Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ምነው ሸዋ?

ዱቄት ከማምረት ባሻገር ዳቦ እየጋገረ ለገበያ በማቅረብና ተወዳጅነት በማትረፍ የረዥም ቆይታ ያለው ሸዋ ዳቦና ዱቄት ማምረቻ ፋብሪካ፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራሩን በመቀየር በሚሸጠው ዳቦ ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን ይፋ አድርጓል፡፡ ነገሩ ግን ‹‹ምነው ሸዋ?›› አሰኝቷል፡፡

ሸዋ ዳቦ በእስከ ዛሬ ጉዞው ከመንግሥት በሚቀርብለት የድጎማ ስንዴ አማካይነት፣ በተሰጠው ልኬት ዳቦ ጋግሮ በመንግሥት የዋጋ ተመን መሠረት ሲሸጥ ቆይቷል፡፡ ከሰሞኑ ግን እንደ ቀድሞ በተተመነ ዋጋ ዳቦ እንደማይሸጥ አስታውቆ እጥፍ ድረስ ጭማሪ በማድረግ መሸጥ የመጀመሩ ነገር ስለ ዳቦ ገበያና ስለ ስንዴ ጉዳይ አንድ ሁለት ጉዳዮችን እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡

ኑሮ ተወዶበት በምሬት ወጥቶ ለሚገባው ሸማች፣ ይህ ዜና የሚስማማ አይደለም፡፡ የቱንም ያህል መንግሥት በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ድጎማ አደርጋለሁ ቢልም፣ የአብዛኞቹ ዋጋ አልቀመስ እያለ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የዳቦ ዋጋ ጭማሪ ሲታከልበት ግን የሸማቹ ምሬት ከነበረውም ከፍ ቢል አያስገርምም፡፡

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት በተለይ አዲስ አበባ ከተማ ዛሬ ሸዋ ዳቦ እንዳደረገው ሁሉ በርካታ ዳቦ ቤቶች ለሚጋግሩት ዳቦ ዋጋ የሚተምኑትና ለገበያ የሚያቀርቡት በራሳቸው ዋጋ ሥሌት እንጂ መንግሥት በሚያወጣው ተመን እንዳልሆነ እሙን ነው፡፡ ዳቦ ቤቶቹ የራሳቸውን ዋጋ አውጥተው የሚሸጡበት ዋነኛ ምክንያት ለዳቦ መጋገሪያ የሚጠቀሙበትን ስንዴ በነፃ ገበያ ገዝተው የሚሠሩ በመሆኑና ለሚሸጡት ዳቦም ‹‹እሴት ጨምረው›› ስለሚያቀርቡ ነው እየተባለ ነው፡፡ ይኸውም ጣፋጭ፣ ገብስና አጃ ወዘተ. እያሉ የሚሸጧቸው፣ በግራማቸው ተለቅ ተደርገው የሚጋገሩ ዳቦዎች ዋጋ በዳቦ ቤቶቹ መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ሸዋ ዳቦ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር መንግሥት በተመነው ዋጋ የሚሸጠው ለዳቦ መጋገሪያ የሚጠቀምበትን ስንዴ በመንግሥት የሚቀርብ ወይም ድጎማ የተደረገበት ስለሆነ፣ ዳቦውን ጋግሮ ሲሸጥ በተቀመጠለት ዋጋ መሠረት ማዳረሱ ግዴታ ይሆንበታል፡፡

ከሸዋ ዳቦ የተደመጠው ቅሬታ ድጎማ የሚደረግበትን ስንዴ እንደ ልብ ስላላገኘ ስንዴውን በገበያ ዋጋ ገዝቶ ለመጠቀም በመገደዱ እንደ ሌሎች ቅምጥል ዳቦ ቤቶች እሱም የራሱን ዋጋ አውጥቶ መሥራት እንደጀመረ ማስታወቁ ነው፡፡ የተደረገው ጭማሪ በእርግጥ ገበያውን ያገናዘበ ነው ወይ? የሚለው ብዙ ያነጋግራል፡፡ የሸዋ ዳቦ ዕርምጃ ጎልቶ ወጣ እንጂ በከተማችን ያሉ ዳቦ ቤቶች የሚሸጡት ዳቦ ጥራትና መጠን ከምንከፍለው ገንዘብ ጋር የማይገናኝ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

የቱንም ያህል የድህነት መጠን ቢኖር ሌላው ቢቀር ማንም ሰው ዳቦ በልቶ የሚያድርባት አዲስ አበባ አሁን ከዚህም የራቀች እየሆነች መጥታለች፡፡ እንደኔ ዓይነቱ አነስተኛ ገቢ ያለው ሰውም ቢሆን፣ በመንግሥት የድጎማ ስንዴ አማካይነት ዳቦ ጋግረው በ‹‹መንግሥት የቁጥጥር ዋጋ›› (ይህ አሠራር አሁን ያለ አይመስልም) ወደሚተመንላቸው ዳቦ ቤቶች መሄድን ይመርጣል፡፡ እዚህም ቢሆን የሚጋገረው ዳቦ በተባለው ልኬት መሠረት አይሸጥም፡፡ በአንዳንድ ዳቦ ቤቶች በሁለት ብር የሚሸጠው ዳቦ ከአንድ ጉርሻና ከአንድ ጉንጭ አያልፍም፡፡ እንዲህ ያለው ተው ባይ ያጣ የዳቦ ገበያ የመንግሥትን ችላ ባይነት ያሳያል፡፡ በድጎማ ስንዴ ዳቦ ይጋግራሉ የሚባሉት እንኳ መንግሥት ባስቀመጠው ልኬት መሠረት ሲሠሩ በአደባባይ እየታዩ በአግባቡ ቁጥጥር ተደርጎባቸው ዕርምጃ ሲወሰድባቸው አናይም፡፡

ይህም እያለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግሥት የድጎማ ስንዴ ዳቦ የሚጋግሩ መደብሮች፣ በዱቄት እጥረት ምክንያት የሚጋግሩት ዳቦ መጠኑ ቀንሷል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ዱቄቱን ፈጭተው የሚያቀርቡት ዱቄት ማምረቻዎችም እንደ ቀደመው እያቀረቡ አለመሆናቸውም ለዳቦ እጥረት መባባስ ሰበብ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡  ካገኙ ይጋግራሉ፡፡ ካላገኙም ዳቦ የለም ነው ነገሩ፡፡

ይህ መሠረታዊ አቅርቦት ጉዳይ በተለያየ መንገድ ችግር ውስጥ ገብቷል፡፡ መታሰብ ያለበት ግን ዳቦ እንደ ማንኛውም ሸቀጥ ጊዜ የሚሰጥ አለመሆኑ ነው፡፡  ቁጥጥርና ክትትል የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ተቀብሎ በአግባቡ መሥራትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡

ጉራማይሌ ገበያ የተፈጠረበት ምክንያት የዳቦ ቅርጫት መሆን በምትችለው ኢትዮጵያ ውስጥ ለዜጎች በቂና እንደ ልብ የሚቀርብ ዳቦ በርካሽ ዋጋ ለማግኘት የሚያበቃ ስንዴ ማጣቷ አንገብጋቢ ነው፡፡ ቢያንስ ለዳቦ የሚውል ስንዴ ለማምረት አቅም ማጣቷ ያንገበግባል፡፡ እርግጥ የሚመረተውም ከውጭ የሚገባውም ስንዴ ለታሰበው ዓላማ ይውላል ወይ? የሚለው መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ለአዲስ አበባና ለአካባቢዋ የተገዛው ስንዴ በጓሮ ወደ ጎረቤት አገሮች እንደሚወጣ እንሰማለን፡፡ መንግሥት ምን እያደረገ ነው? መልስ ያሻዋል፡፡

ዛሬ ሸዋ ዳቦ ዋጋ መጨመሩ ብቻ ሳይሆን፣ በአግባቡ ስንዴ ማቅረብ ባለመቻሉ በጠፋ ዶላር ለስንዴ ግዥ የሚውል የውጭ ምንዛሪ እስኪገኝ እየተጠበቀ ነው፡፡ ይህ ዘርፍ ባለቤት የሌለው ይመስል ያወጣ ያውጣው ብሎ እንዲሁ ለገበያው በመተው የሚታለፍ አይደለም፡፡ ዋናው ጥያቄም እዚህ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን መቻል አቅቷት በየዓመቱ ለስንዴ መግዣ ሚሊዮን ዶላሮችን እየወጣች መሸመቷ የእልህ ቁጣ ቀስቅሶ ምርቱን በአገር ውስጥ አትረፍርፎ ለማምረት የሚያበቃ ወኔ መጥፋቱ ችግሩን አብሶታል ማለት ይቻላል፡፡

ዛሬ ያለንበትም የዳቦ ዋጋ መውደድና የዳቦ ጥያቄያችን አንዱ መነሻ በየዓመቱ ምርታማነቷ ጨምሯል በሚባልበት አገር ውስጥ እንደ ነዳጅ በውጭ ምንዛሪ ስንዴ የማስገባቱ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን እነ ሸዋ ዳቦ ሆኑ ሌሎች ዳቦ ቤቶች ስንዴ ስለሌለ ወይም በገበያ ዋጋ ስለምንገዛ ዳቦ ላይ ዋጋ ጨምረናል እያሉ ሸማች ላይ ዋጋ እንዲጨምሩ ይፈቀድላቸው ማለት አይደለም፡፡

ጉዳዩ የመንግሥትን እጅ የሚፈልግ ነው፡፡ ስንዴ በድጎማ ይቅረብ የተባለው ታስቦበትና የኑሮ ውድነትን ለመደጎም እንደሆነ ሁሉ አሁንም አብዛኛው ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር እስካልተዘረጋና ከዚህ ጎን ለጎን ቢያንስ ለራስ ፍጆታ የሚሆን ስንዴ ማምረት ካልተቻለ ጥያቄው ነገም እየጎላና እየሰፋ ይመጣል፡፡

በአገር ውስጥ የስንዴ ግብይቱን ጠለቅ ብሎ ማየትም ይገባል፡፡ አንዳንዴም ስንዴ የለም እየተባለ በየሥራ ሥሩ የሚከማቹ መሆኑንም ችግሩን ማባባስ የራሳቸው የሆነ ድርሻ አላቸውና ይህንን መቃኘትና የዳቦ ዋጋን የሚያንሩ ሌሎች ጉዳችንም በመፈተሽ በትክክለኛው መንገድ እንዲጓዝ ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ስንዴ ማምረቻ መሬት ያላጣችውን አገር ከስንዴ ገዥነት ማላቀቅ የመንግሥት ቀዳሚ ሥራ መሆን አለበት፡፡

የግብይት ሥርዓቱም ቢሆን ፈር የማይዝ ከሆነ አሁን ያለውን ችግር በአግባቡ ለመቅረፍ ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ዛሬ ዋጋ ጨመረ ብሎ መከራከር ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ ችግሮቹን ለይቶ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት