Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግብርናው በመንግሥት ሐሳብና በባለሙያዎች ምልከታ መካከል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓመቱ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ የማዳበሪያና ኬሚካል ግዥ ተፈጽሟል

የግጭትና የድርቅ ተጎጂዎችን ሳይጨምር ከ7.9 ሚሊዮን በላይ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች አሉ

ከሚመስሉት ተቋማት ጋር ለዓመታት ሲጋባና ሲፋታ የኖረው የግብርና ሚኒስቴር፣ በዚህ ወር መጀመርያ ሳምንት የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ የሪፖርቱ የተወሰኑ ክፍሎች ላይ፣ በተለይ በወጪ ምርቶች ላይ የታየው የጥራትና የአኃዝ ችግር ከአንድ ሚኒስቴር የማይጠበቅ ቢሆንም በጥቅሉ ግን የዘርፉን ክንዋኔ በግርድፍ ለማሳየት ሞክሯል፡፡ 

ሚያዝያ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በቀረበው ሪፖርት ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል በጥቂቱም ቢሆን ስለ ሜካናይዜሽንና አነስተኛ መስኖ ሥራዎች የተጠቀሰው ይገኝበታል፡፡ በአንድ አንቀጽ ብቻ ተወስኖ የቀረበው የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራ፣ ለምርት ማሰባሰብ የዋሉ ማሽነሪዎችን በመጥቀስ ሲያልፋቸውም ይታያል፡፡

ይህም ሆኖ በግብርና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት፣ የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን ለምርት ማሰባሰብ ተግባር በማዋል የሚጠቀሱት የኅብረት ሥራ ማኅበራትና የግል ባለሀብቶች ናቸው፡፡ እነዚህም በመላ አገሪቱ ካለው ሰፊ የግብርና እንቅስቃሴ አኳያ ‹‹651 ኮምባይነሮችንና 569 ሁለገብ መውቂያዎችን በመጠቀም በጠቅላላው 27.4 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ፣ የገብስና የበቆሎ ምርት የሰበሰቡ ናቸው፡፡

መንግሥት ለሜካናይዜሽን ትኩረት መስጠቱን የሚገልጸው ይህ ሪፖርት፣ ‹‹580,302 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፤›› በማለት ይጠቅሳል፡፡ በዚህም ሳይወሰን፣ ‹‹የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት የጉልበትን ቅልጥፍናና ውጤታማነት ከማሻሻል ባሻገር ብክነትን በመቀነስ፣ ጥራትን በማሻሻልና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሚያደርሰውን የምርት ጉዳት ለመቀነስ ባለው ፋይዳ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን. . .››፣ ወደፊትም መልካም የሚባል ተሞክሮ እንደተቀመረበት ለማሳየት ይሞክራል፡፡

በሪፖርቱ ተደጋግሞ እንደሚጠቀሰው ለሚኒስቴሩ ተጠሪ ከሆኑ ተቋማትም ሆነ ከክልሎች የተደራጀና የተጣራ መረጃ ማግኘት አዳጋች ሆኖበት እንደነበር ለመረዳት ይቻላል፡፡ ለአብነትም ለግብርና ግብዓት መግዣ የቀረበ የብድር ገንዘብ አመላለስ ላይ ችግሮች እንዳሉና ሪፖርት በተደረገባቸው ወራት ውስጥ እንደታቀደው ማስመለስ እንዳልተቻለ ሲያትት፣ አንዱ ምክንያቱም መረጃ ማግኘት አለመቻል እንደነበር ያትታል፡፡

ወደ ቅድመ ነገሩ ስንመለስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ፣ ለጋዜጠኞች በሰጧቸው መግለጫዎች ስለግብርናው ደጋግመው የሚናገሩት ለኢትዮጵያ ግብርና መስኖ ዋናው የእርሻ ዘዴ እንደሚሆን የሚያመላክት ነው፡፡ ደጋግመው እንደሚሉትም የመስኖ እርሻ ኢትዮጵያን ውጤታማ ግብርና እንዲኖራት የሚያስችለው መንገድ ነው፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ምንም እንኳ የስምንት ወራት አፈጻጸሙን ያቅርብ እንጂ ስለመስኖ በሚያወሳው የሪፖርቱ ክፍል ግን የመስኖ እርሻን የወደፊት አቅጣጫ የሚያመላክት እንዲሁም እስካሁን የነበረው አሠራር የሚሻሻልበትን መንገድ አላሳየም፡፡

እንደውም በባለሙያዎች የሚተቸውን አነስተኛ የመስኖ እርሻን ተፈጻሚ ስለማድረግ በሰፊው ያትታል፡፡ በአንፃሩ ጉምቱ ከሚባሉት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)፣ በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ በአነስተኛ ደረጃ የመስኖ እርሻን ማራመድ የሚለው የመንግሥት ውጥን ከመነሻው ጀምሮ ሲሟገቱ እንደነበር አብራርተዋል፡፡ መንግሥት የመስኖ እርሻን በጉትጎታ ወደ ሥርዓቱ ሲያስገባውም ቢሆን በአብዛኛው በአነስተኛ ደረጃ ለማካሄድ በማሰብ እንደነበር በዓለም አቀፍ አማካሪነት፣ በበርካታ ጽሑፎችና መጻሕፍት ተደራሽ የሆኑት ደምስ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

የአገሪቱ ግብርና መካከለኛና ከፍተኛ ወይም ሰፋፊ እርሻዎችንም ጭምር በመስኖ ወደ ማልማት ዕርምጃ መግባት፣ ማደግ መወለጥ አለበት ይላሉ፡፡ እንደ ደምስ (ዶ/ር) ያሉ የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይህን ቢሉም በእስካሁኑ የኢትዮጵያ ግብርና ከሦስት ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት ማረስ አልተቻለም፡፡

የስምንት ወራቱ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነም፣ የአነስተኛ አርሶ አደሮችን የመስኖ ልማት ሽፋን ለማሳደግ በተፈጠሩ የመስኖ ውኃ አማራጮች በመጠቀም፣ በ4.8 ሚሊዮን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች አማካይነት 2.1 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ሊለማ መቻሉን አትቷል፡፡ ይህም ከሚኒስቴሩ ዕቅድ አኳያ 68 በመቶ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ሆኖ በመስኖ የለማው መሬት ስፋት መረጃው መጣራት እንደሚኖርበት ሪፖርቱን ላቀረበላቸው እንደራሴዎች ያሳስባል፡፡ በቆላማ የኢትዮጵያ ክፍሎችም ከ3,500 ሔክታር ያላበሰ መሬት በመስኖ መልማቱን ሆኖም 1,210 ከፊል አርብቶ አደሮችና 18 ለንግድ ሥራ የገቡ ባለሀብቶች በመስኖ አማካይነት ያረሱት መሬት ነው፡፡ 18 ባለሀብቶች አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ፣ ቆላማው አካባቢ የተባለው ክፍል በድፍኑ ከመጠቀሱ በቀር የትኛው አካባቢ የሚለው አለመመላከቱ፣ በ15 ገጽ ተመጥኖ በቀረበው ሪፖርት ውስጥ ከታዩ ውስንነቶች መካከል ሊደመር ይችላል፡፡

የአነስተኛ መስኖን በተመለከተ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚጽፉትና እንደሚያስተምሩት ከሆነ፣ አነስተኛ መስኖ የሚባለው በባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ እስከ 100 ሔክታር መሬት ማልማት የሚቻልበት ሲሆን፣ ዘመናዊ የመስኖ እርሻን የሚመለከት ከሆነ ግን እስከ 200 ሔክታር መሬት ለማልማት ይቻላል፡፡ መካከለኛ የመስኖ እርሻ ከ200 እስከ 300 ሔክታር እንዲሁም ሰፋፊ የመስኖ እርሻን ለማልማት ከተፈለገም 300 እና ከ300 ሔክታር መሬት በላይ ማልማት የሚቻልበት ድልድል በምሁራን ሲቀርብ ይታያል፡፡

በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት አቶ ተስፋው መንገሻ ባለፈው ዓመት ባሳተሙት የጆርናል ጽሑፍ፣ ዓባይ፣ ተከዜ፣ ባሮ-ኦኮቦ፣ ኦሞ-ጊቤ፣ አዋሽ፣ ገናሌ ዳዋ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ የስምጥ ሸለቆ ወንዞች፣ የዳንኪል አካባቢ፣ የኦጋዴንና የአይሻ ተፋሰሶች ብቻ ከ3.7 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በላይ ማልማት የሚያስችላቸው አቅም እንዳላቸው አስፍረዋል፡፡ መንግሥት አነስተኛ የመስኖ እርሻን ለማስፋፋት የሚያስበው ለአነስተኛ ባለይዞታ አርሶ አደሮች እንደሆነ መለያ ዓርማውን የቀየረው ግብርና ሚኒስቴር አስፍሯል፡፡ ይህም ይባል እንጂ ኢትዮጵያ ይህ ነው የሚባል ጥቅም ሳይሰጡ ዓመቱን ሙሉ በማዕድን የታጀበ ለም አፈር እያጎረፉ የሚነጉዱ 12 ዋና ዋና የወንዞች ተፋሰስ የሚገኙባት አገር ነች፡፡

በ1960ዎቹ አስከፊ ድርቅ በኋላ በኢትዮጵያ የመስኖ ግብርና በብዛት እየተለመደ እንደመጣ የጸሐፊው መረጃ ቢጠቁምም፣ እስካሁን ማረስ የተቻለው ግን ከሁለት ሚሊዮን ሔክታር አልበለጠም፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ሊለማ የሚችል 112 ሚሊዮን ሔክታር መሬት እንዳላትና ከዚህ ውስጥ እስከ 70 በመቶው በቀላሉ መልማት እንደሚችል ምሁራን ይጽፋሉ፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ እስካሁን ሊለማ የቻለው ክፍል 16 ሚሊዮን ሔክታር ገደማ ሲሆን፣ በአብዛኛው በመስኖ ለማልማት የሚያስችል የገጸ ምድርም ሆነ የከርሰ ምድር ውኃ ክምችት እንዳለ ይታመናል፡፡ በኢትዮጵያ በመስኖ ሊለማ ስለሚችለው መሬት ስፋት የተለያዩ መላምቶችና ሳይንሳዊ ግምቶች ሲቀርቡ ይደመጣሉ፡፡

አንዳንዶቹ እስከ አምስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በመስኖ ሊለማ እንደሚችል ሲያመላክቱ፣ በርከት ያሉት ግን ከዚህም በላይ መሬት በመስኖ ማልማት እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ ለአብነትም ደምስ (ዶ/ር) በዚህ ከሚስማሙት ናቸው፡፡ ከዓመታት በፊት ከአጋሮቻቸው ጋር ባከሄዱት ጥናት፣ መንግሥት የመጀመርያውንና ሁለተኛውን የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመተግበር የሚያስችሉ አሥር ዋና ዋና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ሥራዎች ማስፈጸሚያ ከ18.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልገው ጥናታዊ አኃዝ አቅርበው ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ ለመስኖና ለግብርና ውኃ ልማት የሚለው ከተጠቀሰው ገንዘብ ውስጥ 54 በመቶ መሆን እንዳለበትም ጥናታቸው ማመላከቱን አስታውሰዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ሰፋፊ ጉዳዮች ምላሽ እንደሚሹ በሚነገርባት ኢትዮጵያ፣ የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ ገንዘብ ከሚመደብባቸው መስኮች መካከል የግብርና ግብዓት አቅርቦትና የ‹‹ልማታዊ›› ሴፍቲኔት ፕሮግራም የገንዘብ ሚዛኑን በአብላጫ የያዙበት አኃዝ ገዝፎ የተነሳበትን መንገድ ለሕዝብ እንደራሴዎቹ ከቀረበው ሪፖርት መረዳት ይቻላል፡፡

በአሁኑ ወቅት 8.3 ሚሊዮን በድርቅ የተጎዱና በእርስ በርስ ግጭት የተፈናቀሉትን ወገኖች ሳይጨምር፣ 7.9 ሚሊዮን ዜጎች በሴፍቲኔት ፕሮግራም ታቅፈው ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም በጠቅላላው ከ16 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የምግብ ዋስትና ጥያቄ ውስጥ በሚገኝባት አገር ውስጥ፣ የመስኖ እርሻ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይህ ነው የሚባል ትኩረት ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ ለመስኖ እርሻ የሚውሉ እንደ ጊዳቦ፣ ርብ፣ መገጭና የመሳሰሉት ግድቦች ግንባታቸው ተጠናቆ መመረቃቸው ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የውኃ መሠረተ ልማቶች በምን አግባብ ለመስኖ እርሻ እንደሚውሉ፣ በምን አግባብ ወደ አነስተኛው ገበሬ ማሳ እንደሚደርሱ ዝርዝር መረጃዎች ሲወጡ አይታይም፡፡ ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ግብርና በመስኖ መመራት እንደሚጀምር ደጋግመው ተናግረዋልና ይኸው እንደሚተገበር በተስፋ ይጠበቃል፡፡

ለድርቅና ለእርስ በርስ ግጭት ተጎጂዎች ከ1.34 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወይም ከ39 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ ለዕለት ደራሽ የምግብር ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ በቅርቡ ጥሪ መቅረቡ ይታወቃል፡፡ በግብርና ሚኒስቴር ሪፖርት መሠረት ሥር የሰደደ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውንና በሴፍቲኔት የታቀፉትን 7.9 ሚሊዮን ዜጎች በምግብ ራሳቸውን ለማስቻል በሚካሄደው እንቅስቃሴ ውስጥ 8.8 ቢሊዮን ብር ለክልሎች ተከፋፍሏል፡፡ ክልሎች ለእነዚህ አካላት ሲያቀርቡ የነበረውን ከ375 ሺሕ ኩንታል ያላነሰ እህል እንዲተኩበት ለክልሎቹ የተሰጣቸው ከመሆኑም ባሻገር፣ ከ300 ሺሕ ኩንታል በላይ እህል ለተጠቃሚዎች መተላለፉንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ በድህነት ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ጥሪት መፍጠሪያ ይሆናቸው ዘንድ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ (ለአንድ ጊዜ ብቻ ተከፋይ የሆነ) ገንዘብም ለክልሎች ተሰጥቷቸዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ለምርትና ምርታማነት መጨመር ትኩረት እንደተሰጠው የእርሻ ግብዓት ግዥና አቅርቦት ነው፡፡ በዚህም መሠረት በዚህ ዓመት ከ20 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ ለማዳበሪያና ለልዩ ልዩ ኬሚካሎች ግዥ መመደቡን፣ እስካሁንም በሁለት ዙር ይኸው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ግዥ ተፈጽሞበት ሥራ ላይ መዋሉን ሚኒስቴሩ ለፓርላማው አስታውቋል፡፡ 1.12 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ መገዛቱን፣ እስካሁንም 550 ሺሕ ቶን ወደ አገር ውስጥ መግባቱን፣ የተቀረው መጠንም እስከ ግንቦት መጨረሻ ተጠናቆ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡ የማዳበሪያ ግዥ መጠኑ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ከ100 ሺሕ ቶን በላይ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡

የግብርናውን ዘርፍ አፈጻጸፈም እንዲህ ባሉ ክንውኖች ቢታጀብም፣ ሚኒስቴሩ ያቀረበው ሪፖርት ውስጥ አሻሚ አኃዞችም ታይተዋል፡፡ ለአብነትም በስምንቱ ወራት ውስጥ ከሰብል ምርቶች ከ612 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ስለመገኘቱ ቀደም ብሎ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሪፖርት ቀርቦ ነበር፡፡ ይሁንና የስምንት ወራት የዘርፉን አፈጻጸም በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀረበው ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው፣ በተለይም ከቡና ወጪ ንግድ 431 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሎ መታቀዱን ይጠቅሳል፡፡ በተግባር ግን 104 ሺሕ ቶን ገደማ ቡና ተልኮ 297 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል ቢልም፣ ወረድ ይልና ግን 431 ሚሊዮን ዶላር ከቡና ንግድ መገኘቱን ይጠቅሳል፡፡ ይህ የተምታታ አኃዝ በሥሩ ከሚገኘው ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የሚቀርብለትን ወቅታዊ ሪፖርት እንኳ በአግባቡ እንዳላሰፈረው የሚጠቁም ነው፡፡ ባለሥልጣኑ በስምንት ወራት አፈጻጸም መረጃዎች መሠረት፣ በስምንቱ ወራት ውስጥ ከ168 ሺሕ ቶን በላይ ቡና በመላክ 608 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ለማግኘት ታቅዶ (የሚኒስቴሩ ሪፖርት ከዕቅዱ የተገኘውን ገቢም 431 ሚሊዮን ዶላር ሲል ይጠቅሳል) 131 ሺሕ ቶን ገደማ ተልኮ 423 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ መገኘቱን ሪፖርት ስለማድረጉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ያልተናበቡና ያልታረሙ መረጃዎች ለእንደራሴዎች መቅረባቸው ብቻም ሳይሆን፣ ምክር ቤቱም ተቀብሎ ለሕዝብ ማሠራጨቱም ሳያስገርም አይቀርም፡፡  

በደምስ (ዶ/ር) ምልከታ፣ ግብርናው ያስፈልገዋል የሚባለውን ድጋፍና ትኩረት ቢያገኝ ኖሮ ከ16 ሚሊዮን በላይ የምግብ ተረጂ በአገሪቱ እንዳይኖር ከማድረግ አልፎ ኢትዮጵያ ስንዴ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የምችትልበት ደረጃ ላይ በአሁኑ ወቅት ትደርስ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች