በአንዳርጋቸው አሰግድ
ቅድመ ነገር
የ60’ዎቹ የኢትዮጵያ ተራማጆችና ምሁራን የኢትዮጵያን የብሔሮች ጥያቄ በማንሳታቸው ይወቀሳሉ። አንዳንዶች የሚወቅሷቸው ‘ያልነበረንና የሌለን የብሔር ጥያቄ አንስተው. . .’ በማለት ነው። ለእነዚህኞቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከጥንትም ተጋብተው፣ ተዋልደው፣ ተከባብረው፣ ተቻችለውና ተረዳድተው አብረው የኖሩ ናቸው። ሌላው ቀርቶ፣ የኢትዮጵያ ባለመሬቶችና ጭሰኞችም ተዛዝነውና ተሳስበው በሰላም የሚኖሩ ነበሩ። ሌሎቹ የሚወቅሷቸው ‘ባዕድ የሆነውን የማርክሲዝም ሌኒንዝም ስታሊኒዝም አመለካከትና አቋም በአገሪቱ ላይ ጭነው አገሪቱን የሚከፋፍልና የሚያፈራርስ ፖለቲካ አስፋፉ’ በማለት ነው። እነዚሆቹ ይህንን አመለካከታቸውን በየ አጋጣሚው ለመደጋገም እጅግ ትጉ ናቸው። የሚያስገርመው ግን እስከዚህም ትጋታቸው አይደለም። ለጥቂት ያዳመጣቸው የሚገርመው ይልቁኑ፣ በእጅግ አብዛኞቹ ከማርክሲዝም ሆነ ከሌላ ጸሐፍት ስለጥያቄው አንድም ቅጠል ያላነበቡ ተቺዎች ሆነው በመገኘታቸው ነው። ወይም፣ ለይስሙላ ያህል ያነበነቡ ሆነው በመገኘታቸው ነው።
በሌላው ወገን ከ50’ዎቹ ጀምሮ የተነሱት የብሔር ድርጅቶች የየበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል። የነዚህኞቹ አመራሮች ተገቢ ጥያቄን ይዘው የተነሱና የታገሉ ቢሆኑም፣ አባሎቻቸውንና ብሔራቸውን ለሃምሳ ዓመታት ሙሉ በበደሎች ትረካና በመገንጠል መብት ዙሪያ ብቻ ሲቀሰቅሱ፣ ሲያነሳሱና ሲያታግሉ ኖሩ። ታሪክን እንዳሻቸው እያፋለሱ በመተረክ የስሜታዊ ተከታዮች ማበራከቻና የውጭ ድጋፍ መሸመቻ መሣሪያ ሲያደርጉት ኖሩ። ለሥልጣን ባለቤትነት ሲበቁ ደግሞ፣ ሕዝቦችን በቋንቋ መሥፈርት አጥረውና በግዛት ባለቤትነት ከልለው የመግዢያና የሥለጣን መጠበቂያ መሣሪያ አደረጉት። ይባስና፣ የራሳቸውን ብሔር ጭምር የመበዝበዣና የመጨቆኛ መሣሪያ አድርገው ከበሩበት።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተጋብተው፣ ተዋልደው፣ ተከባብረውና ተረዳድተው አብረው የኖሩ መሆናቸው እውነታ ነው። ከዚህ እውነታ ግን፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጥያቄ አይነሳ የሚል መደምደሚያ ሊከተል አይችልም። ‘ባዕድ አመለካከት በአገሪቱ ላይ ጭነው’ የሚለውም መሠረት የለውም። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሕዝቦቿ ከሚከተሏቸው ሦስት ታላላቅ ሃይማኖቶች፣ ፍትሐ ነገሥትና ክብረ ነገሥት አንስቶ እስከ ወንጀለኛና የፍትሐ ብሔር ሕጎችና የተለያዩት ሕገ መንግሥቶች. . . ወዘተ. ድረስ “ከባዕድ” ያልመጣ ነገር የለም። ዛሪ በሰፊው የሚጠየቁት የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብት፣ የግልጽነት፣ የተጠያቂነት፣ የአካታችነት፣ የሕግ የበላይነት፣ የመልካም አስተዳደር. . . ጥያቄዎች ሁሉ፣ አገር በቀል አይደሉም። ስለዚህም ይልቁኑ የሚበጀው፣ በነባራዊ የነበረውንና ያለውን የብሔሮች መብት ጥያቄ በየምክንያቱ ከማድበስበስ ይልቅ በአንክሮ ለማየትና ለማስተዋል መድፈሩ ነው። አሁንም “ከባዕድ በመጡት” የሰጥቶ መቀበል የፖለቲካ ድርድር ዘዴዎች ለመፍታት በመሞከር ላይ ማተኮሩ ነው።
በዚህ ጽሑፍ ስለኢትዮጵያ ብሔሮች ጥያቄ አነሳስና ሒደት ታሪክ አጭር ማስታወሻ ለማቅረብ እሞክራለሁ። ዓብይ ጥረቴ ከተመለከቱት ክፍሎች ጋራ ለመሟገት አይደለም። ከሃምሳ ዓመታት በኋላ ዛሬም በጥያቄው ላይ ለሚካሄዱት የተካረሩ ምልልሶች፣ በአንድ በኩል የታሪክ ጀርባውን ለማስታወስ ነው። በሌላውም በኩል፣ ጥያቄው ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ የሄደባቸው ምዕራፎች በመጠኑ እንኳን ቢታወቁ፣ እንዳመጣ ከሚነገሩት ሐተታዎች ፈቀቅ ለማለት ይቻል ይሆናል። እንዲያም ሲል፣ ለሰከነ የፖለቲካ ውይይትና ድርድር የሚያግዝ አስተዋጽኦ ሊሆን ይችል ይሆናል የሚል ግምት ስላደረብኝ ነው።
የመጀመሪያዎቹ ዓመታት (1953 እስከ 1961)
የኢትዮጵያ ተራማጅ ተማሪዎችና ምሁራን የመሬት ላራሹንና የዴሞክራሲን ጥያቄ በ1957 ዓ.ም. ለመጀምሪያ ጊዜ አነሱ። ብዙም አልቆየ፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች ጥያቄ በ1959 ዓ.ም. ታከለ። ጥያቄው መነሳት የጀመረው፣ እንደ መሬት ጥያቄ ነባራዊ አገራዊ ጥያቄ ስለነበር እንጂ፣ አንዳንዶች እንደሚያትቱት ከአየር ውስጥ ተጨልፎና ለቲዎሪ ቅንጦት አልነበረም። ወይም፣ አንዳንዶች እንደሚሉት ‹‹የወቅቱ ተማሪዎችና ምሁራን በባዕዱ የማርክሲዝም ቀኖና ስለተለከፉ፤›› አልነበረም። ጥያቄዎችን እንዲያነሱ ያደረጓቸው ሁኔታዎች ይልቁኑ፣ በአካባቢያቸው የሚያስተውሏቸው ነባራዊ ጉዳዮች ነበሩ።
ሲጀመር፣ ጠያቂው የተማሪ ክፍል እንዳመጣ ይጣሉ የነበሩትን የወቅቱን አስነዋሪ፣ ጋንጢጥና አቃቃሪ አባባሎች የሚቃወምና የሚያወግዝ ነበር። ‹‹ከአነጋገር ይፈረዳል፣ ከአያያዝ ይቀደዳል›› የሚለውን የአባቶች ብሂል እያስታወሰ፣ የዜጎቿ ማንነትና ሰብዓዊ ክብር እንዲታወቁና እንዲከበሩ የሚያስተምርና የሚቀሰቅስ ነበር። ወይም፣ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ገና በ20’ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” በተባለው መጽሐፋቸው፣ ‹‹መንግሥት አንዱን ነገድ አጥቅቶ ሌላውን ነገድ ለመጥቀም ሥራው አይደለም። አስተካክለን ካሰብን ዘንድ፣ መንግሥት መቆሙ ለሕዝቡ ነው። ጥረቱ ሕዝቡን ሁሉ በትክክል ለመጥቀም ያልሆነ መንግሥት ሊቆም አይችልም። ለአንዱ ነገድ ወይም ለጥቂት ሰዎች ማድላት ለመንግሥት የሚገባው ሥራው አይደለም፤›› ያሉትን ቁም ነገር የራሱ ያደረገ ነበር።
ነገር ግን በዚያው በተማሪና ምሁር አካባቢ የነበረው የዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሁኔታም ነገሮች ጠለቅ ተበሎ እንዲታዩ የሚገፋ ነበር። አንደኛው ጉዳይ ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ በሚሰጠው ፈተና ለአማርኛ ቋንቋ ዕውቀትና ችሎታ ከፍተኛ ሥፍራ ይሰጥ ነበር። ይህ አሠራር የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ያልነበሩትን ተማሪዎች የሚያበሳጭ ብቻ አልነበረም። የከፍተኛ ትምህርትና የሥራ ማግኘት ዕድላቸውንም የሚወስን ጉዳይ ነበር። ስለነበረም፣ ተራማጅ ተማሪዎችና ምሁራን ያልተቀበሉትና ፍትሐዊነቱን እንዲጠይቁ ያስገደደ ጉዳይ ነበር።
በዚህ ላይ ደግሞ፣ በተፈጥሮው ከተለያዩ ብሔሮች የሚመጡትን ተማሪዎችና ምሁራን ባቀፈው የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ውስጥ የብሔሮች ጥያቄ በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተነሳ አንዳንዴም በአካል እስከ መጋጨት ያደርስ ነበር። ደግሞም፣ ከዛው ከዩኒቨርሲቲው ሳይርቅ ዓመቱን እየጠበቀና ጥምቀትን እየቆጠረ በጃንሆይ ሜዳ በሚካሄደው በዓል ላይ በተለያዩ የብሔሮች የዘፈን ቡድኖች መካከል ግጭቶች ይነሱ ነበር። ራቅም ሲል፣ የካምቦሎጆ የቡድኖች ቲፎዞዎች ግጭቶች ነበሩ። እነዚህን ሁነቶች በቅርብ ይከታተሉ የነበሩ ተማሪዎችና ምሁራን ግለሰባዊና ቡድናዊ የሚመስሉት ግጭቶች ወዴት ሊያመሩ እንደሚችሉ ይጠይቁና ይወያዩ ነበር። በሌላውም ወገን፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለብሔራዊ አገልግሎት በየ ገጠሩ ይሠማሩ ነበር። ከየ ሄዱበት ይዘውት የሚመለሱት መረጃና ግንዛቤ፣ በንጉሠ ነገሥቱ ሥርዓትና አመራር ላይ ብዙ ጥያቄዎችን የሚቀሰቅስ ነበር።
ከዚህም በላይ ግን፣ በ1953 ዓ.ም. የመጀመሪያው ጥይት በኤርትራ ምድር ተተኮሰ። በ1955 ዓ.ም. የሜጫ ቱለማ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ተመሠረተ። በእዚሁ ዓመተ ምሕረት በሶማሊያ መንግሥት የተደገፈው የባሌ ገበሬዎች እንቅስቃሴ ተነሳ። ከላይ በተመለከቱት ሁኔታዎች ላይ የእነዚህ እንቅስቃሴዎች መታከል፣ ተራማጅ ተማሪዎችንና ምሁራንን ከእንግዲህ ምክንያቶቹን አጥብቀው እንዲጠይቁ አደረጓቸው። ፖለቲካዊ መልሶችን የመሻት ጉዞ ተጀመረ። የመጀመሪያው ግልጽ ውይይት የተደረገው በ1959 ዓ.ም. ነበር። ብሔራዊ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ስድስተኛ ጉባዔ በመጋቢት 1959 ዓ.ም. ተደረገ። ‹‹በኢትዮጵያ ስለሚገኙ ከፋፋይ ንቅናቄዎች›› በሚል ርዕስ ተካሂዶ ስለኢትዮጵያ ብሔሮች ጥያቄ የመጀመሪያውን የተማሪ ማኅበር ውሳኔ አሳለፈ። ሁለተኛው፣ በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር በነሐሴ 1960 ዓ.ም. በዩጎዝላቪያ፣ ዛግሬብ ባደረገው ስምንተኛ ጉባዔ ላይ የተወሰነው ነበር። ሦስተኛው፣ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር በነሐሴ 1961 ዓ.ም. በተካሄደው 17’ኛ ጉባዔ ላይ የተወሰነው ነበር።
በሌላው በኩል፣ ከ50’ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በተለያዩት የተማሪ ማኅበራት መጽሔቶች ላይ (ታገል፣ ታጠቅ፣ ትግላችን፣ ቻሌንጅ) ስለብሔሮች ጥያቄ የተለያዩ ጽሑፎች ይወጡ ነበር። ከመጀመሪያዎቹ አንደኛው፣ “ኢትዮጵያዊው ማነው?” በማለት የጠየቀው የኢብሳ ጉተማ ግጥም ነበር። ከዚያም፣ ኃይሌ ፊዳ በሚያዝያ 1960 ዓ.ም. ‹‹የኤርትራ ሕዝብ ትግል ተገቢ አጀማመር ሕዝባዊ ያልሆነ አመራር፤›› በሚል ርዕስ ‘‘ወርዶፋ ገመዳ’’ በሚል የብዕር ስም ለታጠቅ መጽሔት ያቀረበው ጽሑፍና የሰሜን አሜሪካ ተማሪዎች ማኅበር መሪዎች ቻሌንጅ ይባል በነበረው መጽሔት ላይ በ1961 ዓ.ም. ያቀረቧቸው ጥናታዊ ጽሑፎች ተከተሉ። ዋለልኝ መኮንን “On the question of Nationalities in Ethiopia” በሚል ርዕስ ያቀረበው ጽሑፍ በኅዳር 1962 ዓ.ም. ወጣ።. . . ይህ በእዚህ እንዳለ፣ ዘመኑ በሌላው በኩል ደግሞ እንደነ ዮሐንስ ስብሃቱ ያሉት የተማሪው ማኅበር ንቁ ተሳታፊዎች የኤርትራን የነፃነት ግንባሮችን ለመቀላቀል ወደ በርሐ ያቀኑበት ዘመን ነበር።
በዘመኑ በግልጽና በሰፊው ይካሄዱ በነበሩት ውይይቶች፣ በየ ጉባዔዎቹ ውሳኔዎችና በተከታታይ ይወጡ በነበሩት ጽሑፎች ላይ የእነ ዮሐንስ ዕርምጃ መከሰት ግርታን ያሰፈነ ሁነት ብቻ አልነበረም። አንዳንድ የተማሪ ማኅበራት መሪዎች የነ ዮሐንስን ዕርምጃ በወቅቱ በትክክል እንዳነበቡት፣ የመጪውን ዘመን አቅጣጫ ያመለከተ ሁነትና ስለኢትዮጵያ ወደ ፊት ብዙ ጥያቄዎችን የጫረ ነበር። ስለነበርም፣ የወቅቱ ተራማጅ ተማሪዎችና ምሁራን ለብሔሮች ጥያቄ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው ለመንቀሳቀስ ወሰኑ። የተጠቀሱትን የተማሪ ማኅበራት ጉባዔዎች ውሳኔዎች ዛሬ ተመልሶ የሚያነብ፣ ትግሉ ከየት እንደ ጀመረ በቀላሉ ሊገነዘብ ይችላል። የብሔራዊ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ስድስተኛ ጉባዔ ውሳኔ ለምሳሌ፣ የሚከተለው ነበር።
- በኢትዮጵያ ውስጥ ከፋፋይ ንቅናቄዎችን ለማነሳሳት በተደጋጋሚ ሙከራዎች እየተደረጉ መሆናቸውን በመገንዘብ፣
- የመሀከለኛው ምሥራቅ አድኃሪ የዓረብ ኃይሎች በዚህ ቅስቀሳ ላይ ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት በመገንዘብ፣
- በእንደዚህ ዓይነት ከፋፋይ ንቅናቄዎች ላይ ንዑስ ከበርቴዎች፣ አድባርዮችና አድኃሪዎች ያላቸውን ልዩ ጥቅም በመገንዘብ፣
- ይህንንም ፀረ አንድነትና አድኃሪ ኃይሎች ለማራገብ ያላቸውን ፍላጎት በመገንዘብ፣
- እንደዚህ ዓይነት ቡርዣዊና አድኃሪ የሆነ አመለካከት መስፋፋት የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ምሥረታን የሚያሰናክል መሆኑን በመገንዘብ፣
- እነዚህ አዝማሚያዎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ሃቀኛ የፖለቲካ ትምህርት ሒደት እንደ ሚያፋልሱና እንደ ሚመርዙ በመገንዘብ፣
- እንደዚህ ዓይነቱ ከፋፋይነት ኢምፔሪያሊስቶች ለራሳቸው መጠቀሚያ ሊያደርጉት እንደሚችሉ በመገንዘብ፣ ሰፊውን ሕዝብ በተደጋጋሚ በማወናበድ ላይ ካሉ ከሃዲዎንና አድርባዮች ራሱን በንቃት እንዲጠብቅ ለዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሁሉ ጥሪ ያቀርባል። የነሐሴ 1960 ዓ.ም. የአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር ስምንተኛ ጉባዔ ውሳኔም የሚከተለው ነበር፣
- ‹‹ሕዝባዊ መንግሥት ቋንቋንና ነገድን የሚከፋፍለውን ሁሉ አጠቃሎ ሲሰርዘው፣ ሕዝቡ በቀላል የሚማርበትን ቋንቋንና ነገድን የሚያገናኘውን ቋንቋ ከባህሉ ጋር ደግፎ እንዲስፋፋ የማበረታቻ ዘዴ ይፈልጋል፣
- የኤርትራ ግንባር አመራር የሚከተለው ፖለቲካ የኤርትራን ሠራተኛና የገበሬ ጥቅምና ፍላጎት የማያረካ፣ የታጋዩን ሕዝብ ድል ለመሻማት የታቀደ ፖለቲካ መሆኑን በመገንዘብ በጥብቅ ይኮንነዋል። የኤርትራን ሕዝብ ትክክለኛ ተጋድሎ ይደግፋል፣
- የዚህ ማኅበር ምኞት በእኩልነትና በነፃነት ላይ የተመሠረተች፣ በነገድ፣ በዘር፣ በቋንቋና በሃይማኖት ያልተከፋፈለች አዲስ ሕዝባዊት ኢትዮጵያ እንድትመሠረት ነው››።
መኢሶን በሐምሌ 1960 ዓ.ም. ተመሠረተ። በመመሥረቻው ጉባዔ ላይ የብሔሮችን ጥያቄ በሚመለከት የተነሳው ውይይት በቅድሚያ በቅራኔዎች አቀማመጥ ጥያቄና በመርሆዋዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። ‘ከሁሉም በላይ ተፃራሪ የሆነው ወይም ሊታረቅ የማይችለው መሠረታዊ ቅራኔ በመደቦች መሀከል ያለው ቅራኔ ነው። በብሔሮች መሀከል ያለው ቅራኔ በሁለተኛ ደረጃ መታየት ያለበት፣ መሠረታዊው ሲፈታ ተያይዞ የሚፈታና እንዲያም ሲል በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሊታረቅ የሚችል ነው’ ከሚለው አጠቃላይ ስምምነት ላይ ተደረሰ። እንደዚሁም ‘የብሔሮች መብት በመርሆ ደረጃ የሚታወቀው በተለያዩ የአስተዳደር መንገዶች አብሮ ከመኖር አንስቶ እስከ መገንጠል ድረስና መገንጠልንም ጨምሮ እንደሆነ’ ተቀበለ። ከዚህ የመርሆ አቋም ባሻገር ለመገንጠል ጥያቄ ድጋፍ የሚሰጥበትንና የማይሰጥበትን ሁኔታዎች በጭብጥና በሐሳባዊ ደረጃዎች መመልከት በተጀመረበት ጊዜ ክርክሩ ሞቀ። በተለይ የኤርትራን ጥያቄ በተንተራሰ ስለመገንጠልና ስለኤርትራ ግንባር አመራር ተፈጥሮ (በዚያን ጊዜ የነበረው በኦስማን ሳላህ ሳቤ የሚመራው ግንባር ነበር) ከፍተኛ ክርክር ተነሳ። ክርክሩ ግንባሩ ተራማጅ ነው ወይስ አይደለም? በግንባሩ ሥር ነፃ የወጣች ኤርትራ ከብዝበዛና ከጭቆና ነፃ የወጡ ኤርትራውያን ምድር ትሆናለች ወይ? ትግሉ እየገፋ ሲሄድ ምን መልክ ይይዛል?. . . ወዘተ. በሚሉት ጥያቄዎች ዙሪያ የተካሄደ ነበር። በመጨረሻም ‹‹የሕዝቡ ተጋድሎ መደገፍ አለበት፣ ይሁንና ፀረ ሴሞክራሲና ጎሰኛ የሆነውን የግንባሩን አመራር በግልጽ መቃወምና ማውገዝ ያስፈልጋል፤›› ከሚለው አጠቃላይ ስምምነት ላይ ተደረሰ። ይህም ይብዛም ይነስም፣ ኃይሌ ፊዳ በሚያዝያ 1960 ዓ.ም. ለታጠቅ መጽሔት አቅርቦት ከነበረው ጽሑፍ ጋር አንድ ዓይነት አመለካከት ነበር። መኢሶን ሁል ጊዜም ያራመደው አቋም ነበር።
ነገር ግን ‹‹በዚህስ ሁኔታ? በዚያስ ሁኔታ?. . . በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ ብዙ ጥያቄዎች ተነሱ። አንዳንዶቹ ተገንጣዩ ተራማጅና ወደ ሶሻሊዝም የሚጓዝ ከሆነ የሚለውን ቅድመ ሁኔታ ሲያስቀምጡ፣ ሌሎች ወደ ሶሻሊዝም የማይሄድም ቢሆን መደገፍ አለበት የሚለውን አቋም ያዙ። የተደረገው ረጅም ውይይት የተነሱትን በርካታ ጥያቄዎች የፈታ አልነበረም። በመጨረሻ በፕሮግራሙ የሰፈረው የሚከተለው አንቀጽም ጉባዔው የደረሰበትን ውሳኔ የሚያንፀባርቅ አልነበረም፣
- ‹‹በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ነገዶች መሀከል የሚታየውን የሁለተኛ ደረጃ ቅራኔ በማጥፋት ከየ ነገዱ መሀከል መልካሙ ቅርስ እየተወሰደ ስምምነት፣ የአገር ፍቅርና ሰፊ አስተያየትን የሚያዳብር አዲስ ዓይነት ሕዝባዊ ባህል እንዲለማ ይደረጋል።
- ‹‹በነገዶችና በጎሳዎች መሀከል እኩልነትን መፍጠር። በአዲስ መሠረት ላይ አንድነታቸውን መገንባት፣ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን መጠበቅና ማክበር››። ከአንቀጹ እንደሚታየው ብሔሮች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን ያላቸው መብት ‹‹እስከ መገንጠልና መገንጠልንም ጨምሮ ድረስ መሆኑን›› ያሳወቀ አልነበረም። በዚህ መልክ የተጻፈውም፣ ፕሮግራሙ በመንግሥት እጅ የወደቀ እንደሆነ በንቅናቄው ላይ ‹‹አገር ከፋፋይ፣ ገንጣይና. . . ወዘተ.›› የሚለውን ዘመቻ ለመክፈት እንዳያመች አስቀድሞ ለመከላከል በማሰብ ስለወሰነ ነበር። በዚያ ወቅት ለእንደዚህ ዓይነቱ ዘመቻ ተመቻችቶ መቅረብ እንኳን ከሕዝብ ቀርቶ ከራሱ ከተማሪው ማኅብረሰብ የሚነጥል ነበር። ከላይ የተታወሱት የማኅበራቱ ውሳኔዎች የሥጋቱን ነባራዊ ምክንያት በበቂ ያመለክታሉ።
ለማንኛውም፣ የተጠቀሱትን የተማሪ ማኅበራት ውሳኔዎችንም ሆነ የነዋለልኝ ዓይነቱን ጽሑፍ ያልተቀበሉ ተማሪዎችም ነበሩ። ያልተቀበሏቸው፣ በአንድ ወገን ውሳኔዎቹን ከዴሞክራሲያዊና ከሰብዓዊ መብቶች ዕውቅናና ከፖለቲካዊ መፍትሔ መንገዶች አንፃር ሩቅ ሆነው ስላገኟቸው ነበር። በሌላውም ወገን፣ የእነ ዋለልኝ ዓይነቱን አቀራረብና አካሄድ እጅግ ጥራዝ ነጠቅና የአጉል መንገድ ቀስቃሽ ሆኖ ስላገኙት ነበር። በዚሁም ለማለት ይቻላል፣ ሁለተኛው ምዕራፍ ተከፈተ።
ሁለተኛው የውይይትና የውሳኔዎች ምዕራፍ (1962 እስከ 1963)
አንዳንዶችና በተለይም ሕወሓትና ኦነግ የዋለልኝን ጽሑፍ እንድፈር ቀዳጅ እያውለበለቡ ብዙ ብዙ ሲሉ ይሰማሉ። አቶ ሌንጮ ለታ በአንድ በአሜሪካ በተደረገ ስብሰባ ላይም ‹‹እናንተ (ታዳሚዎቹን ማለታቸው ይመስለኛል) ዋለልኝን ካልፈለጋችሁት እኛ እንወስደዋለን፤›› እስከማለት ሄደው ነበር። ይሁንና፣ የዋለልኝ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ተራማጅ ተማሪዎችና ምሁራን ዝክር ውስጥ ለአፍታ ብቅ ብሎ የጠፋ በራሪ እንጂ፣ ሕወሓትና ኦነግ አጋነው እንደሚያራግቡት ይህ ነው የሚባል ሥፍራ የነበረው አልነበረም።
ከላይ እንደተመለከተው የውጭው የተማሪ ማኅብራት መሪዎች በወቅቱ የተመለከቱት እንደውም፣ እጅግ ጥራዝ ነጠቅና ግጭት ጠሪ አድርገው ነበር። ዋለልኝ መኮንን ገና በጽሑፉ መግቢያ ራሱ እንዳለው፣ ጽሑፉ ‹‹ከአጠቃላይ ገለጻ የማያልፍና ተገቢውን ትንተና ያላደረገ ጉስቁል ያለ ጽሑፍ፤›› ነበር (The Article. . . Suffers From Generalizations and Inadequate Analysis)። ዋለልኝ በጽሑፉ ብሔሮች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን እስከ መገንጠል ድረስ ያላቸው መብት እንዲታወቅ የሞገተ ቢሆንም፣ የብሔር እንቅስቃሴዎችን የሚደግፈው መብቱ እንደ መብት እንዲታወቅና እንዲከበር አልነበረም። ይልቁኑ፣ የብሔሮች ትግል ለሶሻሊዝም ለሚደረገው ትግል ማራመጃና ማሳኪያ መሣሪያ ለመሆን፣ ይጠቅማል ከሚል የትግል መሣሪያነቱ ሒሳብ አንፃር ነበር። በሌላ አገላለጽ፣ ዋለልኝ የኢትዮጵያን ብሔሮች ጥያቄ የተመለከተው ከሽጉጥና ከክላሽን የማይለይ የትግል መሣሪያ አድርጎ ነበር።
ዋለለኝ ስለዚህም፣ በአንድ በኩል ለመገንጠል የሚታገሉት የኤርትራ ግንባሮች የሶሻሊስት ግብ እስካላቸው ድረስ ወታደራዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የጠራ ነበር። በሌላው በኩል፣ የብሔር እንቅስቃሴዎች አገዛዙን የሚያዳክሙ ስለሆኑ፣ መደገፍ አለባቸው የሚለውን አስተሳሰብ ያራመደ ነበር። እዚህም ላይ በአንዳንድ የብሔር ድርጅቶች አመራሮች ዘንድ የብሔሮችን መብት ጥያቄ የብሔር ወገንን የመቀስቀሻ፣ የማደራጃ፣ የማታገያና የሥልጣን መጨበጫ መሣሪያ አድርጎ የመጠቀም ዘዴና አካሄድ የተፀነሰው ምናልባት በዚህ ጊዜ ይሆናል ቢባል ሊያስኬድ ይችላል። ሕወሓትና ኦነግ ዋለልኝን አብዝተው የሚያሞካሹትም በዚሁ ምክንያት ይሆናል። ለሥልጣን ሲበቁ ከላይ እንደተመለከተው፣ የመግዢያና የሥልጣን መጠበቂያ መሣሪያ አደረጉት።
ያም ሆነ ይህ፣ በ1962 ዓ.ም. በእነ ዋለልኝ ቡድን በተማሪው ጋዜጦች ላይ ይወጡ የነበሩት ጽሑፎች ከተማሪ ንቅናቄ ሥፍራና ሚና አልፈው በመሄድ ተማሪውን ለትጥቅ ትግል ጠሪና ቀስቃሽ ነበሩ። እንዲያውም ‹‹አብዮታዊው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ የአገሪቱን የአብዮት ኃይሎች እንቅስቃሴ ለመምራት ከሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፤›› እስከ ማለት የሄዱ ነበሩ። ስለነበሩም፣ የንጉሠ ነገሥቱንም መንግሥት ትኩረት የሳቡ ነበሩ።
ከወቅቱ የመንግሥት ጋዜጦች አዲስ ዘመን ለምሳሌ ‹‹ሕግን ለመጣስ፣ በሕይወትና በንብረት ላይ ጥፋት ለማድረስ የሚደረገውን ሙከራ ለመከላከል፤›› እያለ ‹‹መንግሥት ያለበትን ኃላፊነትና የሚወስደውንም ዕርምጃ ተማሪዎችም ሆኑ ወላጆቻቸው አስቀድመው ሊገነዘቡት ይገባል፤›› የሚል ነበር (ኅዳር 19)፡፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያም፣ ‹‹የኢትዮጵያን ጥቅምና ዕድገት የሚቃወምን ጨርሶ ለማስወገድ ካልተቻለ ሰላምና ፀጥታ ዋስትና አይኖረውም፤›› እያለ የሚያትት ነበር (ኅዳር 20)። የኢትዮጵያ ድምፅም፣ ‹‹ለሺሕ ዓመታት የቆየውን ሥርዓት ተማሪዎች ሊያናውጡ ከፈለጉ ሕጉ ይበቀላቸዋል፤›› በሎ አትቶ ነበር (ኅዳር 20)። ኢትዮጵያ ሄራልድ በበኩሉ፣ ‹‹ባለ ሥልጣኖች ከእንግዲህ ምሕረት እያደረጉ መቀጠል አይገባቸውም። የተማሪዎች መጽሔት ባለፈው ሳምንት መታገዱ ትክክለኛው አቅጣጫ እንደተያዘ ይመሰክራል። ይህንን አቅጣጫ እስከ መጨረሻው ድረስ መከተል የማይታለፍ ነው፤›› እያለ፣ መንግሥት ጠንካራ ዕርምጃ እንዲወስድ የሚጠራ ነበር (ታኅሳስ 4)።
ታገል የሚባለው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መጽሔት ኅዳር 5፣ ቀን 1962 ዓ.ም. ታገደ። ታኅሳስ 19 ቀን 1962 ዓ.ም. ጥላሁን ግዛው ተገደል። ተማሪው በፍላት ወጣ። ታኅሳስ 20 እና 21 ዕለት በደረሰው ግጭት በወቅቱ እንደተባለው ከ50 የማያንሱ ተማሪዎች ሕይወት በዩኒቨርሲቲው፣ በመድኃኔ ዓለም፣ በአርበኞች፣ በሐረር መድኃኔ ዓለም ትምህርት ቤቶችና በሃረማያ ኮሌጅ አለፈ። ከዚህ በኋላ በርካታ ተማሪዎች ወደ ውጭ አገሩ ወጡ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮና የዚህም ውጤት ሆኖ ለማለት ይቻላል፣ በኢትዮጵያ ብሔሮች ጥያቄ ላይ የሚደረገው ውይይት በውጭ አገሮች ሆነ። ወደ ውጭ ከወጡት ተማሪዎች መካከል አንደኛው እንደሚታወሰው፣ በነሐሴ 1961 ዓ.ም. አውሮፕላን ጠልፎ ወደ ሱዳን የወጣውና በኋላም ወደ አልጄሪያ የተዛወረው የብርሃነ መስቀል ረዳ ቡድን ነበር። በ1962 ዓ.ም. ብዙዎቹም ወደ ሱዳን፣ ሌባኖን፣ ሞስኮና አሜሪካ ወጡ።
እኔ እስከ ማስታውሰው ድረስ፣ የዋለልኝ ጽሑፍ በውጭው ማኅበራት ዘንድ በግርምትና በአሳሳቢ ከመታየቱ በስተቀር፣ የመወያያ ርዕስ ሆኖም አያውቅም። ሥፍራ የነበራቸው ይልቁኑ፣ የሰሜን አሜሪካው ማኅበር መሪዎች በ1961 ዓ.ም. ያወጧቸው ጽሑፎች፣ የዚሁ ማኅበር 17’ኛ ጉባዔ ውሳኔና ጥላሁን ታከለ በሚል የብዕር ስም በመስከረም 1963 ዓ.ም. የተሠራጨው የብርሃነ መስቀል ረዳና የኢያሱ ዓለማየሁ ጽሑፍ ነበሩ። የአሜሪካው ማኅበር መሪዎች ጽሑፍና ውሳኔ ታሪክ ጠቀስና ይበልጥም ትንተናዊ የነበሩ ቢሆኑም፣ የኢትዮጵያን የብሔሮች ጥያቄ ያጤነው ከቀጣናዊ ቅራኔና ግጭት አንፃር ስለነበር በሌሎቹ ተራማጅ ተማሪዎችና ምሁራን ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም። የነብርሃነ መስቀል ጽሑፍ በበኩሉ በእንካ ሰላንትያ፣ በቅጽሎች፣ በስያሜዎችና በስድብ ጋጋታዎች የተሞላና የታወቁትን የማርክሲስት ወይም ሌኒኒስት ቲዎሪዎች በረጃጅሙ እየጠቀሰ ከመደርደር ያላለፈ ነበር።
የመኢሶን ጽሕፈት ቤት የሁለቱንም ክፍሎች አያያዝና አካሄድ ከገመገመ በኋላ፣ በአውሮፓ ተማሪዎች ማኅበር አማካይነት ተማሪዎች በያሉበት ሥፍራ ሁሉ በየጥናት ክበቦቻቸው ስለብሔሮች ጥያቄ ቲዎሪያዊና ተሞክሯዊ ጥናቶችን በአራት አርዕስት ላይ አተኩረው እንዲያደርጉ ገፋ። የተመረጡት አርዕስት፣ የ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ መንግሥት አመሠራረትና ሒደት፣ ማርክሲያዊ ትንተናና ማርክሲዝም ለብሔሮች ጥያቄ የሚያቀርበው መፍትሔ፣ ከአፍሪካና ከእስያ ቅኝ ተገዢ አገሮች የነፃነት ትግሎች የሚገኘው ተመክሮና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ውሳኔዎችና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ነበሩ። ሌላው ግፊት፣ የአውሮፓ ተማሪዎች ማኅበር ተከራካሪዎቹ ወገኖች ሁሉ የሚሳተፉበትንና በግልጽ የሚወያዩበትን ጉባዔ እንዲያዘጋጅ የማድረግ ነበር።
በዚሁም ለማለት ይቻላል፣ 1963 ዓ.ም. በአንድ ወገን የኢትዮጵያ ተማሪዎችና ምሁራን በየ ጥናት ክበቦቻቸው ስለብሔሮች ጥያቄ በሰፊውና በዝርዝር ያጠኑበትና የተወያዩበት ዓመት ሆነ። ጥናቶቹ የሚካሄዱት በየ ከተማው በሳምንት አንድ ቀን ይደረጉ በነበሩት የጥናት ክበቦች ስብሰባዎች ላይ ነበር። ዓመቱ በሌላውም ወገን፣ ለተባለው ጉባዔ ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገበት ዓመት ነበር። የአውሮፓ ተማሪዎች ማኅበር 11’ኛ ጉባዔ በነሐሴ 1963 ዓ.ም. በበርሊን ከተማ ሲደረግ፣ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ታሪክ ውስጥ በየ ማኅበሮቹ ውስጥ ያሉትን ኃይሎች ሁሉ አንቀሳቅሶ የተደረገ ጉባዔ ሆነ።
ከአውሮፓው ማኅበር የማኅበሩን 11 ቅርንጫፍ ማኅበሮች የወከሉ 150 አባሎች ተሳተፉ። ከሰሜን አሜሪካ አምስት የማኅበሩ አባሎችና በተለይም በዚያ የነበሩትን ሁለት መስመሮች ይወክሉ የነበሩት ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴና ሰናይ ልኬ በአንድ በኩልና የ“ስፓርክ” አዘጋጅ የነበረው መስፍን ሀብቱ በሌላ በኩል ተገኝተው ነበር። የ“ጥላሁን ታከለ” ጽሑፍ አዘጋጆች የነበሩት ብርሃነ መስቀል ረዳና ኢያሱ ዓለማየሁ ከአልጄሪያው ቡድን ተገኝተው ነበር። ተስፋዬ ታደሰም ከሌባኖን። ከመስኮብም፣ በክፍሉ ታደሰ ዙሪያ የነበረው “የፋና” ቡድን ተገኝቶ ነበር። ከሆላንድም በመላኩ ተገኝ ዙሪያ የነበረውና በኋላ “ቡሌቲን” የተባለውን ጋዜጣ ያወጣ የነበረው ቡደን ተሳትፎ ነበር። አሠላለፋቸውን በሚመለከተው፣ የአሜሪካው 17’ኛ ጉባዔ ውሳኔ ባለቤቶችና ደጋፊዎች የነበሩት እነ ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴና ሰናይ ልኬ በአንድ ወገን ሲሆኑ፣ ሌሎቹ የእነሱን አመለካከትና አቋም በመቃወም የተሠለፉ ነበሩ። ጉባዔው ሲፈጸም፣ የሚከተለው ውሳኔ በአብዛኛው ተሳታፊ ድምፅ ተደግፎ ፀደቀ። ማኅበሩ፣ “አንደኛ፣ ብሔሮች የገዛ ዕድላቸውን ለመወሰን ያላቸውን በምንም ዓይነት የማይደፈር መብት ያውቃል። ይህም መብት መገንጠልንም ጭምር የሚጠቀልል ሲሆን እንዲታወቅ ከመታገል አያቋርጥም፣
“ሁለተኛ፣ ዛሬ በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሔሮች ተበዝባዦች በሙሉ የጋራ ጠላቶቻቸውን ለመደምሰስ ፀረ ፊውዳልና ፀረ ኢምፔሪያሊት የሆነ የትግል አንድነት እንደሚያስፈልጋቸው ያምናል። ለዚህ የትግል አንድነት ማኅበራችን ውስጥ የሚገኙ ከየ ብሔሩ የተውጣጡ ተራማጆች በሙሉ የማያቋርጥና የተቀነባበረ የማስተማር ትግል ማድረግ አለባቸው፣ ‹‹ነገር ግን ይህ አንድነት ሊገኝ የሚችለው እነዚህ ብሔሮች በአንድነት ለመኖር ፈቃደኛ ሆነው ሲገኙ ብቻ ነው። በዚህም መልክ በአንድ ሕዝባዊ መንግሥት ሥር ለመኖር የተፈቃቀዱ ብሔሮች ሙሉ በሙሉ እኩልነታቸው እንዲታወቅና የገዛ ኑሮአቸውን በያሉበት በመሰላቸው ለማስተዳደር ያላቸው መብት በማያወላውል ሁኔታ መረጋገጥ አለበት››።
የአሜሪካው ማኅበር በዚሁ በነሐሴ 1963 ዓ.ም. ባካሄደው 19’ኛ ጉባዔው ላይ ይህንኑ ውሳኔ በተመሳሳይ አፀደቀ። ደርግ ወደ ሥለጣን እስካቀናበት 1966 ዓ.ም. ድረስ የአብዛኛው የኢትዮጵያ ተራማጆችና ምሁራን አመለካከትና አቋም ከላይ የተጠቀሰው ነበር። ይሁንና፣ በ1967 ዓ.ም. የተመሠረቱት ሕወሓት በበኩሉ ‹‹የኢትዮጵያ ዓብይ ቅራኔ በብሔሮቿ መካከል ያለው ቅራኔ ነው፤›› በማለት ወጣ። ኦነግም፣ “የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው” እያለ “ቅኝ ግዥዋን ኢትዮጵያ ለመዋጋት” ተነሳ። እዚህም ላይ፣ በብሔሮች ጥያቄ አንፃር የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ሁኔታዎች ያበጀውና ያሰፈነው መሠረታዊ ይዘት ደርግ፣ ሕወሓትና ኦነግ ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ የሄዱበት መንገድና የኤርትራ ግንባሮች ከድሮውም የሄደበት መንገድ ነበር ቢባል እውነታ ነው።
የአብዮቱ ዘመን ውይይቶችና አመለካከቶች (1966 እስከ 1969)
የኢትዮጵያ የብሔሮች ጥያቄ በ1966’ቱ የሕዝባዊ ንቅናቄ ዘመን ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል አንደኛው ነበር። በአብዮቱ ከተሳተፉት ድርጀቶች መካከል መኢሶንና ኢጭአት የ1963’ቱን ውሳኔ በማራመድ ለብሔሮች መብት መታወቅና መከበር በመታገል እንደፀኑ ቆይተዋል። ኢሕአፓም አልፎ አልፎ ከታዩት የአንዳንድ የአመራሩ አባላት መዛነፎች በስተቀር፣ በ1963 ዓ.ም. መንፈስ ቆይቷል። ደርግ በሌላው በኩል ግን፣ ከ1966 እስከ 1969 እና ከ1969 እስከ 70 በኋላ በኢትዮጵያ ብሔሮች ጥያቄ ረገድ ለ17 ዓመታት የሄደበት መንገድ ሁሌም አንድና ያው አልነበረም። አካሄዱን በሦስት ወቅቶች ከፍሎ ማጤኑ ሒደቱን ግልጽ ሊያደርግ ይችላል።
የመጀመሪያው ከሰኔ እስከ ሐምሌ 1966 ዓ.ም. እስከ ኅዳር እስከ ታኅሳስ 1967 ዓ.ም. የነበረው ወቅት ነው። በዚህ ወቅት ደርግ በአንድ በኩል በሐምሌ 2፣ 1966 ዓ.ም. መግለጫው፣ ‹‹(ደርግ) በኢትዮጵያውያን መሀከል ለብዙ ዘመናት የቆየውን በጎሳና በሃይማኖት የተመሠረተውን መለያየትና የኑሮ መራራቅ ‘ኢትዮጵያ ትቅደም’ በሚል እምነት፣ በብሔራዊ ስሜትና በእኩልነት፣ ለአገር ዕድገትና መሻሻል ዓላማ ሕዝቡ ለሥራ ታጥቆ እንዲነሳና በዘመኑ ሥልጣኔ በይበልጥ ተካፋይ እንዲሆን የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል፤›› የሚለውን አመለካከት አራመደ። በሌላም በኩል በኅዳር 1967 ዓ.ም. ከጄኔራል አማን አንዶም ጋራ በተለይ በኤርትራ ጥያቄ በተፋጠጠ ጊዜ፣ “የኢትዮጵያ አንድነት ፍፁምነት” የሚለውን አመለካከት አራመደ። በወሩ በታኅሳስ 1967 ዓ.ም. “የኢትዮጵያ ኅብረተሰባዊነትን” ሲያውጅ ደግሞ፣ ‹‹የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠንከር ብዙ መንገዶች አሉ፤›› ካለ በኋላ የሚከተሉትን ሁለት መንገዶች አሳወቀ፣
- በአገር ውስጥ ያለውን የባህሎችና የልዩ ልዩ ጎሳዎች መቀራረብ ይበልጡን ማጠንከር አንደኛው ዘዴ ነው። ኢትዮጵያ የአንድ ጎሳ ወይም የአንድ ባህል አገር አይደለችም። የተዛመዱ ልዩ ልዩ ነገድና ባህል የሚገኙባት አገር ናት። የዘለቄታ ጥንካሬዋ መሠረትም ይኼው ነው። ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮ በመኖሩ በጋብቻ፣ በባህል፣ በስሜትና በአስተሳሰብ ዝንባሌ፣ በቋንቋ ጭምር የተሳሰረ ነው። የአንድነትን ማጠንከር አንደኛው ዘዴ እንዲህ ያለውን የሚያስተባብር ነገር ሁሉ እንዲዳብር ማድረግ ነው። ዋናዎቹ ቋንቋዎች እንዲስፋፉ፣ ባህል ሁሉ እንዲያድግ፣ የሰው ሁሉ መብት እንዲጠበቅና የአገሪቱ ዜጋ ሁሉ በአንድነት ጥላ ሥር በፍቅርና በመተባበር እንዲሰባሰብ ማድረግ ያስፈልጋል፣
- ‹‹ሁለተኛው መንገድ ደግሞ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር በተለይም ከሱዳን፣ ከሶማሊያና ከኬንያ ጋር ተባብራ የምሥራቅ አፍሪካ ኅብረተ አኅጉር እንድታቆም ማድረግ ነው››። ይህ አመለካከት ከደርጉ “ኢትዮጵያ ትቅደም” ዘመን መግለጫዎች ጋራ ሲነፃፀር የተሻለ ነበር። ደርጉም በዚሁ ጊዜ ታኅሳስ 14 የእስልምና ሃይማኖት ክብረ በዓሎችን ያካተተውን የብሔራዊ በዓሎች ዝርዝር አውጥቶ ነበር። በታኅሳስ 18 ደግሞ፣ የአዲስ አበባ ራዲዮ ጣቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሮምኛ ቋንቋ ፕሮግራሞችን ማስተላለፍ ጀመረ። ሁለተኛው ወቅት፣ የሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት በሚያዝያ 1968 ዓ.ም. ከተቋቋመ በኋላ ደርግ የብሔርን ጥያቄ ጨምሮ በተለያዩ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ የአደባባይ ውይይቶች እንዲካሄዱ የመንግሥት መገናኛ ዘዴዎችን በከፈተበትና የውይይት ክበቦች በየ መሥሪያ ቤቱ ተቋቁመው እንዲወያዩበት በፈቀደበት ወቅት ጀመረ። 1968 ዓ.ም. በዚሁም፣ በብሔሮች ጥያቄ ላይ ይፋ ውይይቶች የተካሄዱበት ዘመን ሆኖ ተጠናቀቀ። ሦስተኛው ወቅት በሁለተኛው ወቅት ዘመን ከታኅሳስ 1968 ዓ.ም. አንስቶ እስክ የካቲት 1969 ዓ.ም. ድረስ በደርግ መሪዎችና በሕዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት አባል ድርጅቶች መካከል ረጅም ውይይቶች የተደረጉበት ወቅት ነበር። ደርግም የመጨረሻ መጨረሻ፣ “የራስ ገዝ አስተዳደር” የተባለውን የአስተዳደር መንገድ እስከ መቀበል ድረስ የሄደበት ወቅት ነበር።
ይሁን እንጂ፣ በ1969/70 የኢትዮጵያን አገር ወዳድ ተራማጆችና ምሁራን አጥፍቶና አግልሎ ሥልጣንን ለመጠቅለል የበቃው የሻለቃ መንግሥቱ የመለዮ ለባሾችና ከፍተኛ ቢሮክራቶች ቡድን፣ በ1970 ዓ.ም. “የራስ ገዝ አስተዳደር” የተባለውን ትቶ፣ ‹‹አንድ ሰውና አንድ ጠብመንጃ እስኪቀር ድረስ፤›› ያለውን አካሄድ ያዘ። ይህም ሦስተኛው ወቅት ሲሆን፣ ‹‹የምሥራቁን ድል በሰሜን እንደግመዋለን›› በሚል ጥሪ የኢትዮጵያን የብሔሮች ጥያቄ በጦር ኃይል “ለመፍታት” የሄደበት መንገድ ነበር። በኋላና ባለቀ ሰዓትም፣ “የብሔሮች ኢኒስቲቲዩት” የተባለውን ተቋም ወደ ማቋቋም ሄዶ ነበር። ጦርነቱ በግንቦት 1983 ዓ.ም. በኤርትራ ግንባሮችና በሕወሓት ኢሕአዴግ አሸናፊነት ተደምድሞ ሻለቃ መንግሥቱ ወደ ዚምባዌ ሸሹ። ኢሳይያስ አፈወርቂ በኤርትራ ነገሠ። የሕወሓት ኢሕአዴግ በአዲስ አበባ።
የግድያና የጦርነቶች ዓመታት (1969 እስለ 1983)
የ1969 ዓ.ም. መጨረሻና የ1970 ዓ.ም. መጀመሪያ ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አንድ አገር ወዳድና ተራማጅ ትውልድ በሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መሪነት በተመለመሉ ገዳይ ቡድኖች ተጨፍጭፎ ያለቀበት ወራት ነበሩ። በዚሁም፣ የ1963’ቱ ውሳኔዎች ባለቤት የነበረው አገር ወዳድና ተራማጅ ትውልድ ከ1970 ዓ.ም. በኋላ በነበረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት ውሰጥ ይህ ነው የሚባል ሥፍራና ሚና ላይኖረው እስኪሆን ድረስ ተዳክሞ አበቃ። ከ1970 እስክ 1983 ባለው የ13 ዓመታት ዘመን ዋና ተዋናዮች ሆነው የቀጠሉት ከላይ እንደተመለከተው ስለዚህም፣ በአንድ ወገን በሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መልማይነትና መሪነት ከ1970 ዓ.ም. ጀምሮ የመንግሥትን ሥልጣን የጨበጠው የመለዮ ለባሾችና የከፍተኛው ቢሮክራሲ ቡድንና፣ በሌላው ወገን የኤርትራ ግንባሮችና የተለያዩት የብሔር ድርጅቶች፣ በተለይም ሕወሓትና ኦነግ ነበሩ።
ሕወሓት ‹‹የኢትዮጵያ ዓብይ ቅራኔ በብሔሮቿ መካከል ያለው ቅራኔ ነው፤›› ባለው የቅራኔ አረዳዱ ገፋ። ከዚያም ከሌሎቹ የትግራይ ድርጅቶችና እስከ መንግሥት ሠራዊት፣ ከኢሕአፓ እስከ ኢዲህ ጋራ ድረስ ካሉት ኃይሎች ጋራ ተዋጋ። ሕወሓት ከተጠቀሱት ኃይሎች ጋራ ያካሄዳቸው ውጊያዎች ስለሚታወቁ አልመለስባቸወም። በዚሁ ዘመን “የኢትዮጵያን ቀኝ አገዛዝ” ሲዋጉ የነበሩት የኤርትራ ግንባሮችና ኦነግ የሄዱባቸው መንገዶችም ስለሚታወቁ እንደዚሁ አልመለስባቸውም።
እንደዚሁም፣ ሕወሓት ከኢሕአዴግ አመሠራረት እስከ ኤርትራ ሬፈራንደም፣ ከሕገ መንግሥቱ መራቀቅና መታወጅ እስከ “የፌዴራል” አስተዳደር አወቃቀር ድረስ የሄደባቸው መንገዶች ስለሚታወቁ አልቆይባቸውም። በአጭሩ፣ ኢሕአዴግ ከ1983 እስክ 2010 ዓ.ም. ድረስ አቶ መለስ ዜናዊ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ባሉት አደረጃጀትና አመራር ለ27 ዓምታት ገዛ። እንዲያም ሲል ለ27 ዓመታት ሙሉ በአንድ ወገን የነፃ ገበያም ሆነ የመንግሥታዊ ካፒታሊዝም ባልሆነው “ካፒታሊዝም” ሲዘርፍ ኖረ። በሌላው ወገን፣ ፌዴራላዊ ባልሆነው “የፌዴራል አስተዳደር” ግዛቶችን ሲከልልና ሲያጥር ኖረ። ኦነግ በ1983 ዓ.ም. ሥልጣንን የተጋራ ቢሆንም፣ ከጥቂት ወራት በኋል በሕወሓት ኢሕአዴግ ተገፍቶ ተሰናበተ። ከዛም ከአሥር በማያንሱ ቡድኖች ተከፋፍሎ በየውጭ አገሮች ሲንቀሳቀስ ቆየ።
ኅዳር 2010
ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአገሪቱ በመላ በተካሄዱት የተለያዩ ትግሎች የሕወሓት ኢሕአዴግ የሥልጣን ወንበር ተነቃነቀ። ሕወሓት ኢሕአዴግ በአንድ በኩል “ተሃድሶና ጥልቅ ተሃድሶ” እያለ በየ አዳራሹ ሲርመሰመስና በሌላው በኩል ባስቸኳይ ጊዜ አዋጆችና ዕርምጃዎች ለመግታት ሲጥር፣ በሁኔታዎች ተቀደመ። በመጋቢት 2010 ዓ.ም. ከሥልጣን ተገለለ። የሚያሳዝነው እንበልና፣ ሕወሓት የራሱ ኢሕአዴግ ጉባዔ ያደረሰበትን ሽንፈት ለመቀበል ተሳነው። በተቃራኒው፣ ወደ መቀሌ አፈግፍጎ ‹‹ሕገ መንግሥቴና የፌዴራል አስተዳደሬ ይነኩና፤›› እያለ ማስፈራራትንና መዛትን መረጠ። ኦነግ፣ አቶ ለማ መገርሳ ለየካቲቱ የኦሮሞ ጨፌ አምርረው እንደገለጹት ‹‹እኛው (ኦሮሞዎች) በእኛው (ኦሮሞዎች) ተጠላልፈን በፈጠርነው ችግር›› የኦሮሞን ሕዝብና አገሪቱን በችግር አጠላልፎ ከማስቸገር ገባ። ሌሎቹም፣ ‘ከእኔ በላይ የብሔሩ ወገን ለአሳር ነው’ በሚል ዓይነት አክርረው መሠለፍ ያዙ። ደግሞ ሌሎቹ፣ ፌዴራላዊ ወይስ አሃዳዊ በሚል ከንቱ ምልልስ ተጠምደው የሆነ ያልሆነውን እየተወራወሩ የሚደመጡ ሆኑ። ሌሎቹም፣ መብት የሚባለው ጉዳይ የሚሸራረፍ ግዑዝ ዕቃ የሆነ ይመስል፣ በዜግነትና በቡድን መብቶች እየበለቱት የተከታዮች መቀስቀሻና የደጋፊዎች ማበራከቻ መሣሪያ አድርገውት መወናኘት ያዙ።
የኢትዮጵያ የብሔሮች ጥያቄ ከየት ወዴት እንደተጓዘ በመጠኑ ለማቅረብ ሞክሬአለሁ። እያወቁም ቢሆን በ60’ዎቹ የኢትዮጵያ ተራማጆችና ምሁራን ላይ የሚዘምቱትን ምንም ለማድረግ አይቻልም። ባለማወቅ ለሚያትቱት ግን፣ መጠነኛ መረጃ እንደቀረበ ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን አንዳንዶች ዛሬም፣ የ60’ዎቹን የኢትዮጵያ ተራማጆችና ምሁራን የትግል ታሪክ ወደ “እናልፋለን ወይም እናሸንፋለን” አውርደው ሲያትቱ ይደመጣሉ። እነዚህ ክፍሎች የትውልዱን የትግል ታሪኩ በውል ቢያስተውሉ ግን፣ የ60’ዎቹ የኢትዮጵያ ተራማጆችና ምሁራን “እናቸንፋለን ወይም እናሸንፋለን” ያሉና “ወዝ፟ ላብ አደር” ያሉ ቢሆኑም፣ የተለያዩት በነዚህ ቃላቶች ምክንያት እንዳልሆነ ባስተዋሉ ነበር። የተለያዩት በወቅታዊ ሁኔታ ምንባባቸውና ትንተናቸው፣ በቅራኔዎች አቀማመጥና በኃይሎች አሠላለፍ አረዳዳቸውና ለትግላቸው በመረጡት የትግል ሥልት ነበር። ከዚህም በተያያዘ ስለየራሳችው አቅም በነበራችው የገዘፈ ወይም የተመዘነ አተያይ ነበር።
አተኩረን ብንመለከት፣ በዛሬዎቹ የፖለቲካ ተዋናዮች መካከል ያሉት የዛሬው ልዩነቶችም በዋናነትና በመሠረቱ በነዚሁ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶች ናቸው። በእኔ ዕይታ ስለዚህም፣ የተመለከቱትን የራስ ጉዳዮች በአንክሮ ከማጤንና ከማስተዋል እንጂ፣ “እናቸንፋለን ወይም እናሸንፋለን” ይባል የነበረውን እየደጋገሙ ለዛሬ ቅስቀሳና ለዛሬ ድጋፍ ማጋበሻ መጠቀም ለዛሬውም ሆነ ለወደፊቱ የሚጠቅምን ትምህርት አያስገኝም። እንደውም ለማለት ይቻላል፣ አካሄዱ የትላንትናውን ቀርቶ የዛሬውንም በውል ለመረዳት አይረዳም። ለነገውም አይበጅም።
የ60’ዎቹ የኢትዮጵያ ተራማጆችና ምሁራን እንደዚሁም፣ አንድ የርዕዮተ ዓለም አመለካከትና እምነት የነበራቸው ቢሆኑም፣ መግባባትና መተባበር ተስኗቸው ተጠፋፉ በሚል ይወቀሳሉ። ስለመጠፋፋታቸው የሚደረገው ወቀሳ በወል የተጠና ባይሆንም፣ በጥቅሉ አግባብነት አለው። ይሁንና አሁንም አተኩረን ብንመለከት ግን፣ አንድ ርዕዮተ ዓለም (ሃይማኖትንም ጨመሮ) ለመስማማትና ለመተባበር ዋስትናን የሚሰጥ መያዣ አይደለም። ሲጀመር ፍልስፍና፣ እምነት፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ፖለቲካ. . . ሁል ጊዜም አከራካሪ ናቸው። ሰዎች ወይም ቡድኖች አንድ ዓይነት የርዕዮተ ዓለም ሆነ የሃይማኖት እምነት ቢኖራቸውም፣ በትርጉምና በትንታኔ መለያየትና መጋጨት በመላው ዓለም ሁሌም የነበረ፣ ያለና ሁሌም የሚኖር ነው። በአገራችንም በ15’ኛው ክፍለ ዘመን በአባ እስጢፋኖስ ደቂቃን ተከታዮችና በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ መንግሥት ካህናት መካከል የከረሩ ልዩነቶች ነበሩ። በ19’ኛው ክፍለ ዘመን በተዋህዶ አማኞች ዘንድም ሦስት ልደት፣ ሁለት ልደት፣ ካራ. . . በሚባሉት ተከታዮች መካከል የከረሩ ፍጭቶች ተካሂደዋል።
በ17’ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓም በካቶሊክና በፕሮቴስታንት ክርስቲያኖች መካከል የ30 ዓመታት ጦርነቶች ተካሂደዋል። በእስልምና አማኞች ዘንድ በሱኒና በሺያ ተከታዮች መካከል አስከ ዛሬ ያልበረደ ግጭት ይካሄዳል። ወደ ማርክሲዝም ስንመጣ በሌኒንና ፕሌካኖቭ፣ ቡካሪንና ካውትስኪ፣ በስታሊኒስቶችና ትሮትስካይቶች፣ በቻይናና ሶቪየት ኅብረት፣ በአልባኒያና ቻይና፣ በኤይሮ ኮሚዮኒዝምና ሶቪየት ኅብረት. . . መካከል የተካሄዱትን ለማስታወስ ይቻላል። በኢትዮጵያ አብዮት ዘመን ‹‹ያንኑ አንድ የማርክሲዝም ርዕዮተ ዓለም ይከተሉ የነበሩት›› ታጋዮች የተለያዩት ዙሮ ዙሮና አሁንም ግን፣ የወቅቱን ሁኔታ በማርክሳዊ የትንተና ዘዴ ተንትነው በደረሱበት ድምዳሜና በቀየሱት የትግል ሥልት ስለተለያዩ ነበር።
በሌላ አገላለጽ እስከ መጠፋፋት የደረሱት ይልቁኑ፣ የሌላውን ሐሳብና አስተሳስብ በማክበር ባህል ያልበለፀጉ ስለነበሩ ነበር። ወይም፣ የሲቪክ ባህል ጉድለታቸው ከፍተኛ ስለነበር ነበር። እንዲያም ሲል፣ ከፖለቲካ ድርድርና ከሰጥቶ መቀበል የፖልቲካ አመራር ባህልና ሥርዓት ሩቅ፣ እጅግ በጣም ሩቅ ስለነበሩ ነበር። የዛሬዎቹ የፖለቲካ ተዋናዮች ስለዚህም፣ በዚህ ረገድ ያለውን ጉዳይ አሁንም ከስሜታዊ መግለጫዎችና ውግዘቶች ወጥተው ጉዳዩን በጥሞና ቢያጤኑት ለዛሬውና ለነገው የሚጠቅም ትምህርት ሊገኝ ይችላል። ዛሬ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ የፖለቲካ ጥያቄዎች “በይዋጣልን” ዓይነት ተፋጠው የሚገኙት የዛሬዎቹ የፖለቲካ ተዋናዮች ይህቺን ትምህርት ቢቀስሙ፣ ከታሪክ አጋጣሚነት ይተርፉ ነበር። ከ60’ዎቹ የኢትዮጵያ ተራማጆችና ምሁራን ልቀው ለመገኘት የበቁ ይሆኑ ነበር።
ኢትዮጵያ ከ2010 ዓ.ም. በኋላ ከመቶ የማያንሱ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚርመሰመሱባት አገር ሆናለች። ይሁንና፣ የመጪዎቹ ጥቂት ወራት ዕጣዋ የሚወሰነው በአንድ ወገን አዲስ አበባና መቀሌ በሚሄዱበት ወይም በማይሄዱበት መንገድ ነው። በሌላው ወገን የየክልሉ የማንነት፣ የወሰንና የከተሞች ተሟጋቾች በሚሄዱበት ወይም በማይሄዱበት መንገድ ነው። እነዚህ ናቸው በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ከማንም በላይ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ክፉ ሊደግሱ የሚችሉት። ከማንም በላይ ሰክነውና ልብ ገዝተው በእኩልነቷ የፈካች የአዲስትና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መሥራች አባቶች ለመሆን የመብቃት ዕድል ያላቸው።
ከማንም በላይና ይልቁኑም ደግሞ፣ ለኢትዮጵያ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ለረሃብ ተጋላጭ ወገኖች፣ ለሦስት ሚልዮን ተፈናቃዮች፣ ለሚሊዮን ሥራ አጦችና በችጋር ደመወዝ ለሚማቅቁት የኢትዮጵያ ወዝ ወይም ላብ አደሮች ለመድረስ መትጋት ያለባቸው። በየ ቴሌቪዥን መስኮቱ እንደሚታየው፣ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጎቢኚዎች ይጨናነቃል። ይሁንና፣ የዛሬዎቹ የፖለቲካ መሪዎችና ተዋናዮች ላውራዲን የተባለችውንም ጎብኚ ቢያደምጡ፣ “ሕዝብ ተኮር” የሚሉት የማኅበራዊ ኢኮኖሚ አመራር “ሕዝብ ተኮር” እንዳልሆነ ይረዱት ነበር (Laura Dean፣ Ethiopia Touts Good Conditions in Factories for Brands Like H&M and Calvin Klein, but Workers Scrape By on $1 a Day‚ The Intercept‚ July 8 2018)። ዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብት፣ ሶሻል ዴሞክራሲ እያሉ ብዙ የሚናገሩት የተቃዋሚ ክፍሎችም፣ በተጨባጭ ለተገፉት የቆሙና የሚታገሉ በሆኑ ነበር።
የኅዳር 2010 ዓ.ም. የሥልጣን ባለቤቶች፣ የዛሬው የፖለቲካ መሪዎችና ተዋናዮች በኢትዮጵያ ብሔሮች ጥያቄ ላይ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ከተሄደባቸው መንገዶች ተምረውና ታርመው፣ ለፖለቲካ የሰጥቶ መቀበል ድርድርና ስምምነት እንዲበቁ ተስፋ ይደረጋል። “ለይዋጣልን” እየቀረቀቡ የሚገኙት ወገኖችም ሰክነውና ልብ ገዝተው ወደ ፖለቲካ ውይይትና ድርድር የመመለስ ብሔራዊ ወይም አገራዊ ግዴታ አለባቸው። በያዙት መንገድ ከቀጠሉ ግን፣ ለብሔራቸውም ሆነ ለአገራቸው ክፉውን ደግሰውና ፈጽመው የሚያልፉ የሺሕ ዘመናት ተወቃሾች ይሆናሉ። የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ኢትዮጵያ አሁንም በፖለቲካ ኃይሎቿ የታሪክ ሽሚያና “መጠላለፍ” ለሌላ ዙር ጦርነት ተዳርገው፣ ደግሞ ደግሞ የሌላ ዙር ጥፋትንና ውድመትን የሚሸከሙበት ትከሻ የላቸውም። የዓድዋው ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ከዛሬ 110 ዓመት በፊት “አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በደረሱት መጽሐፍ ውስጥ፣ ‹‹ምስኪን ኢትዮጵያ! የዕድልሽ ቀን መች ይነጋ ይሆን?›› ብለው ጠይቀው ነበር። የ2011 ዓ.ም. ኢትዮጵያ የፖልቲካ ኃይሎች የአዲሲት ኢትዮጵያ መሥራች አባቶች መሆንን ከመረጡ፣ ኢትዮጵያ የነጋድራስን ጥያቄ ከ110 ዓመታት በኋላ መልሶ የሚያቀርብ ሌላ ገብረ ሕይወት የሚያስፈልጋት አትሆንም።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡