡
የሰሜኑ ጦርነት በአስደናቂ ፍጥነት ወደ መሀል ሀገር ዘልቆ በመግባቱ፣ ማዕከሉን ወልዲያ ላይ ያደረገው የሰሜን ወሎ አስተዳደር ጥቂትም ሳይቆይ በጦርነቱ ተፈናቅሎ በመምጣት የወሎ ሕዝብ ማዕከል በሆነችው ደሴ ከተማ በጊዜያዊነት ተቀመጠ፡፡ ከሰሜን ወሎ አስተዳደር መፈናቀል ቀደም ብሎ በየካቲት ወር 1982 ዓ.ም. ደርግ ትግራይን በአላዋቂነት ሙሉ በሙሉ ለቆ ወጥቷል፡፡ ከጥቅምት 1982 ዓ.ም. ጀምሮ የደቡብ ወሎ ምዕራብ አውራጃዎችን ጥሎ ወጥቷል፡፡ ቀጥሎም ከሰሜንና ከደቡብ ጎንደር ወጥቷል፡፡ ደሴን ለመያዝ በተደረገው ጦርነት የመንግሥት ጦር ተደምስሶ ግንቦት 10 ቀን 1983 ዓ.ም. ደሴ ከተማ በኢሕአዴግ ቁጥጥር ሥር ገባች፡፡ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. የደርግ መንግሥት ተወግዶ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡ በዚሁ ኢሕዲሪ የተባለው የደርግ መንግሥት አስተዳደር አወቃቀር አበቃለት፡፡
ኢሕአዴግና ሻዕቢያ በጣምራ ደርግን ካስወገዱበት ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ወዲህ የአውሳ አውራጃና የአሰብ አስተዳደር ተፈናቅሎ የሕዝቡ የጋራ ማዕከል ወደ ሆነችው ደሴ ከተማ መጣ፡፡ የወሎ ሕዝብ መዲና የሆነችው ደሴ ከተማ በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅሎ በመጣው ከልክ ባለፈ የሰሜን ኢትዮጵያ ሰው ተጨናንቃ ልትሰጥም የደረሰች በየብስ ላይ የምትቀዝፍ መርከብ መሰለች፡፡ ይሁን እንጂ በወሎ ሕዝብ አቃፊነት የተነሳ ሁሉም ተፈናቃይ የችግሩን ዘመን በደሴ ከተማ በቤተኛነት አሳለፈ፡፡ ከየካቲት ወር 1982 ዓ.ም. መስከረም 1984 ዓ.ም. የተፈናቀሉ መምህራንና ተማሪዎችን በደሴ ከተማና አካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶች በማረጋጋት፣ ኗሪው የመኖሪያ ቤቱንና የሚበላውን ምግብ በማጋራት፣ ነጋዴው የንግዱን ሥራ ለተፈናቀሉ ነጋዴዎች በማጋራትና በሸማቾች ላይ ዋጋ ባለመጨመር ‹‹መፈናቀልም ኑሮ ነው›› እስከሚባል ድረስ ሁሉም በአገራዊ ስሜት ተፈናቃዩን አቀፈ፡፡
ደርግ ከተወገደ በኋላ ኢሕአዴግና ሻዕቢያ ኢትዮጵያን በመካፈል አዲስ አበባና አሥመራ በየፊናቸው የገዥ መደብ ሆኑ፡፡ ኢሕአዴግ የሽግግር ወቅት ቻርተር በማርቀቅ በወቅቱ የፖለቲካ ድርጅት ኖሯቸው ትግል በማድረግ ላይ ከነበሩት ቡድኖች በተጨማሪ፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ታዋቂ ግለሰቦች የተወከሉበት በተባለ ጉባዔ የሽግግር ወቅት ቻርተሩ ሐምሌ 1983 ዓ.ም. ፀደቀ፡፡ በሽግግሩ ወቅት የኤርትራና የአሰብ ልዩ ራስ ገዝ (ከአውሳ አውራጃ በስተቀር) በሻዕቢያ አስተዳደር ሥር ሆኑ፡፡ የአውሳ አውራጃ የአስተዳደር ግንኙነት ተመልሶ በደቡብ ወሎ ሥር ሆኖ በደርግ ኢሕዲሪ የተዋቀሩት የደቡብ ወሎና የሰሜን ወሎ እህትማማች ዞኖች በነበሩበት ቀጠሉ፡፡
ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሥራ እንደተጠናቀቀ መስከረም 1986 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) ምሥረታና የሽግግር ወቅት ቻርተሩ ዘመን መጠናቀቂያ ምዕራፍ ሆነ፡፡ ኢሕአዴግ ኤርትራ ከእናት አገሯ እንድትገነጠል በመፍቀድና የአውራጃ አስተዳደር እርከንን በማስቀረት ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፋሽስት ጣሊያንን ትልም ተገበረ፡፡ በዚህ ትልም መሠረት በኢሕአዴግ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበረው ትሕነግ የእኔ ብቻ ነው የሚለውን ትግራይ በነቄነት ለማስፋፋት የኢትዮጵያን መልክ በመቀየር፣ በመርህ አልባነት ከጎንደርና ወሎ መሬት ቆርሶ ሲወስድ ወሎ ክፍለ ሀገርም የዚሁ የተስፋፊነት ዕቅድ ሰለባ ሆነ፡፡ ‹‹እንዶድ በሞኝነቱ ወንዝ ወረደ›› እንዲሉ የወሎ ሕዝብ ይሁንታው ሳይጠየቅ፣ በኢሕዲሪ መንግሥት ለሦስት ተከፍሎ ከነበረው በኢፌዴሪ መንግሥት በእጥፍ ለስድስት አስተዳደር ተከፈለ፡፡
በዚህም መሠረት በደርግ መንግሥት ዘመን መጨረሻ ደቡብ ወሎ ይባል የነበረው የወሎ ክፍለ ሀገር ግማሽ አካል ዳግም ተሸንሽኖ ደቡብ ወሎ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞንና የአፋር ክልል ተብሎ ለሦስት እንዲከፈል ተደረገ፡፡ የደቡብ ወሎ ማዕከል ደሴ ከተማ፣ የሁለቱ ብሔረሰቦች አስተዳደር ማዕከላት ደግሞ ከሚሴና ሰመራ ሆኑ፡፡ የሰሜን ወሎ ከፊል ራያና ዋግ ወደ ትግራይ፣ ከዚህ የተረፈው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ ዞን ተብሎ ማዕከሉ ሰቆጣ ሆነ፡፡ የተቀረው ደግሞ ሰሜን ወሎ ተብሎ ማዕከሉን ወልዲያ ከተማ አደረገ፡፡ ከአሰብ በተጨማሪ አፍ አምቦ ወረዳ ከአውሳ አውራጃ ተነስቶ ለኤርትራ ተሰጠ፡፡
‹‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ›› እንዲሉ ‹‹በወሎዬነት›› ኅብር ለረዥም ዘመን የኖሩትን ብሔረሰቦች በመነጣጠል ወሎና የወሎዬነት ድባብ እንደ ጥጥር ጨው ተከስክሶና ተበጥብጦ እንዲሟማ ተፈለገ፡፡ ጨቋኝ ገዥ መደብን በጋራ ታግለው የጣሉ የወሎ ብሔረሰቦች ይሁንታቸው ሳይጠየቅ እንዲነጣጠሉ ተገደዱ፡፡ የሀገርን አስተዳደር በነገድ/ጎሳ ማዋቀር የመኖሪያ ቤትን ከማፈራረስ አልፎ በእሳት እንደ ማቃጠል ይቆጠራል፡፡ ሕዝቡ በእሳቱ ሲቃጠል ትርኳሹ የገዥው መደብ ቆፈን ማባረሪያ የሙቀት ምንጭ፣ የኋላ ኋላ ረመጡ መቃጠያው ይሆናል፡፡
የወሎ ስድስት ብሔረሰቦች የጋራ ማንነት አለን የሚሉ፣ አሁን ለደረሱበት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውጣ ውረድ አብረው ዋጋ የከፈሉ፣ በጥብቅ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ከወሎ ገባር ሕዝብ የተሰበሰበ የትምህርትና የጤና ታክስ ገንዘብ በሁሉም የወሎ አካባቢዎች ትምህርት ቤት ለማቋቋምና ክሊኒኮችን ለመክፈት ውሏል፡፡ የአገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር ለዘመናት ከወሎ የተጠየቀውን መስዋዕትነት በጋራ ከፍለዋል፡፡ የወል መታወቂያ ካርዳቸው ለመሆን የበቃ አስከፊ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ በጋራ አሳልፈዋል፡፡ በዓለም የታወቀውን ‹‹የወሎ ረሃብ›› ያስታውሷል፡፡
በወ/ሮ ስሂን ትምህርት ቤት በአንድ ላይ የተማሩ የየብሔረሰቡ ተወላጆች ለአገራቸውና ለየአካባቢያቸው የልማት ዕድገት ፋና ወጊ ዜጎች ሆነዋል፡፡ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በተፈጥሮ ሀብት ተጋሪነት ስሜት ከብቶቹን ወደ ወሎ ዝቅተኛ ቦታዎች በመንዳት፣ ከአጎራባች የወሎ ኦሮሞና አማራ ሕዝቦች ከብቶች ጋር የሚያከርመው ወሎዬው የአፋር አርብቶ አደር እንደ አባት አደሩ ዛሬም ከብቶቹን ነድቶ ያውላል፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ በደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ባቲ፣ ወልዲያ፣ ወዘተ ከተሞች የመኖሪያ ቤት ሠርቶ በባለቤትነት ስሜት ፈታ ብሎ ይኖራል፡፡ ብሔረሰቦቹ ዛሬ በሀገር አስተዳደር አወቃቀር ተፅዕኖ ሥር ቢወድቁም፣ ይህ የጋራ ማዕድ ተጠቃሚነትና አብሮነት በፅኑ አስተሳስሯቸዋል፡፡ የብሔረሰቦቹን ታሪካዊ ትስስር፣ የጋራ ሥነ ልቦናና የተዛመደ ህልውና ማጥፋት በአስተዳደር እንዲነጣጠሉ የማድረግን ያህል አይቀልም፡፡ ዳሩ ግን በትስስራቸው ላይ ምንም ጉዳት አላስከተለም ማለት አይደለም፡፡ በጋራ አዳብረው ያቆዩትና ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ የሚገባቸው አኩሪ የጋራ ባህልና ታሪክ የመረሳት ምልክት በግልጽ መታየት ጀምሯል፡፡ ሌሎች ባህላቸውን በዓመታዊ ፌስቲቫል ሲያበለፅጉ፣ የጋራ ባህልንና ቅርስን በሞኖፖል ሲቆጣጠሩ፣ በአንፃሩ የወሎ ማዕከል በሆነችው ደሴ ከተማ በበዓላት ጊዜ ይቀርቡ የነበሩት የ12ቱ አውራጃዎች የባህል ጨዋታዎች እየተዳከሙና እየተረሱ መሄድ የዚህ ጉዳት መኖር ማሳያ ነው፡፡
ኢሕአዴግ ደርግን እንደጣለ ለወሎ ባህል ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ ሲያበረክት የቆየውን ስመ ገናናው የወሎ ባህል አምባን በማፍረስ የወሎ የባህል እሴቶችን ለማዳከም ሞክሯል፡፡ የደቡብ ወሎ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ነባር ባለሙያዎችን በማሰባሰብና የጎደሉትን በማሟላት የባህል አምባው መልሶ እንዲቋቋም ያደረገው ከመስከረም 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የባህል ቡድኑ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ሥር ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ የሚሠሩ የወሎ ተወላጅ የመንግሥት ሠራተኞችን በቀድሞ አውራጃዎች ስም እየለያዩ እርስ በርስ አጋጭቶ ኅብረት በማሳጣት፣ የአካባቢውን ልማት በጋራ እንዳያፋጥኑ እንቅፋት መፍጠርና ብቁ ሰዎች ወደ መድረክ እንዳይመጡ ማፈን ወሎ ከደረሰበት ፈርጀ ብዙ በደል ውስጥ አንዱ ሊጠቀስ የሚገባው ነው፡፡ የሃይማኖት ልዩነትን አጀንዳ በማድረግ ሕዝቡን በሁለት ጎራ ለይቶ ለማጨፋጨፍ የሚደረገው ጥረት ሌላው ነው፡፡ ከሌሎች በመማር ከባለ ታሪክ የወሎ አንጋፋዎች ለወጣቱ ትውልድ ተምሳሌት የሚሆን፣ ሐውልት የሚቆምለት ስመ ጥር እንዳይለይ፣ የተጀመሩ ጥረቶችንም በማቋረጥ ትናንትን የማያውቅ ትውልድ ለመፍጠር የወሎ አንጋፋዎችን የማጣጣል እኩይነት አለ፡፡
የወሎዬነትን የጋራ ሥነ ልቦና፣ ታሪክና የወሎ አንጋፋዎችን ገድል ለአዲሱ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ወሎዬ በሆኑ ወላጆች መዘጋት ያለበት ክፍተት አለ፡፡ ወሎዬነትን ከትውልዱ አዕምሮ ለመፋቅ የሚደረገውን ጥረት በቸልታ መመልከት የታሪክ ተወቃሽ ያደርጋል፡፡ መጋቢት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ‹‹የወሎ ኅብረት ልማት ማኅበር›› እናቋቁማለን/አታቋቁሙም የሚሉ ወጣቶች በወሎዬነት አጀንዳ ጎራ ለይተው የወሎ ማዕከል በሆነችው ታሪካዊቷ ደሴ ከተማ መጋጨት የዚህ ክፍተት ማሳያ ገጽታ ነው፡፡ በመላ ኢትዮጵያ ሊስፋፋ የሚገባው ለዘመናት የተገነባ የአብሮነት እሴት ጠለሸ፡፡
የአማራ መነሻ በሆነው ወሎ (ቤተ አማራ)፣ በወሎዬነት የጋራ ሥነ ልቦና በአንድነት መቆም ካልተቻለ የት ነው መቆም የሚቻለው? ይህ ጥያቄ በሸዋ፣ ጎጃም፣ ጎንደር በትይዩ ሊታይ ይችላል፡፡ በጎንደር ለሁለት የማይከፈል ሕዝብን ቅማንት፣ አማራ በማለት ለማጋጨት የተቻለው በቅድሚያ ጎንደርን በመከፋፈል የጎንደሬነትን የጋራ ሥነ ልቦና ማዳከም በመቻሉ መሆኑን መገንዘብ እንዴት ያዳግታል? መፍትሔውም የጎንደሬነት የጋራ ሥነ ልቦናን ወደ ነበረበት ደረጃ መመለስ ነው፡፡ በነገድ ቋንቋ ላይ የተመሠረተው የክልል አወቃቀር በጨፈለቃቸው ሌሎች የአገራችን ክፍሎችም ወደ ነበረበት መመለስ ያለበት በተፅዕኖ በሕዝብ ላይ የተጫነ፣ ወይም የተቀማ ማንነትና መልሶ መገጣጠም ያለበት የሚናፈቅ ውስጣዊ ብዝኃነት አለ፡፡
ለዘመናት አብሮ የኖረው የወሎ ሕዝብ በብሔረሰብ ቋንቋ እንዲለያይ የተደረገው የነገዶቹ ቋንቋ ለሀገር የውስጥ አስተዳደር ስላላመቸ አይደለም፡፡ በኩታ ገጠም የኖሩት ነገዶች ቋንቋቸውን የተወራረሱ፣ በሌሎች የብሔረሰብ መሥፈርቶች በጥብቅ የተሳሰሩና ሊለያዩ የማይችሉ በደም የተዋሀዱ፣ የጋራ ሀገር፣ ክፍለ ሀገር ባለቤትነት የፈጠረው የጋራ ተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ ናቸው፡፡ በአስተዳደር የተለያዩት ከወሎ ሕዝብ መበታተን የፖለቲካ ትርፍ ለማትረፍ የሚተጋ ቡድን ከበስተጀርባ ስላለ ብቻ ነው፡፡ በአንፃሩ በቋንቋ የተለያዩ በርካታ ብሔረሰቦች በአንድ አስተዳደር እንዲኖሩ ተደርጓል፡፡ ትግሬ፣ ኩናማ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኢሮብ ብሔረሰቦች በትግራይ፣ 56 ብሔረሰቦች በደቡብ ክልል እንዲኖሩ ሲደረግ የእኩልነትና የአብሮነት ዓይነተኛ ተምሳሌት የሆነው ወሎ በመርህ አልባ አወቃቀር ይኼንን ዕድል ተነፍጎ ብሔረሰቦቹን ለምን ተገፈፈ ለሚል ጥያቄ መልስ ያሻል፡፡
ከኢትዮጵያዊነት/ኅብረ ብሔራዊነት አኳያ በወሎ የዘር፣ የሃይማኖት አግላይነት ባለመኖሩ ወሎዬነት እንደ አማራነት ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ በቅንነት ሲታይ ከድብቅ ፍላጎት ፅዱ የሆነ ‹‹የወሎዬነት›› የጋራ ማንነት ጥያቄ፣ ጤናማ የሲቪል ማኅበረሰብ አደረጃጀት ወይም የተቀማ የአካታች የውስጥ አስተዳደር አወቃቀር ይመለስልን ጥያቄ እንጂ የሌላውን ማንነት የመቀማት ወይም የፖለቲካ ሥርዓት ምሥረታ ፍላጎት ሊሆን አይችልም፡፡ አማራነትና ወሎዬነት ሊሳለጡ የሚችሉ ሁለት ተነፃፃሪ አቃፊነቶች እንጂ እርስ በርስ የሚቃረኑ አይደሉም፡፡ በትግራይ ዳብሯል እንደሚባለው የባለ ብዙ ብሔረሰብ ‹‹ትግራዋይነት›› እና ኢትዮጵያዊነት፣ በወሎዬነት ድር ለተሳሰሩት ከአማራ ጋር ጥብቅ የጋራ ሕልውና ላላቸው የወሎ ብሔረሰቦች ‹‹ወሎዬነት›› እና ኢትዮጵያዊነት አይነጣጠሉም፡፡ በወሎዬነት ዘውግ ከሚመሠረት ኅብረ ብሔራዊነት ተነስቶ ኢትዮጵያዊነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመገንባት የሚጠይቀውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ያመቻል፡፡ ኅብረ ብሔራዊነት በማቶት ታስሮ ቁልቁል የሚጣል ከነገድ ቋንቋ የተሠራ የአውራጅ እንጨት አይደለም፡፡ ከታች ጀምሮ በየእርከኑ ዙሪያውን እየተገመደ ወደ ጉልላቱ የሚዘልቅ ፀንቶ የሚቆይ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንጂ! እንደ ወሎ ሕዝብ በአስተዳደር ተነጣጥሎ ከድንበር ማዶ ለማዶ እንዲተያይ፣ በቀበሌና ወረዳ ይገባኛል ጥያቄ ዘወትር እየተጋጨ እንዲኖር ሸር የተሸረበበት የሌላው ክፍለ ሀገር ሕዝብ ሁሉ የዚህን ክፍተት ተፅዕኖ በውል ሊገነዘብ ይገባል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ለሀገር አስተዳደር ጥቅም ሲባል ሕዝብን በቋንቋ (ነገድ/ጎሳ) ከመክፈል ይልቅ በወንዝ ተፋሰስ ወይም በኮምፓስ አቅጣጫ ተመሥርቶ መክፈል ይሻላል፡፡ በመልክዓ ምድር የሚዋቀር የሀገር አስተዳደር ዜጎችን የሚጋሩት ክፍለ ሀገር ባለቤት በማድረግ እርስ በርስ ሲያግባባ በቋንቋ የሚዋቀር አስተዳደር ግን ጤናማ ያልሆነ ፉክክርን የሚቀሰቅስ ከመሆኑም በላይ፣ የአካባቢው ባለቤቶች የእኛ ነገድ/ጎሳ አባላት ብቻ ነን የሚሉ ሕገ ወጥ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ባለቤቶችን የልብ ልብ እንዲሰማቸው በማድረግ ዜጎችን ይለያያል፡፡ የመጀመርያው ዓይነት የአስተዳደር አወቃቀር በአገራችን እንደ ጉድ በመጧጧፍ ላይ ያለውን የነገድ/ጎሳ ፖለቲካ ንግድን በማስቀረት (108 ፖርቲዎችን ያስቡ) የአገራችንን ኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲከኞች አማራጭ የኑሮ ዘዴ እንዲፈልጉ ያስገድዳቸዋል፡፡ ለዜጎች የሚበጀው በቋንቋ ግድግዳ አጥር ውስጥ መታጠር ሳይሆን፣ የዴሞክራሲ መብት ተከብሮ በእኩልነት የሚኖርባት ሀገር ባለቤት መሆን ነው፡፡
ሲጠቃለል ወጣቱ ትውልድ አቃፊ የሆኑትን አማራነትንና ወሎዬነትን በማሳለጥ ሰፊ የነቃ ተሳትፎ የሚሹ ፈተናዎችን በብልኃትና በቆራጥነት መጋፈጥ ወቅቱ የሚጠይቀው የሀገርህን አድን ብሔራዊ ግዴታው መሆኑን ተገንዝቦ፣ ለሚከተሉት አራት ዋና ዋና ነጥቦች ትኩረት ሰጥቶ በአንድነት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡
አንደኛ ወሎና ወሎዬነት ሊከበር የሚገባው የውስጥ አስተዳደር ወሰንና የሕዝብ የጋራ ማንነት ስለሆነ፣ እሴቱን ለድብቅ ፍላጎት ማሳኪያ ከሚጠቀሙ ቡድኖች ነቅቶ መጠበቅ፣ የጋራ ማንነት መብት ጥያቄው በመንግሥት ለተቋቋመው የማንነትና ወሰን ኮሚሽን ቀርቦ ወሎዬነት ቀድሞ ወደ ነበረበት ቁመናው እንዲመለስ ጥረት ማድረግ፡፡
ሁለተኛ በቀድሞ አውራጃና በሃይማኖት ልዩነት በመከፋፈል ኅብረት እንዲጠፋ የሚሠራው የሴራ ፖለቲካ ማርከሻው መድኃኒት፣ የተጠናከረ የወሎዬነት የጋራ ሥነ ልቦና መሆኑ ላይ የጋራ መተማመን በመድረስ ጠላትን ማሳፈር፡፡
ሦስተኛ ከታላላቅ ወሎዬ አባቶች ለወጣቱ ትውልድ ተምሳሌት የሚሆን አንጋፋ/አንጋፋዎች በመምረጥ የኩራት ምንጭ የሆነው የአባቶች ጉልህ ሥራ ሳይረሳ፣ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ የሚያስችል ተጨባጭ ጥረት ማድረግ፡፡
አራተኛ ብሔረሰቦችን ለዘመናት አብረው ከኖሩበት ዘውግ አፈናቅሎ በማይፈልጉት ዘውግ በማካተት አገራችንን መቋጫ ለማይኖረው የማንነቴ ይመለስልኝና የድንበር ይከበርልኝ ጥያቄዎች ተጋላጭ ያደረገውን የኢሕአዴግ የሀገር አስተዳደር አወቃቀር ማረም የማይታለፍ ችግር ነው፡፡ የተጀመረውን ሰላማዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ በማስቀጠል፣ የወቅቱ የአገራችን ቁልፍ ችግር የሆነው ሕገ መንግሥት በጎለበተ የሰከነ የጋራ ውይይት እንዲሻሻል፣ በጥናት ላይ የተመሠረተ የሀገር ውስጥ አስተዳደር አወቃቀር ክለሳ እንዲደረግ ግፊት ማድረግ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በወሎ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የባዮሎጂ ዲፓርትመንት መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡